Sunday, 23 October 2016 00:00

‹‹የስሙኒ መልካም አስተዳደር፤ የሽልንግ ልማት››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(8 votes)

‹‹--- ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት ሳይመሰረቱ ዕድገት ወይም ብልጽግና የሚታሰብ
አይደለም፡፡ የዕድገት ምስጢር ነጻነት ነው፡፡ ያለ ነጻነት ዕድገትና ልማት የህልም እንጀራ ነው፡፡ -----››
ባለፈው ሣምንት ‹‹በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት›› አማካኝነት ‹‹        ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከተደሰቱት ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ልዩ ነበር፡፡ ግን የተፈጠረብኝ ስሜት በደስታ ብቻ አይገለጽም፡፡ የቁጭት ስሜትም አብሮ ነበር፡፡ በአጭሩ፤ የስሙኒ ቁጭት፤ የሽልንግ ደስታ ለማለት እችላለሁ፡፡ የሽልንጉ ደስታ፤ የሐሳብ ልዩነት በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥን እንደማይከለክል ወይም ልዩነት የግጭት መንስዔ አለመሆኑን ከመረዳት የተሸመተ ነው፡፡ የስሙኒው ቁጭት፤ ‹‹እንዲህ ዓይነት መድረኮችን (በመከራ ሳይሆን በፈቃድ ግፊት) ቀደም ብለን ማዘጋጀት እንዴት አቃተን›› ከሚል የዋህ ምኞት የመጣ ነው፡፡
በእርግጥ የሐሳብ ልዩነቶች በርዕዮተ ዓለም ጎራ ከወዲያና ከወዲህ ለመቆምና ለመወጋገዝ ሲዳርግ አይተናል፡፡ ደምም ሲያፋስስ ተመልክተናል፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ የልዩነት ጎራ ፈጥሮ፤ የርዕዮተ ዓለም ባንዲራ አስይዞ፤ ይህ ‹‹ወገን››፣ ያኛው ‹‹ጠላት›› ነው በሚል አስፈርጆ፤ የባላንጣነት ምክንያት ሲያሰላልፈን ከታሪክም ሆነ ከህይወት ልምድ አስተውያለሁ፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች ለግጭት ምክንያት ተደርገው ሲያዙ ማየታችን የማይካድ ነው፡፡ ሆኖም የሐሳብ ልዩነት፤ የግድ - ሁልጊዜ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ በአንድ መድረክ ተቀምጦ ከመወያየት አያግድም፡፡ ሰዎች የተለየ ሐሳብን ይጠሉ ይሆናል እንጂ ሐሳቦች ሰዎችን አይጠሉም፡፡ ሐሳቦች ሐሳብን አይጠሉም። ሐሳቦች ጥራትና ብቃት የሚያገኙት፤ የህግ እና የቋሚ እውነት ማዕረግ የሚያገኙት በተቃራኒ ድጋፍ ሐሳብ ነው፡፡ የሐሳብ ከተማ ውይይት ነው፡፡ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተዘጋጀው የውይይት መድረክ፤ የውይይትን ውብ ገጽታ ለማየት አስችሎኛል፡፡ የደስታን ስሜት አሳድሮብኛል፡፡
በርግጥ የውይይቱን ሙሉ ይዘት ለመከታተል ዕድል አልነበረኝም፡፡ ለመከታተል የቻልኩት፤ ለውይይቱ መነሻ ሐሳብ ያቀረቡ አራት ሰዎችን የየግል አስተያየት ብቻ ነው፡፡ የውይይቱን ሙሉ ስዕል ባለማየት የተዛባ ዳኝነት እንዳይሆን መስጋቴ ባይቀርም፤ የአራቱ ሐሳብ አቅራቢ ሰዎች የነገር አያያዝ ብቻ ለውዳሴ በቂ ምክንያት ይሆነኛል፡፡ ውይይቱ በሁሉም ሚዛን ከተለመደው የተለየ ይዘት ነበረው፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ‹‹ነጥብ ለማስቆጠር›› በሚል መንፈስ የተቃኘ ውይይት አልነበረም፡፡ የነጻ መንፈስ ልዕልና የታየበትና ድሁር ከሚያደርግ የነገር ጓዝ የጸዳ ውይይት ነበር፡፡ ችግርን በመፍታት ፍላጎት የሚመሩ የተጻራሪ ሐሳቦች ጉባዔ ውበት ሲሆን አይቻለሁ፡፡ ከልዩነቶች እሣት ብቻ ሳይሆን ውበትና እውነትም እንደሚፈልቁ አይቻለሁ፡፡
ውይይቱ የጽጌረዳ አበባ ነው፡፡ የጽጌረዳ አበባ እሾህና በቀለም የተዋቡ ቅጠሎች ያሉት ነው። አበባው ጽጌረዳ ከሆነ እሾህና ቅጠል ይኖረዋል። ውብ ቅጠሎች ወይም እሾህ ብቻ የምናይ ከሆነ፤ ጽጌረዳ አበባ እያየን አይደለም፡፡ እውነት ሸፍጧል። እውነቱ፤ ውብ ቅጠሎችና እሾህም ያለበት ነው፡፡ ውይይቱ እንደ ጽጌረዳ አበባ ነበር፡፡
ተወያዮቹ እሾሁን የሚያነሱት ስሜት ለመጉዳት አይደለም፡፡ አበባውን ሲጠቅሱ ለመሸንገል አልነበረም፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ እሾሁ በመጎዳዳት ስሌት አይነሳም፡፡ ባለ ቀለሙ ውብ ቅጠልም በአድርባይነት መንፈስ አይሽሞነሞንም፡፡ አስቀያሚ እውነቶችን በውብ ቅጠሎች ጉዝጓዝ ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ አልታየም፡፡ በቃ፤ ጽጌረዳ እንዲህ ነች፡፡ እሾህና ውብ ቅጠሎች አሏት፡፡
ከውይይቱ የተረዳሁት ሌላ ነገርም አለ። የተናጋሪ ሰው መልዕክት፤ በሚናገረው ነገር ብቻ አይወሰንም፡፡ መልዕክት በአነጋገር ዘይቤ ይወሰናል፡፡ ተወያዮቹ ከሚናገሩት ነገር እኩል፤ ለአነጋገራቸው (ለአቀራረባቸው) ዋጋ ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም በየራሳቸው የአመለካከት፣ የትንታኔ ወይም የእይታ ዛቢያ ይሽከረከራሉ፡፡ ግን የሐሳባቸው ዑደት በአንድ ፀሐይ ዙሪያ ነው፡፡ በራሳቸው የሐሳብ ዛቢያ እየተሽከረከሩ፤ ዑደታቸው ሐገራችን የገጠማትን ችግር በመፍታት ዓላማ ዙሪያ የሚመላለስ ነው፡፡ በአንድ ጸሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ የተለያዩ (ተቃራኒ) ሐሳቦች ህቡርና ስሙር ይሆናሉ፡፡
ተናጋሪዎቹ፤ የሚናገሩትን የሚያውቁ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በደንብ የሚያውቁትን ነገር በደንብ የሚናገሩም ናቸው፡፡ የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ የተረዱ ናቸው፡፡ ንግግራቸው ለመወቃቀስ አይደለም፡፡ ይልቅስ ዓይን ለዓይን ለመተያየት ነው። እንዲህ ያለ የውይይት መንፈስ፤ ውይይታቸውን በሚያዳምጠው ሰው ዘንድ ልዩ ስሜትን ያሳድራል። ሁሉም አንድን ችግር ለመፍታት በመተጋገዝ የሚሰሩና በአንድነት መንፈስ ጥረት የሚያደርጉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች እንጂ፤ ለመሸናነፍ የሚጫወቱ ተቀናቃኞች አይመስሉም፡፡
በገዢው ፓርቲ ላይ የሚቀርቡ የሰሉ ወቀሳዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ተወያዮቹ የሚያነሱት ወቀሳዎች፤ ገዢው ፓርቲ ራሱን መርምሮ ነቅሶ ያወጣቸውና በግልጽ ያቀረባቸውን ችግሮች የሚጠቅሱ ወቀሳዎች በመሆናቸው፤ ራሱ የሚያውቃቸው ችግሮች በሌላ አንደበት ሲቀርቡ እንደመስማት ሊቆጥረው ይችላል። ቋንቋው ወይም አቀራረቡ ይለይ ይሆናል እንጂ ይዘቱ አንድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የአንድ ቡድን ተጫዋቾች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ የሁሉም ዓይኖች በችግሮቹ ላይ ነው፡፡ ልዩነት ቢኖር የችግሩ አፈታት ላይ እንጂ በችግሮቹ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ ለውይይቱ ውበት ልዩ አስተዋጽዖ ነበረው፡፡
በርግጥ፤ ሐገሪቱ ለገጠማት ችግር የመፍትሔ ሐሳብ ሆነው በሚቀርቡ ጉዳዮች ወይም በችግሮቹ ምንጮች ዙሪያ ልዩነት ያለ መሰለኝ፡፡ ነገር ግን ሁሉም (ኢህአዴግን ጨምሮ) መፍትሔ አድርገው የሚያቀርቡት ነገር በገጽታ ካልሆነ በቀር በይዘት ብዙ ልዩነት ያላቸው መስሎ አልታየኝም፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር፤ ሁሉም ሰዎች መፍትሔ የሚሉት ነገር በተቋማት ጉዳዮች የሚያጠነጥን ነበር፡፡ በሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳር ወዘተ ለተጠቀሱ ችግሮች መፍትሔ ብለው የሚያቀርቡት ነገር፤ በትክክለኛ መርህና እውነተኛ እምነት ላይ የተመሠረቱ ተቋማትን በመፍጠር፣ በማደስ፣ በማጎልበት የሚሽከረከር ነው፡፡
እውነት ነው፤ በዓለም ሐገራት መካከል በዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና በሐብት ረገድ የሚታየው ልዩነት መነሻው፤ የህገ መንግስት አንቀጾች መለያየት፤ የቴክኖሎጂ፣ የካፒታል፣ የሰው ኃይል፣ የመሬት፣ የተፈጥሮ ሐብት ወይም የማዐድናት ወዘተ ልዩነት አይደለም፡፡ ሐገራት የኢኮኖሚ ልማት ሊቀዳጁ የሚችሉት ትክክለኛ የሆነ ወይም ዕድገት አሳላጭ (Pro-growth) ፖለቲካዊ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ዕድገት አሳላጭ የኢኮኖሚ ተቋማት የሚፈጠሩትም፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ (ተቋማት) ሲኖሩ ነው፡፡ በአጭሩ፤ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕ፣ የማህበራዊ ወዘተ ተቋማቱ ዕድገት አሳላጭ በሆነ መንገድ ሊፈጠሩ የሚችሉት፤ ዕድገት አሳላጭ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡
ዕድገት አሳላጭ ፖለቲካዊ ተቋማት ሲፈጠሩና ሲጠናከሩ ሐገራት የዕድገት ጎዳናን ተከትለው ብድግ ይላሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ ተቋማት ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እያስተካከሉና እየቃኙ መጓዝ አቅቷቸው ሲቸከሉ ወይም አቅማቸው በተለያየ ምክንያት ሲዳከም ወይም ጨርሶ ሲወድቅ፤ ሐገራት የገነቡት ስርዓት ተርገድግዶ ይፈራርሳል፡፡ ሐገራቱም አይወድቁ አወዳደቅ ይወድቃሉ፡፡
በውይይቱ ከተነሱት ነጥቦች በጣም አሳሳቢ ሆኖ የታየኝ ጉዳይ ‹‹State capture›› (የመንግስት መቀየድ ልበለው) በሚል የተጠቀሰው ችግር ነው፡፡ በፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ‹‹የመንግስት መቀየድ›› በሚል የሚጠቅሱት ችግር ሰፊ ሐሳብ የሚያካትትና አጅግ አደገኛ የሆነ ችግር ነው፡፡ በእርግጥ፤ በማናቸውም ዘመንና በትኛውም ሐገር፤ የመንግስት ስልጣንን ለመቆጣጠርና በራሳቸው ፍላጎት ልጓም የተለጎመ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ይኖራሉ፡፡ መንግስትን የጠባብ ቡድናዊ ወይም ግላዊ ፍላጎታቸው መሣሪያ ሊያደርጉት የሚፈልጉ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የእነሱን መሻት ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ቅይድ መንግስት እንዲኖር የሚጥሩ ወገኖች መኖራቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ወገኖች ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወዘተ ሃይል በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ኃያል ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሰፊ ማህበራዊ ልማትን የሚያደናቅፍ ፍላጎት ይዘው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ የእነሱ ፍላጎት ይሳካ እንጂ የሚሊዮኖችን ዕድል የሚያሰናክል ወይም ሐገር የሚያፈርስ ነገር መያዛቸው ጨርሶ አያሳስባቸውም፡፡ ስለዚህ የፈለጉት እንዲፈጸምላቸው ከመጣጣር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሐገር የሚያጠፋ ተግባር ቢሆንም ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አያመነቱም፡፡ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ምንጊዜም ይኖራሉ፡፡ ታዲያ እነዚህን የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣን ያላቸው ኃያል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አደብ እንዲገዙ ማድረግ የሚቻለው፤የእነሱን ፍላጎት ተረድቶ አንቅስቃሴአቸውን መቆጣጠር የሚችል ህይወት ያለውና ብቁ-- ንቁ የዴሞክራሲ ስርዓት በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው አማራጭ ሁለት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንዳሻቸው የማድረግ ዕድል እንዳያገኙ በሩን ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ የዴሞክራሲ ስርዓት  መገንባት ወይም ሐገር ሲፈራርስ ቁጭ ብሎ መመልከት ብቻ ነው፡፡
ይህን ማድረግ የሚቻለውም ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት በመፍጠር ነው፡፡ ጠንካራ የፍትህ ወይም የፖለቲካ ተቋማት ሳይመሰረቱ ዕድገት ወይም ብልጽግና የሚታሰብ አይደለም፡፡ የዕድገት ምስጢር ነጻነት ነው፡፡ ያለ ነጻነት (በሁሉም ገጽታ) ዕድገትና ልማት የህልም እንጀራ ነው፡፡
የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ታሪክ መፈተሽ ይቻላል፡፡ ሐገራትን ሐብታም ወይም ድሃ የሚያደርጋቸው፤ የፖለቲካ መዋቅራቸው ልዩነት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የዓለም ሐገራት ባለጸጋ ለመሆን የቻሉት፤ ሁሉን አካታች፣ ሳይዛነፍ የሚሰራ፣ የስልጣን ክፍፍልን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ተቋማትን መፍጠር በመቻላቸው ነው፡፡ መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት ለውጥ ሳንፈጥር፤ ጥሩ የኢኮኖሚ ሐሳቦችን መያዝና ምርጥ ፖሊሲዎችን መንደፍ ለውጥ አያመጣም፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማቱ ተደጋግፈውና ተሳስረው ካልሰሩ ልማት አይገኝም፡፡ ‹‹የሽልንግ መልካም አስተዳደር እና የሽልንግ ልማት›› ለመፍጠር መትጋት ይኖርብናል፡፡

Read 2898 times