Sunday, 16 October 2016 00:00

የፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ዳናዎች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

ሁልጊዜ ሕይወት ዥንጉርጉር ናት እንላለን፡፡ ዥንጉርጉርነትዋ የሚታየው ግን ከአንድ ማማ ላይ ተቁሞ አይደለም፡፡ በመኖር ምህዋር በመሽከርከር እንጂ! የሰው ልጅ በሕይወት ሲኖር የየቀኑ ዳና በህይወቱ ገጾች ላይ ይኖራሉ፤ ልዩነቱ ያንዱ ዳና፣ በንፋስ እንደሚሸፈን ትቢያ፣ ሥር የሌለው መሆኑና የሌላኛው ደግሞ፣ በእርጥብ ሲሚንቶ ላይ እንደሚቀረፅና ለሁልጊዜም ታትሞ እንደሚቀር ጠንካራ መሆኑ ነው፡፡
ይህንን ዳና ለማየት ደግሞ የሰው ልጆችን የህይወት ጉዞ፤ ወይ በወረቀት አሊያም በፊልም፤ ካልሆነም በድምፅ ቀርፆ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በአገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የትልልቅ ሰዎችን የሕይወት ጉዞ የሚያሳይ የህይወት ታሪክና ግለ-ታሪክ ማየት  ጀምረናል፡፡ በተለይ በመጽሐፍት የተጠረዙትን፡፡ ታዲያ ከእነዚህም ውስጥ የሚበዙት የወታደራዊ ተጋድሎዎችና የፖለቲካ ጉዞ ማስታወሻዎች ናቸው፡፡… እኔ በዛሬ ጽሑፌ ልዳስስ ያሰብኩት ግን ከምሁራን አምባ ከፍ ያለ ሀገራዊና አህጉራዊ ሚና ያላቸውን የፕሮፌሰር ሽብሩን ተድላን ግለ ታሪክ የያዘውንና ‹‹ከጉሬዛም ማሪያም እስከ አዲስ አበባ›› በሚል ርዕስ የታተመውን መጽሐፍ ነው፡፡
ይህ መጽሐፍ በግሌ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከታተሙት መጻሕፍት በላይ የታወቁ የፖለቲካ፣ የሳይንስና የሥነ ጽሁፍ ሰዎችን ያካተተ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ጓድ መንግስቱ ገመቹ (የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፀሐፊ)፤ አቶ ብርሃኑ ባይህ (የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባል)፤ አቶ ያየህ ይራድ ቅጣው፤ ቢልልኝ ማንደፍሮ (የትምህርት ሚኒስቴር የነበሩ) ጓድ ፍስሃ ደስታ (የኢትዮጵያ ም/ፕሬዚዳንት የነበሩ) በአሉ ግርማ፤ ዶክተር አክሊሉ ለማ፣ እሸቱ ጮሌ፣ ደበላ ዲንሳና የመሳሰሉት በታሪኩ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተካትተዋል፡፡
ደራሲው ፕሮፌሰር ሽብሩ፣ዘመናዊ የሕይወት ታሪክ አፃፃፍ አፅንኦት ለሚሰጠው የልጅነት ታሪካቸውም በርካታ ገፆች ሰጥተው፤ በችግኝነት ዘመናቸው ሊያጣምሟቸው የመጡትን ነፋሳት ሁሉ ተቋቁመው፣ አበባና እሾህ አልፈው የሄዱበትን መንገድ በሚጥም ሁኔታ ተርከውታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔም ልጅነት ላይ የሬዲዮ ፕሮግራም ለሦስት ዓመታት ያህል፣ በቴሌቪዥን ደግሞ ለስምንት ወራት ያህል ስሰራ ያጤንኩትን የሚመሥል ኢትዮጵያዊ መልክ አይቼ ተደንቄበታለሁ፡፡… ልጅነታቸው ያስቃል፤ ያስደንቃል፤ ያስተምራል፡፡
ፕሮፌሰር ሽብሩ የስማቸው ስያሜም፣ ከጣሊያን ዘመን ሽብር ጋር ተያይዞ የወጣላቸው ስለሆነም በሀገራችን ስም አወጣጥ በራሱ ከሕይወት ገጠመኝ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ያሣያል፡፡ የገጠር ልጅ ጨዋታ፣ የገጠር ልጅ ሥነ-ልቦና፣የተማሪነት ሕይወት፣ ስሜትና ሕልም ሁሉ ይታይበታል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ገፆችም ለልጅነት ሕይወት ጓደኝነት ተሰጥቷል፡፡ በታሪኩ መጀመሪያም የፕሮፌሰሩ ውልደትና ልጅነት ትረካ ከመጀመሩ በፊት ብዙዎች የውጭ ፀሀፍት እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ የፕሮፌሰሩ አባትና እናት ቀዳሚ ታሪክ ተፅፏል፡፡ ይህ ደግሞ የቀጣዩን የታሪኩን ባለቤት ሰብዕናና መልክ ለማየት በእጅጉ ይረዳል፡፡ የመጀመሪያዎቹን የልጅነት ምዕራፍ ስላሳለፉበት ደብረማርቆስ ከተማ ሲተርኩ እንዲህ ይላሉ፡-
“አንድ ዓመቴ ጥር ላይ አልፎ በሚያዚያ 1933 ዓ.ም ጣሊያን ተባረረና ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ መንግሥት ከመሰረቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባቴ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ደብረማርቆስ ተቀጠረ፡፡ ስለሆነም ከሁለት ዓመቴ ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመቴ ድረስ ደብረማርቆስ ከተማ፤ አብማ ከሚባለው አካባቢ ነበር ያደግሁ”፡፡
ታዲያ እኚህ  የዛሬው ፕሮፌሰር የያኔው አንድ ፍሬ ልጅ ማርቆስ ነበር፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ፊደል የቆጠረው፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ መቀጠሉ አልሆነለትም፡፡  ያኔ ልጅ የነበረው ሽብሩ የዋዛ አይደለም፤ እልኸኛ ነው፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት ገጠመኛቸውን እንዲህ ገልጸውታል፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን ባለቤታቸው (የቄስ አስተማሪው) እንጀራ መጋገሪያ የሚሆን ባህር ዛፍ ቅጠል ሰብስቤ እንድመጣ መምህሩ አዘዙኝ፡፡ እኔም በኛ ቤት ውስጥ ምንም ሥራ ታዛዤ ስለማላውቅ (እንዴት ተደፈርኩ ይመስላል) አላደርገውም አልኩ። ከዚያም ሮጥኩ፡፡ እርሳቸው ዓይነ ስውር ስለነበሩ አባረው ሊይዙኝ አይችሉም፤ ሌሎች ተማሪዎችና ባለቤታቸው ተጋግዘው አባረው ይዘውኝ ለመምህሩ አስረከቡኝ፡፡ መምህሩም ባልተዛመደ አንጀታቸው ከባድ ቅጣት ቀጡኝ፤… በዚህ ሁኔታ ጥቂት እንደቆየን ባለቤታቸው ነጠላቸውን ደርበው ከቤት ወጥተው ተጓዙ፡፡ ተማሪዎች ‹‹ሀ…ሁ›› እያሉ ሲጯጯኹ፣ ከአካባቢው ጥቂት ለውርወራ የሚያመቹ ድንጋዮች በኪሴ አስቀምጬ፤ ብዙ ሳይቆይ መምህሩን ጅንፎ (ዱላ ጫፍ ላይ ያለው ከብረት ጥምዝ የተሰራ) ባለው በራሳቸው መቋሚያ ራሳቸውን ፈንክቻቸው ሮጥኩ።”
ልጅ ሽብሩ ኃይለኛ እንደነበረ የሚያሣዩ ብዙ ሁነቶች አሉ፡፡ በልጅነት ከጓደኞቹ ጋር በዘመኑ የሞት ፍርድ፤ (በስቅላትና በጥይት) በተፈረደባቸው ግለሰቦች ላይ፣ፍርዱ ሲከናወን ለማየት የሚያደርጉትን ክትትል እንደ ፊልም እናያለን። ከዚያም በተጨማሪ የልጅነት ታሪኩ ከተለያዩ ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ባንድ ጠጠር ብዙ መምታት የተቻለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ብቸና ከሹሙ አባቱ ጋር የገቡት በላይ ዘለቀ በተሰቀለ በሁለተኛው ዓመት እንደሆነ መጽሐፉ ይነግረናል፤ የማሕበረሰቡ ልማድና ወግ፣ በዐላትና ሌሎችም ነገሮች ይተረካሉ፡፡
የወገን ጦር ከጣሊያን ሰራዊት ጋር ባደረገው ጦርነት ጎጃም ደጃዝማች ገሠሠ በለው በመንግሥት ላይ አኩርፈው ስለነበር፣ ከጠላት ጋር መዋጋት አሻፈረኝ ብለው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ይመሥላል፡-
     እኔስ አልወርድም ስቲት
ሸዋ እንደበላ ይሙት----- የተባለው፡፡
ይህ የግለ-ታሪክ መጽሐፍ መቸቱ ከ”ፍቅር እስከ መቃብር” ጋር ኩታ ገጠም ስለሆነ በእጅጉ ስሜት የሚነቀንቅ፤ ወደ ኋላና ወደ ፊት የሚወዘውዝ ዓይነት  ነው፡፡ ስለ ዲማ ጊዮርጊስ የሃይማኖት ሊቃውንት ሲያወራ፤ እነ ፊታወራሪ አሰጌ፣ እነ ፊታውራሪ መሸሻ ከፊታችን ድቅን ማለታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ የሀገራችንን የጥበብ ምንጭና የትምህርት ጅማሮ በማስታወስ የጀንበርዋን ፀዳል በሃሳባችን መፈትፈት ግድ ነው፡፡
የዲማ ደብተራዎች ብራና ፍቀው፤ ቋሚ የሃይማኖት መጻሕፍት እየገለበጡ ለአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ይሸጡ እንደነበር ፀሀፊው ሹክ ይሉናል፡፡ በተለይ የሊቀ ጠበብት አድማሱ ጀንበሬ የመጽሐፍ ሽያጭና በአቡጀዴ የተሰፉ ጠገራ ብሮች ነገር ብዙ ነው - ብዙ፡፡ መቼም ሁሉም አይፃፍ ሆኖ እንጂ!
የአሁኑ ፕሮፌሰር የልጅነት ጨዋታ፣ ትምህርትና ገጠመኝ በእጅጉ መሣጭና ውብ ነው፡፡ ይህ ውበት ደግሞ ፈገግታ አጫሪነትና ሣቅ ፈጣሪነቱን ብቻ ሳይሆን፣ የማሕበረሰቡን የእርስ በርስ ትሥሥር የሚያሣይና የዘመኑን ማኅበረ ፖለቲካዊ፣ ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ-ባህላዊ መልክ - ምዕራፎች ሥዕል ያስቀመጠ መሆኑ ነው፡፡ ልጅነት ውስጥ የሚታየው አጠቃላይ የማህበረሰቡ መልክ ቢሆንም ገፅ 34 ላይ ያነበብኩት የትንሹ ሽብሩ ተድላም ማንነት በኋላ ላየኋቸው የዱክትርናና የፕሮፌሰርነት ዘመን መልክ ጠቋሚዬ ነበር፡፡ ይህ ገጠመኝ ብዙ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለን ብዙዎቻችን እንደምናደርገው፣ መፀዳጃ ቤት ብልግና ነክ ፅሁፍ ፅፈው ማን እንደፃፈው በተማሪዎች ላይ ምርመራ ተጀመረ፡፡ በኋላም በተማሪዎች እጅ ፅሁፍ ለመለየት ሙከራ ሲደረግ የፃፉት እነ ሽብሩ አምልጠው፣ አያሌው ወልዴ የተባለው ጓደኛቸው ላይ ተፈረደ። የቅጣቱ ቀን ዓርብ ሲደርስ ግን የሽብሩ ተድላ ልብ እምቢ አለች፡፡ ከዚያም “የፃፍኩት እኔ ነኝ” በሚል ፍርዱን ወደ ራሱ መለሰ፡፡
ይህንን ባህርይ በተለያዩ የዕድሜ አንጓዎች በግለ ታሪክ ፀሐፊው ህይወት ገምግሜያለሁ፤ ለጓደኛ ዋጋ መክፈል፣ ስለ ዕውነት መቆምና ራስን ማካፈል! ይህ ባህርይ ምናልባት ከእናት ማንነት ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡ የዚህ ልጅ (ሽብሩ ተድላ) ቸርነት የተባለ ጓደኛ እናቱ ብትሞትበት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት እርሱ ቤት እንዲኖር አድርገዋል፡፡ ከአሁኑ ስግብግብነት ጋር አስተያይቼ በእጅጉ ገርሞኛል። ሕይወትን ማካፈል ያኔ ሕይወት፣ ዛሬ ቂልነት ነው! … የዘመን ዐውድ ብዙ ያሳያል፡፡ የቀድሞ ዘመን ጓደኝነትን ጥብቀትና ኪዳን በግርምት ያየሁበትም መጽሐፍ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ግለ ታሪክ ሲፃፍ የአንድን ሰው ሕይወትና ማንነት ብቻ ሳይሆን የዘመኑን ሁለንተናዊ መልክ ማሳያ ስለሆነ በተለይ “ጓደኝነት” በሚለው ርዕስ፣ ባየሁት ከወንድምነት ያልተናነሰ መደጋገፍና ፍቅር ከልቤ ቀንቻለሁ፡፡ ምነው ዛሬስ ቢኖር! … በሚል ቁጭት ከንፈሬን ነክሻለሁ፡፡ ዛሬ ሸቀጥ ንጉስ ሆኖ ዙፋን ላይ ሲንጠላጠል፣ የሰው ልጅ ሸለቆ ገብቶ ወደ ዙፋኑ ከፍ ሊል ይቧጥጣል! … ፈጣሪ ግን ለሰው ልጅ የሰጠው ስፍራ ከፍታ እንጂ ዝቅታ አልነበረም፡፡ ራስነት እንጂ ጅራትነት አይደለም!
ልጅነት ላይ ገፅ 57 ሶስተኛው አንቀፅ ላይ ያለው የልጅ ሽብሩ ተድላ ኃይለኛነትና እልህ በጣም አስደንቆኛል፤ጥቃት አይወድም፡፡ ብዙ ነገሩ የልጅነት ጓደኛዬን ምንተስኖት ገላግሌ የሚባል የሲዳሞ ልጅ (ጎጃሜ) ያስታውሰኛል፡፡ በጣም ተንኮለኛ፣ ግን ለቀረበው፣ በተለይ ለኔ የልብ ጓደኛ። በብሄራዊ ውትድርና ቢያልፍም በዓመት ቢያንስ ሶስቴ በህልሜ ይመጣል፡፡
 በጥቅል ሳየው መጽሐፉን ፀሀፊው የተረኩበት መንገድና ፍሰት በእጅጉ የሚጥም ነው፡፡ ለዚህ ጣዕም ደግሞ ምክንያቱ ጎጃም ውስጥ ማደጋቸው (ቋንቋ በተወለዱ ሳይሆን ባደጉ ነውና!) ብቻ አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ እናትየው በጣም ብሩህ አስተሳሰብ የነበራት አስተዋይ፣ ባትማርም ብዙ ትውፊት የምታውቅ መሆንዋ ነው፤ እንደ ፀሐፊው አባባል፡፡ አዋቂ ነበረች፣ በግጥምም ታንጎራጉር ነበር። እሳቸው እንዳሉት፤ጥበብ ከእናት እንደሚጋባ የጀርመኑ ገጣሚና ደራሲ ገተንና የቲኤስ ኢሊየትን እናት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የስነ - ልቡና ጠበብት እንደሚሉት፤ ልጆች ከእናታቸው ጋር ብዙ ጊዜ ስለሚያሳልፉ ብዙ ነገራቸውን ይቀስማሉ፡፡ የሽብሩ ተድላም ከዚህ የተለየ አልመሰለኝም፡፡
ሌላው በመጽሐፉ ውስጥ ያስተዋልኩት፣በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁነቶች የተነሳ የኢትዮጵያውያን ባህልና ቋንቋ መዛነቅን ጭምር ነው፡፡ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይና ከሌሎችም ቦታዎች የመጡ ሰዎች ተጋብተው፣ ተዋህደው መኖራቸው፣ ማንነታችን የሰርገኛ ጤፍ ዓይነት ነው እንደተባለው ለመለየት እንኳ የሚያስቸግር ሆኗል፡፡ አሁን አውቀን ባናጠፋው!
ከስነ ጽሑፋዊ  ለዛ ጋር ተያይዞ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያስተዋልኩት፣ ስራዬ ተብለው የተሰበሰቡ የስነ ቃላት ውበት ነው፡፡ በዚህ ዘውግ ውስጥ ከሚካተቱት ዝርያዎች የሙሾ ግጥም፣ ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ፣ ጸሎት፣ ምርቃት በተለይ ባላድስ መካተታቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል፡-
ጎሹ እንደ ኦርዮን ዓሊ እንደዳዊት
ከጥንት አይደለም ወይ ተልኮ መሞት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ ዘይቤን (ንቡር ጠቃሽ) የተጠቀመ ግጥምና ሌሎችን ማየት ይቻላል፣ አንድ ልጅዋ በፈንጣጣ በሽታ የሞተባት ሴት እግዜር ላይ አንጀቷ ቢቃጠል እንዲህ ብለዋለች፡-
አንድ ትገድላለህ፣ ሰባት ታድናለህ
የሴት ልጅ ነህና፣ መች ፍርድ ታውቃለህ፡፡ ብላዋለች፡፡ (ሰባት ልጅ ያላት አንድ ልጅ ሳይሞትባት፣ የርሷ አንድ ልጅ በፈንጣጣ ሞቶባት ነው)
ሌላም ብላለች፡-
አብ እሳት፣ ወልድ እሳት፣ መንፈስ ቅዱስ እሳት፣
ወትሮም ልማዱ ነው አሳይቶ መንሳት፡፡
የጥቃት ቀኖች ላይ የተገጠሙ አሉ፡-
የሱ ቤት ተከድኖ፣ የኛ ቤት ያፈሳል፣
የሱ ማሳ ታርሶ፣ የኛ ዳዋ ለብሷል፣
የኛም መሄጃችን፣ የርሱም ጊዜ ደርሷል፡፡
 በመጽሐፉ ውስጥ የስነ ልቡናዊ ማንነትና የአስተሳሰብ ለውጥ ሀሁ የሚጀምረው ከምዕራፍ ስምንት ነው፡፡ ምዕራፍ ስምንት ወጣቱ ሽብሩ ተድላ፣ የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ አልፎ ኮተቤ የገባበት ጊዜ ነው፡፡ በልጅነቱ ከአካባቢው የተመለከተውን ሽፍትነትና ጠመንጃ ማንገብን ብቻ ይመኝ የነበረው ወጣት፤ የሰፊዋን ዓለም መልክ የሚያይበትን መነፅር የገጠመውና የመጪውን ረጅም ጉዞ ጎዳና የጠረገው እዚህ ነው፡፡ በኋላ ታላላቅ የተባሉ ሰዎችም የተገናኙበት መስክ እዚሁ ነው፡፡ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኮሎኔል ፍስሀ ደስታን ጨምሮ፡፡ (ከፍስሀ ጋር ለአራት ዓመታት ያህል በአንድ ትምህርት ቤት ተምረዋል) ኮተቤ ከገቡ ከወራት በኋላ ወጣት ሽብሩ ሲኒማ ቤት ገብቶ አዲስ ህይወት አጣጥሟል፡፡ ኮተቤ በማህበራዊ ህይወት የነበረውን አዲስ ክስተት ገፅ 153 ላይ እንዲህ እናነባለን፡-
“ከኮተቤ ተማሪዎቹ ጋር የነበረኝ ግንኙነት በፊት ጎጃም ውስጥ ከነበረኝ የተማሪዎች ግንኙነት በጣም የተለየ ሆነ፤ ኮተቤ እንደ ልብ ማንንም ልጋፋ አልቻልኩም፡፡ እየተጣላሁም ተደባድቤያለሁ፣ ብዙ ጊዜ በተሸናፊነት ደረጃ ስለሆነም፣ አቅምን አውቆ መኖርን መለማመድ ጀመርኩ፡፡ ኮተቤ አመጋገቡም ይለይ ነበር፡፡ አኗኗሩም ትምህርቱም የመጻሕፍቱም ብዛት እንደዚሁ! …“
የቋንቋ ነገርም ለጥቂት ጊዜ እንዳስቸገራቸውና በኋላ ግን ለምደውት ከአዲስ አበቤዎቹ እኩል እንዳቀላጠፉት ይነግሩናል፡፡ መጻሕፍት በማንበቡም በኩል “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ከሚለው የአቶ ተማቹ ታሪክ በቀር ጎጃም በገዛ ፍቃዱ ልቦለድ ያላነበበው ተማሪ ሽብሩ፤ አስረኛ ክፍል ገብቶ በእንግሊዝኛ የተፃፉ አጫጭር ልቦለዶችን ለማንበብ በቃ፡፡ የልጅነትና ወጣትነት ጊዜው በሃይል የተሞላው ሽብሩ፤ ኳስ ሜዳ ገብቶ ጎል ሲጠብቅ እንኳ ጎል ያገባበትን ልጅ ችካል ነቅሎ ያባረረ ነው፡፡ ይህ ዕድሜው ሲያልፍ ደግሞ፣ ከፍ ወዳለ ማስተዋልና ሩቅ ማየት የተለወጠ ሰው፡፡
ዘጠነኛ ክፍል እያለም አንድ ተማሪ “እናትክን” ብሎ ሰድቦት መልሶ የሚሰድበው መስሎት ሲጠባበቅ ሙሉ የነበረ የቀለም ብልቃጥ ወርውሮ ፈንክቶታል። ሌላው እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካነበብኩት ታሪክ ሁሉ ሌት ተቀን በህሊናዬ እየመጣ የሚጎተጉተኝ ታሪክ፣ በወሎው ድርቅ ዘመን ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የነበረ አንድ ዶክተር ታሪክ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ደግሞ የዛሬም ማንነታችን መስተዋት ነው፡፡
ፀሐፊው እንዲህ አስቀምጠውታል፡- (ጊዜው የድርቅ ጊዜ ነበር)
“የትምህርት ፋካልቲ መምህር (ዶክተር) ቢሮው ሄጄ፣ አዲስ ለተቋቋመው የዩኒቨርሲቲው የእርዳታ መዋቅር የሚውል አስር ብር እንዲለግስ ስጠይቀው፣ ገንዘብ ለማዋጣት የማይችል መሆኑን ገለጠልኝ። የሰጠኝም ምክንያት፣ በዚያን ጊዜ በዱሮው አውሮፕላን ጣቢያ አካባቢ ቪላ እየገነባ መሆኑን ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ራሱ የህዝብ ብሶት ተቆርቋሪ ሆኖ በቀበሌ ተመራጭነት የአካባቢውን ሰዎች ለመምራት ዕድል ተሰጥቶታል፡፡ የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻን ካስተባበሩት ሰዎችም አንዱ ነው፡፡” … የባንዲራ ሥር ቁማርተኞች ሁሌም እንዲህ ናቸው - የአዞ እንባ የሚያነቡ!….
በቀጣዩ ዳሰሳዬ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፣ ከታላላቅ ባለስልጣናትና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጓደኞቻቸው ጋር በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ የነበራቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምሁራዊ ሚና ምን እንደሚመስል አስቃኛለሁ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን!

Read 1594 times