Sunday, 23 October 2016 00:00

የፖለቲካ ቀውሱ፤ ከኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ አንጻር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ከአለፈው ዓመት ህዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል፣ ከዚያም በአማራ ክልል ተስፋፍቶ የቀጠለው ህዝባዊ አመጽና ተቃውሞ፣ለበርካታ ዜጎች ህልፈት፣ የአካል ጉዳት፣ እስርና ስደት መንስኤ የመሆኑን ያህል ቀላል የማይባል የኢንቨስትመንት ውድመትም አስከትሏል፡፡ የአበባ እርሻዎች ወድመዋል፡፡ የትራንስፖርት መኪኖች ተቃጥለዋል፡ ፡ የግለሰብ ቤቶችና ሆቴሎች ወድመዋል፡፡ የመንግስት ተቋማት ጋይተዋል፡፡
በእሬቻ ዓመታዊ በዓል የተከሰተውን አስደንጋጭ እልቂት ተከትሎ ባገረሸው ህዝባዊ ቁጣም፣ በቢሊዮኖች ብር የሚገመቱ ኢንቨስትመንቶች ወድመዋል፡፡ ፋብሪካዎች፣ሎጆች፣ እርሻዎች፣ መኪኖች በእሳት የጋዩ ሲሆን ሁኔታው በኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ ስጋትና ዋስትና ማጣትን
ፈጥሯል፡፡ በአገሪቱ ላይ ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅም ምክንያት ሆኗል፡፡በኢንቨስትመንቶች ላይ የደረሰው ውድመት በቀጣይ የአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ምን ያህልተጽዕኖ ያሳድራል? የውጭ ኢንቨስተሮችን የማሸሽ አቅም ይኖረው ይሆን? በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጉዳትስ? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማሱ
ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያውን ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ አነጋግሯቸዋል፡

• ፋብሪካዎች ሲቃጠሉ፣ ንብረት ሲዘረፍ -----ኢንቨስተሮች ይደነግጣሉ፤ይፈራሉ
• ኬንያ በምርጫ ማግስት ከገባችበት ቀውስ ለማገገም 8 ዓመት ፈጅቶባታል
• ህዝብ ተደራጅቶ የሚሰራበትና ከችግር የሚወጣበት መንገድ ሊበጅለት ይገባል
• የውጭ ባንኮች ገብተው የሚሰሩበትን ሁኔታ እንደገና መመርመር ያስፈልጋል

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በርካታ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወድመዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ በተለይ ወደ ኋላ ላይ የመንግስትና የውጭ ባለሃብቶች ንብረቶችን ወደ ማቃጠልና ማውደም የገቡት ለምንድን ነው?--- ብዙዎችን በተለይ ባለሃብቶችን ያስደነገጠ ክስተት ነው፡፡ እርስዎ ከምን የመነጨ ይመስልዎታል?
በእንዲህ አይነት ተቃውሞ ህዝቡ በተለያዩ ተፅእኖዎች መንግስት እንዲሰማው ጫና ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ትልቁ ችግር በዚህ መሃል አጋጣሚውን ተጠቅመው፣ሀገር ለመበጥበጥና ንብረት ለመዝረፍ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡ ንብረት ዘርፈው ሲጨርሱ መዝረፋቸው እንዳይታወቅ የቀረውን አቃጥለው ይሄዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ በምሬት በመነሳሳት ሊከሰትም ይችላል፡፡ መንግስት እያደግሁ ነው ማለቱን መነሻ በማድረግ፣ “እስቲ ያሳደገውን ነገር እናፍርሰው” በሚል እልህ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን ህዝባዊ ተቃውሞው መሪ ቢኖረው ኖሮ፣ወደዚህ ዓይነት ውድመትና ጥፋት  ሊቀየር አይችልም ነበር፡፡ በህዝብ ጥያቄ ላይ ተንተርሰው ሀገር ለመበጥበጥ የሚፈልጉ ሰዎችም እድሉን አያገኙም ነበር፡፡
በተለይ በቅርቡ በውጭ ኢንቨስተሮች ንብረት ላይ ተነጣጥሮ የተሰነዘረው ጥቃት ብዙ ውድመት ማድረሱ ይታወቃል፡፡ ክስተቱ የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ከመሳብ አንፃር የሚያስከትለው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው?
እንደዚህ ዓይነት ረብሻ ተፈጥሮ፣ በተለይ ኢንቨስትመንቶችን ማውደም፣ ፋብሪካዎችን ማቃጠል፣ መዝረፍ ሲያጋጥም----ምንም ጥርጥር የለውም ኢንቨስተሮች ይደነግጣሉ፤ ይፈራሉ፡፡ ገንዘባቸውን አፍሰው የሰሩት ነገር ሲፈራርስባቸው ለኪሳራም ይዳርጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ሀገሪቱን “ችግር ያለባት ናት” ብለው መሰየማቸው በራሱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ይጎዳዋል፡፡ ከቱሪዝም የምናገኘው ገቢ ይቀንሳል። የውጭ ኢንቨስተሮችም በዚህ አይነት ሁኔታ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ያስፈራቸዋል፡፡
አንዳንድ ከፍተኛ ንብረት የወደመባቸው የውጭ ባለሃብቶች ከዚህ በኋላ ዳግም ኢንቨስት ለማድረግ ዋስትናችን ምንድነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንዴት ነው ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሃብቶች ዋስትናቸውን ማረጋገጥ የሚቻለው? በአጭር ጊዜ የሚሳካ ይመስልዎታል?
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከረ ነው ያለው፡፡ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻ ሳይሆን የሀገር ሽማግሌዎች ከያሉበት ተሰባስበው ህዝቡን የሚመክሩበትና ሰላምና መረጋጋት የሚያመጡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በየቀዬው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ መንግስት በበኩሉ ይሄን ጊዜ ተጠቅሞ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ከቁጥጥር  ውጭ የሆኑበትን ጉዳዮች ማረም አለበት፡፡
የፖለቲካ ቀውስ ረዘም ላለ ጊዜ ሲዘልቅ ኢኮኖሚውን ወደቀድሞው ቦታው ለመመለስ ብዙ ዓመታት እንደሚፈጅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአሁኑ ውድመት በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ባያደርስ እንኳን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ሊያስተጓጉለው ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ በእርስዎ እይታ ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃትና ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
እንግዲህ ከጎረቤታችን ከኬንያ እንደምንማረው፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ በኪባኪና በኢዲንጋ መካከል በተነሳው ውዝግብ፣ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ፣ አገሪቱ ወደነበረችበት ለመመለስ 8 ዓመት ገደማ ነው የፈጀባት፡፡ ኢንቨስተሮችን መልሶ ለማምጣት፣ ኢንቨስትመንትን በድጋሚ ለማነቃቃት ከፍተኛ ትግል ጠይቋታል፡፡ በኢትዮጵያ ምን ያጋጥማል የሚለው በሂደት የሚታይ ቢሆንም፣ መንግስት በአስቸኳይ ነገሩን ማረጋጋት መቻል አለበት፡፡
አንዱ ትልቁ የሀገሪቱ ችግር ከዩኒቨርሲቲና ከሙያ ትምህርት ቤቶች የሚወጡ ወጣቶች ስራ አለማግኘታቸው ነው፤ ስለዚህ መንግስት ይሄን ለማስተካከል መጣር አለበት፡፡ የግል ዘርፉ አሁን ባለው የባንኮች የመዋዕለ ንዋይ አቅም ሊንቀሳቀስ እንደማይችል በመገንዘብ፣ የውጭ ባንኮች የሚገቡበት ሁኔታን እንደገና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱን እናረጋጋለን፤ ለችግሩ መፍትሄ እናበጃለን የምንል ከሆነ፣ እነዚህ ነገሮች በአስቸኳይ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ በብዙ ሀገሮች ወጣቱ ለረብሻ የሚዳረገው ስራ አጥነት ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሄ ላይ አተኩሮ በመስራት፣  በአስቸኳይ ለውጥ ማምጣት ይጠይቃል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በመንግስት ሥራ፣ በአስፈፃሚነት ያሉ ግለሰቦች እንዲሁ ዝም ብሎ በፓርቲ ታማኝነት የተመደቡ መሆን የለባቸውም፡፡ በእውቀትና በልምድ የጎለበቱ፣ ለስነ ስርአትና ባህል ተገዢ የሆኑ፣ ህዝብ የሚያከብራቸውና የሚቀበላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዋናዎቹ የስራ ፈጠራዎች ያሉት በዞንና በወረዳ ደረጃ እንደመሆናቸው፣ ስራዎች መሰራት ያለባቸው በነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡ የሙስና ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የቀን ዘራፊዎችን አስወግዶ ብዙ የተማሩ ወጣቶችን ወደነዚህ የአስተዳደር እርከኖች ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በፌደራል ደረጃ ብቻ ሰዎች መቀያየራቸው ለውጥ አያመጣም፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር፣ ሀገራችን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ነው የምትገኘው፤ ነገር ግን የህዝብ ኑሮ ሊቀየር አልቻለም፡፡ ፈጣን እድገት ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን ይዞ ይመጣል፡፡ አገሪቱ ብዙ የተማረ ሰው ባፈረች ቁጥር፣ ህገ መንግስቱን አንብቦ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መብት ጠያቂ ይፈጠራል፡፡ ወጣቶች እነዚህን ህገ መንግስታዊ መብቶች መጠየቃቸውን መንግስት በበጎ ሊቀበለው ይገባል እንጂ እንደ ረብሻ ማየት የለበትም፡፡
በሁለቱ ክልሎች ተቃውሞና አመጽ ከተቀሰቀሰ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ከመውደማቸውም በላይ አብዛኞቹ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተቃውሞና በአድማ ሲስተጓጎሉ ቆይተዋል፡፡ የፖለቲካ ቀውሱ በኢኮኖሚው ላይ ያስከተለውን ጉዳት መገመት ይቻላል? የወደፊት ተጽዕኖስ ይኖረዋል?
ተቃጠሉ የሚባሉት ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎች፣ ኢንዱስትሪዎች ---- መጠናቸው ታውቆ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸው አስተዋፅኦ ተለይቶ፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ምን ያህል እንደሚጎዱት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የአገልግሎት ዘርፉ እያደገ ከመሆኑ አንጻር በፖለቲካ ቀውሱ ምን ያህል ተጎዳ የሚለው መጠናት አለበት፡፡ የቱሪስቶች መቅረት ሆቴሎችን ይጎዳል፣ የትራንስፖርት ድርጅቶችን ይጎዳል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ አለማቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ያደርጋል፡፡ ሀገሪቱ ችግር አለባት ብለው ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት ሊታቀቡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የጀርመኗ ቻንስለር አንገላ መርከል መምጣቷ ራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሂደት በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ጉዳቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ስራዎች ሊስተጓጎሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መንግስት በፍጥነት ህዝቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥቶ አገሪቱን ማረጋጋት አለበት፡፡
አንዱ የህዝቡ ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሰፊ የስራ ዕድል በተለይ ለወጣቱ የሚፈጠርበት ሁኔታ ይኖራል ብለው ያስባሉ?
አንድ ሥር የሰደደ አስተሳሰብ አለ፡፡ ሁሌም መንግስት ራሱን አቅራቢ፣ አልሚ፣ ሁሉን ነገር ሰጪ አድርጎ ነው የሚቆጥረው፡፡ በሌላ በኩል ህዝቡን ተቀባይና ተለጋሽ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ በታሪካችን ግን ይህቺን ሀገር ለ3ሺ ዓመታት በትጋት እየሰራ ያቆያት፣ ህዝቡ እንጂ መንግስታት አይደሉም። ህዝቡ በራሱ የሚሰራበትና ራሱን የሚያሻሽልበት ሁኔታ ነው መፈጠር ያለበት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ስልጣን ላይ የሚወጣ ቡድን፣ ሀገሪቱን ልግዛ እንጂ ይሄን ሁኔታ ላሻሽል አይልም፡፡ ሆኖም መንግስት ሁሉን ነገር አድራጊ ፈጣሪ ሊሆን አይገባም፤ ለህዝብ ቦታ መሰጠት አለበት፡፡ የመንግስት ድርሻ ሊሆን የሚገባው ፖሊሲ መቅረፅ፣ የሀገርን ደህንነት መጠበቅ፣ ትልልቅ ግድቦችን (በግሉ ዘርፍ ሊሰሩ የማይችሉ)፣ የባቡር ፕሮጀክቶችን ----- ከማከናወን ማለፍ የለበትም፡፡
ህዝቡ የምንለው የግል ሴክተሩን ነው፡፡ አርሶ አደሩ አምርቶ ምርቱን ገበያ እስካደረሰ ድረስ አንድ የግል ሴክተር ነው፡፡ ይሄ ግንዛቤ ሀገራችን ውስጥ እስከ ዛሬ የለም፡፡ መንግስታት ሁልጊዜ፤ ”የምንወድህና የምትወደን ህዝባችን” ነው የሚሉት። አሁን ከዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወጥተን፣ ህዝብ ተደራጅቶ ስራ የሚሰራበትና ከችግር የሚወጣበት መንገድ ሊበጅለት ይገባል፡፡
መንግስት ከውጭ የሚመጣውን እርዳታም ሆነ ሌሎች ሀብቶችን እያሰባሰበ፣ በሰው ሀብት ልማት ላይ ማዋል አለበት፡፡ ወጣቶች በኢንጂነሪንግ ተመርቀው ስራ የማያገኙ ከሆነ መማራቸው በትምህርት ደረጃ ነው የሚጠቅማቸው እንጂ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ አያበረክቱም፡፡ ስለዚህ ይሄ አካሄድ መቀየር አለበት።






Read 2841 times