Sunday, 16 October 2016 00:00

ሳምሰንግ “ጋላክሲ ኖት 7”ን እርም ብሎ ተወው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - እየጋየ ያስቸገረውን ይህን ምርቱን በማቆሙ 17 ቢ. ዶላር ያጣል
                       - ደንበኞቹ በአስቸኳይ ስልኩን መጠቀም እንዲያቆሙ አሳስቧል

       በቅርቡ ለገበያ ያቀረበው የጋላክሲ ኖት 7 ምርቱ ባትሪው በቀላሉ የሚግልና እሳት የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የሰነበተው የደቡብ ኮርያው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሰንግ፣ ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ ከአሁን በኋላ ምርቱን ለማቆም መወሰኑን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በአለም ዙሪያ የሚገኙ ወኪሎቹንና የሞባይል መሸጫ መደብሮችን “ጋላክሲ ኖት 7 መሸጣችሁን አቁሙ፣ እኔም ማምረቴን እስከወዲያኛው አቁሜያለሁ፤ የሸጥኳቸውንም መልሼ እሰበስባለሁ” ሲል መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ ጋላክሲ ኖት 7 ለገዙ ደንበኞቹም እሳት ሊፈጥርና አደጋ ሊያደርስባችሁ ስለሚችል አሁኑኑ መጠቀማችሁን አቁሙ በማለት አስጠንቅቋል፡፡
ባለፈው ወር በምርቱ ላይ የባትሪዎች መቃጠልና መፈንዳት አደጋ መከሰቱን በተመለከተ በርካታ ደንበኞች አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተከትሎ ኩባንያው በአለም ዙሪያ የሸጣቸውን 2.5 ሚሊዮን የጋላክሲ ኖት 7 ስማርት ፎኖች መልሶ መረከቡን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ምርቱን ማቆሙን ገልጧል፡፡ ጋላክሲ ኖት 7 የገዙ ደምበኞች የከፈሉት ገንዘብ እንደሚመለስላቸው አልያም በምትኩ ሌላ የፈለጉት የጋላክሲ ስማርት ፎን ሊቀየርላቸው እንደሚችል ኩባንያው ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ማምረት ማቆሙን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ የኩባንያው የአክስዮን ድርሻ 8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና በዚህም 20 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱ የተነገረ ሲሆን፣ ኩባንያው በጋላክሲ ኖት 7 ቀውስ 17 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ሊያጣ ይችላል መባሉንም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ኩባንያው በአመቱ አራተኛ ሩብ አመት 500 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ትርፉ በ85 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልና በመጪው 2017 ከሞባይል ገበያ አገኘዋለሁ ብሎ ያቀደው ትርፍም በ22 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያዎች ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጋላክሲ ኖት 7 ስማርት ፎኖች ላይ የታየው ችግር ኩባንያው በአለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ያለውን ተቀባይነት ክፉኛ እንደሚጎዳውና የደንበኞቹን አመኔታ እንደሚያሳጣው የዘርፉ ተንታኞች መናገራቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፣ የደቡብ ኮርያው የፋይናንስ ሚኒስትርም ኩባንያው ምርቱን ማቆሙ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር መናገራቸውን አስታውቋል፡፡ የአለማችንን የስማርት ፎን ገበያ 98.7 በመቶ ድርሻ የያዙት ሳምሰንግ እና አፕል ኩባንያዎች እንደሆኑ የዘገበው ዘ ስትሪት ድረገጽ በበኩሉ፣ የሳምሰንግ ወቅታዊ ቀውስ ለተፎካካሪው አፕል መልካም ዕድል እንደሚሆን መነገሩን ጠቁሟል፡፡

Read 1445 times