Sunday, 16 October 2016 00:00

ሰመጉ በ25 ዓመታት ጉዞው - ጥረቶችና ተግዳሮቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

· የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት የምናደርገው መንግስትን ለማሳጣት ሳይሆን ጉድለቶች እንዲታረሙ ነው
· ከፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት፣ “ሁለተኛ ሪፖርታችሁን ወደ ጽ/ቤታችን እንዳትልኩ፤” ተብለናል
• ከመንግስት የተደረገልን ትብብር፣ ከእነጭራሹ ሳይዘጋን መቆየታችን ነው

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት እያከበረ ነው፡፡ በዚህ የሩብ ክፍለ
ዘመን ዕድሜው ለአገሪቱ ህዝቦች የሰብአዊ መብቶች መከበር ምን አስተዋጽኦ አበረከተ? አቅሙስ ምን ያህል ጎለበተ? በእነዚህ ዓመታት ተቋሙ ምን ተግባራትን አሳካ? ምን ተግዳሮቶችስ ገጠሙት?
ከመንግስት ጋር ያለው ግንኙነትስ ምን ይመስላል? የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ
የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብፅአተ ተረፈ ጋር በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

ሰመጉ ባለፉት 25 አመታት ያከናወናቸው አብይ ተግባራት ምንድን ናቸው?
ለህብረተሰቡ የሰብአዊ መብት ትምህርት ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ለመንግስት ባለስልጣናትም ስለ ሰብአዊ መብት ግንዛቤ ሰጥተናል፡፡ በሌላ በኩል የሰብአዊ ጥሰቶች በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሲደርሱ፣ መርማሪዎቻችን በመላክ አጣርተን በመሰነድ፣በቂ ማስረጃ እንደያዝን ስናረጋግጥ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርቶችን በማጠናቀር በኢትዮጵያ በሰፊው ይፋ ሲያደርግ የቆየ መንግስታዊ ያልሆነ ብቸኛው ተቋም ሰመጉ ነው፡፡ በ25 ዓመት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙት በመንግስት እርከን ላይ ባሉ አካላት በመሆናቸው የኛን ስራ ከባድ አድርጎት ዘልቋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 36 መደበኛ መግለጫዎችና 141 ልዩ መግለጫዎች ማለትም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ይፋ ያደረግን ሲሆን መደበኛ መግለጫዎች አጠቃላይ የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርቶቻችሁን ለማነው የምታቀርቡት?
አንደኛ ለመንግስት ነው የምንሰጠው፡፡ አግባብ ላላቸው እንደ ተወካዮች ም/ቤት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ጨምሮ ለየክልሉ መስተዳድር እናደርሳለን፡፡ በተጨማሪም ለህዝብም እናደርሳለን፡፡
በነዚህ አመታት ውስጥ ከሪፖርቶቻችሁ በመነሳት፣መንግስት የእርምት እርምጃ የወሰደበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው?
 ምንም ተቀብሎ ያስተካከለው የለም ብለን መደምደም አንችልም፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ ተቀብሎ አስተካክሏል ግን እነሱም ከበቂ በታች ነበሩ፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር በተፈጠረበት ጌድኦ ዞን፣ በተወሰኑ የብሄር አባላት ላይ ከዚህ በፊት ጥቃቶች ተፈጽመው እንደነበር ሪፖርት አድርገን ነበር፡፡ ቡሌ የሚባል አካባቢ በአብዛኛው በድርጊቱ የመንግስት ባለስልጣናት ስለመሳተፋቸው በቪዲዮ ማስረጃ ጭምር ያቀረብንበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ባለስልጣናቱ የወጣቶችን ድርጊት ከማስቆም ይልቅ ማበረታታትና በዝምታ ቆመው መመልከት መምረጣቸውን በቪዲዮ፣ በፎቶግራፍና በሰነዶች አረጋግጠን ይፋ አድርገን ነበር፡፡ በወቅቱ ከተወሰኑ ወራት በኋላ አጥፊዎች ተጠይቀዋል፡፡ መጠየቃቸው ምን ያህል በቂ ነው የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ፣ ለተጎጂዎች ካሳ መከፈሉን ግን በቂ ባይሆንም ሰመጉ በበጎ መልኩ እንደሚመለከተው ገልፀናል፡፡ ሌላው በተመሳሳይ በደቡብ ክልል የተፈፀመን የመብት ጥሰት ሪፖርት ማድረጋችንን ተከትሎ፣ አመራሮች የኛን ሪፖርት ጠቅሰው እርምጃ መውሰዳቸውን አስታውሳለሁ። በ25 አመት ውስጥ 141 ሪፖርቶችን ያወጣን ቢሆንም የማስታወሳቸው እነዚህን ሁለቱን የእርምት እርምጃዎች ነው፡፡
እኛ በመሰረቱ ሪፖርት የምናደርገው መንግስትን ለማሳጣት ሳይሆን ጉድለቶቹን አይቶ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ነው፡፡ መንግስት ሆይ፤ባለስልጣኖችህ በዚህ ቦታ እንዲህ አድርገው መብት ጥሰዋል፤ የእርምት ኢርምጃ ውሰድ ብለን የመምከር ስራ ነው የምንሰራው፡፡ መንግስት ሪፖርቶችን አይቶ እንደ መስታወቶቹ ቆጥሮን፣ በራሱ እርምጃ እንዲወስድ ነው ጥረታችን፡፡
ከመንግስት ተደረገልን የምትሉት ትብብርና ድጋፍ ምንድን ነው?
 በመንግስት የተደረገልን ትብብር እንግዲህ እንደምታየው እስከ መጨረሻው አልዘጋንም። አሁንም አለን፡፡ በርካታ ነፃ የሲቪክ ማህበራት ህልውናቸውን ሲያጡ እኛ ግን አሁንም አለን። በጣም ባለመኮርኮም እስካሁን በህይወት ለመኖራችን መንግስት አስተዋፅኦ አለው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በህግ ማዕቀፍ በኩል፣ በገንዘብ ድጋፍ፣ እውቅናና ማበረታቻ በመስጠት በኩል የተደረገ ትብብር የለም፡፡ እንደውም ከፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት፣ “ሁለተኛ ሪፖርታችሁን ወደ ጽ/ቤታችን እንዳትልኩ፤ ከላካችሁም እንመልስላችኋላን” ተብለናል። ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ እየተሻሻለ ሲሆን እናንተ ግን አጋናችሁ ነው የምታቀርቡት በሚል ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ቢስተካከሉ መልካም ነው፡፡
አባል የሆናችሁባቸው አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ማህበራት አሉ?
አዎ! አባል የሆንባቸው አለማቀፍ ተቋማት አሉ። አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ፌዴሬሽን የሚባል አለ፤ በ120 ሀገራት የሚንቀሳቀስ፣ 178 ተቋማትን የያዘ ነው፤ የዚህ አባል ነን፡፡ በቅርቡ ነው ሙሉ አባል የሆንነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ፕሮጀክት አባልም ነን፡፡ የዚህ ደግሞ መስራች አባልም ነን፡፡ የአለማቀፍ ፀረ ስቃይ ድርጅትም አባል ነን፡፡
ሪፖርቶቻችሁን ለተባበሩት መንግስታትና ለሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት የምታደርሱበት አሰራር አላችሁ?
አዎ!  እናደርሳለን፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እየደረሰ ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት እኛ መረጃዎችን የምናወጣው መንግስትን ለማሳጣት ሳይሆን ጉድለቶችን ለማመላከት ነው፡፡ ሁሉም አካላት በኢትዮጵያ ጥረት እንዲያደርጉ ግፊት እናደርጋለን፡፡ አሁን ደግሞ የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስትን ተቋማት በርን እያንኳኳን ነው፡፡
የተቋሙ ሁነኛ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
በተለይ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ በርካታ ባለሙያዎቻችንና መረጃዎቻችን ልክ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ በማስመሰል በመነገሩ፣ ተቋማችንን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ አዳክሞን ቆይቷል፡፡ ሌላው በ2001 የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ተፅዕኖ አሳርፎብናል፡፡ በተለይ በጀት ከውጭ አለማግኘታችን ጽ/ቤቶቻችን እንዲዘጉና በርካታ ሰራተኞችን እንድንቀንስ አድርጎናል፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ በአቅም ግንባታ ላይ አተኩረን እየሰራን ነው፡፡
አሁን የገቢ ምንጫችሁ ምንድን ነው?
አዋጁ ከውጪ ምንጮች ድጋፍ እንዳናገኝ መከልከሉ ብቻ ሳይሆን ከአዋጁ በፊት ከአባላት የተዋጣ 8 ሚሊዮን ብር በፍ/ቤት ውሳኔ ታግዶብን፣ ያንን ገንዘብ እስከ ዛሬ ማግኘት አልቻልንም፡፡ በዚህ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብናል፡፡ 90 በመቶ ከአገር ውስጥ የሚለውን ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም። ለጋሾች እንኳን ለኛ መዋጮ ሊያደርጉ ይቅርና ሻይ እንኳን አብሮን የሚጠጣ የለም ነበር፡፡ ከፍተኛ ፍርሃት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በኋላ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር አንድ ስምምነት ላይ ይደርሳል፡፡ ይህ ስምምነት አውሮፓ ህብረት ለሀገራቱ ከሚሰጣቸው የልማት ድጋፍ ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ለሲቪል ተቋማት እንዲውል የሚል ነው፡፡ መንግስት ይህን ስምምነት በመቀበሉ ከሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ሲቪል ሶሳይቲዎች ጋር በፕሮፖዛል ተወዳድረን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ለ22 ወራት የሚቆይ የ199 ሺህ ዩሮ የበጀት ድጋፍ ከህብረቱ አገኘን፡፡ በዚህ በርካታ ተግባራትን አከናወንን፡፡ ያ ካለቀ በኋላ ደግሞ እንደገና ተወዳድረን ለ30 ወራት የሚቆይ 250 ሺህ ዩሮ አግኝተን በሱ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይሄም በቂ ባለመሆኑ አሁን የተለያዩ የገቢ ማሰባሰብ ስራዎች ልንሰራ አስበናል፡፡
ለምንድን ነው ስያሜያችሁ ከ “ኢሰመጉ” ወደ “ሰመጉ” የተቀየረው?
አንድ ድርጅት በስሙ ላይ “የኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ ማስገባት ከፈለገ ቢያንስ በ5 የሀገሪቱ ክልሎች ጽ/ቤቶች ሊኖሩት ይገባል ይላል። እኛ ግን በነበረብን የአቅም ችግር ምክንያት ሌሎቹ ተዘግተው በ3 ክልሎች ብቻ ነበር ጽ/ቤቶች የነበረን። በዚያ የተነሳ ስማችን ተነጠቀ፡፡ እናም ሰመጉ ብለን ቀጠልን፡፡ ዛሬ 6 ፅ/ቤት ደርሰናል፤ ስለዚህ “የኢትዮጵያ” የሚለውን ለማስመለስ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሀገሪቱ አሁን የገባችበት ቀውስ፣ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅና በርካታ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የግዴታ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ መፍጠር እንዳለብን አምነን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሚከሰቱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ  ለማጣራት የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ተቃውሞ ምክንያት የደረሰውን የሰብአዊ ጥሰት ከ340 ወረዳዎች 33 ወረዳዎችን መርጠን የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት አውጥተናል፡፡ ቀጥሎም በሁለተኛ ዙር 24 ወረዳዎችን አጣርተን ሪፖርት አድርገናል፡፡ በአማራ ክልል ከወልቃይት ጋር በተያያዘ በጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳርና በሌሎች ቦታዎች ላይ ማጣራት አድርገናል፡፡ ችግሩ እነዚህን ሪፖርቶች እያቀናጀን ሳለ ኮንሶ ችግር ተፈጠረ፤ የኮንሶን ስናጣራ የኢሬቻ ችግር መጣ፣ የኢሬቻ ስንል የጌድኦ መጣ፡፡ በጣም ተቸግረናል፡፡ ከአቅማችን በላይ ሆኗል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ብናጣራም ሪፖርቶችን መስራት አልቻልንም፡፡ ከአዲስ አበባ ቤቶች መፍረስ ጋርም የተያያዘ ማጣራት አድርገናል። እነዚህን አቅም ስናገኝ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡  አሁን የምርመራ አቅጣጫችንን መገምገም ውስጥ ነው ያለው፡፡ በገንዘብም በሰው ኃይልም አቅማችን መጎልበት አለበት፡፡   

Read 2510 times