Sunday, 16 October 2016 00:00

የጌድኦ ዞን ከተሞች ነደዱ

Written by  መንግሥቱ አበበ እና አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

     በጌድኦ ዞን ላሉ የወረዳ ከተሞች የ2009 ዓ.ም የመስከረም ወር የመጨረሻ ቀናት ጥሩ አልነበሩም፤ በየከተሞቹ በሚኖሩ የጌዴኦ ተወላጆች ቤንዚን እየተርከፈከፈባቸው ጋዩ፤ ከቡሌ ከተማ በስተቀር። የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ መኪኖች ተቃጥለዋል፣ የቡና ማበጠሪያና ማጠቢያ ሳይቶች ነደዋል፡፡ በዲላ ከተማ ብቻ የ10 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ በይርጋጨፌ ከተማ ደግሞ 4 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የዚህ ሁሉ ጥፋት መንስኤ በግልጽ አይታወቅም። በዲላ ከተማ ባሉ ባለአክሲዮኖችና በይርጋጨፌ የቡና ዩኒየን መካከል የተፈጠረ ያለመግባባት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የባለአክሲዮኖቹ መሬት ለይርጋጨፌ የቡና ዩኒየኖች ይሰጣል፡፡ የቀድሞዎቹ ባለመሬት ለሌላ ሰው ሊሰጥብን አይገባም በማለት ይከራከራሉ። ፍ/ቤትም የክስ ሂደቱን ሲያይ ቆይቶ ለባለአክሲዮኖቹ ይገባል በማለት ብይን ይሰጣል፡፡ የይርጋጨፌ የቡና ዩኒየን ፍርዱን በይሁንታ መቀበል አልቻለም። በዚህም ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ለበርካታ ንብረት ውድመት የዳረገው ግጭት እንደቀሰቀሰ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
በብጥብጡ ከፍተኛ የቤት ቃጠሎና የንብረት ውድመት የደረሰው በይርጋጨፌ ከተማ ነው። የተቃጠሉ ቤቶች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ አራት የቡና ማበጠሪያና ከ20 በላይ የቡና ማጠቢያ ሳይቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ተብሏል፡፡
ወ/ሮ ሂሩት ብርሃኑ በይርጋጨፌ ከተማ ተወልደው፣ እዚያው አድገው ተምረውና ተድረው፣ እዚያው በቡና ንግድ ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የ37 ዓመቷ ወ/ሮ ሂሩት፤ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ስለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሲናገሩ እንባቸውን መንታ መንታ እያወረዱና ሲቃ እየተናነቃቸው ነው። “ስለሁኔታው ሳስብ ግራ ይገባኛል፡፡ ተመልሼ እሰራለሁ? ምን ይሰራል? እንዳለ ሙሉ በሙሉ ወድሟልኮ … እኔ እንጃ …” በማለት ሀሳባቸውን በእንባ አቋርጠዋል፡፡
“ረብሻው የተጀመረው ሐሙስ ወደ ማታ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡ ዓርብ ዕለት የምሰራበት የቤተሰቦቼ የደረቅ ቡና ማበጠሪያ ተቃጠለ፡፡ ከነሙሉ ንብረቱ ወድሟል፡፡ ምንም የቀረ ነገር የለም፡፡ 3 መጋዘን፣ ቢሮዎች፣ 14 ክፍሎች ያሉት መኖሪያ ቤት፣ የእኛ 6 መኪኖች፣ እኛ ጋ ያቆሙ ሰዎች 5 መኪኖች፣ በአጠቃላይ 11 መኪኖች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ በማግስቱ አምና የተገነባውን (ገና ከተገነባ አንድ ዓመት የሆነውንና ሥራ ያልጀመረውን የቡና ላብራቶሪ ከነዕቃው) ቢሮዎች፣ መጋዘን እንዳለ አወደሙብን። እንዴት ሆነ? ብትለኝ መልሴ እንጃ ነው፡፡ ወደ ስራም እንዴት እንደምንመለስ አናውቅም፡፡”
“የዚህ ውድመት ምክንያቱ እኛ እንደምናስበውና ሰው እንደሚያወራው የመንግስት ተቃውሞ አይደለም፡፡ ይህን መቶ ፐርሰንት መናገር እችላለሁ፡፡
“ብዙ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ብዙ መኖሪያ ቤቶች፣ ግሮሰሪዎች፣ ሽሮ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ቆቄ ሰፈር፣ ሐሩ ሰፈር፣ አዲስ ከተማ የሸማቾች ሱቆች እንዳለ ተቃጥለዋል፡፡ አራሞ ላይ ባንቆ ጉቱ የሚባለው የወንድሜ የቡና ማጠቢያ ሳይት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ መንግስት የመልሶ ማቋቋሙን ነገር ሊሰራበት ይገባል፡፡ ከአሁን በኋላ እንዴት ነው የምንሰራው? 20 ቋሚና ከ250 - 300 ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉን፡፡ እነዚህን ሰራተኞች እንዴት ነው መልሰን የምንቀጥረው? እንዴት ነው ከአሁን በኋላ ወደ ስራ የምንገባው? ምክንያቱም የምንሰራበት ነገር እንዳለ ወድሞብናል፣ በጣም ነው የሚከብደው፡፡
“የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በጨፌ ከተማ አራት ወጣቶች ሞተዋል፣ ብዙ ንብረት ነው የወደመው፡፡ ከ20 በላይ የግል ባለሀብት የቡና ማጠቢያ ተቃጥሏል፡፡ ጋዜጠኞች ሄዳችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ፡፡ የጥቂት የጌዴኦ ማህበረሰብ ባለሀብቶች ንብረት ነው የተረፉት። የአገሬው ተወላጆች፤ በጉልበታቸው ሰርተው ባገኙት ሌሎች ሰዎች ላይ መጥፎ ጥላቻ አላቸው። እነዚህ በወረዳዋ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በአንድ ዓመት ለመንግስት 23 ሚሊዮን ብር ነው ያስገቡት ይባላል፡፡ ከ44 ወረዳ ቀበሌ ተሰብስቦ ግን የገባው 300 ሺህ ብር እንኳ አይሞላም፡፡ ባለሀብቱ ለአካባቢው ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ለአገር ኢኮኖሚም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ለምን እንደምንጠላ ግን አይገባኝም፡፡ መጥፎ ፊት ነው የሚያሳዩን፡፡ 300 ሰው ለወረራ ከመጣ፣ ሦስት መቶውም ቤንዚን ይዞ ወጥቶ ነው አርከፍክፎ የሚያቃጥለው፡፡
“ይኼ ድርጊት በአንድ ቀን የታሰበ አይደለም። ሐሙስ ቅስቀሳ ተደረገ፤ አርብ፣ ቅዳሜ፣ እሁድ ጨለለቅቱ፣ ፍስሐገነት፣ ወናጎ፣ ይርጋጨፌ አምስቱም የወረዳ ከተሞች እስከ ዞን ድረስ ተቃጠሉ፡፡ ይርጋጨፌ ከተማ 75 ከመቶ ወድማለች፡፡ ይርጋጨፌ፣ ዲላ፣ ወናጎ፣ ፍስሐገነት፣ ላይ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ለዚህ ሁሉ ማነው ተጠያቂው? መከላከያ የገባው በሦስተኛው ቀን ነው - ብዙ ነገር ካለቀና ብዙ ነገር ከወደመ በኋላ፡፡ በአንድ ቀን የታቀደ ሳይሆን ፕሮግራም ተይዞ፣ ታቅዶና ታልሞ የተፈጸመ ድርጊት ነው፡፡
“የጌዴኦ ባለሀብቶች ጥቂትም ቢሆኑ በከተማዋ አሉ፤ የጌዴኦ ዩኒየን አለ፡፡ ነገር ግን በእነሱ ሳይት የቡና መፈልፈያ ላይ አንድም ጥቃት አልተፈጸመም፡፡ ባለሀብት ከተባለ እነሱም ባለሀብት ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኩት ይርጋጨፌ ነው፤ ቤተሰቦቼ ኑሮ የመሰረቱት ይርጋጨፌ ነው፤ አገርሽ የት ነው? ኑሮሽ የት ነው? ብትለኝ መልሴ ይርጋጨፌ ነው፡፡ ዘር ተመርጦ አድሏዊ ነገር ሲፈፀም አዕምሮዬ መሸከም አይችልም፡፡ “ጌዴኦ ለጌዴኦ፣ ጌዴኦ ነፃነት ማግኘት አለበት፤ ከአገራችን ውጡ!” የሚሉ ቃላት ሲነገሩ ነበር፡፡ እኔ እዚያ ተመልሼ መሥራት የምችልበት አቅም የለኝም፡፡ እኔ የምፈልገው ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ሕግ ፊት ቀርበው ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ነው። (ለቅሶ) አዕምሮዬ ባጣም ተጎድቷል፤ ልጆቼን እንኳ የማሳድግበት አቅም አጥቻለሁ፡፡ ትናንትና ከትናንት ወዲያ … እንዴት ነው የምንንቀሳቀሰው? ብዬ በጣም ጨንቆኝ ነበር፡፡
ወ/ሮ ሂሩት ሕልም ሆኖ ቀረ እንጂ ዱመርስ ቀበሌ በነበረው ላቦራቶሪ ትልቅ ራዕይ ነበራት። በጌዴኦ ዞን ቅምሻ ለማካሄድ፣ ቡና ቆልቶና ፈጭቶ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ነበራት። በነበር ቀረ እንጂ፡፡ ከውጭ አገር በ7 ሚሊዮን ብር ተገዝተው የገቡ የላቦራቶሪው ዕቃዎች በሙሉ መውደማቸውን የምትናገረው ሂሩት፤ ‹‹7 ሚሊዮን ብሩ አይደለም፡፡ ቀጣይ የምንሠራው እንዴት ነው? እንዴት ነው መቋቋም የምንችለው? ሞራላችን እንዴት ነው መመለስ የሚችለው?›› የሚሉት ሦስት ጥያቄዎች እያሳሰቧት ነው፡፡ መልስ ማግኘት ትፈልጋለች፡፡
ሌላው ንብረቱ ሙሉ በሙሉ የወደመበት ተበዳይ አቶ ሱራፌል ብርሃኑ ነው፡፡ የ31 ዓመቱ አቶ ሱራፌል ይርጋጨፌ ተወልዶ ያደገ፤ እዚያው ትዳር መሥርቶ፣ ሁለት ልጆችን ያፈራ ነው። አቶ ሱራፌል በይርጋ ጨፌ ወረዳ የታጠበና የደረቀ ቡና አቅራቢ ነው፡፡ በአብሥራ ፒኤልሲ ባለአክሲዮን ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የቡና ማበጠሪያ፣ መኖሪያ ቤት፣ ቡና  ማስለቀሚያ፣ መጋዘን፣ የእሸት ቡና መያዥያ 1000 ጆንያ፣ የቡና ማድረቂያ፣ ወንፊት፣ ፕላስቲኮች፣ ቢሮ፣ ዶክመንቶችና መጠነኛ ገንዘብ … በአጠቃላይ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ዕቃዎች በሙሉ ተቃጥሎበታል። በወናጎ ወረዳ ባንቆ ጉቱ ቀበሌ የነበረው የእሸት ቡና መፈልፈያም ወድሞበታል፡፡ የወደመበትን ንብረት መጠን በትክክል መናገር ቢያስቸግረውም 25 ሚ. ብር እንደሚገመት ገልጿል፡፡ እውነት ለዚህ ጥፋትና ውድመት ተጠያቂው ማነው? ተጎጂዎች ፍትህ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡

Read 2144 times