Sunday, 16 October 2016 00:00

ዱባይ በአለማችን ረጅሙን ማማ መገንባት ጀመረች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ይፈጃል ተብሏል

    የአለማችን ረጅሙ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የሆነው ቡርጂ ከሊፋ መገኛ የሆነቺው ዱባይ በእርዝማኔው አቻ የማይገኝለት ይሆናል የተባለውን ማማ መገንባት መጀመሯን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቃለች፡፡
ኢማር ፕሮፐርቲስና ዱባይ ሆልዲንግ የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች በጋራ የሚያሰሩት አዲሱ ማማ ግንባታው በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የዘገበው ሮይተርስ፣ማማው ምን ያህል እንደሚረዝም ግልጽ መረጃ አለመውጣቱን ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ግንባታው የተጀመረው ማማ፣ 829.8 ሜትር ከሚረዝመው የአለማችን ቁጥር አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ቡርጂ ከሊፋ የሚበልጥ እርዝማኔ እንደሚኖረው መረጃዎች መውጣታቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ኢማር ፕሮፐርቲስ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በሰጠው መግለጫ ለማማው ግንባታ 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚደረግ ማስታወቁን ሲቢቢ የዜና ወኪል አስታውሷል፡፡
ማማውን ዲዛይን ያደረገው ስፔናዊው አርክቴክት ሳንቲያጎ ካላትራቫ ቫልስ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የከተማዋን ሙሉ ገጽታ ማሳየት የሚችል መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአለማችን ረጅሙን ማማ ሆኖ የተመዘገበው በቶክዮ የሚገኘው ስካይ ትሪ የተባለው ማማ ሲሆን፣ 634 ሜትር ቁመት እንዳለው ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 2087 times