Sunday, 16 October 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የስልጣን ፍላጎት የሌለው አካል መቋቋም አለበት”
አቶ ወንድወሰን ተሾመ (የኢዴፓ አመራር)
የነዚህ ቀውሶች መነሻ ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ወደ መፍትሄው ለመሄድ ከተፈለገ ግን የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት የሌለው አካል መቋቋም አለበት፡፡ ውይይቶች በስፋት ከተደረጉ ብዙ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ መንግስት አሁን ባለው ሁኔታ በመደበኛ ተግባሩ ላይ ቀጥሎ ሂደቱ መካሄድ አለበት እንጂ የሽግግር መንግስት ምናምን የሚለው የማያስኬድ ነው፡፡ ለስልጣን ፍላጎት የሌለው ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ፣ ብሄራዊ እርቅ ላይ ጠንከር ተብሎ መሰራት አለበት፡፡ “መንግስት የመፍትሄው አካል መሆን የለበትም፣ የሽግግር መንግስት ይቋቋም” በሚለው ሃሳብ አልስማማም፡፡ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ቢባል ማን ነው የሚያቋቁመው? ስለዚህ አንድ ነፃ አካል የግዴታ መቋቋምና ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበትን እድል መክፈት ያሻል እንጂ ይህ ስርአት እንደወደቀ አድርጎ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት የሚለው እኔ ብዙም አይታየኝም፡፡

===========================

“ተቃውሞ የሚገታው ጥያቄዎችን በመመለስ ነው”

በላይ ማናዬ (ጋዜጠኛና ጦማሪ)
በኔ ግምት የተቃውሞዎቹ መነሻ የመብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ህዝቡ የመብት ጥያቄ ማንሳቱ ደግሞ የተነፈጉ መብቶች መኖራቸውን ነው የሚያመለክተው፡፡ ጥያቄዎቹ በሰላማዊ መንገድ ነበር የተጀመሩት፡፡ መንግስትም ህገ መንግስታዊ ናቸው ብሎ ያመነበት ሁኔታ ነበር፡፡ በተለይ የማስተር ፕላኑን ጉዳይ በተመለከተ በአግባቡ እያወያዩ ለህዝቡ ምላሽ በመስጠት ረገድ የታየው ዳተኝነት የችግሩ መነሻ እንደነበር መንግስት ራሱ ሲገልፅ ነበር፡፡ ስለዚህ በኔ እምነት የእነዚህ ሁሉ ተቃውሞዎች መነሻ ህዝቡ የተነጠቀው መብት መኖሩ ይመስለኛል።
መንግስት ለነዚህ ተቃውሞዎች ምላሽ የሰጠበት መንገድ አጥጋቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡ በተለይ በሰለጠነ መንገድ ይበልጥ ውይይቶችን እየፈቀደ፣ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ያደረገው ጥረት ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚያም ነው ተቃውሞዎቹ እየበረቱ የሄዱት። የህዝቡ ተቃውሞ አሁን በያዘው ቅርፅና መልክ ወደተለያዩ ቦታዎች ሳይዳረስና ሳይስፋፋ፣ከህዝቡ ጋር በሰፊው ተነጋግሮ መፍትሄ ለመስጠት ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ የተቃውሞ ድምፆች በፓርላማው ሊኖር ይገባ ነበር፡፡ የህዝብ መተንፈሻ መኖር ነበረበት፡፡  ይህ በሌለበት ሁኔታ የታመቀ ነገር ይኖራል፡፡ የታመቀ ነገር ደግሞ ይፈነዳል፡፡ አሁን እያየን ያለነው እንዲህ ያለውን ነገር ነው፡፡
የዘገዩ ነገሮች እንዳሉ ባምንም አሁንም ቢሆን በትልቁ መፍትሄውን ማሰብ እንችላለን፡፡ ሁሉን አቀፍ ለውጥ የሚያመጣ መድረክ አዘጋጅቶ በውይይት መቀራረብ ያሻል፡፡
መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ ሊያበጅ ይችላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ረጅም ጊዜን ይወስዳል። በነዚህ ጊዜያት መንግስት የበለጠ ከህዝቡ ጋር መወያየትና ህዝቡን አዳምጦ ተገቢ ምላሾችን ሊሰጥ ይገባል፡፡ የተቃውሞዎቹ መግቻ ነው ብዬ የማምነው፣ከስር ከስር ጥያቄዎችን እየመለሱ መሄድ ነው፡፡  

============================

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ወደ መፍትሄው የሚወስደን መሆን አለበት”
ጁሃድ ሳዲቅ  (የጋዜጣ አምደኛ)

በእኔ እይታ አሁን ያለው ተቃውሞ ዋናው መንስኤ የዲሞክራሲ እጦት ነው፡፡ የመናገር፣ ሃሳብን የመግለፅ የመሳሰሉት መብቶች በሚገባ  በተግባር ላይ አልዋሉም፡፡ የፕሬስ ነፃነቱም በሚገባ አልተተገበረም። ዲሞክራሲ ሳይኖር ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር አይችልም፡፡ የሁሉም ነገር ዋና ማዕከል ዲሞክራሲ ነው፡፡ መንግስት ዲሞክራሲን ረስቶታል ማለት እንችላለን፡፡ ሁልጊዜ ስለ ልማት ብቻ ነው የሚነሳው፡፡ እርግጥ ልማትን ሁሉም ይደግፈዋል፤ ለሀገራችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ትልቁ ክፍተት ዲሞክራሲን ከልማት ጋር በሚገባ ማያያዝ አለመቻሉ ነው፡፡ መንግስት ለዚህ ቶሎ መፍትሄ መስጠት አለበት፡፡ ሌላው የፕሬስ ነፃነትን የተመለከተ ነው፡፡ በቅርቡ ሶሻል ሚዲያውን ዘግቷል። ያሉት ፕሬሶች መንግስት የሚገልፀውን ብቻ ዋቢ አድርገው የሚጠቀሙ ናቸው፤ ራሳቸው አጀንዳ ቀርፀው አይሰሩም። ህብረተሰቡ ከነሱ ያጣውን ለማግኘት ወደ ማህበራዊ ሚዲያው አዘንብሏል፡፡ የትኛውም ሰው ሃሳቡን የሚገልጽበት ነፃ መድረክ ሆኗል፡፡ ውጭ ሀገር ሆነው የሚፅፉ ሰዎች አሉ፡፡ ሰው የነሱን ሀሳብ ይከተላል፡፡ ለዚህ መፍትሄው መንግስት ፕሬሱን በሰፊው መክፈት ነው፡፡
በሌላ በኩል የምርጫ ስርአት መስተካከል አለበት። ተቃዋሚዎች የህዝብ ወኪልና ጆሮ እንደመሆናቸው ህዝባቸውን የሚወክሉበት በቂ ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ የወሰዱት የህጋዊነት ፍቃድ የግድግዳ ላይ ጌጥ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አሁንም መንግስት ወደ ድርድርና ንግግር መምጣት አለበት፡፡ ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሰፊ መድረክ መስጠት አለበት፡፡ ለሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ቦታ የማይሰጥ ከሆነ፣ ማህበረሰቡ ውጭ ወዳለው ተቃዋሚ ያዘነብላል፡፡ ውጭ ሀገር ያለው የፖለቲካ ቡድን ሀገር ውስጥ ካለው ጋር ብዙ ግጭቶች አሉበት፡፡ ህዝቡ ግን አማራጭ ሲያጣ ወደነሱ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎችን በሚገባ አቅርቦ መወያያት አለበት፡፡
ሌላው ተቃውሞዎቹ በሙሉ የመንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነፀብራቅ ናቸው። ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ጀምሮ እስካሁን ያለውን ችግር በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እየተቻለ ወደ ሌላ አቅጣጫ ነው የተመሩት፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊዎችም እርስ በእርሱ የተምታታ መረጃ ነበር ለህዝቡ ሲያስተላልፉ የነበሩት። በኦሮሚያ ኦፌኮ በተደጋጋሚ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ እንወያይ የሚል ጥሪ አድርጓል፤መንግስት ግን ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ በመጨረሻ ነው ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ያለው። ይሄን ካለ በኋላ ደግሞ በወቅቱ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የታሰሩት መፈታት ነበረባቸው። እነዚህ ሰዎች ማስተር ፕላኑን ነበር የተቃወሙት፤ ስለዚህ ሊፈቱ ይገባ ነበር፡፡ ለሟች ቤተሰቦችና ንብረት ለወደመባቸው ካሳ መክፈል ነበረበት፡፡ መንግስት ይቅርታ የጠየቀባቸውን ነገሮች በሚገባ ማስተካከል ሲገባው ዳተኝነት አሳይቷል፡፡  
አሁንም ከዚህ በኋላ ገዥውም ተቃዋሚውም ግልፅ ፖለቲካን ያራምዱ፡፡ የህብረተሰቡን ችግር ይስሙ፣ ይረዱ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ አገራችን ሙሉ ሰላም ያገኘችበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፤ ይሄ ያሳዝናል። ባለንበት ዘመን ይሄ መለወጥ አለበት፡፡ በውይይትና በምክክር ችግሮችን የመፍታት ባህል መዳበር አለበት። ሰው በመረጃ መበልፀግ አለበት። የተበላሸው የሚዲያ ምህዳር መስተካከል አለበት። መንግስት ችግሩን ብቻውን ለመፍታት መታገል የለበትም፡፡
ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን አለበት። ህዝቡ ስለሃገሩ ሁኔታ የማወቅ፣የመቆርቆር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡
ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማ የሚገቡበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ መንግስት፤ ህዝብ ዝም ቢልም እየታዘበው መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በሚገባ ወደ መፍትሄው የሚወስደን መሆን አለበት እንጂ ይበልጥ የሚያፍን መሆን የለበትም፡፡

Read 2762 times