Sunday, 16 October 2016 00:00

ስለ ዴሞክራሲ ሞተ

Written by  ተፊሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

     ሐይማኖትና እምነት ዋና የህይወት ጎዳና ባልሆኑበት ምዕራባውያን ዘንድ የገና በዓል በልዩ ስሜትና ትኩረት ይከበራል፡፡  የገና ዛፍ ይዘጋጃል፡፡ ከቤተሰብ ራቅ ብሎ የሚኖረው ሁሉ ከያለበት የዓለም ክፍል ሻንጣውን ቀርቅቦ፣ ውቂያኖስ አቋርጦ ይጓዛል፡፡ የገና ሸመታ ሰፊ ነው፡፡ ስጦታው ብዙ ነው፡፡ የገና ዛፍ በብርሃን ይደምቃል። በዓሉ እንጂ የበዓሉ ምክንያት አይታሰብም። በቃ ወግ ነው፡፡
ይህን ግርምቢጥ የሆነ ነገር የሚጠቅሰው አለን ብሉም የተባለ አሜሪካዊ ፀሐፊ፤ ‹‹እኛ አሜሪካውያን ፍቅር ምን እንደሆነ እንኳን ጠፍቶብናል›› ይላል። የአሜሪካ ወጣቶች ከፍቅረኛቸው ጋር ተጣልተው ሲለያዩ፤ ‹‹I love you ይባባሉ›› ይላል፡፡ በዚህ የወጣቶቹ ነገር የተገረመው ብሉም፤ ‹‹I love you ማለት፤ አልወድሽም የሚል መልዕክት ያለው ይመስላል›› ይላል። አክሎ፤ ‹‹አሜሪካውያን ወጣቶች አንድ የማይታሙበት ነገር አለ። የሰዎችን ነጻነት በማክበር በኩል አይታሙም። ‹መብቱ ነው፡፡ መብቷ ነው› ይላሉ፡፡ የመብታቸውና የነጻነታቸው መሠረት ምን እንደሆነ በውል አያውቁትም›› ሲል ይተቻል፡፡
ፀሐፊው የዩኒቨርሲቲ መምህር ነው፡፡ ከዚሁ ካነሳው ችግር ጋር የተያያዘ አንድ አስገራሚ ጉዳት ይጠቅሳል፡፡ በክፍል ውስጥ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎቹ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ በተያዘችው ህንድ አንድ ልማድ አለ፡፡ ባል ሲሞት፤ ሚስቲቱ ከነህይወቷ ከባሏ ጋር ትቀበራለች። በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ መስተዳድር፤ አንድን የህንድ ግዛት የሚያስተዳድረውና ‹‹ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር  የማይገሰስ መብት አለው›› በሚል የፖለቲካ መርህ ተወልዶ ያደገው እንግሊዛዊ አስተዳደሪ፤ ይህን የህንድ ልማድ ለመቀበል ተቸገረ፡፡ ሰው ከነ ህይወቱ ሲቀበር ዝም ብሎ ለማየት አልቻለም፡፡ ሆኖም ‹‹እንዲህ ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ መከልከል፤ የህንድን ባህል ካለማክበር የሚቆጠርበት ስለሆነ በሥጋት ተወጠረ፡፡
ይህን ታሪክ ለተማሪዎቹ የተረከላቸው መምህሩ አለን ብሉም፤ በማያያዝ ለአሜሪካውያን ተማሪዎቹ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ‹‹ለመሆኑ እናንተ የህንድ አስተዳዳሪ ብትሆኑ ምን ታደርጋላችሁ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ የሰዎችን ነጻነት በማክበር የማይታሙት ተማሪዎቹ በጥያቄው ተቸገሩ፡፡ በነገሩ ብዙ ካሰቡበት በኋላ በመጨረሻ የሰጡት መልስ፤ በሽሽት ጎዳና የሄደ መልስ ነበር፡፡ ‹‹የሟቹ ባለቤት አብራ ልትቀበር አይገባም›› የሚል መልስ ሣይሆን፤ ‹‹እንግሊዝ ወደ ህንድ መሄድ አልነበረባትም›› የሚል መልስ ነበር የሰጡት፡፡ ምላሻቸው አስገራሚ ነው። መብትና ነጻነት ከመሠረታዊ የፍልስፍና መነሻቸው ተነጥለው ሲያዙ የሚፈጠረው ችግር እንዲህ ያለ ነው፡፡ የገና በዓልን ከክርስቶስ ልደትና ከሞራላዊ አንድምታው ለይተው እንደያዙት፤ መብትና ነጻነትን ለሁሉም መብቶችና ነጻነቶች (የባህል መብት) መሠረት ከሆነው በህይወት የመኖር መብት ነጥለው ይዘውታል፡፡
የአሜሪካ ዴሞክራሲ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ዓይነት ሰው ለመቀበልና ረጅም ርቀት ይዞት ለመሄድ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ ይህ አጋጣሚ የዴሞክራሲን ሞራላዊ ዳራ ለመቃኘት ያስገድዳል፡፡ የዴሞክራሲ እናት በሆነችው ግሪክ፣ በሶቅራጥስ ዘመን ዴሞክራሲ ወይም የህግ የበላይነት፤ እንደ እምነት ወይም ሐይማኖት የተያዘ ጉዳይ ይመስላል፡፡ በዓለ ገናን ከክርቶስ እና ከኢየሱስ አስተምህሮ መነጠል እንደማይቻል፤ ዴሞክራሲን ከሞራላዊ ዳራው ተለይቶ ሊቆም አይገባም፡፡ የሶቅራጥስ ህይወት ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡
አውደ-ሐሳብ
ሠረቀ ብርሃን ገብረ እግዚእ የተባሉ የሀገሬ ሰው ‹‹ክሪቶን›› በሚል ርዕስ (በ1947 ዓ.ም) ባሳተሙት አንድ መጽሐፍ፤ ስለ ሶቅራጥስ ሐገር ስለ አቴና ሰዎች ሲናገሩ፤ ‹‹ከፍጥረቱ ስጉ፣ ንቁ፣ ጠያቂ እና ተመራማሪ የሆነው የአቴና ሕዝብ በአምልኮ፣ በባህልና በሐሳብ ልዩ ልዩ ከሆኑ ሕዝቦች ጋር ግንኙነት በማድረጉ፤ በመጠያየቅ፣ በመወያየት፣ በመነጋገርና በመከራከር ይበልጥ ነቃ›› ይላሉ፡፡ የዴሞክራሲ ማህጸን በሆነችው አቴና የነበረው ‹‹ማህበራዊ ዓውድ፤ ፍቱን የሚሆን የአዕምሮ ምርመራ ለመከተል ዝግጁ የሆነ አስተሳሰብ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹በዕውቀት ወይም በህሊና ለመመራትና ለመረዳት ችሎታ ያለው መሆኑን የተገነዘበው የሰው ልጅ፤ በምናብ ከሐሳቡ የፈጠራቸውን አማልክት በዕውቀት ሊሽራቸው ደፈረ፡፡››
ሠረቀ ብርሃን አክለው፤ ‹‹ይህም የስህተት መጋረጃ መቀደዱ የሰውን ልጅ ከክህደት የጣለው መሰለ፡፡ ፍልስፍና ፍቱን ማስረጃ በሚሰጥ ጎዳና እየተመራች የጣዖትን መቅደሶች ግርማ ካጠወለገች በኋላ፤ ሥነ ፍጥረትን፣ ረቂቅ የሓሳብ ሁኔታን፤ በተለይም በስነ ፍጥረት ላይ የማሰብ ችሎታ የተሰጠውን የሰው ልጅ ትክ ብላ ተመለክታ፤ የሰውን ልጅ ሥነ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን የማህበራዊ አኗኗሩን ስሜቱን ሐሳቡን፣ መንፈሱን፣ የአዕምሮና የህሊናውን ሁኔታ መርምራ የማወቅን ነገርን ሥራዬ ብላ ያዘች›› ይላሉ፡፡
ሠረቀ ብርሃን፤ ‹‹በአጎራ አደባባይ ከሚናገሩት ፈላስፎች አንዳንዶቹ እጅግ ረቂቅ መንፈሳዊነት የሚሰማቸው ነበሩ፡፡ ሁኔታቸው ወደ ነቢይነት ወይም ወደ መናኝነት ያዘነበለ ነበረ›› ይላሉ፡፡ ታዲያ ከእነዚህ ፈላስፎች አንዱ ሶቅራጥስ ነበር፡፡ ሶቅራጥስ የድሀ ወገን ነው፡፡ አባቱ ሐውልት የሚያንጽ ባለሙያ ነበር፡፡ እናቱም ምጥ የያዛትን ሴት የምትረዳ አዋላጅ ነበረች፡፡ ሶቅራጥስ ከዓይኑ በስተቀር ሌላው መልኩ ሁሉ ጅል የሚመስል ሰው ነበረ፡፡ ‹‹ይህ ሰው የት ተማረ ሳይባል፤ እንዲሁ አልባሌ መስሎ የአቴናን አደባባይ ሲመለከተው ቆይቶ ጊዜው ሲደርስ ወይም የደረሰ መስሎ በተሰማው ጊዜ ተጠጋው፡፡››
እርሱም የተራ ሰው መሰል ጥያቄዎች እያነሳ በተጠየቅ ሥርዓተ-ሐሳብ ነገር ብሎ ያነሳውን ጉዳይ ማበራየት የሚችል ፈላስፋ ነበር፡፡ ርትዕ፣ እኩይ ወይም ሠናይ ምንድነው? ምንስ ይመስላችኋል? እያለ ይጠይቅና፤ ተጠያቂው ሰው በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተመስርቶ፤ ለተነገረው ነገር ተቃራኒ የሚሆነውን ወይም የሚዛመደውን፣ ተመሳሳዩን፣ ተወራራሹን፣ ወይም በፍጹም ጋፊኛ የሚሆነውን ሐሳብ እያስከተለ የሰውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ህላዌ በሚመለከት መመራመርና መከራከር ሲጀምር መነሻው ‹‹ራስህን ዕወቅ›› የሚል ነበር፡፡ ሶቅራጥስ ሁሉን ሥነ ፍጥረት ያደንቃል፡፡ ነገር ግን የሰውን ልጅ ከሁሉ አብልጦ ይመለከት ነበር፡፡
‹‹ማወቄ ምንም የማላውቅ መሆኔን መገንዘቤ ነው››  ብሎ የተነሳው ሶቅራጥስ፤ ጥያቄ ሲያነሳ ራሱ ለመማር የሚሻ እየመሰለ ነው፡፡ ሆኖም እንዲያ ባለ ሁኔታ የጀመረው ነገር፤ ‹‹ቀጥ ባለ፣ በማያላውስ፣ የመጨረሻውን እውነት እንጂ አስተያየትን በማይቀበል ሥርዓተ -ሐሳብ የዕውቀትን፣ በጠቅላላው የህላዌን ነገር፤ ህላዌ-ሥጋን፣ ህላዌ-ነፍስን ምንነት ይመረምር ያዘ፡፡ ሠናይ ወይም እኩይ የሚባለው ምንድነው? ርትዕ፣ ጽድቅ ምንድነው? መንግስት፣ ህግ፣ አስተዳደር፣ ሥርዓት፣ ምግባር፣ ዳኝነት፣ ፍርድ፣ መብት ግዴታ ፍቅር መውደድና ወዳጅነት ሐሴት ኀዘን፣ ተድላ፣ ችሎታ፣ ሐኬት፣ ሙያ፣ እንከን፣ ጥበብ፣ ብልኃት……ምንድናቸው እያለ ይጠያይቅ ነበር፡፡
ተፍጻሜተ ነገረ
ስፓርታና አቴና ለሰላሳ ዓመታት ያካሄዱት ጦርነት ሲያበቃ፤ በእርሱ ሰላማዊ አካሄድ ሥልጣን ለመጨበጥ ተከራካሪ በነበሩት ተማሮቹ ሲመራ የነበረው የኦሊጋርኪያ አስተዳደር ወገን በዴሞክራሲያውያኑ ወገን ሲቸነፍ በሽማግሌው ፈላስፋ ላይ ክስ ለመመስረት ተመከረበት፡፡
በወቅቱ የ‹‹ዴሞክራቶች›› እና የ‹‹ኦሊጋርኪ›› ሐሳብ አራማጅ የሆኑ አቴናውያን ነበሩ፡፡ ታዲያ አኒቶስ የሚባል ሰው የዲሞክራቶቹ ደጋፊ ነበር፡፡ ጥቅሙን ከዲሞክራቶቹ ጋር አዛምዶ የነበረ ሰው በመሆኑ ኦሊጋርኪያዎቹን ጠምዶ ይዟቸው ነበር፡፡ ስለዚህ የሶቅራጥስ ዋና ከሳሹ ሆኖ የተነሳው አኒቶስ የሚሉት ሰው ሆነ፡፡  
የሶቅራጥስ ጠላት ሆኖ የተነሳው አኒቶስ፤ በአንድ ወቅት በጦር አዝማችነት ታዝዞ የተሰጠውን ግዳጅና ግዴታ በሚገባ ሳያከናውን ቀርቶ፣ በክስ ፍርድ ቀርቦ በገንዘብ እርዳታ ከቅጣት የዳነ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ሶቅራጥስ የሚያስተምረው ትምህርት የእርሱን እንከን የሚያጎላባት ስለሚመሰለው ጠልቶታል፡፡ ሶቅራጥስ ስለ አስተዳዳሪዎች የሚያሰማው ሐተታ በቀጥታ የሚነካው ይመስለው ስለነበረ፣ ሽማግሌው ፈላስፋ ይጠላዋል፡፡ ከዚህም በላይ የገዛ ልጁ የሶቅራጥስ አስተሳሰብ አራማጅ በመሆኑ ይናደድ ነበር፡፡
ስለዚህ የእርሱ ከሳሽ ሆኖ ከእርሱ ጋር ከፍርድ ቤት ለመቋቋም በመቻሉ እጅግ ደስ አለው፡፡  እናም እንደ እርሱ ከተከፉ ሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በሶቅራጥስ ላይ ክስ አቀረበ፡፡ ክሱም፤ ‹‹ሶቅራጥስ ሐገሩ በሚያምንባቸው አማልክት ባለማመኑና እንግዳ መናፍስትን በመስበኩ ዓመጸኛ ነው፡፡ የወጣቶችንም ጠባይ የሚያጠፋ ወይም የሚያበላሽ በመሆኑ ያምጻል፡፡ ስለዚህ ሞት ይገባዋል›› የሚል ነበር፡፡
ይህ ክስ፤ ከዘመኑ ባህልና መንፈስ አንጻር ከባድ ክስ ነበር የሚሉት ሠረቀ ብርሃን ገብረ እግዚእ፤ ‹‹የክሱ መንፈስ፤ የሶቅራጥስ ነገር የሚታወቅ ነው፡፡ መንግስቱና ህዝቡ መስሏችሁ ታግሳችሁ ባቆያችሁት ነገር ሐተታ ማብዛት አያስፈልግም፤ ከማለት የሚቆጠር ክስ›› እንደ ነበር ይጠቅሳሉ፡፡ እውነትም ነገሩ በቋፍ የቆየ ስለነበር፤ የፈላስፋው መከሰስ  ከአስቸጋሪ ሰው የሚገላግል ሁነኛ ዘዴ ሆኖ ታየ፡፡ ስለዚህ ከሳሹ አኒቶስ ፓሊክራቲስ በተባለ የመናገርና የመጻፍ ልዩ ችሎታ በነበረው ሰው የተዘጋጀ የክስ ዝርዝር ይዞ ችሎት ቀረበ፡፡ ችሎቱም የአቴና ህዝብ በሙሉ የተገኘበት ይመስል ነበር፡፡
ለባለስልጣናቱ ብቻ ቀርቦ የነበረው ክስ በአደባባይ ተገልጦ ታወቀ፡፡ የክሱ ማብራሪያ የሆነው መርዘኛ ንግግር ከተሰማ በኋላ ተከሳሹ ሽማግሌ እንዲከላከል ተፈቀደለት። ነገር ግን ከፍ ያለ መንፈስ የሚሰማው ሶቅራጥስ፤ ከፍ ባለ መንፈስ የሚመራ ስለሆነ፤ ከተራ ዝርዝር ሳይገባ በጠቅላላው በደለኛ አለመሆኑን ከተናገረ በኋላ ‹‹ለመከላከል የተፈቀደለትን ጊዜ ለመገሰጽ የተጠቀመበት መስሎት ሥጋዊ ህላዌውን ለማቆየት ሳያስብ፣ በነቢይ የመንፈስ አለንጋ ተጋረፈበት፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው 501 ከነበሩት አቴናውያን ዳኞች ውስጥ 220ው ነጻ ሲያወጡት 281 ጥፋተኛ ብለውት፣ በ61 የድምጽ ብልጫ ይሙት በቃ ተፈረደበት፡፡››
ፈላስፋው የተወሰነበትን ፍርድ በእርጋታ ሰምቶ፣ ብዙ እጅግ ኃይለኛና ጥልቅ ሐሳብን አሰምቶ፤ ‹‹………..እንግዲህ እኔ እንድሞት እናንተም ለመኖር መለያየታችን ነው………›› ብሎ ከተናገረ በኋላ የችሎት መልስ ሆኖ ወደ እስር ቤት ሲያመራ ፍርድ ቤቱ በመጥበቡ፣ በውጭ ቆይተው የነበሩ ወዳጆቹ ተስፋ ቆርጠው ሲያለቅሱ፤ ‹‹…….ገና ስወለድ እንድሞት ከፍጥረት የተወሰነ እንደነበረ አታውቁምን……? ለምን ……ታለቅሳላችሁ ?›› በማለት ሊያጽናናቸው ተናገረ፡፡
ሶቅራጥስ በእስር ቤት ከገባ በኋላ፤ እንደቆየው ልማዱ፣ ሐሳቡ ሳይደክምና ከጥንት ንቃቱ ምንም ሳይቀነስበት ከወዳጆቹና ከተማሪዎቹ ጋር በመከራከር ማስተማሩን ሳያቋርጥ የፍርዱን ፍጻሜ ይጠብቅ ነበር። በመጨረሻም ወዳጆቹና ተማሮቹ ክሪቶን በተባለ ጥብቅ ወዳጁ አማላጅነት ከእስር እንዲጠፋና ከአቴና ርቆ እስከተወሰነለት ጊዜ ሥጋዊ መኖሩን እንዲያቆይ ሊረዱት በብዙ ደከሙ፡፡
ሶቅራጥስ የተጣለበት ፍርድ ያልተቀበለውና ፍርዱም የተፈረደበት ሲነቅፈው በነበረ መንግስት ቢሆንም፤ በህግ የተወሰነበትን ፍርድ በአመጽ ለመሻር አልፈለገም። ህግና ስርዓት በኃይል ወይም በአመጽ እንዲደፈር እና እንዲፈርስ አልፈለገም፡፡
ህግን በአመጽ ለማፍረስ ህሊናው የማይፈቅድለት ሆኖ፤ በደልን በበደል ለመሻር መሞከር  ተገቢ አይደለም ብሎ ጸና፡፡ ህግን በኃይል (ህገ ወጥ በሆነ አካሄድ) በመጣስ መንቀሳቀስና የሐገርን ሥልጣን መጋፋት ከርኩሰት የሚቆጠር ተግባር መሆኑን ተቀብሎ ለፍርዱ መፈጸም ታመነ፡፡ ሶቅራጥስ ረቂቅ በሆነ እምነት ተመርቶ፤ የወዳጆቹን ሐዘን ወደ አመጽ የሚመራ እንጂ ትክክለኛ ሓሳብ የለበትም ሲል ነቅፎ ውድቅ አደረገው፡፡ ይህን ሲያደርግ ሐሳቡን በእምነት ጠብቆ ለመዝለቅ ሲል እንጂ ኑሮን በመሰልቸት ወይም በፈላስፋ ትዕቢት ተመርቶና ከሌሎቹ ሰዎች ተለይቶ ለመታወቅ አልነበረም፡፡
ሶቅራጥስ መንፈሳዊነትን እና የኅሊና ቅንንነትን፣ የጽድቅ እና የርትእን፤ እንዲሁም የሰናይ ምግባርን በተግባር ገንዘቡ ያደረገ ሰው ስለነበር፤ መንፈሱ የአመጻን ሐሳብ ሊቀበል የሚችል አልነበረም፡፡ ራሱ ‹‹የኃይል እና የአመጻ ሥራ›› የሚለውን ነገር ድል አድርጎ ከማቸነፍ ይልቅ ግፍን መቀበልን ፈቀደ፡፡
በእርሱ እምነት የአንድ ማህበረሰብ ስርዓትና ህግ፤ በውይይት በክርክርና በመግባባት ሊሻሻሉ ይችላሉ እንጂ በኃይል እንዲፈርሱ ማሰብ አይገባም ባይ ነው። በዚህ መንገድ የሚሻርና የሚለወጥ ህግ፤ በሰላም እና በስምምነት የሚደረግ  በመሆኑ ስልጣኔ ነው፡፡ ህዝብን ያስተባብራል። ያስማማል፣ ያሳድጋል፡፡ በኃይል የተለወጠ ነገር ግን ምንጩ አመጽ ነው፡፡ ስለዚህ በህዝብ ህሊና ፍርኃትን ያሳድራል፡፡ ተጠራጣሪ ያደርጋል፡፡ በምንም ነገር እምነት የሌላቸውና ለማመንም የማይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ጸጥታን ይነሳቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ህሊናቸው ስለሚደክም፤ ከዕለት ጉዳይ የሚበልጥ ነገር ለማሰብ ወይም ለመመኘት እንኳን የማይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሶቅራጥስ በእንዲህ ያለ እምነት የአዕምሮ ፍርድ ሓሳቡን ከስህተት የሚጠብቅ ሰው ነበር፡፡
ስለዚህ ቅር ሳይለው በሚነቅፈው መንግስት፣ ፍርድ ቤት በተንኮል በተነሳሱ ሰዎች በተመሰረተበት ክስ የተጣለበትን ፍርድ፣ ፍጻሜ እንዲሆን የሞትን መንገድ ተከተለ፡፡ ከክርስቶስ በፊት የኖረ ክርስቲያን የሚል ስም ያተረፈው ሶቅራጥስ፤ በአዕምሮ ብርሃን ወደተለመከተው መንፈሳዊ ዓለም አለፈ፡፡ እንዲህ ባለ አሟሟት ፍጹም እምነትንና እውነትን ገለጠ፡፡ የተከሰሰባቸውን ኃጢአቶች በአንደበት ሳይሆን በግብር አስተባበለ፡፡ ትክክለኛ ህግ አክባሪነቱ እስከ መጨረሻው ፍጹምና ለወጣቶች ከፍ ያለ አብነት የሚሆን ሰው መሆኑ፤ህግ ከመጣስ ይልቅ ልሙት በሚል አቋሙ ታየ። ‹‹ከጥቂት ዓመታት በኋላ አቴናውያን በሶቅራጥስ ላይ የተፈጸመውን ግፍ አወቁ፡፡ አዘኑ፡፡ የሰው ዘር በእውነት እንዲያምን ደምና ሬሳን ማየት ይፈልጋል፡፡ ጸጸቱን ለመርሳት፣ ኅሊናውን ለማባበል የቻለ ሲመስለው ደግሞ ለበደላቸው ሰዎች፣ ግፍ ላደረገባቸው ሰዎች፣ ከድንጋይ ሐውልት አንጾ  ያቆምላቸዋል፡፡…… ይህም በየዘመናቱ የሚደጋገም፤ የእውነት መልዕክተኞችና ምስክሮች እና የክፋት ባሮችም ታሪክ ነው፡፡
ታዲያ የሐተታዬ የሞራል ታሪክ፤ ዴሞክራሲ እንዲህ ያለ እምነት የሚፈልግ ሆኖ ሳለ፤ አሁን በፖለቲካ ነጋዴዎችና ገበያተኞች ዋጋዋ ጠፍቷል የሚል ነው፡፡

Read 1407 times