Monday, 10 October 2016 07:04

‹‹ይሄ ወጣት ቴአትር ቢማር ምን ይመስላችኋል?›› - ቀዳማዊ ኃይለስላሴ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

      ሀረር ውስጥ ጎረጉቱ በተባለ ቦታ ተወልደው ደደር በተባለች ከተማ አደጉ፡፡ የቄስ ትምህርታቸውን እስከ ዳዊት በዚህችው ከተማ ተከታትለው በስምንት አመታቸው ለዘመናዊ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ፣ በባቡር መጡ የዛሬው እንግዳችን ደራሲ ተርጓሚ፣ ገጣሚ ተዋናይና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ፡፡ እኒህ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰው በቅርቡ 80ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በድምቀት ያከበሩ ሲሆን የልደት በዓል አከባበራቸው ተከታይ ክፍል የሆነው የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና እንዲሁም “ረጅም ጉዞ ወደ ነፃነት” የተሰኘው የማንዴላ የህይወት ታሪክ መፅሀፍ ምረቃ በቀጣዩ ሀሙስ ይካሄዳል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከፕሮፌሰር ተስፋዬ ጋር በህይወታቸው፣ ሙያቸውና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

         ከተወለዱበትና ካደጉበት አካባቢ  ለምን ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት?
ከትውልድ አካባቢዬ የመጣሁት አዳሪ ት/ቤት ለመግባት ነው፡፡ ከዚያ ተፈሪ መኮንን ገባሁ። ቀጥዬ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፤  በእኛ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሁለት ፋኩልቲ ብቻ ነበረው፡፡ ሳይንስና አርት ማለት ነው፡፡ በአርት ፋኩልቲ ውስጥ ጠቅላላ የአርት ትምህርቶች እንማርና ወደፊት የበለጠ ልትማሪ የምትፈልጊውን ትምህርት እንዲሁ ትማርያለሽ። ኢኮኖሚክስ፣ ህግ ሶሲዮዎሎጂና የመሳሰሉትን ትምህርቶች ማለት ነው፡፡ በወቅቱ እኔ ምርጫዬ ህግ ስለነበር ቅድመ ህግ ትምህርቶችን ተምሬ ነበር፤ ተቋረጠ፡፡
የህግ ትምህርቱ የተቋረጠው ሰምቻለሁ፡፡ “ኢዮብ” የተሰኘ ቴአትር ላይ ሲተውኑ ጃንሆይ ካዩት በኋላ ነው የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ ጉዳይ ያጫውቱኝ?
 የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከመመረቄ ቀደም ብሎ “ኢዮብ›› የተሰኘ ቴአትር ላይ ተዘጋጀና እኔ መሪ ተዋናይ ሆኜ ተጫወትኩ፡፡ አዘጋጁ የወቅቱ የፍልስፍና መምህራችን ነበረ፡፡ ይህ ቴአትር የተዘጋጀው ዛሬ ብሔራዊ ቲያትር እየተባለ የሚጠራው፣ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደተከፈተ አካባቢ ነው፡፡ ገና ሁለት ዓመቱ ነበር ከተከፈተ፡፡ ቴአትሩ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ከታየ በኋላ በቴአትር ቤቱ ለህዝብ ቢታይ ጥሩ ነው ተብሎ፣ ጃንሆይም ተጋበዙና ተመለከቱት፤ ወደዱት፡፡ በማግስቱ አስጠርተውኝ፤ ምን መማር እንደምፈልግ ጠየቁኝ፡፡ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትሩንም ፕሮቶኮሉንም የያዙት እሳቸው ነበሩ፡፡ ምክትል ሚኒስትሩ ደግሞ እንዳልካቸው መኮንን ነበሩ፡፡
ህግ መማር እፈልጋለሁ አልኩኝ፡፡ ጃንሆይም እንዳልካቸውን ‹‹ህግ የሚማሩ ስንት ልጆች አሉ-? ብለው ሲጠይቁ፤ ‹‹12 ያህል ይሆናሉ›› ብለው መለሱ፡፡ ‹‹ለህግ አስሩ ይበቃሉ፤ ይሄ ወጣት ግን ቴአትር ቢማር ምን ይመስላችኋል›› አሉ፡፡ እጅ ነሳሁ እንጂ ‹‹ይሄን አድርጉልኝ›› አላልኩም፡፡ በመጀመሪያ የእጅ ሰዓታቸውን ፈትተው ከሰጡኝ በኋላ፤ ‹‹አቶ እንዳልካቸው የፈለገው አገር ሄዶ የቴአትር ትምህርት እንዲማር ይሁን›› ብለው አዘዙ አሜሪካ ት/ቤት ተገኘና ሄጄ ተምሬ ማስተርሴን ይዤ ተመለስኩ፡፡
በአሜሪካ የነበርዎት የትምህርት ቆይታ ምን ይመስላል?
አሜሪካ ሄጄ ለመማር (የቅድመ ምረቃ) ትምህርት መውሰድ ነበረብኝ ይሄ በቴአትር ብቻ ነው፡፡ በሌላው ትምህርት የቢኤ ምሩቅ ነኝ አገሬ ላይ፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ሄጄ ልዩ ልዩ የቴአትር ትምህርቶችን ማለትም የንድፈ ሀሳብ፣ የታሪክና የተግባር ትምህርቶችን ተምሬ፣ ወደ ግራጁየት ኮርስ ለመግባት 1 ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡ ከዚያ ተፈትኜ ካለፍኩ በኋላ ነው፡፡ ይሄ የመሰናዶ ትምህርት መሆኑ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ቺካጎ ውስጥ ኖርዝ ዌስተርን ይባላል፡፡  ማስተርሴን ይዤ ወደ አገሬ ተመልሼ መስራት ጀመርኩ፡፡
እርስዎ በውጭ አገር ቴአትር ተምረው የተመረቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነዎት ማለት ነው?
እውነት ነው፤ የመጀመሪያው ነኝ፡፡
የተማሩት ቴአትር ቢሆንም ገጣሚም ተዋናይም፣ ደራሲም ተርጓሚም ነዎት፡፡ ስሜትዎ ለየትኛው የበለጠ ያደላል?
 እኔን ይገልፀኛል የምለው ትወና ነው፤ የምመኘውም እርሱን ነበር፡፡ የቴአትር ትምህርቱም ዕድል የተገኘው “ኢዮብ”ን መሪ ተዋናይ ሆኜ ስጫወት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ትወናው አደላለሁ፡፡  ነፍሴ ወደ ትወናው የበለጠ ታደላለች፡፡
እስኪ “ላቀችና ድስቷ” ስለተሰኘው የመጀመሪያ ቴአትርዎ ያጫውቱኝ?
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እያለሁ “አስናቀችና ድስቷ” የተሰኘ አጭር ልቦለድ በእንግሊዝኛ ፅፌ ነበር፡፡ እሱን ወደ ቴአትር ነው የቀየርኩት፡፡ ይህ ቴአትር ለምንማረው ትምህርት የኮርስ ማሟያ ጥናታዊ ፅሁፍ መፃፍ አለብሽ፣ ቴአትር ማዘጋጀት አለብሽ፤ እንደገና ለትወናውም በተግባር ተውነሽ ፈተናውን ማለፍ አለብሽ እነዚህን ካላሟላሽ ዲግሪሺን አታገኚም፡፡ ለዚያ ማሟያ ለፀሐፊ ተውኔትነት “ላቀችና ድስቷን ፃፍኩኝ፡፡
ዳይሬክት አደረግኩት፡፡ አንዱን ገፀ-ባህሪ ወክዬም ተጫወትኩ፡፡ ሶስቱንም ነገሮች ‹‹በአንድ ድንጋይ ሶስት ወፍ›› እንደማለት ነው፤ ‹‹የላቀችና ድስቷ›› ቴአትር ታሪክ፡፡
ከኦማርኻያም ታሪክና ግጥሞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለዎት ይታወቃል፡፡ ግጥሞቹንና የህይወት ታሪኩን መተርጎምዎ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ግን የስብሀት ገ/እግዚአብሄር ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ምን ነካሽ? ስብሀት እኮ የአማር ኻያምን ሩቢያቶች ማለትም እንግሊዝኛውን በቃሉ ነው የሚያነበንባቸው፡፡ የኦማር ኻያምን ስራዎች በዓለም እንዲታወቁ ያደረጋቸው ተርጓሚው በጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መተርጎሙ ነው፡፡ ስብሃት ሁሉንም ሩቢያቶች በቃሉ ይላቸዋል በእንግሊዝኛ ከተተረጎመ በኋላ ወደ ብዙ የዓለም ቋንቋዎች መተርጎም ጀመረ፤ ወደ ፈረንሳይኛ፣  ጀርመንኛና በሌሎችም ቋንቋዎች… እኔም እንደ አቅሜ ወደ አማርኛ ተረጎምኩት ማለት ነው፡፡ እሱ ግጥም አልችልም በሚል አልተረጎመውም፡፡ እኔና ስብሀት ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ትውውቅ አለን፡፡ እሱ ሃይለኛ አንባቢ ነው፡፡ እኔ እግር ኳስ፣ ሩጫና፣ መሰል ነገሮች ላይ አተኩራለሁ፡፡ እሱ ጥሩ ጥሩ ታሪክ ያለውን መፅሀፍ በመቃረምና በማንበብ ይታወቃል፡፡ ካነበበ በኋላ ለእኔም ያውሰኛል፡፡  እሱ አምስት ያነበበ እንደሆነ፣ እኔ አንድ አምስተኛውን ባነብ ነው፡፡ እና ያን ጊዜ ስብሀት የኦማር ኻያምን ስራዎች ባነበነበ ቁጥር፣ እኔ ወደ አማርኛ ስነ ግጥም ለመለወጥ ፍላጎቴ እየጨመረ መጣ ተረጎምኩኝ፡፡ የስብሃት ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡
ወደ ‹‹ሽልንጌ›› የአጭር ልብ ወለድ ታሪክ እንምጣና፤ በቀድሞ የአማርኛ መማሪያ መፅሀፍ ላይ የነበረው ይህ አጭር ልብ ወለድ ከእርሶ የህይወት ገጠመኝ ጋር ቁርኝት እንዳለው ሰምቻለሁ…?
ገጠመኙ ምን መሰለሽ ሀረርጌ ጎረጉቱት ነው የተወለድኩት ብዬሻለሁ፡፡ በስምንት አመቴ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለክረምት ትምህርት ሲዘጋ፣ በየዓመቱ ወደ ሀረርጌ ለእረፍት እሄዳለሁ። የምሄደውም የምመለሰው በባቡር ነው፡፡ ከእነዚህ ጉዞዎቼ በአንዱ ከሀረር ወደ አዲስ አበባ ስመጣ፣ ባቡሩ በየጣቢያው ይቆማል፡፡ መኤሶ ላይ ይመስለኛል፡፡ ባቡሩ ሲቆም ፓፓያ፣ ሙዝና መሰል ፍራፍሬዎችን የሚሸጡ ሴቶች አሉ ለተሳፋሪው፡፡ እኔ ፓፓዬ ገዛሁና ግማሹን ከፍዬ ሽልንግ ቀርቶብኛል ለካ… ባቡሩ ውስጥ ገብቼ ባቡረ ሲነሳ፣ የሸጠችልኝ ሴት ሱማሌ ትመስለኛለች፡፡ እጇን እያወናጨፈች ‹‹ሽልንጌን ሽልንጌን›› እያለች ስትጮህ፣ ባቡሩ ደግሞ ሸከተፍ ሸከፈት እያለ እልም አለ፡፡ እጄን ኪሴ ስከት ድፍን ሀምሳ ሳንቲሟ (ሽልንጓ) ቁጭ ብላለች፡፡ ምን ማድረግ እችላለሁ፡፡ ደንገጥኩ፡፡ ያቺ ገጠመኝ ወደ ልቦለድ ተቀየረች ማለት ነው፡፡
ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አቋቁመዋል፡፡ ሀገር ፍቅርና ብሄራዊ ቴአትርን በስራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሆነው አገልግለዋል … እና በስራዎ ደስተኛነዎት? የሚገባኝን ቦታ አግኝቻለሁ ብለው ያምናሉ?
እንዴታ! እንዴታ! የአገር ፍቅር ዋና ስራ አስኪያጅ ስሆን የሙያዬ ቁንጮ ላይ ደረስኩ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የአገራችን ነባር ቴአትር ቤት ሀገር ፍቅር ነው፡፡ የዚህ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ መሆን የሙያው ጫፍ ላይ መድረስ ነው ለኔ፡፡ ሌላው ደግሞ በትልቅነት፣ በዘመናዊነት ብሄራዊ ቴአትር ይበልጣል፡፡ በዚህ ቴአትር ቤትም ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኜ ስመረጥ፣ የሙያው ጫፍ ላይ ደረስኩ ማለት ነው፡፡ ይህን ስልሽ ሹመት የሙያ ስለሆነ ደስተኛ ነኝ የፖለቲካ ሹመትና ስልጣን አልመኝም፣ ምኔም አይደለም፡፡ በሙያ መሾም ራሱን የቻለ ትርጉም አለው፡፡ ሀገር ፍቅር ስራ አስኪያጅ እንድሆን የሾሙኝ ጃንሆይ ናቸው፡፡ የብሄራዊ ቴአትርን ደግሞ ደርግ ነው የሾመኝ፡፡ ስራ አስኪያጅነቱ የሙያ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ሹሞች፤ ከተሾሙ በኋላ ያሰራሉ እንጂ አይሰሩም፡፡ መድረክ ላይም አይወጡም፡፡ እኔ ግን አብሬ እተውናለሁ። አዘጋጃለሁ፡፡ ቴአትር እፅፋለሁ፡፡ አስተዳዳሪም ሰራተኛም ሆኜ ነው ሳገለግል የቆየሁት፡፡
በብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ይመስለኛል … ለአንጋፋ ባለሙያዎች ደሞዝ በመጨመርዎ የመገምገምና ከስራ የመሰናበት እጣ ገጥሞዎት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
ከስራ መሰናበት ሳይሆን ከስራ አስኪያጅነትና ከደሞዝ እርከን ዝቅ አድርገውኛል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ከቦታዬ አንስተው ወደ ቴሌቪዥን ቢሮ ላኩኝ፡፡ ሲልኩኝ ገና ቢሮ አልተሰጠኝም፡፡ “በቃ ቢሮ ስጡት” ተባለና ሄድኩኝ፡፡ ለብዙ ጊዜ ቢሮ ሳላገኝ እየፈረምኩ ብቻ እውጣ ነበር፡፡
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ (ብሄራዊ ቴአትርም) ሆነ የሀገር ፍቅር ሰራተኞች ገና ሲቆረቆር ጀምሮ … እነሱም ከልጅነታቸው ጀምረው ልጅነታቸውንና የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉት በነዚህ ቴአትር ቤቶች ነው፤ ደሞዛቸው ግን በጣም ትንሽ ነው። በወቅቱ አንድ የመንግስት ፖሊሲ ነበር፡፡ ምሩቅ የሆንሽበትን ወረቀት ካመጣሽ፣ የተሻለ ይከፈልሻል፤ በኛ ጊዜ BA ዲግሪ መነሻው 450 ብር ነው፡፡ MA ከሆነ 500 ብር፡፡ እነዚህ ወረቀት የሌላቸው ነገር ግን እድሜያቸውን ሙሉ ያገለገሉ ሰዎች ከ80 ብርና ከዚያ በታች ተነስተው 300 ብር ቢደርሱ ነው፡፡ ከዚያ በላይ አይከፈላቸውም በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ፣ በተውኔት እድሜያቸውን ሙሉ ያሳለፉ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከቴአትር ዲፓርትመንት ተመርቀው የሚመጡት በ500 ብር ይቀጠራሉ፡፡ እነ አውላቸው ደጀኔ፣ እነ ጌታቸው ደባልቄ፣ እነ አስናቀች ወርቁና መሰል አንጋፋዎቹ ትንንሽ ነው ደሞዛሞቸው፡፡ የጡረታ ጊዜያቸውም እየደረሰ በመሆኑ፣ በዚህ ትንሽ ደሞዝ ጡረታ ከወጡ ምን ሊበሉ ነው? የሚለው በጣም አሳሰበኝ። ቀድሞውኑ አዝማሪና የመድረክ ጥበብ ባለሙያ መብትም ሆነ የጡረታ መብት አልነበረውም፡፡ ይህ መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉ ተወጥቷል፡፡
እንደውም በዚህ ሰልፍ ላይ የህይወት መስዋዕትነት መከፈሉንም ሰምቻለሁ?
እውነት ነው፡፡ ለመንግስት ሰራተኛ ከጉልበት ሰራተኛ ጀምሮ የደመወዝ እርከን አለ፡፡ የነዚህኞቹ እርከንም ደረጃም የለውም፡፡ እኔ ደግሞ ‹‹ጀማሪ ተዋናይ››፣ ‹‹ተዋናይ›› ‹‹ብቁ ተዋናይ›› ከዚያ ‹‹ኮከብ ተዋናይ›› የሚል እርከን ሰራሁ፡፡ የሙዚቀኛንም እንዲሁ እርከን ሰራሁ፡፡ ለዚህ በጀት ስለማይመደብ በጡረታ የተገለሉና በሞት የተለዩ ሲኖሩ፣ የእነሱን ደሞዝ እጨፈልቅና የእድገት ኮሚቴ አቋቁሜ፣ ለእነዚህ አንጋፋዎች በተራ በተራ እየሰጠሁ፣ ሶስት ዓመት ያህል ዘለቅሁ፡፡ በ1975 ዓ.ም ተነቃብኝ፡፡ ‹‹ከየት አምጥተህ ነው ይህን ሁሉ ገንዘብ የሰጠኸው›› ስባል፣  እንዴት እንደሰጠሁ? ከእድገት ኮሚቴው  ጋር እንዴት እንደሰራነው ተናገርኩኝ፡፡ ይህ ደግሞ ከፖሊሲ ውጭ ነው፡፡ ሁለተኛ እኛን አላስፈቀድክም በሚል ከደረጃዬም ዝቅ አደረጉኝ፤ ከቦታዬም አንሰተው ወደ ቴሌቪዥን ላኩኝ፡፡ ደሞዜም ከ1400 ወደ 1085 ዝቅ አደረጉት፡፡ የመኪና አበልም ነበረን፤ አነሱት፡፡ ከዚያ ቴሌቪዥንም ገብቼ፣ አማካሪ ተባልኩና ከሰው ጋር ደባል ሆኜ ቢሮ ተሰጠኝ፡፡
አቤቱታ አላቀረቡም?
በኋላማ አቤት አልኩኝ፡፡ ደሞዜንም ደረጃዬንም አንዴት ዝቅ ታደርጋላችሁ? ብዬ ብጠይቅ፣ ‹‹1085 ብር እኮ የብርጋዴር ጀነራል ደሞዝ ነው፤ አነሳህ እንዴ›› ብለውኝ አረፉ (በጣም እየሳቁ) በእርግጥ የዛን ጊዜ ከሺህ ብር በላይ ማግኘት ብዙ ነው፡፡ ከዚያ ወደ ዩኒቨርሲቲ መጣሁ፡፡ እንዳልሺው … የባህል ማዕከሉንም አርኬስትራ ኢትዮጵያንም አቋቋምኩ። መምህር ሁኜ ሳገለግል ቆየሁ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ነበርኩ፤ ከዚያም ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆኜ ነው ጡረታ የወጣሁት፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ በስራዬ፡፡
በአብዛኛው ስራዎችም ሲደነቁና ሲወደሱ ይኖራሉ፤ ሆኖም ‹‹ተሃድሶ›› በተሰኘው ተዋናይንና ታዳሚን በሚያሳትፈው ቴአትርዎ ይወቀሳሉ፡፡ ይህን ቴአትር በተለይ ስለ ኢህአፓ የሚያነሳውን ሀሳብ ተከትሎ፣ ብዙ ወጣቶች መገደላቸውም ይነገራል፡፡ እስኪ በዚህ ላይ እናውራ?
ነገሩ ምን መሰለሽ … የዛን ጊዜ የነበሩ ካድሬዎችና ባለስልጣናት ወጣቱን፣ ህዝቡን፣ ስታዲየምና መሰል ቦታዎች ይሰበስቡና “በምታካሂዱት ነገር ስማችሁ ተጠቁሞ፣ በዝርዝር ተፅፋችኋል፣ ይህን አውቃችሁ በራሳችሁ ጊዜ ካልመጣችሁ ወዮላችሁ” ይሏቸዋል። ይሄ መላኩ ተፈራ ይጠቀምበት የነበረ የጎንደር ቴክኒክ ነው፡፡ እኔ በአብዮቱ በአራተኛ ዓመት ነው ተውኔቱን የፃፍኩት፡፡ እንዳልሺው ‹‹ተሀድሶ›› ነው የሚባለው። ደበበ እሸቱ ነው ቴአትሩን ያዘጋጀው። እነ ተክሌ ደስታ፣ እነ አለምፀሐይ ወዳጆ፣ ተውነውበታል። ኃይለኛ ቴአትር ነው። ዳራሹ ውስጥ ታደመው ህዝብ ልክ ስታዲዬም ና ተብሎ እንደተጠራው ህዝብ በርካታ ነው፡፡ ትወናው እንዳልሽው ተዋናይ ታዳሚ የሚሳተፍበት ነው። በያኔው ቋንቋ ለትግል የሚወጣው ‹‹የለውጥ ሀዋሪያ›› ይባላል፡፡ ተዋናዩ ይሄድና “አንተም እንደዚህ አድርገሀል” ይላል ታዳሚውን፡፡ ታዳሚው ደንግጦ፤ ‹‹ እኔን ነው?›› ማንን ነው? ይላል፡፡ ቴ
አትሩ በየክፍለሀገሩ ዞሯል እስከ ምፅዋ ድረስ ነው የታየው፡፡ ይሄ በ1971 ዓ.ም መጨረሻ ይመስለኛል፡፡ ትያትሩ እንግዲህ ሁለት ሰይፍ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢህአፓንና ፀረ አብዮተኞችን ማጋለጥ ነው። ሌላው ደግሞ እንዴት እንዲህ ያለ ኢ-ፍትሀዊ የሆነ ነገር በመንግስት በኩል ይሰራል? የሚለውን ያሳያል፡፡ ያን ጊዜ “ስምህ ተይዟል፤ ተጠቁመሀል” እያሉ ሰውን እየወሰዱ ይገድሉ ነበር፡፡ በዚህ ቴአትር ሁለቱንም ለማሳየት ተሞክሯል ሰው ግን ያየው አንዱን ወገን ነው፡፡ ግን ፀረ አብዮተኛውንም አብዮተኛ ነኝ ብሎ ሰው እየወሰደ የሚገድለውንም ነው ቴአትሩ የሚኮንነው፡፡ በዚህ ምክንያት ቴአትሩ ሁሉንም አጋልጧል፡፡ ሰው ፍ/ቤት ቀርቦ፣ ጠይቆ ጥፋተኛ ነህ ሳይባል የሚገደልበት፣ ቶርቸር የሚደረግበትና ያለጥፋቱ ወህኒ የሚወረወርበት አግባብ መኖር የለበትም፡፡ ፀረ አብዮተኛውም አግባብ ያልሆነ ነገር መስራት የለበትም እኔ የፃፍኩት ይሄንን ነው ሰው በገባው መጠን ተርጉሞታል፡፡ እኔ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ሰው መገደሉን አላውቅም፤ ነገር ግን ቴአትሩ ላይ “አንተ ነህ” ተብለው ሲጠሩ የወጡ፣ መታሰራቸውን አውቃለሁ፡፡ ሀረርጌ፣ ደብረ ብርሀን እና ብዙ ቦታ ታይቷል፡፡ እዛ ላይ እየወጡ የታሰሩና የሞቱ ካሉ፣ እኔ ሁሉን ልከታተልና ላውቅ አልችልም፡፡
ይህን ቴአትር ባልሰራሁት ብለው ተፀፅተው ያውቃሉ?
በፍፁም! እንዴት እፀፀታለሁ! እንደውም በሁለት በኩል የተሳለ ውጤታማ ስራ ነው የሰራሁት፡፡ በስኬቱ እደሰታለሁ እንጂ ልፀፀት አልችልም፡፡

Read 3988 times