Sunday, 23 October 2016 00:00

ከማበዴ በፊት፣ ያበድኩ ሰሞን እና ካበድኩ በኋላ

Written by  (ያዕቆብ ብርሃኑ) (singorbrid@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

 “በፍልስፍና ውስጥ ጥያቄዎች አያልቁም፤ መልሶችም አይነጥፉም”
                                
               አሁን በቀደም ዕለት የማይነጋ በሚመስለው ረጅም ሌሊት፣ 8 ሰዓት ላይ፣ ፀጥ ባለው የቦሌ ጎዳና፣ ጥቂት በእግሬ ለመንሸራሸር ወጥቼ ነበር። በቀኑ ክፍለ ጊዜ በሙሉ ኃይሏ የምታንባርቀው አዲስ አበባ፤ በአንፃራዊነት በዚያ ውድቅት ሌሊት ፀጥታ መላበሷን አየሁ፡፡ የሌሊት የእግር ጉዞ በዓለም ላይ ካሉት አስደሳች ነገሮች ሁሉ የበለጠው መሆኑን እንዴት ላስረዳችሁ ይቻለኛል? በለጋዋ ጨረቃ የልጃገረድ የሚመስል ተሽኮርማሚ ጨዋታ እየመሰጥኩ ጥቂት እንደተጓዝኩ፣ ድንገት በጎዳናው ላይ ትኩረት የሚሰርቅ ትእይንት ተመለከትኩ፡፡ ከመጋቢ መንገድ ወጥቶ ዋናውን አስፓልት የተከተለ፣ አንድ ብዙ ዓይነት ኮተቶች የተሸከመ እብድ ጮክ ብሎ እያወራ ከፊቴ ቀደመኝ፡፡ የሚለውን ለመስማት ብጣጣርም አልተሳካልኝም፡፡ በእኔ እምነት የዚህ ከንቱ ዓለም ምስጢር በከፊል የተገለፀላቸው ዕብዶች ናቸው፡፡ የእስቲቭ ጆብስን የረፈደበት ልቅሶ አልሰማችሁም? “ይህች ዓለም ሙሉ በሙሉ እንኳን ለዕብዶች ፈጠራት” ለሚባለው አምላክም የገባችው አይመስለኝም፡፡ የሆነ ሆኖ እጆቹን እያወናጨፈ ጥቂት እንደተጓዘ፣ ከተሸከማቸው እንቶ ፈንቶዎች መካከል የተጣጠፈች አንዲት ወረቀት እንደዘበት ወደ መሬ ወደቀች፡፡ ስደርስበት በግዴለሽነት አንስቼ እጥፋቷን ገልጬ አነበብኳት … ፈፅሞ ያልጠበኩትን አስገራሚ ፍልስፍናዊ ወጎችን አጭቃ አገኘኋት፡፡ እነሆ አንብቧት፡፡
*    *   *
ከማበዴ በፊት ያው እንደ እናንተ እብድ ነበርኩኝ፡፡ እኔም እናንተም እኮ እብዶች ነን፡፡ ልዩነቱ እኔ በማወቅ፣ እናንተ ባለማወቅ መሆኑ ብቻ ነው። እንዳልኳችሁ ከማበዱ በፊት እንደ እናንተ … እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፤ መንጋ! … ሂድ ሲሉኝ የምሄድ፣ ቁም ሲሉኝ የምቆም፡፡ የዘለዓለምን ድሪቶ የምጥፍ አንድ ደቃቅ ፍጡር … የልማድ እስረኛ። ሰው ወደዚህ ምድር በተፈጥሮ ይሁንታ ሲመጣ ሌጣውን ነው፡፡ እናንተ ግን …
ከእናንተ የቀደሙት አባቶቻችሁ ያወረሷችሁን የዘለዓለም ደበሎ፣ ድሪታችሁን ያለ ውዴታው ታሸክሙታላችሁ፡፡ ከዚያ ወዲያ ሰው እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እናንተ ይሆናል፡፡ እንደ እናንተ ሙስሊም ወይም እንደ እናንተ ክርስቲያን … ከምንም ውጪ እንዲሆን አትፈቅዱለትማ፡፡ እንደ እናንተ ኢትዮጵያዊ ወይም እንደ እናንተ አሜሪካዊ፣ እንደ እናንተ ሀብታም ወይም እንደ እናንተ መናጢ ድሃ … ኤዲያ ሰው ከዚህ ውጪ የሕይወት ቅኝት የለውም ማለት ነው? እንዳልኳችሁ ነው፡፡ ከማበዴ በፊት እኔ እንደ እናንተ … እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፡፡ በሚያዳልጠው ህዋ ላይ ሞትን ዘወትር የምሸሽ ፈሪ ፍጥረት፡፡ ለእናንተ ጣዖታት ሱባኤ የምይዝ፣ ለእናንተ አማልክት መስዋዕት የማቀርብ ድንጉጥ ሰው፡፡ እንደ እናንተ ህሊናን የሚያክል ትልቅ እግዚአብሔርን እያታለልኩ፣ ከደመና በላይ በምናብ ለሰቀልኩት እግዜር የለበጣዬን የማጎበድድ፡፡ እንደ ሴቶቻችሁ በቀለም ከንፈሩን ደም የላሰች ውሻ አስመስዬ፣ እምብርቴን አስጥቼ፣ የሞራል ዝቅጠቴን እንደ ስልጣኔ የምቆጥር ግልብ ነበርኩ፡፡ ነገርኳችሁ በቃ … ከማበዴ በፊት እንደ እናንተ እንደ እያንዳንዳችሁ ነበርኩ፡፡ በተዘፈነበት የምጨፍር፣ በተለቀሰበት የማለቅስ፣ ጮክ ብዬ የምስቅ ተራ ሰው … ለነገሩ ከእናንተ የወጣ ሰው፤ እንደ እናንተ ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ዕጣ አለው? አትፈቅዱለትማ … ዕብደቱ ሲጀማምረኝስ ምን ሆንኩ? ለእናንተ እንዲገባችሁ እንጂ ዕብደት ማለቴ ነገርዬው ያው ፍልስፍና ነው። መጀመሪያ ቤተሰቦቼን ተውኩ፡፡ በመቀጠል የእናንተን የእያንዳንዳችሁን አስተሳሰብ ናቅኩ። እግዜራችሁም አላስፈለገኝም፡፡ በመጨረሻስ? በመጨረሻማ የማይቀረው ዕጣዬን … ራሴ መካድ ሆነ፡፡ በፍልስፍና ህይወት ትልቁ መገለጥ እኮ ይሄ ነው፡፡ እንዳልኳችሁ ከማበዴ በፊት እንደ እናንተ…. እንደ እያንዳንዳችሁ ለማዳ እንስሳ ሆኜ፣ ከቤት ወደ ስራ፤ ከስራ ወደ ቤት መመላለስ የማይሰለቸኝ፣ ቤተሰቤን እያልኩ መንጋዬን የምከተል ነበርኩ፡፡ አሁን ይሄ ታሪክ ተቀየረ፡፡ የአበድኩ ሰሞን እግዚአብሄርን መንገድ ላይ አግኝቼው ነበር፡፡ ላናግረው ስል ተሰወረብኝ፡፡ እብዶችን ይፈራል ልበል? ነው ወይስ በራሱ መንገድ አብዷል? መቼም ያላበደ አምላክ፤ ይህችን እብድ አለም ሊፈጥር አይችልም። ስቀልዳችሁ ነው ባካችሁ… የእናንተ እግዜር እኮ ልክ በልጅነታችን እናቶቻችን እኛን ዝም ለማሰኘት እንደሚጠቀሙባቸው ማስፈራሪያዎች ፈጠራ ነው። ያበድኩ ሰሞን መጀመሪያ የተገለፀልኝ እውነት ግን የእናንተ የእያንዳንዳችሁ ህይወት ጥቂትም ለዛ ያገኘው ስለ አምላክ ባላችሁ ቀቢጸ ተስፋ ላይ መሆኑ ነው፡፡ እውነትስ ይህ ምስኪን ጉስቁል ህዝብ…. ‹‹እግዚአብሔር የለም›› ቢሉት እንደተጋለጠ ሰይጣን ሆኖ፣ መጠለያ ሊያጣ አይደለምን? ለነገሩ እኔም እናንተም እንሸሻለን፡፡ ልዩነቱ የመሸሻ መጠለያችን ብቻ ነው፡፡ እኔ ወደ ምንምነት አዘቅት፣ እናንተ ደግሞ ወደ እምነት ቀቢፀ ተስፋ…. እኔ በእውቀት፣ እናንተ በደመነፍስ!... ካበድኩ በኋላ በዓለም መሀል እያለሁ ከአለም ተነጥያለሁ፡፡ ግን የቱንም ያህል ብሸሽ ላመልጣችሁ አልቻልኩም፡፡ እንደ ትንኝ በየሄድኩበት ትከተሉኛላችሁ፡፡ ለነገሩ ታስፈልጉኛላችሁ፡፡ ሀኪሞች መድሀኒቶቻቸውን በአይጦች እንደሚሞክሩት… እንደዚያ እኔም በእናንተ ጎስቋላ ሕይወት መመራመሩን ወድጀዋለሁ። አሁን እኔና የእናንተ አምላክ የለንም፡፡ እናንተ፤ የእኔ ፍልስፍና እና አምልኮታችሁ ግን አላችሁ። በነገራችን ላይ በዓለም ላይ እንደ ሁሉም እንድሆን…. ቢፈቀድልኝ የእናንተን እግዜር ግን መሆን አልፈልግም፡፡ ውዳሴና ምስጋናን አምርሬ እጠላቸዋለሁ፡፡ አስቡት እስቲ…. ወፈ ሰማይ መላእክት እግሬ ስር ጠብ እርግፍ፣ ጧ ፍርጥ እያሉ ሲሰግዱልኝ ማየት እንዴት ያስጠላል። ለነገሩ የእናንተ እግዜርና የምድር ነገስታት አንድ ናቸው፡፡
የሚገዙላቸውን ይወዳሉ፡፡ የሚያምጹትን በሰይፍ ይቀጣሉ፡፡ አለቀ፡፡ ትናንት ጣኦታቱ ሀውልቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ ጣኦታቱ ከደመና በላይ ናቸው፡፡ እኔ ለእናንተ አብጃለሁ፡፡ እናንተ ለእኔ ሙልጭ ያላችሁ እብዶች ናችሁ፡፡ በዚህ መሀል አውነት የለም፡፡ ለነገሩ ለእኔ እውነት አለ ከምል ሰይጣን አለ ብል ይቀለኛል፡፡  ይሄ የምርምሬ ግኝት ነው፡፡ ፈላስፋ ወታደር ቢሆን ጥይቱ ጥያቄው ነው። በፍልስፍና ውስጥ ጥያቄዎች አያልቁም መልሶችም አይነጥፉም፡፡
ፍልስፍና የአንድ ብቻ ዕብደት፣ የአንድ ብቻ ውበት፣ የአንድ ብቻ ዓለም… ሳይሆን ይቀራል? ሆኖም ሁሉም መረዳት፣ አስተውሎት ሁሉ የጥርጣሬ የምናልባት ብቻ እኮ ነው፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ አብጃለሁ፡፡ በምንም ለምንም የማልጓጓ፣ በምንም ለምንም የማልፈራ፣ በምንም ለምንም የማልደነግጥ…  ሆኛለሁ፡፡ እንደ እናንተ የጊዜ ቅጣትና በረከት ለእኔም ደርሶኛል። ውርጩ ያወረዛኛል፡፡ ዝናቡ ያበሰብሰኛል፡፡ ፀሐዩ ያቃጥለኛል። ኢትዮጵያዊነት ቢጠበስ አይሸተኝም። ለእኔ ሃገራትን የፈጠራቸው ፖለቲካ ነው፡፡ አሁን ረሃብን ረስቸዋለሁ፡፡ ማፍቀር ተዘንግቶኛል፤ መጥላትም ተረስቶኛል፡፡… እናስ አለምን አላሸነፍኳትም ትላላችሁ? በምን ታታልለኛለች?
እንደ ዘበት በተጣለችው ወረቀት ላይ የተጻፈው ነገር ያነበባችሁትን ይመስላል፡፡ ቆይ ግን ከመጋቢው መንገድ ወጥቶ ዋናውን አስፓልት ሲቀላቀል ያየሁት የመሠለኝ ዕብድ የእኔ ጥላ ሳይሆን ይቀራል? ስለዚህ ወድቆ የተገኘ ወረቀት አለመኖሩንም ደርሰንበታል፡፡ እናም የፃፍነው እኛ ነን፡፡ ያበደውስ? እኛ?

Read 1773 times