Sunday, 16 October 2016 00:00

‹‹ይህ ወጣት ቴአትር ቢማር ምን ይመስላችኋል›› ቀዳማዊ ኃይለስላሴ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ካለፈው የቀጠለ
ከልጅነት እስከ ሽምግልና ሙሉ ዕድሜያቸውን በቴአትር ሙያ ላይ ያሳለፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ፤ ባለፈው ሳምንት የ80ኛ ዓመት ልደታቸውን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር በህይወታቸውና በዘርፈ-ብዙ የጥበብ ሙያቸው ዙሪያ ያደረጉትን ዘለግ ያለ ወግ አቅርበን ነበር፡፡ ቀሪው ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ (በነገራችን ላይ ተስፋዬ ገሰሰ “ረጅም ጉዞ ወደ ነጻነት” በሚል  የተረጎሙት የኔልሰን ማንዴላ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ሰሞኑን ተመርቋል፡፡)
ለእስር ስለዳረገዎ ‹‹ዕቃው›› ቴአትር ያውጉኝ እስኪ?
‹‹ዕቃው›› ከ ‹‹ተሃድሶ›› በፊት ሀገር ፍቅር እያለሁ የሰራሁት ቴአትር ነው፡፡ ያኔ ብልጠት ነበረኝ፤ ሞኝ አይደለሁም፡፡ ታሪኩ የተመሰረተው በዚምባብዌ ላይ ነው፡፡ በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ ላይ ‹‹አፓርታይድ›› የተሰኘ በዘር ልዩነት ማለትም ነጮች በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱት በደል ነበር። ማንዴላ ይህን የሚታገሉበት ወቅት ነበር፡፡ ያን ጊዜ ዚምባቡዌ ‹‹ሮዲዢያ›› ነበር የምትባለው፡፡ በወቅቱ ሙጋቤ አልነበረም ገዢው፤ ነጭ ነበር፡፡ እና ታሪኩ የሚያሳየው አንድ ጥቁር አፍሪካዊ  በነጮች አገዛዝ የሚደርስበትን ፈተና ነው፡፡ በጃንሆይ ጊዜ መድረክ ላይ አይታይም ተብሎ በሳንሱር ምክንያት ተከልክሏል፡፡ ነገር ግን በመፅሀፍ መልክ በ1961 ዓ.ም ታትሟል፡፡ እዛ ላይ ‹‹ዕቃው›› ገዢው፣ ሰውን እንደ እቃ ያያል፤ ክብሩን ሰው ከእንስሳም ያሳንሳል የሚል መልዕክት አለው፡፡
የመፅሀፉ ሽፋን ላይ ያለው ስዕል ራሱ እቃው፣ ሰውየውና ወንበሩን አንድ አድርጎ ያሳያል፡፡ የሳለው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ነው፡፡ የታሪኩ መጨረሻ ላይ ያ ታጋይ ይገደልና እንደ ዕቃ ይጣላል፡፡ በደርግ ጊዜ ሰራሁት፡፡ ቴአትሩን እኔም ተውኜበታለሁ፤አብራር አብዶም አለበት፡፡ እኔ ነጩን ገዳዩን ሆኜ ነው የተጫወትኩት፡፡ ዶ/ር ሆኜ ጥቁሩን አድንሀለሁ ብዬ ነው በመርፌ የምገድለው፡፡ ያኔ ደርግ ሰውን ይገድላል፡፡ አንዳንዶቹን የራሳቸውን የመቃብር ጉድጓድ አስቆፍሮ፣ እዛው ላይ ይረሸናቸዋል እየተባለ ይወራ ስለነበር፣ተስፋዬም የዚህ አይነት መልዕክት ያለው ቴአትር እያሳየ ነው ብለው ከሰሱኝ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ መጡና ከቢሮዬ ወስደው አሰሩኝ። እኔ ደግሞ አንድ ትልቅ መከራከሪያ አነሳሁ፡፡ እኔ ይህን ቴአትር ደርግ ይመጣል ብዬ አልሰራሁትም፤ ትንቢተኛም አይደለሁም፡፡ የተፃፈውና የታተመው በ1961 ነው ብዬ ሽንጤን ገትሬ ተከራከርኩ፡፡ ስመረመርም ይህን ጭብጥ አጠንክሬ ተከራከርኩ። ያው ከደርግም ውስጥ አንዳንድ ደህና ሰዎች አይጠፉም፡፡ ለምሳሌ ፍቅረስላሴ ወግደረስ በጣም ጥሩና ለምሁራን አጋዥ ነበር፡፡ “ለምሁራኖቻችን ትንሽ ነፃነት አንሰጥም እንዴ ተዉ እንጂ” ብሎ መርማሪዎቹን አለዝቦልኛል፡፡ እንግዲህ የብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ የሆንኩት ከዚህ እስር ከተፈታሁ በኋላ ነው፡፡ እነሱ የጃንሆይን ስርዓት “ሰው በላ” ብለው በኋላ እነሱም ሰው ቢበሉም ሁሉንም ነገር ጨለማ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በደርግ ስርዓት ሳንሱር ነበር፡፡ አሁን በመርህ ደረጃ ሳንሱር ቢነሳም ሌሎች ኪነ-ጥበቡን የማያላውሱ ቴክኒካዊ አሰራሮች አሉ ይባላል። እርስዎ የቀድሞውንና የአሁኑን የሳንሱር ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
እዚህ ላይ ለማስተካከል ያህል በኢህአዴግ ጊዜ የቀረው ቅድመ-ሳንሱር ነው፡፡ ድህረ-ሳንሱር አለ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው … በደርግ ጊዜ ቅድመ ህትመት ወይም ቅድመ ትርኢት ሳንሱር ነበር፡፡ አሁን “ቅድመ”ው ቀርቷል፡፡ ይሄም አንድ እፎይታ ነው፡፡ አርቲስቱ ይተነፍሳል፤ ቢያንስ ይፅፈዋል፡፡ የተወሰነ ጊዜም መድረክ ላይ ለህዝብ ያቀርበዋል፡፡ ለምሳሌ “ወይ አዲስ አበባ” የተሰኘው የ97 ምርጫ ሰሞን ላይ የተሰራውና ጌትነት እንየው አዘጋጅቶት የነበረው ቴአትር የቀረው በድህረ ሳንሱር ነው፡፡ ቅድመ ሳንሱር አልነበረበትም። በብሄራዊ ቴአትር ታይቶ ነበር፡፡ ጋዜጣም እንደዚሁ ነው፤ ፈቃድ ታወጪያለሽ ታሳትሚያለሽ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አታሚውም አሳታሚውም አዘጋጁም ሁሉም ይያዛሉ፡፡ ጋዜጣውም ይዘጋል፡፡ ይሄ ነው ድህረ ሳንሱር፡፡
ታዲያ ከቀድሞው ምኑን ተሻለ?
እእ … ይሻላል፡፡ ቢያንስ ለትንሽ ጊዜም ያስተነፍሳል፡፡ ኢህአዴግ እንደመጣ እነ “ምኒልክ”፣ “ጦቢያ” እና ሌሎች በርካታ ጋዜጦች ወጥተው አንድ ሰሞን ፍንደቃ ላይ ነበርን፡፡ አሁን “አዲስ አድማስ” እና “ሪፖርተር” ናቸው የቀሩት፡፡ ሌላ ምን አለ? ይሻላል ያልኩት ትንሽም ቢሆን ትተነፍሻለሽ፤ መጀመሪያውኑ ተከልክለሽ ቁጭ ከምትይ ለማለት ነው፡፡
“ስንብት” የሚል ቴአትር ሰርተው አድናቂዎችዎን አስደንግጠው ነበር ይባላል፡፡ በቃ ከዚህ በኋላ ተስፋዬን በኪነ ጥበቡ አናገኘውም የሚል ስሜት ተፈጥሮ ነበር፡፡ እስቲ ስለእሱ ያጫውቱን …
“ስንብት” ቃሉ አሻሚ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔና አንቺ እዚህ ቆይተን ስንለያይ “ደህና ሁን፣ ደህና ሁኚ” እንባባላለን፡፡ ይህ ማለት ሌላ ጊዜ አንገናኝም ማለት አይደለም፡፡ በቴአትሩም ጉዳይ በቃሉ (በርዕሱ) አሻሚነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እኔ ከአንድ ዓመት በኋላ ጡረታ ትወጣለህ ተብዬ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠኝ፣ አብረውኝ የኖሩት የኪነ ጥበብ ሰዎች እነሱም ሳይሞቱ እኔም ሳልሞት አንድ ትርኢት ላቅርብ ብዬ ነው “ስንብት”ን የሰራሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ በስንብት ቴአትር ታሪክ ላይ መጨረሻ ኦማር ኻያም ይሞታል፡፡ ሰው የእውነት መሰለውና ስጋት ገባው፡፡ ለምሳሌ በ”ኦቴሎ” ላይ ኢያጎን ሆኖ ሲሰራ የእኛ አገር ተመልካች የእውነት እንደ ኢያጎ ነው የሚመስለው፤አበበ ባልቻ የተጫወተው፡፡ አስናቀም የእውነት ይመስላቸዋል። ያኔ እኔም የኦማር ኻያም ገፀ ባህሪ ሲሞት፣ እኔ እንደሞትኩ ቆጠሩት፡፡ የኦማር ኻያምን ወደ ተውኔት ለውጬው ነው ‹‹ስንብት›› ያልኩት። በቋሚነት በሰራተኝነት አታገኙኝም ለማለት ነው፡፡ አሁን ሰዎች ቃና ቲቪን ሲመለከቱ፣ ከገፀ-ባህሪው ጋር ሲሰዳደቡ አያለሁ፤ ቤቴም ያሉ ሰዎች ‹ይሄ ተንኮለኛ ክፉ› ይላሉ፡፡ እውነተኛውን ሰው ከገፀ-ባህሪው መለየት አይችሉም፤ተመልካቹ ገና አልሰለጠነም፡፡ ያኔ አንዱ ነፍጠኛ፣እኩዩን ገፀ ባህሪ ካልገደልኩ ብሎ ሲኒማ አድዋ ላይ ተኩሶ ስክሪኑን ብትንትኑን አውጥቶታል፡፡
እስኪ እስከዛሬ የሰሯቸውን ተውኔቶች፣ ትርጉሞች፣ ድርሰቶችና ግጥሞች ያስታውሱኝ?
ያው አብዛኛዎቹንና ዋናዎቹን በጭውውታችን አንስተሻቸዋል፡፡ አሁን ሁሉንም መግለፅ አልችልም። በደፈናው ከ12 በላይ ተውኔቶች፣ ከ10 በላይ ልቦለዶች፣ የጥናት ስራዎች የእነ ሼክስፒርና የኦማር ኻያም አራትና አምስት የሚሆኑ ትርጉሞች ሰርቻለሁ። በትወናውም ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ የሰራኋቸውን በአጠቃላይ ‹‹ይሉኝታና ፍቅር›› በተሰኘው ልቦለድ መፅሀፌ ላይ ዘርዝሬያቸዋለሁ። የታተሙትን ማለት ነው፡፡ በርካታ ያልታተሙ አሉ።
ወደ ግል ህይወትዎ ስንመጣ … አንዳንዶች ሁለት ልጆች እንዳሉዎት ሲናገሩ፣ ሌሎች አምስት ልጆች አሏቸው ይላሉ፡፡ ትክክለኛው የትኛው ነው?
ሁለቱን ልጆቼን የወለድኳቸው ከመጀመሪያ ባለቤቴ ነው፡፡ የአሁኗ ባለቤቴን ሳገባ ሶስት ልጆች ቀድማ ወልዳ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ገና ልጆች ነበሩ፤ እኔ ነኝ ያሳደግኳቸው፡፡ ከአብራኬ ባይወጡም ልጆቼ ናቸው፡፡ ከባለቤቴም ጋር ላለፉት 30 ዓመታት በፍቅርና በመተሳሰብ ኖረናል፡፡ ከቀድሞዋ ሚስቴ ጋር ብንለያይም ሰላማዊ ግንኙነት ነው ያለን፡፡ ስለዚህ ልጆቼ አምስት ናቸው፡፡ ሁሉም ለእኔ እኩል ናቸው፡፡ 10 የልጅ ልጆችም አሉኝ፡፡ ደስተኛ አያት ነኝ፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ምንስ ይበጃል ይላሉ?
ይሄን ጥያቄ ፖለቲከኛ ቢመልሰው ይሻል ነበር። ከያኒ የስሜት ሰው ነው፤ የማመዛዘንና የማነፃፀር ችሎታው ይህን ያህል አይደለም፤ብዙ ጊዜ ስሜታዊ ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ህይወት ሲጠፋ አግባብም አስፈላጊም አይደለም፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ድርቅ መጣ፤ በወሎ 300 ሺህ ሰው አለቀ ተባለና አገዛዛቸው እክል ገጠመው፡፡ ደርግ ይህንን ተጠቅሞ ፈነገላቸው፤ ረሀብና እልቂት በደርግም አልቀረም። አሁንም በኢህአዴግ ረሀብና ቸነፈር ገብቶ ህዝቡ ተቸገረ፤ አሁንም የሰው ህይወት እየጠፋ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ በነጭና በቀይ ሸብር አንድ ሙሉ ትውልድ አልቋል፡፡
አሁንም ቢሆን ባለፉት የምርጫ ጊዜዎች ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሞተዋል፡፡ በቀደም በኢሬቻ ላይ መዓት ሰዎች አለቁ፡፡ የአገር መሪዎች ጃንሆይም ሆኑ መንግስቱ፣ መለስም ሆነ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በግላቸው ሰው እንዲሞት ፍላጎት ባይኖራቸውም ለሚከሰተው ነገር መሪ በመሆናቸው ህዝብ ይጠይቃቸዋል፡፡ በወቅቱ ሁኔታ ላይ ስትጠይቂኝ ከህዝቡ ጎን ቆሜ ጥያቄዬን አቀርባለሁ፤ እነሱም ትክክለኛ መልስ መስጠት አለባቸው፡፡ መልቀቅ ካለባቸው ይልቀቁ፡፡ ምንድነው ስልጣን ላይ ጥብቅ ማለት፡፡
እንደ ኃይለ ስላሴ ተዋርዶ ዙፋን መልቀቅም አለ እኮ! ያ ከመሆኑ በፊት በትክክል መምራት፣ ካልቻሉ ደግሞ በቃ ይልቀቁ፡፡ ምንድነው ነገሩ? ምን አይነት እርግማን ነው ሀበሻ ላይ የወደቀው? በጣም አዝናለሁ። አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልገው ችግር ነው የተከሰተው፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም ማለት አልችልም፡፡

Read 1907 times