Monday, 10 October 2016 06:58

የጎፋ ህዝብ ብርቅዬ የማኅበራዊ ዋስትና እሴቶች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ዛሬ ስለ ጎፋ ህዝቦች የማይሸረሸሩ ብርቅዬ የማኅበራዊ ዋስትና እሴቶች አጫውታችኋለሁ፡፡ ስለ ማኅበራዊ እሴቶቹ የነገረኝ ደግሞ የቱሪዝምና ባህል ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ነው፡፡ ሄኖክ ከጋዜጠኝነት ሙያው ባሻገር የተለየ እሴት ያላቸው ህዝቦች እሴቶቻቸው እንደ ቱሪዝም ምርት እንዲተዋወቁ፣ እንዲለሙና ለማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋል፡፡
ከሚያደርጋቸው ጥረቶች አንዱ በየዓመቱ በጎፋ ብሄረሰብ የሚከበረው የጎፋ ጋዜ ማስቃላ ፌስቲቫል ነው፡፡ የጎፋ ህዝብ በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን ይኖራል፡፡ ዞኑ 5 ብሄረሰቦች የያዘ ሲሆን እነሱም ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዘይሴ፣ አይዳና ጊዲቾ ናቸው፡፡ የጎፋ ብሄረሰብ በ5 ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ይኖራል፡፡ ወረዳዎቹም ደምባ ጎፋ፣ ገዜ ጎፋ፣ ዛላ፣ ኡባ ደብረፀሐይ መሎኮዛ ናቸው፡፡ ከተማው ሳውላ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡
የጎፋ ህዝብ በታላቅ ክብር ከሚያከብራቸው ባህላዊ እሴቶች ዋነኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡ አከባበሩ የሚጀምረው ከ3 እና 4 ወር በፊት ነው። የመስቀል በዓልን ምንም አያደበዝዘውም፤ ምንም ጥላውን አያጠላበትም፡፡ በመስቀል ዕለት ሰው ቢሞት እንኳ አይቀበርም፡፡ አይለቀስም፡፡ ኀዘንተኛው ሬሳውን እቤት አስቀምጦ ወጥቶ፣ ዮ ማስቀላ (መስቀል እንኳን መጣህልን) እያለ ከዕድምተኞች ጋር ይጨፍራል፡፡ መስቀል ከተሸኘ በኋላ ነው ሟች ተለቅሶለት የሚቀበረው፡፡
የጎፋ ህዝብ በገናና ንጉሦች (ካዎች) የሚተዳደር ትልቅ ህዝብ ነው፡፡ ከእነዚህ ገናና ንጉሶች መካከል የደምባ ጎፋው፤ የዛላው፣ የኡባው፣ የባዮው ካዎ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጎፋ ካዎች ከሌላው ብሄረሰብ ካዎ የሚለያቸው ባህርይ አላቸው፡፡ ይኸውም የየራሳቸውን ግዛት ድንበር የሚያስከብሩት በመገፋፋት፣ በጉልበት ወይም በጦርነት ሳይሆን በስምምነት ነበር፡፡ የአንዱ ንጉሥ ድንበር የት ድረስ እንደሆነ ሌላው ንጉሥ ያውቃል፤ ያከብርለታልም። በራሳቸው ግዛት የራሳቸውን ሉዑላዊ መንግስት መስርተው የሚኖሩ ንጉሶች ነበሩ፡፡ የጋራ በሆነ ጉዳይ ደግሞ ለምሳሌ የጎፋን ህዝብ ሊያጠቃ የመጣ ጠላትን በጋራ ይመክታሉ፣ ይከላከላሉ፡፡ ለምሳሌ የምኒልክ ጦር ወደ አካባቢው ሲደርስ፣ ንጉሦቹ ተሰበሰቡና “እንዴት ነው? እንመክተው? ወይስ ምን ይሻላል?” በማለት ተመካከሩ፡፡ ንጉሦቹ ጀብደኞች አልነበሩም፡፡ ብልህና አስተዋዮች ነበሩ፡፡ የምኒልክ ጦር በወቅቱ የታጠቀው መሳሪያ “ዘመናዊ” ነበር፡፡ እነሱ የነበራቸው ደግሞ ባህላዊው ጋሻ፣ ጦርና ጎራዴ ብቻ ነበር፡፡ የጦር መሳሪያ ኃይል ሚዛን ወደ ምኒልክ ሰራዊት ማዘንበሉን ተገነዘቡ፡፡ ስለዚህ ህዝባቸው እንዳይጎዳ ጦርነት መግጠሙን ተውትና መጠነኛ መከላከል አድርገው ጦሩ እንዲገባ አደረጉ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የጎሳ መዋቅር በጣም ጠንካራና ፍትሀዊ የሆነ ማኅበራዊ ትስስር እንዲኖር ያደርጋል ይላል ሄኖክ፡፡ የጎፋም ህዝብ የጎሳ መዋቅር አለው፡፡ በዚህ መዋቅር ከምንም በላይ ለበአልና ለማኅበራዊ መስተጋብሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚኖር ህዝብ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ጎፋዎች ከሚወደዱበትና ከሚከበሩበት እሴቶቻቸው አንዱ ለእንግዳ የሚሰጡት ማኅበራዊ ዋስትና ነው፡፡ ሄኖክ እንግዳ ወይም ከሌላ አካባቢ የመጣ ሰው፣ ጎፋዎች መኻል ሆኖ ሰማይና መሬት ያልፋል እንጂ ራሱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር አይገጥመውም፣ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የጎፋ ህዝብ ካላለቀ በስተቀር እንግዳው አደጋ አያገኘውም በማለት አስረድቷል ጋዜጠኛ ሄኖክ፡፡
ጎፋዎች አሁን ባሉበት ማኅበራዊ አቋም ሆነ ክርስትናና እስልምና ከመስፋፋታቸው በፊት የአካባቢው ማኅበራዊ ዋስትና የተረጋገጠ ነው፡፡ ከወንጀል ከግድያ፣ ከዝርፍያ፣ … ጋር የተገናኙ መጥፎ አጋጣሚዎች በጎፋ ምድር አይከሰቱም፤ ዕጣ ፈንታም የላቸውም፣ አይስተዋሉም ይላል ሄኖክ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢስተዋሉ እንኳ ከተሜነት በተስፋፋባቸው ቦታዎች እንጂ ገጠሩ፣ እንደ ትናንትናውና ከትናንት በስቲያው ከብቱን ጫካ ለቆ ለምድሪቷ አደራ ሰጥቶ የሚኖር ህዝብ ነው በማለት አስረድቷል፡፡
በሰለጠኑት አገራት ማኅበራዊ ደህንነትን ለመጠበቅ ዘመናዊ ካሜራዎች በየቦታው ተሰቅለው፣ የደህንነት ሰራተኞች በህዝቡ መኸል እየተሽለኮለኩ የተባለውን ማኅበራዊ ደህንነት ዋስትና ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ በጎፋ ያለው ማህበራዊ ደህንነት ምስጢሩ ምን ይሆን? ጎፋ ያልተበረዘ ጠንካራ የባህል መሰረት ያለው ህዝብ ነው፤ ይላል ሄኖክ፡፡ “ያ ባህል ሁሉንም ይገዛል፤ በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናት ሂደት ተሸርሽረው አልቀው ይሆናል እንጂ እንደ ጎፋ ዓይነት ባህላዊ እሴት ያላቸው ብሄረሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ የጎፋ ህዝብ ምርቃት ይወዳል፣ እርግማን የሚፈራ ህዝብ ነው፡፡ ምርቃት አሁን ካለሁበት ምዕራፍ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የሚያሻግረኝ መሳሪያ ነው ብሎ የሚያምን ማኅበረሰብ የዚያኑ ያህል እርግማን ይፈራል፡፡”
አባቶቹ የተለሙለት ነገር አለ፡፡ የሰው ሀቅ እንዳይነካ፣ ሰውን ያለ አግባብ እንዳይበድል፣ በሰው ላይ ክፉ እንዳይሰራ፣ ከጠብ፣ ከቁጣ፣ ከአምባጓሮ፣ ከጭቅጭቅ፣ … እንዲርቅ አባቶቹ ተልመውታል። ከዚህ መውጣት መረገም ነው፡፡ ከዚህ መውጣት የሚፈልግ የለም፡፡ ለባህሉ የሚሰጠው ትልቅ ክብርና ቦታ ነፍስ ዘርቶ በገበያዎች ሁሉ ታየዋለህ፡፡ በጎፋ ገበያዎች ውስጥ ገንዘብ ልትዘረዝር የምትሄድ ሻጭ፤ አጠገቧ ያለችውን ሴት “እያየሽልኝ” አትልም። ዝም ብላ ከመደቧ ተነስታ ወዲያ ሄዳ ሽንኩርት ገዝታ ትመለሳለች፡፡ ፍየሎች ከመጡ፣ ገበያተኛውና አጠገቧ ያሉት ሰዎች “ክስ” ብለው ፍየሎቹን ያባርራሉ፡፡፡ ይኼ የሚያሳየው ማኅበራዊ ዋስትናው በጠንካራ የባህል ሞራል ላይ የተገነባ መሆኑን ነው። የባህሉ ትልቅነት የፈጠረው የሞራል ልዕልና ነው፡፡
እኔ የወጣቶቻቸውና የጎረምሶቻቸው ሁኔታ ይገርመኛል፡፡ የበላይነትን እንዲሁም ጉልበትና ኃይላቸውን የሚገልጹት በስራ ፍቅር፣ ቤተሰብን በማገዝ … በመሰል ነገሮች እንጂ እርስ በርስ በመደባደብ፣ በቅሚያ፣ በዝርፊያ፣ … አይደለም። እነዚህ ነገሮች ዋነኛ መነሻቸው ባህል ነው፤ የአባቶታቸው ትውፊት፡፡ የአባቶቻቸውን መልካም እሴቶች ማስቀጠል በመቻላቸው ያገኙት ልዕልና ነው፡፡ ከተሜነት ይህን ይበርዛል፣ ከተሜነት ቆቅ መሆን ነው፡፡ ከተሜነት የሚሰብከው ያለመቀደምን ነው፡፡
የጎፋ ህዝብ ትሁት ነው፡፡ ከትህትና መገለጫ ውስጥ አንዱ በቋንቋ    ው “ኤሮ” ይላል፡፡ “ኤሮ” -እሺ! ማለት ነው፡፡፡ አንድን ጎፋ ስታወራው በየደቂቃው “ኤሮ፣ ኤሮ” እሺ! እሺ! ይላል፡፡ እንቢ የለም፤ ሁሉንም ነገር እሺ! ነው፡፡ ማድረግ የማይችለው ነገር እንኳ ሲኖር “እሺ! አደርገዋለሁ፡፡ ነገር ግን እንዳላደርገው የሚያግደኝ ነገር አለ …. ብሎ የማይችልበትን ምክንያት ይገልጻል እንጂ “እንቢ” ብሎ አይጀምርም፡፡ ይህ የትህትናው መገለጫ ነው፡፡
የጎፋ ህዝብ በማህበራዊ ህይወት፣ በሰላምታ ይረበሻል፡፡ ለምሳሌ ሰላም ይልሃል፣ ዝም ትለዋለህ። መልስ ያልሰጠኝ ሳይሰማኝ ነው ብሎ ስለሚያስብ ቆይቶ ሰላም ይልሃል፣ ዝም ትለዋለህ፡፡ ከዚህ በኋላ አይታገስም፡፡ ምንድነው? የበደልኩት ነገር? በማለት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የበደለህን ነገር ስትነግረው ይገባል፡፡ እኔ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ የተጣሉ ሰዎች እንኳ ሰላም ሲባባሉ አያለሁ፡፡ እኔ ባደግሁበት አካባቢ የጠብ መገለጫው ያለመነጋገርና መኳረፍ ነው፡፡ በጎፋ ህዝብ ዘንድ ይህ የለም፡፡ “አሻም” ሲልህ “አሻም” ብለህ፣ “ሃይ መላ ሰሮ” ሲልህ “ሰሮ” ብለህ መልስ መስጠት አለብህ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ኩርፊያ። በእርግጥ ኩርፊያ እንዳይኖር የሚያደርግ ማኅበራዊ ትስስር አለ፡፡ ጎሳዊ መዋቅር ስላለ አንተ በዳይ ሆንክ ማለት ጎሳህ በዳይ ሆነ፣ እንደበደለ ኖረ ማለት ነው። ስለዚህ ያንተ በደል ስርየት የሚያገኘው ወይም የበደልከውን ይቅር እንድትለው የሚፈልገው፣ በዳዩ ብቻ አይደለም፣ የጎሳህም አባል ነው፡፡ ወንድሞችህ፣ እህቶችህ፣ አጎቶችህ፣ አክስቶችህ … የአክስቶችህ የአጎቶችህ ልጆች ጭምር ናቸው፡፡
የጎፋ ህዝብ ምንም ቢሆን መስቀልን ከእነቂሙ አያከብርም፡፡ በመስከረም ውስጥ አዲሱን ዓመት ሲቀበል፣ ቂሙን ክረምት ውስጥ ያራግፈዋል፡፡ ቂም ይዘህ ተጣልተህ ተራርቀህ የበደለ ዘመድህን በዓይነ ቁራኛ እያየህ መስቀልን አታከብርም፡፡ መታረቅ አለብህ፡፡ በጣም ጠንካራ ቂመኛ ከሆንክ ቂም የመያዝ አቅምህ 12 ወራት ነው፡፡ መስከረም 20ዎቹ ውስጥ የያዝከውን ቂም እንደፈለክ አድርገህ ብታቆየው ከሚቀጥለው ዓመት መስከረም 10 በላይ አይሻገርም፤ ያበቃል፤ “ዮ ማስቀላ መጣ፣ ዳናው ዳና አልባሱ ማዳ ዳና” በማለት የመጣለት በዓል ስለሆነ ይህንን በዓል በነበረብህ ቁርሾ፣ ቅሬታ፣ ደስ ባላለህ መንፈስ፣ አትቀበለውም፡፡ ሀዘን እንኳ መስቀልን አያደበዝዘውም፡፡ የመስቀል ዕለት ሰው ቢሞት አይለቀስም፣ አይቀበርም፡፡ “መስቀል በላ” ይባልና ህይወት በቀደመው መልኩ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም፣ ተለምኖ፣ ተናፍቆ “ዮ ማስቃላ!” ተብሎ የተገኘ በዓል ስለሆነ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በጎፋ ህዝብ ዘንድ መስቀል እጅግ የተለየ ትርጉም አለው፡፡   

Read 3482 times