Print this page
Monday, 10 October 2016 07:19

ዊኪሊክስ ስለአሜሪካ ምርጫጥብቅ ሚስጥር አወጣለሁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 10 ሚሊዮን ሚስጥራዊ መረጃዎች እንዳሉት አስታውቋል

      የመንግስታትንና የታላላቅ ተቋማትን ጥብቅ ሚስጥሮች ፈልፍሎ በማውጣትና በማጋለጥ የሚታወቀው የዊኪሊክስ ድረገጽ መስራች ጁሊያን አሳንጄ፣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተመለከተ ጥብቅ ሚስጥር በቅርቡ ይፋ አደርጋለሁ ማለቱን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘገበ፡፡
አሳንጄ የዊክሊክስን 10ኛ አመት የምስረታ በዓል በማስመልከት በቪዲዮ ሊንክ ባስተላለፈው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ መጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሚከናወንበት ከህዳር ወር መጀመሪያ በፊት ከምርጫው ጋር የተያያዙ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለአለም ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ዊክሊክስ ከዚህ በተጨማሪም በመጪዎቹ አስር ሳምንታት ውስጥ ከጦር መሳሪያዎች፣ ከጦርነቶች፣ ከጎግል ኩባንያና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አዳዲስ ጥብቅ ሚስጥሮችን በየሳምንቱ እንደሚዘከዝክና ይፋ የሚያደርጋቸው 10 ሚሊዮን ያህል ጥብቅ ሚስጥራዊ መረጃዎች እንዳሉት አሳንጄ ተናግሯል፡፡
ከሰሞኑ ዊኪሊክስ ከሂላሪ ክሊንተን ጋር በተያያዘ ጥብቅ መረጃ ያወጣል ተብሎ ቢጠበቅም ምንም ነገር አለማውጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣በሌላ በኩል አሳንጄ የሄላሪ ክሊንተንን የምርጫ ቅስቀሳ ለማደናቀፍ አሲሯል በሚል የሚናፈስበትን ሰሞንኛ መረጃ በዚሁ መግለጫው አስተባብሏል፡፡ አሳንጄ በቀረቡበት ክሶች ለስዊድን ተላልፎ እንዳይሰጥ በመስጋት፣ ከ2012 አንስቶ ለንደን ውስጥ በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሴ በጥገኝነት ተጠልሎ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

Read 2140 times
Administrator

Latest from Administrator