Sunday, 16 October 2016 00:00

የግል ማተሚያ ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ ጋዜጣ አናትምም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

መንግስት ድርጊቱ ከአዋጁ መንፈስ ጋር አይገናኝም ብሏል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ የግል ማተሚያ ቤቶች፤ ጋዜጣና መፅሄት አናትምም በማለታቸው ህትመታቸው መስተጓጎሉን የ “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ እና “የሀበሻ ወግ” መፅሄት አሳታሚዎች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጠቃላይ አቃቤ ህግ ማብራሪያ በሰጠበት ወቅት ሃይማኖት ከሃይማኖት፣ ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩና አመፅና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ፅሁፎችን ማተም፣ ማሳተምና ማሰራጨት ሊከለከል ይችላል መባሉን መነሻ በማድረግ የግል ማተሚያ ቤቶች በተለይ ፖለቲካ ነክ ፅሁፎች ያሉባቸውን ጋዜጦች አናትምም ማለታቸውን አሳታሚዎቹ ተናግረዋል፡፡
ዘወትር ቅዳሜ ታትሞ የሚወጣው ሳምንታዊው “የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ባለቤት አቶ ጌታቸው ወርቁ፤ ቀድሞ ጋዜጣው ይታተምበት የነበረውን ማተሚያ ቤት ጨምሮ ከ3 በላይ ማተሚያ ቤቶች አዋጁ እንዳስፈራቸው በመግለፅ፣ ለማተም ፍቃደኛ እንዳልሆኑላቸው አስረድቷል፡፡
አዋጁ ገና ዝርዝሩ ወጥቶ እንዳልፀደቀና ጋዜጣቸው በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ የሚሰራ ሚዲያ መሆኑን በመግለፅ ማተሚያ ቤቶቹን ለማግባባት ሞክረው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ማተሚያ ቤቶቹ ግን ፍቃደኛ ሊሆኑ እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ ማተሚያ ቤቶቹ ጋዜጣውን አናትምም ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወዳሏቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤትና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መ/ቤት በማምራት ስለተፈጠረው ችግር ለሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ማስረዳታቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ የስራ ኃላፊዎቹ የማተሚያ ቤቶቹ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን የገለፁ ቢሆንም መንግስት በአሳታሚዎችና በማተሚያ ቤቶች መካከል ባለ የንግድ የስራ ግንኙነት ውስጥ መግባት እንደማይችል እንደገለፁላቸው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ቀደም ሲል “ቆንጆ” የተሰኘ ሳምንታዊ መፅሄት ያሳትም የነበረው ቴዎድሮስ ካሳ፤ ከ2 ዓመት በፊት በተለያዩ መፅሄቶች ላይ መንግስት ክስ መመስረቱን ተከትሎ፤ ድርጅቱን በመዝጋት ወደ ኬንያ ከተሰደደ በኋላ በናይሮቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማቶች ጋር በመነጋገር ‹‹ወደ ሀገር ውስጥ ገብታችሁ ያለ ምንም ችግር መስራት ትችላላችሁ›› የሚል ቃል እንደተገባላቸውና ወደ ሀገር ቤት በመመለስ፣ “የሀበሻ ወግ” የተሰኘ መፅሄት የመጀመሪያ ህትመት ለማሳተም ከ10 በላይ ማተሚያ ቤቶችን ቢያነጋግሩም ሁሉም ማተሚያ ቤቶች አዋጁን ምክንያት በማድረግ ሊያትሙላቸው አለመፍቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ማተሚያ ቤቶች “የፖለቲካ ይዘት ያላቸውን ፅሁፎች ከመፅሄቱ እንድናወጣ ጠይቀውን ነበር” ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ “እኛ ግን ይሄ ሳንሱር በመሆኑ አልተቀበልነውም” ብለዋል፡፡
መፅሄቱ ዘወትር ቅዳሜ ታትሞ እንዲወጣ በማሰብ፣ ከ3 ወራት በላይ የቆየ ዝግጅት አድርገው ወደ ስራው ገብተው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታው አምባው፤ አዋጁ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው አዋጅ መሆኑን አስረድተው፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ የሰጠበት የአዋጅ ማብራሪያ ላይ እንጂ የተተገበሩ ገደቦች ላይ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
‹‹በአዋጁ ላይ ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭና መጠራጠርን፣ መቃቃርን፣ ጥላቻን የሚፈጥርና የሚዘራ ነገር ማሳተም፣ ማተም ይከለክላል ነው የተባለው እንጂ የህትመት ድርጅቶች ይቆማሉ የሚል ምልከታ የለውም›› ብለዋል፡፡
“ማተሚያ ቤቶቹ በራሳቸው ጊዜ የፈጠሩት ችግር እንጂ ከአዋጁ መንፈስ ጋር የማይገናኝ ነው” ያሉት አቶ ፋንታው፤ ህብረተሰቡ መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው ጠቅሰው አናትምም በማለታቸው ህብረተሰቡን መረጃ የማግኘት መብቱን እየነፈጉት ነው፤ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትንም እየተጋፉት ነው” ብለዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን፤ አዋጁን ያልተገነዘበ ህብረተሰብ እንዲገነዘብ በማድረግ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሚዲያው ይሄን ተግባሩን እንዲያከናውን አለመፍቀድ አግባብ አይደለም ብለዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡

Read 8760 times