Sunday, 23 October 2016 00:00

የቦክስ ዓለም ወግ

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(0 votes)

ማን ነበር ያ ቦክሰኛ፣ “የቦክስ ግጥሚያን የምወደው ሪንጉ ውስጥ ማን እንደሚመታኝ … እና ለማን አፀፋውን እንደምመልስ ስለማውቅ ነው፡፡ ከቦክስ ሪንጉ ውጭ የሚመታኝ ፖለቲከኛ ወይንም ፅንሰ ሐሳብ … ወይንም … የኢኮኖሚ ስርዓት የቱ እንደሆነ ስለማላውቅ ራሴን መከላከል አልችልም” ብሎ የተናገረው? … ስሙን እረስቼዋለሁ ግን አባባሉን ተሸክሜው እየዞርኩኝ ነው፡፡
አሁን በቦክስ ሪንጉ ውስጥም ህጉ ተለውጧል መሰለኝ፡፡ ማን እንደሚመታህ ግልፅ የነበረበት ጊዜ አልፏል፡፡ ድሮ የቀለም (Race) የቡጢ ግጥሚያ ነበር በሪንጉ ውስጥ የሚታየው፡፡ ነጭ ኮርነር ያለው ሻምፒዮን ሆኖ ቀበቶውን ከዘመን ዘመን እንደታጠቀ ይዘልቅ ነበር፡፡ ጥቁሩ ጥግ ያሉት ደግሞ በነጭ ቡጢ እንደተዘረሩ … ሁሌ በመጀመሪያው ዙር ወድቀው እንደተባረሩ ነበር፡፡ በኋላ በድንገት የጨዋታው ህግ ተለወጠ፡፡ በአጥቂና ተጠቂ መሀል የነበረው የቀለም ልዩነት በሚስጥር ተወገደ፡፡ የቦክስ ግጥሚያ ትርዒቱ በሁለት ቀለም የማይለይ ሆኖ በምስጢር መጥረጊያ ምንጣፉ ስር ተጠርጎ ተጨመረ፡፡ የዚህን ጠርጎ የማስወገድ ሂደት “አፈርማቲቭ አክሽን” ብለው ጠራጊዎቹ ጠሩት፡፡ ተጠረገ እንጂ አልተሰወረም፡፡
በተጠረገው ፈንታ ሌላ ግጥሚያ በቦክስ አይነት ሪንግ ውስጥ መጣ፡፡ በቀለም ፋንታ … “ግራ” እና “ቀኝ” የሚል የርዕዮተ ዓለም ተወካዮች ሰውነታቸውን በኪሎ አመጣጥነው መፋለም ጀመሩ፡፡ …. ስማቸውን “ቀኝ” እና “ግራ” በሚል መወከያ ተኩ እንጂ … ተፋላሚዎቹ የቀኝም ሆነ የግራ አዝማሚያ በቡጢ አሰነዛዘራቸው ላይ አይታይም። ሁለቱም ተፋላሚዎች ለመቀጣቀጥ ቀኝና ግራ እጃቸውን እየለዋወጡ ይጠቀማሉ፡፡ … ተፋልመው ሲጨርሱም በዳኛው አማካኝነት ግራ ወይንም ቀኝ እጃቸውን ወደ ላይ ያነሳሉ፡፡
ለነገሩ በፊትም ቢሆን ነጭና ጥቁርነት የቡጢን ምክኒያት አይገልፅም፡፡ ለመጋጨት በመሰረቱ ምክኒያት አያሻም፡፡ የመጋጨታቸው ምክኒያት የኪሎ መመጣጠናቸው ካልሆነ በስተቀር ሌላው ምክኒያት በሙሉ ውሃ የሚቋጥር ወይንም ወደ ኋላ መለስ ብለው ቢያጤኑት ተጋጣሚዎቹን ራሱ የሚያሳምን አይደለም፡፡ ግን ተጋጣሚዎቹ የተመልካቾቹ ተወካይ ናቸው፡፡ በአስፈለገ ምክኒያት ለመፋለም ወደ ሪንጉ የገቡ ተፎካካሪዎች ዘወትር ድጋፍ አላቸው፡፡ ቡጢ የሚሰናዘሩትን ለመደገፍ ወደ ግራ እና ቀኝ ለሁለት ተከፍሎ ተመልካች ይደግፋል፡፡ በፍልሚያው ወቅት በሁለት ጎራ የተከፈለው ደጋፊ፣ ፍልሚያው ሲጠናቀቅና አንዱ ተጋጣሚ በአሸናፊነት ሲወጣ … ግማሽ ደስታና ግማሽ ሀዘን ሆኖ ይለያያል። የውክልና ግጥሚያው በምን ምክኒያት እንደመጣ የሚጠይቅ የለም፡፡ “ግጥሚያ አያስፈልግም” የሚል ሦስተኛ ወገን አይገኝም፡፡ የቦክስ ግጥሚያ ባህሉ እንጂ የሚቀጥለው … ተጋጣሚማ ከዘመን ዘመን ይለዋወጣል፡፡
ቅድም የጠቀስኩት ቦክሰኛ፣ በሪንጉ ውስጥ ከአንድ ባላንጣው ጋር ሲገጥም ብቻ የፍልሚያው ትርጉም እንደሚገለፅለት ተናግሯል፡፡ ከሪንጉ ውጭ ባለው አለም ያለውን ግራ መጋባት መልስ የሚፈልገው በሪንጉ ውስጥ ነው፡፡ ሪንጉ ውስጥ ይዞ የሚመጣው የውጭኛውን አለም እልሁን ነው። ግን ይህ ሁኔታ ለተመልካቹም ተመሳሳይ ነው። ተመልካቹም በየስራ መደቡ ... በየግል ህይወቱ ውስጥ ከአለቃው ጋር ወይ ከሚስቱ ጋር ወይ ከአከራዩ ጋር የሚጋጭበት መድረክ አለ፡፡ ይኼንን መድረኩን ነው በቦክሰኛው ወክሎ ለመመልከት ወደ ግጥሚያው አዳራሽ የሚመጣው፡፡ የወከለው ቦክሰኛ ቢያሸንፍለት … በቤቱ ወይንም በመስሪያ ቤቱ ያለበት የግሉ ፍልሚያ እልባት እንደማያገኝ በውስጡ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እያወቀም ግን ለድጋፍ ወደ ቦክስ ግጥሚያው መድረክ መምጣቱን አያቆምም። ለህይወቱ ወይንም ለተጨባጭ ህልውናው ተጨባጭ መፍትሄ የሚያገኘው በቦክሱ ትርዒት ላይ እንዳልሆነ ቢያውቅም .. ከማይታዩ የህልውናው ኃይሎች የሚደርስበትን ጫና በሚታየው የቦክስ መድረክ ላይ ወክሎ ተስፋን ከመፈለግ ራሱን ማቀብ አይችልም፡፡
እፎይታ በተጨባጭ የማይገኝ ከሆነ በህልም ላይ ከመፈለግ የሚያግደው ሀይል ግን አይኖርም። ስለዚህ ይፈልጋል፡፡ የራሱን ህልም በቡጢኛው አካልና ኪሎ ወይንም ዝና ላይ አሳርፎ ቲፎዞ ይሆናል፡፡ የወከለው አካል እንዲያሸንፍ እየተመኘ፣ ግጥሚያውን ለመታዘብ ቲኬት ቆርጦ ይገባል፡፡ ከገንዘብ ትርፍና ኪሳራ ባሻገር ሌላ ትርፍ የለውም የቦክስ ግጥሚያ። መንፈሳዊ ክብደት የለውም፡፡ የከባድ ሚዛን የቦክስ ግጥሚያ ከባድ መንፈሳዊ ሚዛን ያለው አይደለም፡፡
መንፈሳዊነት ያላቸው ፍልሚያዎች በአካል ተወክለው፣ በቦክስ ህግ ታጥረው ሊወሰኑ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የቦክስ ተጋጣሚዎች በመልካም መንፈስና በዕኩይ መንፈስ ተወካይ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የዚህን መንፈሳዊ ተልዕኮ ከባድ ሚዛናቸው ሊሸከመው አይችልም፡፡ ግን መጀመሪያ ያ ቦክሰኛ እንደተናገረው፤ “የቦክሱ ሪንግ ግልፅ ነው” ማን በማን ላይ ምን እንዳደረገ ይታያል። ፍልሚያውም ህግን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ህግን የሚያስከብር ዳኛና ህግ መከበሩን እማኝ የሚሆን ተመልካች ባለበት የሚደረግ ነው፡፡ ተመልካችም የቲፎዞ ስሜታዊነት አሸንፎት ሚዛኑን ሊያስተው ስለሚችል ፖሊስም በአካባቢው ተገኝቶ ተግባሩን ያከናውናል፡፡ የፍልሚያው ምክኒያት ወይንም መንስኤ እንጂ የማይታወቀው (በሪንጉ ውስጥ) ፍትሀዊነቱ የተሟላ ነው፡፡ ፖለቲካ የለውም፡፡
ከሪንጉ ውጭ ግን ምን እንደሚካሄድ አይታወቅም፡፡ ህጉም ሆነ ተፋላሚዎቹ ተቀያያሪ ናቸው፡፡ ማን እንዳሸነፈና ማን እንደተሸነፈ የሚወስን ዳኛ የለም፡፡ ዳኛውም ሆነ ተፋላሚዎቹ በተለያዩ ጭንብሎች ስር የሚመላለሱ ናቸው፡፡ ተፋላሚዎቹ የሚመላለሱበት ርዕዮተ ዓለም ሕቡዕ ከሆነ… ቲፎዞውም ሆነ ተመልካች ከተፋላሚዎቹ ጎን የሚቆመው በሚታይ መንስኤ ወይንም ምክኒያት ሊሆን ፈፅሞ አይችልም። እንዲችልም አይጠበቅም። ከጠባቡዋ የቦክስ ሪንግ ባሻገር ለተመለከተ ሰው …. አለም ዘወትር የፍልሚያ መድረክ መሆኗን ለመገንዘብ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ በትንሹ የቦክስ ሪንግ ውስጥ ያለው ፍልሚያ ስርዓት ያለው እንደሆነም ይረዳል፡፡ አለምም የቡጢ መድረክ ናት፡፡ ማን ማንን እንደሚመታ ወይንም ማን ምንን እንደሚያስመታ … ግን አይታወቅም፡፡ አይታወቅም ስል፤ ቢያንስ ተመልካችን ሆኖ ወይንም ተራ ሰውን ሆኖ ማወቅ አይቻልም… ማለቴ ነው፡፡ በየትኛውም ማኑዋል መሰረት የተፃፈ አይደለም የዓለም ቡጢ ፍልሚያ ህግ፡፡
ማድረግ የሚቻልና የማይቻል የግጥሚያ ስነ ስርዓት የለም፡፡ ኪሎው የማይመጥን ተጋጣሚ፣ ኪሎውን በጦር መሳሪያ አስተካክሎ … ኪሎው ከሚመጥንና ግን ከቡጢው ሌላ መለኪያ የሌለውን ተጋጣሚውን ለማጥቃት ወደ ሪንጉ ሊገባ ይችላል፡፡
ተጋጣሚውን ለማጥቃት የተጋጣሚውን ቤተሰብ በድሮን (drone) በመደብደብ የቦክስ ግጥሚያውን ቀበቶ መውሰድ ይችላል፡፡ … የቦክሱ የፍልሚያ ህግ የተፃፈ ስላይደለ ሁሉንም ማድረግ ይቻላል፡፡ … ከቦክሱ ሪንግ ውጭ ያሉ የባላንጣውን ቲፎዞዎች መግደል ይችላል፡፡
ለመግደልም ምንም የተረጋገጠ መንስኤ ላይኖረው ይችላል፡፡ አንድ ወይ ሁለት ፍረጃዎችን ለጥፎ፣ ከዛ መደምሰስ ነው። ወይንም ፍረጃም ካጠረ ዝም ብሎ መደምሰስና ድርጊቱን የመካድ መብት አለው፡፡ … ሁሉንም ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምን የተደረገው ሁሉ እንዳስፈለገ ግን ማንም መግለፅ አይችልም፡፡ ለመግለፅ እና “Justify” ለማድረግ የሚጥሩ ፅንሰ ሀሳቦችም … የተፈጸመውን ድርጊትና የማድረግ አስፈላጊነትን ማመጣጠን ችለው አያውቁም። በተጨባጭ ያቃተን ነገር ለማመጣጠን ሁለተኛ ዙር ዘመቻ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ሁለተኛው ዙር ዘመቻ በፕሮፓጋንዳ ጦር መሳሪያ የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ፤ ቦክሰኛው በሪንጉ ውስጥ ቢያንስ መጠነኛ ስርዓት ስለሰፈነ ነው ከህይወት ፍልሚያ የበለጠ እመርጠዋለሁ ያለበት ምክኒያቱ፡፡  
የቦክሱ ህግ ወደ ዓለም ተወስዶ ቢያንስ መስራት የነበረበት ቢሆንም … በተቃራኒ የዓለም ህግ (ከሪንጉ ውጭ ያለው ህግ) ወደ ውስጥ መጥቷል፡፡ ከዓለም ግራ የተጋባ ኢ-ፍትሃዊነት ለመሸሸግ ተጋጣሚዎች ከእነ አጋጣሚዎቻቸውና ቲፎዞአቸው ወደ ቦክስ ስፖርት መጥተው መደበቅ አይችሉም፡፡ ዓለምና ውጥንቅጧ በሁሉም ስፍራ መጥታለች … ህግ አፍራሽነቷን … ህገ ደንብ አድርጋዋለች፡፡ በብዕር ስም የምታስመስልባቸውን የህግ ስርዓቶችን በግልፅ ሽራ፣ በእውነተኛ ስሟ ብቅ ብላለች፡፡
ምንም ስውር ምክኒያት መፈለግ አያሻም። ግራ እና ቀኝ፣ … ጥቁር እና ነጭ …አማኝ እና ከሀዲ እየተባለ ግጭትን የፍትሃዊ ካባ ማልበስ አያስፈልግም፡፡ መንስኤም ሆነ ምክኒያት የለውም፤ … ቀድሞውንም ቢሆን አልነበረውም።
“እኩይም” ይሁን “ሰይጣን” ለህልውናው ምንም ምክኒያት አያስፈልገውም፡፡ ምክኒያት መፈለግ የሰዎች ቋንቋ እንጂ … የሰይጣን ቋንቋ አይደለም፡፡ ምናልባት ምክኒያት ሁሉ ሲያልቅ እኩይ እንደ እኩይነቱ ተገልፆ ያለ መሸፋፈኛ ይወጣል፡፡ ምናልባት መልካምን ለማመን መጀመሪያ እኩይን እንደ እኩይነቱ፣ ያለ ማስመሰያ መገንዘብ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

Read 1314 times