Sunday, 09 October 2016 00:00

የእነ አጋም ትብብር

Written by  ጋሻው ሙሉ
Rate this item
(4 votes)

አጋም፣ ቀጋና ግራር ሆነው ተሰብሰቡና በእንጨት ለቃሚዋ ሴትዮ ላይ መመካከር ጀመሩ። ‹‹እኛኮ ባለመተባበራችን እንጂ ብንተባበር ኑሮ ይቺ እንጨት ለቃሚ እየመጣች እኛን እየገነጠለች፣ እየሰበረች ወስዳ አንድዳ አመድ ባላደረገችን ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ‹ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም› እንዳለው ሰው፣ ያለፈውን ትተን አንድ ሆነን፣ አንዳችን ስንነካ ሌሎቻችን ዝም አንበል፣ ፈጣሪ የሰጠን እሾህ ከጠላት እንድንከላከልበት እንጂ ለብሰን ዝም እንድንል አይደለም›› ተባባሉና እንጨት ለቃሚዋን በሾሀቸውን እየጠቀጠቁ ለመውጋት ተስማሙ፡፡
ትንሽ እንደቆዩ እንጨት ለቃሚዋ፣ ድልዳሏን በወገቧ አስራ ገመዷን ታጥቃ እየዘፈነች ደረሰች። ከዚያም ወደ ጫካው ስትገባ፣ ቅርጫፉ የደረቀ የግራር እንጨት አየችና ደስ እያላት ወደ እንጨቱ ስታልፍ ከስር አጋም በባዶ እግሯ ላይ እንደ ጦር ተተከለባት፡፡ የለመደችው ስለሆነ ብዙም ሳትደናገጥ ያጋሙን እሾህ ነቀላ ጣለችው፡፡ ቀጠለና ቀጋ ጆሮ ግንዷ ላይ ጠቅ ጠቅ… እያደረገ ወጋት፡፡ ካጋሙ ይልቅ የቀጋው እሾህ አሳመማት፡፡ እነሱን አልፋለሁ ስትል የግራር እሾህ ውስጥ እግሯ ላይ ትክክል አለባት፤ ነቅላ ልታወጣው ስትስበው ተሰብሮ ቀረ፡፡
ቁጭ ብላ በወረንጦ ነቀላ አወጣች ና አሁንም ወደ እንጨቱ አመራች፡፡ እንደ ቅድሙ ተረባረቡባት። ምርር! አላት፡፡ ‹‹እንዴ ዛሬ ደግሞ ምን ጉድ ነው?›› በንዴት፡፡ በስራቸው ተደሰተው ሁሉም አቅራሩ፤ ፎከሩ፡፡ ‹‹የት አባቷንስና እስከ ዛሬ እየዘነጠለች ሰባብራ አመድ ያደረገችን አይበቃትም? እኛ ማን መሰልናት? ቆሮ ገና ምን አይተሸ… ከዚህ በኋላ አንድ ለበቅ እንጨት አታገኝም! ድሮ አባቶቻችንም ሞኝ ሆነው ዝም ብለው እየተቆጡ ተማገዱልሽ፡፡ አሁን ግን እኛ ልጆቻቸው እንደነሱ አንምሰልሽ እሺ?›› በማለት ተራ በተራ ደነፉ፡፡
አሁንም እንጨት ለቃሚዋ የሚጠዘጥዛትን ቻል አድርጋ፣ ያንን ፍሪዳ የመሰለ የግራር እንጨት ለመስበር ወደ ፊት ስትራመድ ጭራሽ ከቅድሙ የባሰ ፊቷን፣ እጇን፣ እግሯን ጠቅ…ጠቅ…በማድረግ ተቀባበሏት፡፡ ባስ ብለው የውስጥ እግሯን እሾህ ልታወጣ ቁጭ ስትል መቀመጫዋን ወጓት፡፡ ታዲያ ቀጋ እየሳቀ፤ ‹‹እናንተ እዚህ ላይ ወግታችሁ ብታረግዝ ልጁ የማንኛችን ሊሆን ነው?››  ሲል በሁለቱ ላይ እያፌዘ መሳቅ ጀመረ፡፡ ለሁለቱም እየሳቁ፤ ‹‹ሰው የሚባለው ፍጡር በኛ የሚያረግዝ ቢሆን ኖሮ ስንቱ ወንድ ባረገዘ ነበር›› አሉ፡፡
እንጨት ለቃሚዋ ተናዳ ተመልሳ ወደ ቤቷ እየሮጠች ሄደች እንግራርም እየተጨባበጡ ደስታቸውን ከመጠን በላይ ገለጹ፡፡
‹‹ከዚህ በኋላ መሰበር፣ መማገድ፣ አመድ ሆኖ ታፍሶ በየሜዳው መደፋት፣ በነፋስ መብነን፣ ያህያ መንከባለያ መሆን፣ በጅብ መቃም ቀረ!›› እያሉ እርስ በርስ ሲሞጋገሱ፣ እንጨት ለቃሚዋ ጥለቆዋን ይዛ እየበረረች መጣች፡፡
አሁንም አንድ ለመሆን ተመካከሩ፤ ‹‹እንደውም ከቅድሙ በበለጠ እየተቀባበልን መድረሻ ማሳጣት አለብን›› እያሉ ተያይዘው የበለጠ አገጠጡ፡፡ እንጨት ለቃሚዋ እንደደረሰች፣ ጥልቆዋን አስተካክላ፣ አጋሙን ለመቁረጥ ስትመታ፣ እሾሁ ነደፋት፤ የግራሩ ቅርንጫፍ ጥልቆውን ይዞ አስቀረው፡፡ ቀጋው ንፋስ እንዳወዛወዘው መስሎ ተኮረባብቶ በጀርባው ተሰገሰገ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ነፍሷን አሳታት፡፡ ጥልቆዋን ጥላ አራቅ ብላ ሄደች፡፡ ሳር ላይ እየተነክባለለች የጀርባዋን ቁስል ለማስታስ ሞከረች፡፡ እነሱ በስራቸው ተደስተው እርስ በርስ እተሞጋገሱ፣ በነፋስ ዳንኪራ እየረገጡ ‹‹ሽው….ሽው….›› እያሉ ጮክ ብለው ዘመሩ፡፡
እንጨት ለቃሚዋ፤ ህመሙ ትንሽ መለስ ሲልላት፣ አሁንም ተነስታ ወደ እነሱ ቀረበችና በአንዴት፤
‹‹አጋም? አንተ ልጋጋም
ቀጋ? አንተ ጠውላጋ››
በማለት ሁለቱ ላይ እየፈጠጠች ተሳደበች፡፡ ይሄን ሲሰሙ አጋምና ቀጋ በየባሰ ተናደዱ፡፡ ግራር ግን ባለመሰደቡ ደስ ብሎት ከአድማው እራሱን ለማግለል መወላወል ጀመረ፡፡ እንጨት ለቃሚዋ ጥልቆዋን አንስታ አጋምን ከስር መምታት ጀመረች፡፡
አጋም፤ ‹‹ግራር?...ቀጋ?... ምነው ዝም አላችሁ…. ውጓት እንጂ? እየቆረጠችኝ እኮ ነው፡፡ ቀጋ?...አንተ ግራር? ምነው ዝም አላችሁኝ?›› እያለ መጮህ ጀመረ፡፡ ግራር፤ ‹‹እኔን አልሰደበች… እንደውስ እኔ ምን አገባኝ?›› አለ እራቅ ብሎ የአጋምን ስቃይ እያየ። ቀጋም የጥልቆውን ስለት እያየ በፍርሃት ሽምቅቅ! ብሎ ‹‹በዚህ ስለት ከመቆረጥ አመድ መሆን ይሻላል›› እያለ ሳይተባበር ቀረ፡፡ እንጨት ለቃሚዋም አጋምን በስለታም ጥልቆዋ እየቆረጠች፤
‹‹አጋም? አንተ ልጋጋም
እ? እስቲ አሁን ተዋጋ?››
እያለች እልፎ አልፎ ሲፈራገጥ ቢወጋትም ቻል አድርጋ ቆራርጣ ጣለችው፡፡ ወዲያው ጥልቆዋን ይዛ ቀጋ ዞረችና፤ ‹‹ቀጋ? አንተ ጠውላጋ›› ብላጥልቆዋን አስተካክላ ሳትመታው ከቃጣችው በኋላ ትታው አለፈች፡፡ ግራር ጋር ስትደርስ እየሳቀች፤ አይ ግራር ሞኙ ሰው አማኙ›› አለችና የጥልቆዋን ስለት በግራር ገላ ላይ ማሳረፍ ጀመረች፡፡
‹‹ስማ? በኛ በሰዎች ምን እንደሚባል ታውቃለህ? ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ይባላል፤ ሌላው ደግሞ ‹‹የማያዋጣ ጠሎት ለቅስፈት›› ይባላል፡፡ የናንተ አድማ የማያዋጣ ጠሎት ነው እሺ?›› እያለች ግራርን ቆራረጠችው፡፡ ‹‹ዶሮም ሲፈጥረኝ ላመድ ነው›› አለ ግራር፤ አመድ ለመሆን እየተዘጋጀ፡፡ አጋም በጓደኞቹ መካዳት ስላዘነ መጀመሪ ሲያብብና ሲፈራ ቀይና ነጭ ይሆንና መጨረሻ ላይ ሀዘኑን ሲያስታውሰው ፍሬው እንደ ምጣድ ጥቁር ይሆናል፡፡ ይሄም የመጨረሻውን ሰዓት ሀዘኑን ማስታወሱ ነው፡፡
ቀጋ ደግሞ ‹‹ከዚህ በኋላ ከማንም ጋር አልተባበርም›› በማለት ማንም እንዳይደርስበት ከግር እስከ ራሱ መላ ሰውነቱን እሾህ ሸፍኖ ይኖራል። የተጠጋውን ሁሉ እንዳልቢን ማጭድ በተሳለ እሾሁ ይተለትለዋል፡፡
ግራር መጨረሻ ላይ በሰራው ስህተት፣ ሰው እየቆረጠ እየፈለጠ ለማገዶ፣ ላጥር፣ ገበሬ ጠርቦ ካስተካከለው በኋላ ለድግር፣ እንዲሁም ለሙቀጫነት ከዛፍ ሁሉ እሱን እየመረጠ ይጠቀምበታል፡፡ በዚህ የተነሳ ግራር እጅግ በጣም በማዘኑ አንባው ከውስጡ ፈንቅሎ ወደ ውጭ በመውጣቱ በሰው አጠራር ‹‹ሙጫ›› እየተባለ የሚጠራው የሀዘን እንባው ነው። ብዙዎች እንደነ አጋም፣ ቀጋና ግር አንድ ሆነው ይጀምሩና ይለያያሉ፡፡ ‹‹መለያየት ሞት ነው›› አይደል ያለው ጥላሁን ገሠሠ?

Read 1483 times