Sunday, 23 October 2016 00:00

አይጢቱ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ?

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የቻይና ንጉስ፤ አማካሪ የሚሆነው ሁነኛ ሰው ይፈልግና አንድ አዋቂ ሊቅ አለና ወደ እሱ እንዲሄዱ፣ እንዲያሳምኑትና እንዲያመጡት ብልህ ባለሟሎችን ይልካቸዋል፡፡
ያ አዋቂ ሰው በአንድ ኃይቅ ዳርቻ ነው የሚኖረው፡፡ የንጉሡ ባለሟሎች ወደ አዋቂው ሰፈር ሄዱ፡፡ አዋቂውን ሰው አገኙትና፤ “እንደምነህ ወዳጃችን? ከንጉሡ መልዕክት ይዘን የመጣን ባለሟሎች ነን” አሉት፡፡
ሊቁ አዋቂ፤
“ምን ጉዳይ ገጥሟችሁ ወደኔ ዘንድ መጣችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ባለሟሎቹም፤
“ንጉሥ አስተዋይ፣ ታጋሽ፣ አርቆ አሳቢ፣ ዕውቀት የማይጠግብ ፈላስፋ ሰው ይፈልጋሉ፡፡ የመረጡትም አንተን ነው፡፡ ለዚህ ነው ወደ አንተ ዘንድ የመጣን” አሉት፡፡  
ሊቁ አዋቂም፤
“መምጣታችሁስ ደህና፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡”
ባለሟሎቹ፤
“መልካም ጥያቄህን ሰንዝር” አሉት
ሊቁ፤ “ጥያቄዬ፣ ንጉሡ ትክክለኛ አማካሪያቸው፣ እኔ መሆኑን በምን አወቁ? ዕውቀታቸው ትክክል ከሆነስ ለምን ለአማካሪነት አሰቡኝ?”
ባለሟሎቹ፤
“ነገሩ አልገባህም ማለት ነው፡፡ ንጉሡ የሚያምኑት ደመ - ነብሳቸውን ነው፡፡ ቀልባቸው የወደደውን! ያ ደግሞ አንተ ነህ፤ አለቀ” አሉት፡፡
ሊቁም፤ “ንጉሡ ቤተ መንግስት ውስጥ አንድ ከወርቅ የተሰራ ኤሊ አለ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“አዎን” አሉት፤ ስለ ኤሊው በማወቁ እየተገረሙ፡፡ ከዚያም አጠገባቸው እጭቃ ላይ የሚሄድ አንድ የውሃ-ኤሊ አሳያቸውና፤
‹‹ይሄን ኤሊ ተመልከቱ፡፡ ይሄ ኤሊ ንጉሡ ዘንድ ካለው የወርቅ ኤሊ ጋር ቦታ ትለዋወጣለህ ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ ምን የሚል ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
ባለሟሎቹም፤
‹‹እምቢ የሚል ይመስለናል›› አሉት፡፡ ሊቁም፤ ‹‹በወርቅ ተለብጦ ጠረጴዛ ላይ ከመቀመጥ እዚሁ ሰፈሩ ውስጥ በሕይወት መኖሩን መረጠ፡፡ እንግዲህ የእኔም መልስ እንደዚያው ነው፡፡ እዚሁ ያለሁበት መሬት ላይ መኖርን እመርጣለሁ፤ በሉና ለንጉሡ ንገሩልኝ›› ብሎ አሰናበታቸው፡፡
*     *     *
ትክክለኛ ቦታቸውን የሚያውቁ ሰዎች ብልሆች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ሰዎችን ለመምረጥና በትክክለኛ ቦታ ለማስቀመጥ የሚችሉ ሰዎችም እጅግ ብልሆች ናቸው፡፡ የራሳቸውን አቅምና ብቃት በአግባቡ መዝነው፡፡ “ይህ ቦታ ለእኔ አይሆንም፡፡ አልመጥነውም›› ለማለት የሚችሉ ሰዎች ራሳቸውንም፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንም፤ ህብረተሰብንም ከስህተት ያድናል፡፡
ዛሬ የህዝብ ጥያቄዎች ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነትና የጉዳዩ ባለቤት መሆን ነው፡፡ በሀገራችን የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ ስናነሳም አንዱ ችግራችን በሥራ መደቡ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ወይ ብቃት ሲያንሳቸው፤ ወይ ቅንነት ሲያንሳቸው ወይ ደግሞ የማይችሉትን የሚችሉ መስለው ለመታየት፣ ያልሆነ ምስል ፈጥረው ሲገኙና ሥራን ሲበድሉ ነው፡፡ ከቶውንም የመልካም አስተዳደር ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ እኒሁ ሰዎች ስለ መልካም አስተዳደር መጉደል ጮክ ብለው እያወሩ መፍትሄ ሳያገኝ ሥር-የሰደደ በሽታ ሆኖ ቆይቷል። They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ እንደማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ችግራችን ሙስና እና ሙስናን ለመሸፈን የሚደረግ ኃይለኛ የአስተዳደራዊና የተላላኪዎች መረብ መዘርጋት ነው፡፡ እከክልኝ ልከክልህ፣ ሸፍነኝ ልሸፍንህ ነው፡፡ በሀገራችን ስለ ሙስና ሲነገር እጅግ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ ከመባባሱ በስተቀር ሁነኛ ለውጥ አልመጣም። ሙሰኞቹም ከዕለት ዕለት እየናጠጡ፣ የ‹‹አይደረስብንም” መተማመን እያበጁ፣ “በማን ይነካናል” ኩራት እየተደገጉ ይኖራሉ፡፡ ጉዳዮችን አጥርቶ ፍትሀዊ መፍትሄ የሚሰጥ በመጥፋቱ ነገሮች እየተጓተቱ ወደ ጤነኛ ዕድገት ከመሄድ ይልቅ አድሮ ጥሬ ወደ መሆን ያመራሉ፡፡ ኃላፊነት የመውሰድና የተጠያቂነትን መርህ አለመቀበል ወይም ተቀብሎ በሥራ ላይ አለማዋል፣ በስልጣን መባለግን ማስከተሉ መቼም አሌ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል አንዴ ከተጀመረ የሱስ ያህል የማይላቀቁት ጠንቅ ነው፡፡ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው” የሚባለውን ተረት ልብ ይሏል። ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ የመረጃ ማጥፋት ተግባር ነው፡፡ ብልሹ አሰራር ባለበት ቦታ የሰነዶች በቦታቸው አለመገኘት አይንቅም፡፡ ያን ብልሹ አሰራር በጥንቃቄ ፈትሾ፣ የውስጥ ቦርቧሪን ማግኘት ግድ ይሆናል፡፡ የውስጥ ቦርቧሪ እያለ መልካም አስተዳደርን መመኘት ምኞት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ራስ ማየትና ውስጥን መመርመር ትክክለኛውን የጥፋት ቦታ፣ ትክክለኛውን ቀዳዳ ለማግኘትና አፋጣኝና ቁርጠኛ መፍትሄ ወደ መፈለግ እንዲኬድ ያደርጋል፡፡ የምንሰጠው መፍትሄም የ“ከአንገት በላይ” መሆን የለበትም፡፡ በሥልጣን የባለገ መውረድ ካለበት መውረድ አለበት! ወለም ዘለም አያዋጣም፡፡ ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም፣ ይሏልና፡፡ የችግርን ዕውነተኛ ገፅታ ካገኘን፣ የችግሩን ፈጣሪ ክፍሎችን ለይቶ ማውጣት አዳጋች አይሆንም፡፡ ምነው ቢሉ፤ “አይጢቱ ከሌለች ጉድጓዱ ኬት መጣ?” ብሎ መጠየቅ የአባት ነውና!

Read 5863 times