Sunday, 16 October 2016 00:00

የቻይና ቢሊዬነሮችና ኩባንያዎቻቸው በዓለም እግር ኳስ ላይ….

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 በ900 ቢ.ዶላር በጀት፤ 20ሺ የእግር ኳስ አካዳሚዎች
                    እስከ 2025  50ሺ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ማፍራት
                    እስከ 2030  የዓለም ዋንጫን ማዘጋጀት…
                    ከ3 ቢ. ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት በአውሮፓ ክለቦች
                    የዝውውር ገበያውን የሚመራው  ሱፕር ሊግ
                    በብሄራዊ ቡድኑ  ግልፅ ያልሆነ የዓለም ዋንጫ ህልም…

     ቻይና እግር ኳስን ለመጀመርያ ጊዜ የፈጠረች አገር እንደሆነች በመጥቀስ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር / ፊፋ በታሪክ መዝገብ አስፍሯታል፡፡  በጥንታዊት ቻይና በ2ኛውና 3ኛው መቶ ክፍለዘመን በነበረው የሁ ዋን ስርወ መንግስት ‹‹ሱ ቹ›› በሚል ስያሜው ይታወቅ እንደነበር በመግለፅ ነው፡፡
ይሁንና በቅርብ ጊዜ ምናልባትም ከ20 ዓመታት በፊት እግር ኳስ በቻይናውያን ብዙም የማይዘወተር ስፖርት  ነበር፡፡  ባለፉት 3 ኦሎምፒያዶች በምትሰበስባቸው የሜዳልያዎች ብዛት  ከ1 እስከ 3  ደረጃ በምታገኘው ቻይና ተወዳጅ ከሆኑት  ስፖርቶች መካከል አትሌቲክስ፤ ጅምናስቲክስ፤ ማርሻል አርትስ ቴኒስ እና ባድሜንተን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ግን  በኢኮኖሚ፤ በፖለቲካ እና በስልጣኔ ዓለምን እየተቆጣጠረች የመጣችው ቻይና በእግር ኳሱም ኃያልነቷን ለማረጋገጥ በያዘችው አቅጣጫ ልዩ ትኩረት መስጠት ጀምራለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ስፖርቱ በመንግስት ከፍተኛ በጀት የተመደበለትና ፖለቲካዊ ድጋፍ የሚያገኝ፤ የቢሊዬነሮችና ኩባንያዎቻቸውን የኢንቨስትመንት ትኩረት የሚስብ፤ በቻይናውያን የሚዘወተር እና ተወዳጅነቱ በየጊዜው የሚያድግ፤ በስፖርት ኢንዱስትሪው ትርፋማ አቅጣጫዎች የሚታዩበት ሆኗል፡፡ ስለሆነም በመላው ቻይና የእግር ኳስ ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ እድገት ሊያሳይ የሚችልባቸው ምቹ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡
አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ በሆነችው ቻይና ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እና ታዳጊዎች ስፖርቱን የሚያዘወትሩ ሲሆን ፕሮፌሽናልነት ሙያቸው ያደረጉት ብዛታቸው  ከ7ሺ እስከ 50ሺ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።   ኔልሰን ስፖርት የተባለ ተቋም በቅርቡ በሰራው ጥናት እንደጠቆመው ባለፉት 3 ዓመታት ቻይናውያን  ለእግር ኳስ የሰጡት ትኩረት 4 በመቶ እድገት አሳይቷል። በሌላ በኩል በአፍሪካ፤ በኤስያ እና በካራቢያን አገራት የቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችና ባንኮች በስፖርት መሰረተልማቶችና በተለይ በስታድዬሞች ግንባታ እና እድሳት በርካታ ፕሮጀክቶችን  በስኬት በማከናወናቸው አገሪቱን በስፖርት ዲፕሎማሲው ትርፋማ እንድትሆን እያስቻላትም ነው፡፡ እግር ኳስ በቻይና ተወዳጅ እየሆነ ከመጣባቸው  ዓለም አቀፍ ተፅእኖዎች መካከል በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች  ዋና የገበያ መዳረሻ እየሆነች በመምጣቷ ነው፡፡   
በቻይና የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ከ127 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም የጣሊያኖቹ ክለቦች  ኢንተር ሚላን እና ኤሲ ሚላን እያንዳንዳቸው ከ106 ሚሊዮን በላይ ደጋፊዎች ማፍራታቸው እንደማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች መካከል በቻይና በሚያገኙት ተወዳጅነት ዙርያ ድምፅ ተሰብስቦ በተሰራ ጥናት 45.5 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚው የስፔኑ ላሊጋ ሲሆን፤ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ 35.7 በመቶ፤ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ 13.5 በመቶ እንዲሁም የጣሊያኑ ሴሪኤ 3.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት በተከታታይ ደረጃቸው ይቀመጣሉ፡፡ ከ30 በላይ የአውሮፓ ክለቦችን በአገሪቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች 70 ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ይከታተላሉ፡፡
የዚንፒንግ  ስትራቴጂ
የቻይና ፕሬዝዳንት ዛይ ዚንፒንግ እግር ኳስን አፍቃሪ ናቸው፡፡  ስፖርቱ ከፍተኛ እድገት አሳይቶ  ከዓለም የእግር ኳስ ኃያላን አገራት ተርታ አገራቸውን እንዲያሰልፋት ይፈልጋሉ። እስከ 2050 እኤአ ከዓለም እግር ኳስ ልዕለ ኃያላን ተርታ የምትጠቀስበትን ስኬትም ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ከ2 ዓመታት በፊት እግር ኳስ የመንግስታቸው አበይት የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ በመግለፅ 50 ነጥቦች በዝርዝር ያስቀመጠ  ስትራቴጂ  አውጀዋል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ እስከ 2025 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን የታቀደ ሲሆን፤ በቻይና መንግስት ከ900 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የተመደበለት ነው።  በእግር ኳስ ስፖርት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉና ለፕሮፌሽናል ደረጃ የሚበቁ 50 ሚሊዮን ታዳጊዎች እና ተጨዋቾች ለማፍራት፤ ብሄራዊ ቡድኖችና ክለቦች ከኤስያ አህጉር በውጤታማነታቸው ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱበትን ታሪክ ለመስራት ነው። በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ዛይ ዚንፒንግ ቻይና እስከ 2030 እኤአ የዓለም ዋንጫን የምታዘጋጅበት እድልንም አስበዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድናቸው የዓለም ሻምፒዮንነትን እንዲያሳካ ምኞታቸው መሆኑን በይፋ ሲናገሩም ዓለም ዋንጫን የምናሸንፈው ከ100ሺ በላይ ወጣት እና ምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ሲኖሩን ነው ብለዋል፡፡ በስትራቴጂው መሰረት የእግር ኳስ ስፖርት በአንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በካሪኩለም ደረጃ ተቀርፆ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ የቻይና ትምህርት ሚኒስቴር እስከ 2017 መጨረሻ 20ሺ የእግር ኳስ ትምህርት ቤቶችን በመላው አገሪቱ ገንብቶ የሚያጠናቅቅ ሲሆን በ2025 እኤአ የትምህርት ቤቶቹ ብዛት ወደ 50ሺ የሚያሳድግ ይሆናል፡፡ 20ሺዎቹ የእግር ኳስ ማሰልጠኛዎች እና አካዳሚዎች ከ70ሺ በላይ የእግር ኳስ ሜዳዎችን በመያዝ እስከ 50ሺ ወጣቶችና  ታዳጊዎችን የሚያሳተፉ ናቸው፡፡
የቻይና ቢሊዬነሮችና ኩባንያዎቻቸው
በተለያዩ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት መስኮች በዓለም ዙርያ ግንባር ቀደም ሆና የቆየችው ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ  በዓለማችን ትርፋማ እና ተወዳጅ ስፖርት  በሆነው እግር ኳስ  ከፍተኛ  ተፅእኖ እየፈጠረች ነው፡፡ በርካታ የቻይና ቢሊዬነሮች እና ኩባንያዎቻቸው እየተከተሉት በመጡት አቅጣጫ ሲሆን፤ በአውሮፓ እግር ኳስ ኢንቨስትመንታቸው  ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል፡፡ በ2016 እኤአ  በ14 የአውሮፓ ክለቦች የቻይና ቢሊየነሮች እና ኩባንያዎቻቸው በተለያየ ደረጃ የባለቤትነት ድርሻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ በ2014 እኤአ ላይ በአውሮፓ እግር ኳስ በቻይናዊ ኩባንያ የተያዘ ክለብ ብቸኛው ክለብ በሆላንድ ኤርዲቪዜ የሚወዳደር ክለብ ነበር፡፡  በክለቦች ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን በስፖርት ማርኬቲንግ ፤ ብሮድካስት፤ የውድድሮች መስተንግዶ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመንቀሳቀስም ላይ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ የስፖርት ኢንዱስትሪ  የጎላ ድርሻ እያበረከቱም ናቸው፡፡
የቻይና ቢሊዮነሮች እና ኩባንያዎቻቸው በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በሚገኙ ክለቦች ኢንቨስትመንታቸውን  እያጠናከሩ የመጡት ባለፉት ሁለት ዓመታት ነው፡፡ በተለይ በጣሊያን የሚላን ከተማ ክለቦችን ኢንተር ሚላንና ኤሲ ሚላን፤ በስፔኖቹ ክለቦች እስፓኞልና አትሌቲኮ ማድሪድ፤ በእንግሊዞቹ ክለቦች አስቶን ቪላ፣ ማንችስተር ሲቲ፤ ዎልቨር ሃምፐተንና ዌስት ብሮሚች እንዲሁም በፈረንሳይ በሚገኙ ክለቦች የባለቤትነት ድርሻ ይዘዋል፡፡
የእንግሊዙን ክለብ አስቶን ቪላ በ86 ሚሊዮን ዶላር የግላቸው ያዳረጉት ባለሃብት ከሬኮን ግሩፕ ዶር ቶኒ ዚያ  ናቸው፡፡ በቻይና ቁጥር ሁለት ደረጃ የተሰጣቸው ባለሃብትና የዳሊያን ዋንዳ ግሩፕ  ባለቤት የሆኑት ዋንግ ጂያኒል በስፔኑ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ በ52 ሚሊዮን ዶላር  20 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ በቻይና እውቅ የመኪና አምራች የሆነው ራስተር ግሩፕ ደግሞ በሌላው የስፔን ክለብ ኢስፓኞል በ60 ሚሊዮን ዶላር 56 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በጣሊያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን የሱኒንግ ዛንግ ጂ ዶንግ ኩባንያ ባለቤት በ307 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት 55 በመቶ የባለቤትነት ድርሻቸውን  የያዙ ሲሆን፤ ከቻይና ቢሊዬነሮች እና ኩባንያዎቻቸው ትልቁ የእግር ኳስ ኢንቨስትመንት የተባለው ሜንላንድ ኮንሰርቲዬም የተባለው ኩባንያ በጣሊያኑ ክለብ ኤሲ ሚላን ኢንቨስት ያደረገው 821 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በሌላ በኩል የቻይና ሚዲያ ካፒታል የተባለው ኩባንያ በእንግሊዙ ክለብ ማንሲቲ 11 በመቶ አክሲዮን በመግዛት እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል፡፡   በፈረንሳይ አይዲጄ ካፒታል ፓርትነርስ  በኦሎምፒክ ሊዮኔስ 112 ሚሊዮን ዶላር፤ ቴክ ፕሮ ቴክኖሎጂ ዴቨሎፕመንት በሶሾክ ኤፍሲ 8 ሚሊዮን ዶላር፤ በእንግሊዝ ላይ ጎውቻን ሌድ ግሩፕ በዌስትብሮሚች አልቢዮን  230 ሚሊዮን ዶላር እና ፎስዋን ኢንተርነናሽናል በዎልቨርሃምፕተን 40 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቻይና እስከ 600 ቢሊየነሮች የሚገኙባት አገር መሆኗን የጠቀሰ ዘገባ ከ30 በላይ ቢሊየነሮችና ኩባንያዎቻቸው በእግር ኳስ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በማውሳት በቀጣይ በአውሮፓ ክለቦች ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉት እየጨመሩ እንደሚሄዱ አመልክቷል፡፡  ሊቨርፑል እና አርሰናል በቻይና ባለሃብቶች የቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው ከሚገኙ ትልልቅ የእንግሊዝ ክለቦች ሲገኙበት፤ በቅርቡ 1 ቢሊዮን ፓውንድ የዋጋ ግምት ያለውን ሊቨርፑል ለመግዛት የቻይና ባለሃብቶች ያሳዩት ፍላጎት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በአንድ ወቅት ሲናገሩ የቻይና ገንዘብ መላው የአውሮፓ ክለቦችን ወደ ሩቅ ምስራቅ የማስኮብለል አቅም አለው በሚል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኙና በአውሮፓ እግር ኳስ ተፎካካሪ ለመሆን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸው በርካታ  ክለቦች በዚሁ አቅጣጫ ትኩረት ለማግኘት መጣራቸውም ይወሳል፡፡ በአንዳንድ የአውሮፓ ሊጎች ደግሞ ከክለቦች ባለቤትነት ባሻገር የቻይና ቢሊዬነሮች እና ኩባንያዎቻቸው በውድድር አስተዳደር፤ በቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ በስፖርት ትጥቅ እና መሰረተልማቶች እንዲሳተፉ ፍላጎትም ተፈጥሯል። የቻይና ቢሊዮነሮች እና ኩባንያዎቻቸው በዓለም እግር ኳስ ላይ የያዙት መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት በአገራቸው የስፖርት ኢኮኖሚን ለማስፋፋት እና የሊግ ውድድርን ለማጠናከር  ብቻ ሳይሆን እግር ኳሱ ከፍተኛ እድገት ካስመዘገበባቸው በስፖርት አስተዳደር ያሉ ባለሙያዎችን፤ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችንና አሰልጣኞችን በማፍለስ ጠቃሚ ተመክሮዎችን ለመቅሰም እንደሆነም  ይገለፃል። በተለይ በትርፋማው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ  የቻይና ቢሊየነሮች እና ኩባንያዎቻቸው ማተኮራቸው ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ሞዴል በቻይና የስፖርት ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር በማቀድ ነው፡፡ በተጨማሪም   የኩባንያዎቻቸውን ብራንድ  ለማሳደግ እና ገበያቸውን ለማስፋት ውጥን አላቸው።   በስፖርት  ትጥቆች እና ቁሳቁሶች አምራችነት እና አቅራቢነት የሚኖራቸውን የገበያ ድርሻ ለማስፋፋት፤ በግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለመሳተፍ እና  በስፖርት የብሮድካስት ኢንዱስትሪው ዘልቆ ለመግባት ተስፋም ያደርጋሉ፡፡  በነገራችን ላይ በስፖርት ብሮድካስት ኢንዱስትሪው  የቻይና ኩባንያዎች ኢንቨስት  እያደረጉ ሲሆን አሊባባባ ስፖርት ከአሜሪካው የእግር ኳስሊግ ኤን ኤፍ ኤል፤ ሌኮ ስፖርትስ ከጣሊያኑ ሴሪኤና ከእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ፤ ፒፒቲቪ ከስፔኑ ላሊጋ፤ ቴሰንት ኦንላየን ከአሜሪካው የቅርጫት ኳስ ሊግ ጋር ተሻርከው መስራት መጀመራቸው ይጠቀሳሉ፡፡
የዝውውር ገበያን የሚመራው
 ሱፕር ሊግ
የቻይና ሱፕር ሊግ ባለፉት 5 ዓመታት ከፍተኛ  እድገት እያሳየ ነው፡፡ በኤስያ  የእግር ኳስ ገበያ ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ የሚገኘው ሱፕር ሊጉ ከ12 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ነው፡፡ የቻይና ወጣቶችን ተሳትፎ በማጠናከርና ከመላው ዓለም እውቅ ፕሮፌሽናሎች በማሰባሰብ  የሊጉ ክለቦች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ስፖርቱ በየስታድዬሞቹ በቂ ተመልካች እንዲኖራቸው በማስቻል በቻይና የስፖርቱን ተወዳጅነት እያሟሟቀው ይገኛል። በቲቪ የስርጭት መብት በሚያስገባው ገቢም ተሳክቶለታል። በትራንስፈር ማርከት ድረገፅ በቀረበው መረጃ መሰረት 16 ክለቦችን በሚያወዳድረው  ሱፕር ሊግ የሚሳተፉት 476 ተጨዋቾች አጠቃላይ የዋጋ ተመናቸው ከ329 ሚሊዮን ዶላር  በላይ ነው፡፡ በ1.25 ቢሊዮን ዶላር የቲቪ ስርጭት መብቱን ለ5 ዓመታት የሸጠው ሱፕር ሊጉ በሚያገኘው የቲቪ ተመልካች ብዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ 6ኛ ሲሆን በ2016 እኤአ ብቻ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግቧል፡፡
የቻይና ሱፕር ሊግ ለታዋቂ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በሩን ክፍት በማድረግም ትኩረት ስቧል፡፡ በሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስባቸው 5 ፕሮፌሽናሎችን ከሌሎች አገራት እንዲያካትቱ የሚፈቅድ ደንብ ያለ ሲሆን በ1 ጨዋታ አራቱን ማሰለፍ ይችላሉ፡፡  በቻይና ሱፕር ሊግ በደቡብ አሜሪካ፤ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ፤ በአውሮፓ፤ በኤስያ እና በአፍሪካ ከሚገኙ ከ40 በላይ አገራት የተውጣጡ ፕሮፌሽናሎች በመጫወት ላይ ናቸው፡፡ ከ170 በላይ ፕሮፌሽናሎች በሊጉ ክልቦች በማሰማራት ብራዚል ግንባር ቀደም ናት። እያንዳንዳቸው ከ30 በላይ ፕሮፌሽናሎችን በማቅረብ ከደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና ከአውሮፓ ሰርቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ ከምእራብ አፍሪካ ደግሞ ከናይጄርያ ከ25 በላይ፤ ከሴኔጋል እና ከካሜሮን ከእያንዳንዳቸው ከ10 በላይ ፕሮፌሽናሎች በቻይና ክለቦች ተቀጥረዋል፡፡ በሱፕር ሊጉ ተወዳዳሪ ከሆኑ ክለቦች መካከል በውድ የዝውውር ክፍያ ከተገዙ የዓለማችን ምርጥ ፕሮፌሽናሎች መካከል  የሚጠቀሰው ከራሽያው ክለብ ዜኒት ፒተርስበርግ በመልቀቅ ወደ ሻንጋይ ሲፒግ ክለብ በ83.1 ሚሊዮን ዶላር የፈረመው የ29 ዓመቱ ብራዚላዊ ጂያቫኒልዶ ቪዬራ ደ ሱዛ ወይም ሃልክ ነው፡፡ በ2016 የውድድር ዘመን ብቻ በእግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ በሱፕር ሊጉ የሚወዳደሩ የቻይና ክለቦች ከ440 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት በዓለም እግር ኳስ ግንባር ቀደም ሆነዋል፡፡  ከአውሮፓ 5 ታላላቅ  ሊጎች ሁሉ የላቀ ኢንቨስትመንት ሲሆን፤  በተመሳሳይ የዝውውር ገበያ ወቅት በእንግሊዝ ያሉ ክለቦች 354 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ማድረጋቸውን በማነፃፀር መረዳት ይቻላል፡፡
የቻይና እግር ኳስ ያድጋል ወይ…
የቻይና ቢሊየነሮች እና ኩባንያዎቻቸው በዓለም እግር ኳስ ላይ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተፅእኖ በመፍጠራቸው  አነጋጋሪ ቢሆኑም ይህ አቅጣጫ ለቻይና የእግር ኳስ እድገት የሚኖረው ፋይዳ የሚያከራክር እየሆነ ነው፡፡ በተለይ ገንዘብ ስኬትን ሊገዛ አይችልም የሚሉ ተቺዎች ለስፖርቱ ያለው ፍቅር የማያድግ ከሆነ የቻይና እግር ኳስ የትም አይደርስም እያሉ ናቸው፡፡ ከስፖርቱ ኢንቨስትመንት  ጎን ለጎን የአገሪቱ እግር ኳስ ሊያድግ የሚችልበት እድል ጠባብ ነው በሚል የሚቀርበው  ትችት የቻይና ሁለገብ ልዕለ ኃይልነት ካለመቀበል የተፈጠረ የፖለቲካ አጀንዳ እየመሰለ ነው፡፡
በፊፋ ወርሃዊው የዓለም እግር ኳስ ደረጃ ላይ በወንዶች ብሄራዊ ቡድን ቻይና የምትገኘው 78ኛ  ላይ ነው፡፡ ይህን ለመቀየር በርካታ የልማት እና አስተዳደራዊ ተግባራት እንደሚያስፈልጓት ይገለፃል፡፡ በተለይ ከሰሞኑ ብሄራዊ  ቡድኑ በ2018 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በሽንፈት መጓዙን ሲቀጥል የነበሩ ቅሬታዎች አገርሽተዋል።  ዋና አሰልጣኙ ሃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ  በብሄራዊ ቡድኑ ደካማ ውጤት ዙርያ በየጊዜው የሚገለፁ አስተያየቶች ሰሞኑን ከየአቅጣጫው እየጎረፉ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያው የ4ኛ ዙር ጨዋታ የቻይና ብሄራዊ ቡድን በሜዳውና በ40ሺ ደጋፊዎቹ ፊት  በሶርያ 1ለ0 መሸነፉ ተከትሎ በቻይና የእግር ኳስ አብዮት ስኬታማነት ላይ አዳዲስ ጥያቄዎችም ተፈጥረዋል።
ቡድናቸው ባልተረጋጋችው እና በእግር ኳስ ደረጃዋ 114ኛ ላይ በምትገኘው ሶርያ በመሸነፉ ሆድ የባሳቸውና የተበሳጩ ቻይናውያን ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። ብዙ ዘገባዎች የቻይና የዓለም ዋንጫ ህልም እንዳበቃለት ቢዘግቡም ቀሪ የ6 ዙር ጨዋታዎች መኖራቸውን ያገናዘቡ አይደሉም፡፡ የእንግሊዞቹ ዘ ሰን ፤ ዘ ጋርድያን እና ቢቢሲ የቻይና እግር ኳስ ቀውስ ላይ መሆኑን በሚያወሱ ዘገባዎቻቸው ሰሞኑን ቢወጡም የቻይና መገናኛ ብዙሃናት ትችቶቹ እውነት ያልሆኑ፤ ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው ናቸው በሚል አጣጥለዋቸዋል፡፡ በተለይ ብሄራዊ ቡድኑ ለውድቀት የተዳረገው ከልክ ያለፈ ወጭ እና ደሞዝ በሚከፈልበት የቻይና ሱፕር ሊግ ብቁ ተጨዋች ለማፍራት  ስለማይቻል ነው በሚለው ትችት በእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንም ላይ የሚታየው ተመሳሳይ ችግር በቻይና መግነኑ ተገቢ  አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫን በ48 ብሄራዊ ቡድኖች ለማካሄድ በፊፋ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የቀረበው ሃሳብ ለእነቻይና ተስፋ የሚፈጥር በሚልም ያሾፉም ዘገባዎች ተስተውለዋል። ቻይና በዓለም ዋንጫ አንዴ የተሳተፈች ሲሆን እሱም በ2002 እኤአ ላይ ጃፓንና ኮርያ በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ነበር፡፡
በኤስያ የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላቸው ጃፓን፤ ሰሜን እና ደቡብ ኮርያ መሆናቸውን በመጥቀስ ምሬታቸውን ያወሱት የቻይና ሚዲያዎች በበኩላቸው በአገሪቱ እግር ኳስ በታዳጊዎች እና ወጣቶች ፕሮጀክቶች ደካማ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በስፋት እና በተደጋጋሚ እየተቹት  ናቸው፡፡ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት፤ የውጭ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ግዢ በማብዛት በሚካሄደው ሱፕር ሊጉ ላይ ያነጣጠሩ ትችቶችም አሉ፡፡
በሱፐር ሊጉ ያሉት ክለቦች ለብሄራዊ ቡድኑ መጠናከር የጎላ አስተዋፅኦ እንደሌላቸው በመጥቀስ የሚነቅፉት ዘገባዎች ሊጉ በአገር ውስጥ ስታድዬም የሚገቡ ተመልካቾችን በማብዛት እና የቲቪ ስርጭትን በማጠናከር ጉልህ ውጤቶች ቢስተዋሉበትም በአህጉራዊ የክለብ ሻምፒዮናዎች ላይ ቻይናን በመወከል የሚሳተፉ የሱፕር ሊጉ ክለቦች የረባ ውጤት አለማስመዝገባቸው ጥያቄዎችን ያስነሳል ይላሉ፡፡

Read 2702 times