Monday, 10 October 2016 06:50

የሸዋው ንጉሥ ምኒልክና የዛላው ካዎ (ንጉሥ) አማዶ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     የምኒልክ ሠራዊት ጎፋን ከተቆጣጠረ በኋላ የማዕከላዊው መንግሥት መቀመጫ የነበረችው በና የተባለችው ቀበሌ ነበረች፡፡ ካዎ አማዶ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር በጣም ቅርበት ነበራቸው፡፡  ከማዕከላዊ መንግሥት ወረዳውን እንዲያስተዳድሩ ተመድበው የተላኩት ሹምና ካዎ አማዶ፣ ቅርበትና የግል ግንኙነት ነበራቸው፡፡ አንድ ቀን ሹሙ፤ ካዎ አማዶ ቤተ-መንግሥት ሄደው እየተጫወቱ ሳለ፣ ሹሙ የያዙት መሳሪያ በጣም አስገረማቸውና፤ “ካዎ አማዶ! እስቲ እስቲ መሳሪያህ እንዴት ያምራል፣ አምጣው ልየው›› ብለው ተቀብለው እያገላበጡ ሲመለከቱት፣ ድንገት ባረቀባቸውና ሹሙን ገደሏቸው፡፡ ምኒልክ ወሬውን ሲሰሙ በጣም ከማዘናቸውም በላይ፤ በጣም ተናደዱ፡፡ ‹‹ካዎ አማዶ ተይዞ ይምጣ›› ሲሉ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ መልዕክተኞቹም ካዎ አማዶን ‹‹ሰሞኑን በተፈጠረው ሁኔታ ምኒልክ በጣም አዝዋነል፡፡
ሊያነጋግሩዎት ስለሚፈልጉ ወደ ሸዋ ተጠርተዋል›› አሏቸው፡፡ ካዎ አማዶም በጣም ተገረሙና፤ ‹‹እኔ ምን አጠፋሁ? ባርቆብኝ እንጂ አውቄ አልገደልኳቸው፡፡ እንሂድ ካላችሁ ለእኔም ጥሩ ነው፡፡ በዚያውም የአማራን ካዎ አያለሁ›› በማለት ወደ ሸዋ ለመሄድ ተስማሙና ተይዘው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡
ካዎ አምዶ በሰው እኩልነት፣ በዓለም  ጥግ ያሉ ካዎች ሁሉ አንድ ዓይነት አቅም፣ አንድ ዓይነት ሥልጣንና ጉልበት፣ አንድ ዓይነት መንፈሳዊና ሥነ-ልቡናዊ ንፅህና አላቸው ብለው የሚያምኑ ሰው አንደነበሩ የዛላ አባቶች እንደሚናገሩ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዮም ገልጿል፡፡ ካዎ አማዶ፤ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሲደርሱ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ፡፡
የሰሜን መሳፍንትና መኳንንት እንደሚያደርጉት፤ ዙፋን ስር ተንበርክከው አልነበረም ሰላምታ የሰጡት፣ ተንደርድረው ሄደው የምኒልክን ጉንጭ ግራና ቀኝ አገላብጠው ሳሙ፡፡ ያልተለመደ ነገር ስለሆነ ምኒልክ፣ የሸዋ መሳፍንትና መኳንንት በጣም ተገረሙ፡፡ ካዎ አማዶ ግን ምንም አልመሰላቸውም። የእኩልነት እንጂ የበታችነት ስሜት ሳይሰማቸው፤ ‹‹አንተ ነህ የሸዋ ካዎ?›› እያሉ በመደጋገም ይጠይቃሉ፤ የተቀመጡበትን ወንበር ይመለከታሉ፡፡
ምኒልክም በሰውዬው ሁኔታ በመገረም፤ ‹‹የእኔን ሹም በመግደልህ ተናድጄ ነበር እዚህ ድረስ ያስጠራሁህ፡፡ አሁን ግን ምሬሃለሁ›› አሉ። ካዎ አማዶም፤ ካዎች ሁሉ እኩል ናቸው የሚል ስሜት ነበራቸው፡፡
የሸዋ ካዎ ይገድለኛል፤ ያስረኛል ይቆርጠኛል ይፈርድብኛል የሚል አስተሳሰብ ስላልነበራቸውም፣ በልበ ሙሉነት፤ ‹‹ባትምረኝ ምን ልታደርገኝ ነበር?›› አሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ተመላለሱ፡፡ ረዥሙን ታሪክ ላሳጥረውና ምኒልክ፤ ‹‹እኔ እዚያ ድረስ ሰራዊቴን ልኬ፣ አካባቢውን ተቆጣጥሬ ሥልጣኑ የእኔ ሆኗል፡፡ ከአሁን በኋላ ዛላ ለእኔ ነው የሚገብረው›› አሉ፡፡ ካዎ አማዶም፤ ‹‹አንተ የሸዋ ካዎ ነህ፣ እኔም የዘላ ካዎ ነኝ፡፡ እኔ እያለሁ እንዴት ነው የዛላ ሕዝብ ለአንተ የሚገብረው?›› በማለት ጠየቁ፡፡ ንጉሥ ሚኒልክም፤ የሰውዬውን ቅንነት፣ የዋህነትና እውነተኛነት ተገንዝበው፤ ‹‹አንተና ቤተሰብህ አትገብሩም፤ ነፃ ናቸሁ፡፡ የዛላ ሕዝብ ግን ለእኔ ይገብራል›› አሏቸው፡፡ ‹‹አሃ! እኔና ቤተሰቤ ያለነው‘ኮ በዘላ ሕዝብ ነው፡፡ የዛላ ሕዝብ ለአንተ ከገበረ፣ እኔና ቤተሰቤ ምን እንሁን? የዛላ ካዎነቴስ ምኑ ላይ ነው?›› በማለት ሞገቱ፡፡
ከብዙ ምልልስ በኋላ ምኒልክ፣ ‹‹ማዕከላዊ መንግሥት እየመሠረትን ነው፡፡ እዚያ ድረስ ወታደሮቼን የላኳቸው፣ ዛላ ለእኔ እንዲገብር አይደለም ወይ? በል እንግዲህ ያንተ ገባሮች ላንተ ይገብራሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ ለእኔ ይገብራሉ›› አሏቸው፡፡ ካዎ አማዶም፤ ‹‹የእኔን ገባሮች አሳይሃለሁ፡፡ ከእኔ ገባር ውጭ ያለው ለሸዋ ካዎ ይገብራል›› ብለው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሄኖክ አጫውቶኛል፡፡

Read 1317 times