Sunday, 16 October 2016 00:00

ኢስቶኒያ ቆሻሻ ከውጭ አገራት እየገዛች ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢስቶኒያ መንግስት ላቋቋመው ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ተቋም በግብዓትነት የሚውል ቆሻሻ እጥረት በማጋጠሙ ከውጭ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ እየገዛ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
አገሪቱ ከቆሻሻ ሃይል ለሚያመነጨውና ኢሩ በተባለው አካባቢ ለሚገኘው ተቋም በቂ የሆነ ቆሻሻ በአገር ውስጥ ማግኘት ስላልቻለች፣ ከተለያዩ አገራት ቆሻሻ ለመግዛት መገደዷን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው አመት ብቻ 56 ሺህ ቶን ቆሻሻ ከውጭ አገራት ገዝታ እንዳስገባች ገልጧል፡፡
የሃይል ማመንጫው ባለፈው አመት ብቻ 245 ሺህ ቶን ቆሻሻ በጥሬ እቃነት መጠቀሙንና በአገር ውስጥ በቂ ቆሻሻ ባለመገኘቱ ሳቢያ ስራ ሊያቆም የሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የአገሪቱ መንግስት ቆሻሻን ከውጭ አገራት በመግዛት ስራውን ለማስቀጠል መወሰኑንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ለኢስቶኒያ መንግስት ቆሻሻ በመሸጥ ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል ፊንላንድና አየርላንድ ይገኙበታል ያለው ዘገባው፣ ቆሻሻን ከውጭ አገራት ገዝቶ በማስገባት ሃይል የማመንጨት ኢንቨስትመንቱ አዋጪ እንደሆነ አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን መናገራቸውንም አክሎ አስታውቋል፡፡

Read 1061 times