Sunday, 16 October 2016 00:00

‹‹ፍኖተ አእምሮ›› - የራስ ካሣ ኃይሉ ፍልስፍናዊ ዕይታዎች

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(5 votes)

     ባለፈው ሳምንት ‹ራስ ካሣ ኃይሉ፤ ስደተኛው መጽሐፋቸው እና ፍልስፍናዊ ቀመራቸው› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ጀምሬ ነበር፡፡ በዚያም ጽሑፍ ራስ ካሣ ኃይሉ ማን እንደሆኑ፣ በጽሑፍ ሥራ ውስጥ ምን እንደሠሩ እንዲሁም ፍኖተ አእምሮ የሚለው መጽሐፋቸው ምን አይነት መዋቅር እንዳለው ለማየት በመሞከር፤ ለዛሬ ደግሞ የዚህን መጽሐፍ ፍልስፍናዊ ዕይታዎች ለመመልከት ቀጠሮ ይዤ ነበር፡፡ ይሄ ከዚያ የቀጠለ መጣጥፍ መሆኑ ነው፡፡  
በፍልስፍናው ዘርፍ በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም ሰፊ የሚባል የአረዳድ ልዩነት እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም የፍልስፍናን የጀርባ አጥንት አመክንዮ ሲያደርገው፣ የምሥራቁ ዓለም ደግሞ የፍልስፍና የጀርባ አጥንት ዕምነት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ያለ ዕምነት የሚሆን ሁሉ ሐጢአት ነው የሚለው መንፈሳዊ አስተምህሮ የጥበብ ሁሉ መነሻና መድረሻ በሆነው የምስራቃዊያን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ሁሉ ይስተዋላል፡፡ ክርስትናን እስልምናን፣ ቡድሂይዝምንና ሌሎችንም የምስራቅ አስተምህሮቶች ከምዕራባዊው ዘመናዊነትና አብረኆት (modernity and enlightenment) ጋር ማነጻጸሩ ይህንን መሰረተ ሀሳብ ለመገንዘብ ሳያስችል አይቀርም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው በኢትዮጵያዊ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ከማደግ አልፈው ምንኩስናን በወጣትነት የተመኙትና አስቀድሞ በልጅነታቸው ኢየሩሳሌምን የተሳለሙት ራስ ካሣ ኃይሉ የምስራቁን ፍልስፍናዊ ዕይታ ያዳብሩ እንጅ ፍልስፍናዊ ዕይታቸው ንጹህ ምስራቃዊ ወይም ንጹህ ምዕራባዊ ያልሆነ፣ተመስጦንም አመክንዮንም የሚጠቀም ነው፡፡ በምሳሌ እንየው፡፡
የምዕራቡ አመክንዮ ለምስራቁ አስተምህሮ ምንም አለመሆኑ ብዙ ጊዜ በአማኞችና በማያምኑት መካከል የሀሳብ ፍጭት እንዲነሳ ያደርጋል። የማያምኑት ለማመን ምርምርን ያደርጋሉ፤ የሚያምኑት ለማያምኑት አለመመራመርን ይመክራሉ፡፡ ራስ ካሣ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹…..ልቦናህ ግን አላርፍልህ ብሎ ብዙ መመርመር ቢፈልግህ ዳርቻውን አታገኘውም፤ ….. እንኳን ፈጣሪ ፍጡርም ጌታ ቢሆን ሱሪህን ፈትቼ ልብስህን ገልጬ የውስጥ አካልህን አይቼ ልገዛህ ቢሉት ከድፍረትና ከንቀት ቆጥሮ ይጣላዋል እንጅ መርምሮ ሊወደኝ ነው አይልምና…..››
ራስ ካሣ በዚህ ዕይታቸው ምዕራባዊው የአመክንዮ ፍልስፍና ዋጋ ቢስ መሆኑን ህይወትም እንደማይሆን ያስባሉ፡፡ በሌላ በኩል በየትኛውም ሃይማኖት ልክነት ወይም በየትኛውም ፈጣሪ ፈጣሪነት ላይ የሚደረግን ክርክር ምእራባዊ በሆነው አመክንዮ ሲፋለሙት ይታያል፡፡ እንዲህ እያሉ፤
‹‹ሰዎች የጌታቸውን መልክ በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ አንዱ እንዲህ ያለ ነው፤ ሁለተኛው እንዲህ ያለ ነው ብለው ባንድ ሰው መልክ ላይ ቢከራከሩ፣ ጌትነቱን አምነው ስልጣኑን ፈርተው ከተገዙለት ጌትዬው ከነሱ ላይ የሚፈልግባቸው የጌትነቱን መጠንና የትዕዛዙን ቅርጽ መፈጠም ብቻ ነው፤ እንጅ በመልኩ ቅርጽ ላይ የሚከራከሩት ግን ርቀው በሚመለከቱበት በአይናቸው ብርሃን መጠን በሚያዩት የመሰላቸውን ብቻ የሚያወሩ ስለሆነ አላዋቆች ህጻናት እንደሚጫወቱበት ቃል እያደረገ ንግግራቸውን እየናቀ ያልፈዋል እንጅ……..››
በዚህ ሐሳብ የምዕራባዊያኑ ሥነ እውቀታዊ (epistemological) መረዳት ጠቃሚ መሆኑን ይዘክራሉ፡፡ በሥነ-መለኮታዊው ድስኮራ (theological discourse) ውስጥ መሰረታዊ የውዝግብ አጀንዳ የፈጣሪ ህልውና እና የፈጣሪ ፈጣሪነት እንደመሆናቸው የምዕራቡ ፍልስፍና ይህንንም ዲበአካላዊ ሙግት (metaphysical thought) መደበኛ በሆነው ሥነ-እውቀታዊ (formal epistemology) ሊዳኝ ይሞክራል፡፡ ይህም መንገድ ‹‹እውቀት ማለት በበቂ ምክንያት የተደገፈ እውነተኛ እምነት ነው›› የሚል ነው። ምዕራባዊያኑ (knowledge is justified true belief) እንደሚሉት ማለት ነው፡፡
ራስ ካሣ የፈጣሪን የትኛነት ወይም የዓለም ሃይማኖቶች በሙሉ ከሚያመልኩት ፈጣሪ ውስጥ የትኛው ነው ትክክለኛው ፈጣሪ የሚለውን አወዛጋቢ ጥያቄ ሊመልሱ የሞከሩት በዚህ ምዕራባዊ የስነ-እውቀት ዘዴ ይመስላል፡፡ ፈጣሪውን የሚያመልክ ሁሉ ፈጣሪውን በሩቁ ያየዋል፤ በርቀት ማየቱ ደግሞ ሁሉም እንደ እይታው አድማስ ስለ ፈጣሪው የራሱን ምስል እንዲስል ያደርገዋል፤ ይህ በአማኞች ልቦና ውስጥ ያለው የፈጣሪ ምስል ደግሞ ያንዱ ካንዱ ሊወዳደር አይገባውም፤ ምክንያቱም ማንኛውም አማኝ ቢሆን ስለፈጣሪው ከማመን ውጭ በበቂ ምክንያት ሊያስመረኩዘው የሚችል እውነተኛ እምነት (justified true belief) የለውምና! በዚህም የተነሳ ይላሉ ራስ ካሣ፤ በዚህም የተነሳ ማንኛውም አማኝ ያመነው ልክ መሆኑን ከመቀበል ውጭ እኔ ያመንኩት ወይም በኔ ልቦና ውስጥ ያለው የፈጣሪ ምስል ነው ትክክል ቢል ከመሳሳቱም በተጨማሪ የሚያምነው አምላክም እንኳ እንደ ጨቅላ ቆጥሮ ይስቅበታል፡፡
በ”ፍኖተ አእምሮ” ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላነሣው የፈለግሁት የራስ ካሣ ኃይሉ ፍልስፍናዊ እይታ አለ፤ ይህም በመደበኛው የፍልስፍና መንገድ ቢታይ ትምህርታዊ ፍልስፍና (philosophy of education) በሚባለው ተግባራዊ (applied) ፍልስፍና ውስጥ ሊጠቃለል የሚችል ነው፡፡ በዚህ ዘመን ያሉት የትምህርት ፍልስፍና ተፈላሳፊዎች አብዝተው ከሚያነሷቸውና ሐሳቦቻቸውን ከሚያጎርፉባችው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የትምህርት ምንነት፣ የትምህርት ሥነ-ዘዴ እንዲሁም የትምህር ግብ ምን መሆን አለበት የሚሉ ይገኙባቸዋል። ከነባራዊው ሀቅ ጋር እያዛመድን ለማየት እንዲያስችለን ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ መንግስት ይመራቸዋል በሚባሉ ሀገሮች ውስጥ ለዚህ አይነት ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች የሚሠጡ መልሶች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ‹ችግር ፈች› የሚል እሳቤ ላይ ይወድቃሉ፡፡
ትምህርት ምንድን ነው ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ ልማታዊ መንግስት የሚሠጠው መልስ፤ ‹በቀለም ወይም በተግባር የሚሠጥን አንድን ችግር መፍቻ መንገድ ወይም ዘዴ ማስታወስ ነው›› ከሚል የሚርቅ አይሆንም፡፡ አስተማሪዎቹ ከተማሪዎቹ ፊት ቆመው ስለ አንድ ነገር ያወራሉ ወይም ያሣያሉ፤ ተማሪዎቻቸውን ሲፈትኑም የነገሯቸውን ወይም ያሣዩአቸውን ነገር አንድም ሳያዛቡ ከደገሙላቸው መልካም ውጤት ይሰጣሉ፡፡
ትምህርት በምን ዘዴ ይሰጥ ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ የሚሰጠው መልስም ከዚሁ ከችግር ፈችነት የሚርቅ አይሆንም፤ ለምሳሌ ተደራሽነት አንዱ ነው። ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ ለሁሉም ዜጎች አንድ አይነት እና እኩል የሆነ እድል ማመቻቸት ላይ ያተኩራል፡፡ ሶስተኛውም መሰረታዊ ትምህርታዊ የፍልስፍና ጥያቄ የሚያገኘው ልማታዊ መልስ፣ ከችግር ፈችነት የሚዘል አይደለም፡፡ ከመሃይምነት መውጣት ወይም ተምሮ ስራ መያዝ የሚል ይሆናል። በፍልስፍና መንገድ ይህ ልማታዊ ፍልስፍና ስህተት የሚሆንበት አንዳች ምክንያት የለም፤ ይልቁንም አንዱ የፈላስፎች እይታ እንጅ!
በሌላ በኩል ሶስዮሎጅስቶች የምዕራብ ምሁራንን እየጠቀሱ እንደሚሉት ትምህርት አራት አይነት ትውልድን ይቀርጻል፡፡ ይህ ትውልድ አራት ደረጃዎች አሉት፤ የመጀመሪያው የተማረውን አስታዋሽ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ የተነገረውን መልሶ በመናገር ስኬታማነቱን ያውጃል፤ ሁለተኛው የተማረውን ማገናዘብ የሚችል ትውልድ ነው፣ ይሄኛው ትውልድ ደግሞ የተማረውን ነገር ከሚኖርበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያገናዘበ ለመመልከት ብቃቱ ያለው ሲሆን የተነገረውን ብቻ መልሶ ከሚተፋ ‹ቴፕ› ትውልድ ዘለግ ያለ ብቃት አለው፡፡ ሦስተኛው ትውልድ ከሁለተኛው ከፍ ያለ ሲሆን በተማረው ትምህርት አማካኝነት ያለበትን ሁኔታ ከመገንዘብ አልፎ በሚኖርበት ሁነት ውስጥ ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ብቃት ያለው ትውልድ ነው፡፡ እንደነዚህ ሰዎች አረዳድ፣ በትምህርት አለም ውስጥ ያለው አራተኛው ትውልድ፣ በተማረው ትምህርት አማካኝነት አዳዲስ ፈጠራዎችን መፍጠር የሚያስችል የፈጠራ ብቃት ያለው ትውልድ ነው፡፡
የራስ ካሣን ትምህርታዊ ፍልስፍና (philosophy of education) ፍኖተ አእምሮ ከሚለው መጽሀፋቸው ነጥለን ለማውጣት ብንሞክር፣ በተለይ የትምህርት ግብ ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ የሚያስቀምጡትን ግልጽ ምላሽ ማግኘት እንችላለን። ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው አራት አይነት መደብ ሁሉ ከጽ 30 እስከ ገጽ 38 ባለው የመጽሐፋቸው ክፍል የትምህርት ዓላማ አራት መደብ መፍጠር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ለራስ ካሣ ትምህርት የሚፈጥረው ከታች ወደ ላይ የሚደረደሩና እርስ በእርሳቸው የሚበላለጡ ትውልድን ወይም መደብን ለመቅረጽ ሳይሆን አራት አንገብጋቢና አስፈላጊ መደቦችን መፍጠር ነው፡፡ እኒህ መደቦች እርስ በእርስ የሚበላለጡ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ (interdependent) ናቸው፡፡
የመጀመሪያው መደብ የተገዥ መደብ ነው፤ በራስ ካሣ አረዳድ ተገዥ ማለት የበታች ማለት አይደለም። ተገዝቶ መኖር ባለትልቅ ዋጋ ነው የሚሉትም ለዚሁ ነው፡፡ እኒህ ተገዥ መደቦች ለሚኖሩበት አካባቢ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት በክህሎታቸው፣ በእውቀታቸውና በፍላጎታቸው ነው፡፡ ይሄኛው መደብ ተገዥ የተባለው ፖለቲካው ውስጥ የመሪነትን ሚና ስለማይጫወት እንጂ የበታች ስለሆነ አይደለም፡፡ የሙያተኛ ወይም የሰራተኛ መደብ ነው፡፡ በሌላ አባባል ገዥ (መሪ) የሚባለው መደብ እንዲኖር ይህኛው የተገዥ ወይም የተመሪ መደብ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ አሁንም በሌላ አባባል የተገዥ መደብ በእውቀቱ፣ በፍላጎቱና በክህሎቱ መሰረት ተገዥ በመሆኑ በብዙ የአፍሪካ ሀገር እንደምንመለከተው ያለ ችሎታው ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የሚያቦካ እይደለም ማለት ነው፡፡
በራስ ካሣ አረዳድ የትምህርት ውጤት የሚሆነው ሁለተኛ መደብ ደግሞ የገዥ መደብ ነው፡፡ ይህ መደብ የበላይ ነው ማለት አይደለም፡፡ በክህሎቱ በፍላጎቱና በእውቀቱ የተነሳ አካባቢውን ሊያገለግል የሚችለው በመሪነት ነው ማለት እንጅ። የትምህርት ግብ ይህ መደብም እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዘርፉ የሚያስፈልገውን የመሪነት ጥበብ ማላበስ መቻል ነው፡፡
ሦስተኛው መደብ ደግሞ የመንፈሳዊያን መደብ ነው፡፡ ይህ የመንፈሳዊያን መደብ ለራስ በመመንኮስና ለራስ በመጸለይ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ለአካባቢው በሙሉ መንፈሳዊ ክዋኔዎችን የሚከውንና ምግባርን የሚያስተምር እንጅ፡፡ (እንዲህ ያለው ነገር በተለይ በምስራቁ ፍልስፍና ትልቅ ቦታ ያለው ነው) ይሄኛውም መደብ እንደ በፊቶቹ ሁሉ የበታች ወይም የበላይ አይደለም፤ በዚህ መደብ ውስጥ ያሉ በፍላጎታቸውና በእውቀታቸው ማህበረሰባቸውን የሚያለግሉበት እንጅ፡፡
እንግዲህ አራተኛው መደብ የሚሆነው የጥበበኞች፣ ያስተማሪዎች፣ የጸሀፍት በጥቅሉ የፈላስፎች መደብ ነው፡፡ እኒህም በክህሎት በእውቀትና በፍላጎታቸው መሰረትነት ማህበረሰቡን ያገለግላሉ እንጅ የበላይ ወይም በታች ማለት አይደሉም፡፡ በመሆኑም እንደ ራስ ካሣ ፍልስፍናዊ እይታ፤ ትምህርት እኒህን አራት መደቦች የሚፈጥር ነው፡፡ ይህም ማለት የትምህርት ግቡ ለሚለው ፍልስፍናዊ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ነው፤
እንደ ራስ ካሣ አተያይ፤ ትምህርት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ አራት መደቦችን የመፍጠር ግብ አለው፡፡ (የራስ ካሣን የትምህርት ፍልስፍና ለማየት እንዲበጀኝ እኔ ይህን መንገድ መረጥኩ እንጅ በትምህርት ፍልስፍና ውስጥ የሚነሱት ጥያቄዎች እኒህ ብቻ ናቸው፤ መልሶቹም እኒህ ብቻ ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ የትምህርት ፍልስፍና ከዚህም ባለፈ ብዙ ዝርዝር ጥያቄዎችን ያነሳል፤ በትምህርት አይነት፣ በትምህርት እድሜ፣ በማስተማሪያ መንገድ፣ በማስተማሪያ ቋንቋ፣ በመፈተኛ መንገድ፣ በፈተና ምንነት፣ በተማሪ ቅጣት ምንነት፣ በተማሪ ቅጣት አይነት ወዘተ ላይም ያጠነጥናል)
በሶስተኛ ደረጃ ልመለከተው የፈልግሁት የራስ ካሣ ፍልስፍናዊ እይታ በመደበኛው አጠራር የምግባር ፍልስፍና (moral philosophy) ነው፡፡ በብዙ ማህበረሰቦች ውስጥ የጥሩ (what is good) እና የመጥፎ (what is bad) ምላሾች ላይ የጋራ ስምምነት ያለ ቢመስልም ወደ ፍልስፍናው አለም ሲገባ ብዙ የሚያምታቱና የሚያወዛግቡ ነጥቦችን የያዘ የፍልስፍና ዘርፍ ነው፡፡
ለአንድ ማህበረሰብ ጥሩ የሆነው ለሌላው ጥሩ ላይሆን ይችላል የሚለው አንጻራዊነት (relativity) እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁሉም አለም መጥፎ ብሎ የፈረጃቸው እንደ ሰው መግደል ያሉ ነገሮች እንኳ ጥሩ የሚሆኑበት የምግባር ፍልስፍና የሙግት አይነት አለ፡፡ ለምሳሌ ሰው መግደል መጥፎ (bad) ነው፡፡ ወንጀለኛ ሰውን መግደልስ? ይሄም ቢሆን አወዛጋቢ የምግባር ጉዳይ ነው፡፡ ለዚያ ነው አንዳንድ ሀገራት የሞት ቅጣትን በህጋቸው ውስጥ ሲያካትቱ፣ ሌሎች ሀገራት የሞት ቅጣትን የማይቀጡት፡፡ የራስ ካሣን የምግባር ፍልስፍና ለማየት የሚከተለውን ሀተታ እንመለክት፡፡
‹‹አጥቶ ከሚቀማ ድሃ ሊሰጥ ከጌታው የተቀበለውን ገንዘብ አልሰጥ ብሎ የሚያስቀምጥ ከሆነ ከድሃው ቀሚ ጋራ ጌታው በቅሚያው ይተካከልና በፍትሐ አምላክ አጥቶ ከሚቀማ ድሃ ጋራ አብረው ይቀጣሉ እንጅ ቀማኛው ጌታ በድሃው ቀማኛ ላይ ዳኛ ሊሆን አይገባውም››
በራስ ካሣ እይታ፤ ቸግሮት የሰረቀ ድሃና እያለው ያልመጸወተ ሃብታም አንድ ናቸው፡፡ እያለው ያልመጸወተ ባለጸጋ ወይም ጌታ ሲቀማ በተገኘ ድሃ ላይ ዳኛ ሆኖ ለመፍረድ የምግባር ልዕልና አይኖረውም፡፡ እሱም ያው ቀማኛ ነውና፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው ሀተታ ጋር አያይዘው የሚያነሱትን ጥያቄና መልስ ተመልክተን ከማርክሳዊያን የምግባር ፍልስፍና ጋር እናስተያየዋለን፡፡
ጥያቄ
በእርሻ በእጅ ስራ የሚኖር ምንደኛና  አራሽሳ ቀማኛ የሚያሰኛቸው ገንዘብ ይኖርባቸው ይሆን?›
ምላሽ
አራሽና ምንደኛ ብላዕ በሀፈ ገጽከ (በፊትህ ወዝ ብላ) የተባሉ ወዛቸውን አፍስሰው ድካማቸውን ሸጠው የሚያገኙት ገንዘብ ከሆነ ዋጋቸውም የአካላቸው ዋጋ ነው እንጅ የሚቀበሉት የአፍኣ ገንዘባቸውን የሚሰጡ የሚያስቀምጡ አይደሉምና ቢያጠራቅሙም ባይሰጡም ንፉግ እንጅ ቀማኛ አያሰኛቸውም
ራስ ካሣ ከላይ በጥያቄና ምላሽ ያስቀመጡት ሀሳብ ፍሬ ነገር፤ ሰርቶ አደሩ በጉልበቱና በወዙ የሚኖር ነው፤ ሀቀኛም ነው፤ የሚያገኘው ገንዘብ የራሱ ነው፤ ባያካፍል ንፉግ ቢባል እንጅ ደክሞ አግኝቶታልና ቀማኛ አይደለም የሚል ነው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው ሀተታ ውስጥ ለሌላ አላካፍል የሚል ጌታ ግን ቀማኛ ነው ብለዋል፡፡ ይሄ ካርል ማርክስ እንደሚለው፤ ቡርዥዋ በዝባዥ ነው፣ ካፒታሊዝም ደግሞ የቡርዥዎቹ መበዝበዣ መንገድ ነው፣ በዚህም መንገድ ድሆችን እየጨቆኑ የእነሱ ያልሆነውን ሁሉ ይሰበስባሉ፤ ድሃው ይበልጥ ድሃ ይሆናል ሀብታሙም ይበልጥ ሀብታም ይሆናል። የራስ ካሣ ዕይታ ከዚህ የማርክስ እይታ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አሁን የራስ ካሣን ዕይታ ከማርክሳዊያን የምግባር ፍልስፍና (Marxian ethics) ጋር እናተያየው፡፡
በማርክሳዊያን የምግባር ፍልስፍና ውስጥ ካፒታሊስቶች ወይም ቡርዥዎች በዝባዦችና ጨቋኞች ናቸው፡፡ በራስ ካሳ ዕይታ ደግሞ ጌቶች ቀማኞች ናቸው፡፡ በራስ ካሣ ዕይታ እኒህ ቀማኛ ጌቶች፣ ዳኞች ለመሆን የምግባር ልዕልና የላቸውም፤ለራሳቸው ቀማኝነትም ዳኛ ሊሾምባቸው ይገባልና፡፡ በማርክሳዊያን ዘንድም አዎ ቡርዥዎቹ በዝባዦች በመሆናቸው ዳኛ ሊሆኑ ቀርቶ በህይወት ሊኖሩ አይገባም፡፡ በመሆኑም በማርክሳዊያን የምግባር ፍልስፍና መልካም ምግባር (good) ማለት በየትኛውም መንገድ እኒህን በዝባዦች ማስወገድ ነው፡፡ እነሱን መግደል፣ መስቀል፣ ማሳደድ ወዘተ የመልካም ስነምግባር መገለጫ ነው፡፡
ሁለቱ የምግባር ፈላስፎች በአንድ እይታ መጥተው የተለያዩት በመዝጊያው ነው፡፡ የልዩነታቸውም መንስኤ ግልጽ ነው፡፡ ለራስ ካሣ ሃይማኖት የጽድቅ መንገድ ሲሆን ለማርክስ ደግሞ ሃይማኖት ማለት ማህበረሰብን ለዘመናት ሲያደነዝዝ የኖረ እጸ ፋርስ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በጌታ ላይ ማመጽ ለራስ ካሣ ነውር (ምናልባት ኃጢአት) ለማርክስ ደግሞ በዝባዥን በአብዮት ማውረድና ማዋረድ የስኬትና መልካም ምግባር መገለጫ ሆኗል። ያም ሆኖ ሁለቱም በመሰረተ ሐሳብ ደረጃ የተግባቡ አሳቢዎች ይመስሉኛል፡፡
በጥቅሉ የራስ ካሣ ‹‹ፍኖተ አእምሮ›› ብዙ ሊባልልለት የሚችል፣ ብዙ ፍልስፍናዊ ዕይታዎች ያሉበት ጥብቅ መጽሀፍ ነው፡፡ ከሃምሣ ስድስት ዓመታት በኋላ ድጋሜ መታተሙና በገበያ ላይ መገኘቱ ታላቅ እድል ነው፡፡ እኔ ወደፊትም በዚህ መጽሐፍ ላይ በሌላ ጽሑፍ የምመለስ ይመስለኛል፤ ሌሎችም ብዙ የሚሉበት ይመስለኛል፡፡ ያሰንብተን!

Read 3778 times