Sunday, 16 October 2016 00:00

“ትራምፕ በምርጫው ካሸነፉ አለማችንን አደጋ ላይ ይጥሏታል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር

      የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ሪፐብሊካንን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት በመወዳደር ላይ የሚገኙት አነጋጋሪው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ አሸንፈው ከተመረጡ አለማችን የከፋ አደጋ ላይ ትወድቃለች ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አስፈሪና አሸባሪ አመለካከቶችን የሚያራምዱት ትራምፕ፤ ይህን አቋማቸውን የማይቀይሩና በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ለአለማችን ትልቅ ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው ያሉት ዛይድ፣ በተለይም ትራምፕ ግርፋትን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ማለታቸውንና በተጋላጭ ማህበረሰቦች ላይ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ክፉኛ ተችተውታል፡፡
በየትኛውም አገር በሚካሄድ ማንኛውም አይነት የፖለቲካ ቅስቀሳ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት ዛይድ፣ ግርፋትን በሚያስፋፋና ተጋላጭ ማህበረሰቦችን የሰብአዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በሚያደርግ መልኩ የሚቋጭ ምርጫ ሲያጋጥም ግን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ብለዋል፤ባለፈው ረቡዕ ጄኔቫ በሚገኘው የተመድ ዋና ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
ዛይድ በቅርቡ በሄግ ባደረጉት ንግግር ዘረኝነት የተጠናወታቸው አደገኛ ሰው ናቸው ሲሉ የትራምፕንና የሚከተሉትን ፖሊሲ በይፋ ተችተው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩስያ አምባሳደር በበኩላቸው፤ አንድ የተመድ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ የውጭ አገራትን መሪዎችና መንግስታትን መተቸት አይጠበቅበትም ሲሉ የኮሚሽነር ዛይድን ንግግር መቃወማቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Read 3943 times