Sunday, 16 October 2016 00:00

1 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከየመን እስር ቤት አመለጡ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

- የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች እስረኞቹ እንዲያመልጡ ትብብር አድርገውላችዋል

    በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ገብተዋል በሚል በደቡባዊ የመን በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩ 1 ሺህ ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባለፈው ረቡዕ ሌሊት አምልጠው መጥፋታቸውን አንድ የአገሪቱ የደህንነት ሃላፊ ማስታወቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በህገወጥ መንገድ ወደ የመን ገብተዋል በሚል ሻባዋ በተባለቺው የአገሪቱ ግዛት ውስጥ ታስረው ከነበሩትና ወደ አገራቸው ሊመለሱ ከተዘጋጁት 1 ሺህ 400 ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል አንድ ሺህ የሚሆኑት ባለፈው ረቡዕ ሌሊት እስር ቤቱን ሰብረው በመውጣት መጥፋታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ስደተኞቹ እንዲያመልጡ ትብብር እንዳደረጉላቸው ተረጋግጧል ያለው ዘገባው፤ ስደተኞቹ በተቀናበረ መንገድ ካመለጡ በኋላም በተዘጋጀላቸው መኪና በቡድን በቡድን እየሆኑ በአቅራቢያ ወደሚገኙት ማሪብ እና ባይዳ የተሰኙ ግዛቶች መሄዳቸውን አስታውቋል፡፡ የየመን መንግስት ባለፈው ወር ብቻ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ገብተዋል በሚል ከ220 በላይ አፍሪካውያን ስደተኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ አገራቸው እንደመለሰ ያስታወሰው ዘገባው፤ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ጠቁሟል፡፡

Read 3937 times