Sunday, 23 October 2016 00:00

“ያልገነባነውን አንሸጥም”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 የሪል እስቴት ቤት አልሚዎች በኢትዮጵያ ከተከሰቱ ሃያ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ቁጥራቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን እንደ ብዛታቸው በቤት ጥራት፣ ታማኝነትና ተደራሽነት የሚያደርጉት ፉክክር አልነበረም፡፡ እንደውም ግማሽ/ሙሉ የቤት ዋጋ ተቀብለው የሚሰወሩት ለዓመታት አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አንዳንዶቹም በተባለው ጊዜ ማስረከብ ተስኗቸው ፍርድ ቤት የሚቆሙበት ጊዜም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ቤት ፈላጊውና አቅርቦቱ ሊመጣጠን አልቻለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤት ፈላጊዎች ገንዘብ ሰብስቦ ለግንባታ ማዋል ወይም መሰወር ቀርቶ በራሳቸው ወጪ ቤት ገንብተው የሚሸጡ ድርጅቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ያልገነቡትንም እንደማይሸጡ ማስታወቂያ እያስነገሩ ይገኛሉ፤ መልካም ጅምር፡፡
ከዚህ ተነስተን የመንግስትና የግል ድርጅቶች አመራር ግንባታ፤ የጋራ ማህበረሰብ ግንባታ፤ የኢኮኖሚ ልማት ግንባታና የማህበረሰብ የልቡና ውቅር ግንባታ ---- በኢትዮጵያ በሚገባ ተከውኗል ወይ ብለን እንጠይቅ፡፡ የቤት ግንባታው ከዓመታት በኋላ እንዲሻሻል ተጽዕኖ የፈጠረው የተበዳይ ግለሰቦችን ጩኸት ተከትሎ፣ መንግስት ያወጣው ሕግ ነው፡፡ ሳይገነቡ ገንዘብ መሰብሰብ ተከለከለ፡፡ አልሚዎቹም፤ “ያልገነባነውን አንሸጥም” አሉ፡፡
በሀገሪቱም ለዓመታት ሳይገነባ በቀረ አመራርና አስተዳደር የተነሳ ህዝቦች የተበዳይነት ጩኸት እያሰሙ ነው፡፡ ቆራጥና አፋጣኝ ውሳኔ ማሳለፍ የተሳነው አመራር በመኖሩ፣ በየክልሉ አስተዳደራዊ በደልና ሙስና በማህበረሰቡ ላይ እስከ አፍ ገደፉ እያደረሰ ነው፡፡ አብዛኛው የአስተዳደርና አገልግሎት ሰጪ ተቋም በዕውቀት፣ በዘመናዊ አሰራር ስርአትና በሰብአዊነት (Humanity) ላይ የተገነባ ባለመሆኑ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅሩ ቅንነትን፣ ዕውቀትና ትጋትን መሰረት አድርጎ ባለመቋቋሙ፣የጋራ ማህበረሰባዊ ግንባታው ላይ ተጽዕኖው የጎላ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ቅይጥ ማህበረሰቦችም ሆነ ኩታ ገጠም ወረዳዎች መሃህል አለመግባባትና ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጎታል፡፡ በዚሁ በቅጡ ባልተደራጀ አመራርና አስተዳደር ሳቢያ፣ የኢኮኖሚ ልማት ግንባታና ስርጭት ውስን ሆኗል፡፡ በአስቸጋሪ ሰዓት ቡጢ ከመጨበጥ ይልቅ የሸሚዝን እጅጌ መሰብሰብና ቃል የተገባውን መፈፀም ተገቢ ነው፡፡ መንግስት በሃቅ፤ “ያልገነባውን አንሸጥም” ማለት አለበት፡፡ ድርጊት እንጂ የሚዲያ ሽፋን ፍትህን፣ እኩልነትና ልማትን አያስገኝምና፡፡
በኢትዮጵያ ከኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ዘመናዊ የህዝብ አስተዳደር ትምህርትን ከሰለጠነው ዓለም በመውሰድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ይኸው አስተዳደራዊ (የአመራር) ትምህርት ለፖለቲካዊ፣ ህዝባዊ አገልግሎት፣ መያድና የንግድ ድርጅቶች ተቋማቶቻቸውን እንዴት ለስኬት እንደሚያበቁ የሚያስተምር ነው፡፡ ሆኖም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንዳሉት እኩያትና መልካም አገልጋዮች፤(አንደኛው በድግምትና ሰይጣናዊ ስራን በማስፋፋት፤ ሌላኛው እግዚአብሔርን በማገልገልና ቅድስናን በመዝራት እንደሚጠመዱት ሁሉ) የዘመናዊ አመራርና አስተዳደር ተመራቂዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንዱ ወገን ህዝባዊ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ሲደክም፤ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ቢሮክራሲያዊ አሰራርን በማስፋፋትና የጥቅም ተጋሪዎችን በጎሳና ሃይማኖት ማዕቀፍ በማደራጀት፣ከሚኖርበት አካባቢ የዘለለ ግንዛቤ የሌለውን ማህበረሰብ መበዝበዝና ሀብት ማካበት ላይ የተጠመደ ነው፡፡ በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ቢስፋፋም የአመራርና የአስተዳደር አተገባበር ላይ ዘመናዊነት አይታይም፡፡
በየተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች ትኩረታቸው አመራሩን ለማዘመን ሳይሆን የበታች ሰራተኞችን እንዴት መቆጣጠርና ወጪን በመቀነስ በውስን የሰው ኃይል ስራውን ማሰራት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አመራሮች የስራውን ሂደት መረዳትና መምራት ሲገባቸው፤ የተቋማቱ ባላባቶች ሆነው የድርጅቱን ወጪ በስብሰባ አበል፣ ስልጠና እና መሰል እርባና-ቢስ ተግባሮች በማናር፣ የድርጅቱ ገቢ አሽቆልቁሎ በኪሳራ እስከ መዘጋት ያደርሱታል፡፡ የግልም ሆነ መንግስታዊ ተቋማት አመራሮች ለድርጅቱ የገቢ ማሽቆልቆል ተጠያቂ የሚያደርጉት ከጊዜው ጋር የማይሄድ፣ የራሳቸውን አስተዳደራዊ ክህሎትና ደካማ ስነ ምግባር ሳይሆን የፈረደበትን የበታች ሰራተኛ ነው፡፡ ይህ ከህዝብ የተሰጠን ኃላፊነት ለማይገባ ተግባር ማዋልና ተከትሎ ከሚመጣ ተጠያቂነት መሸሽ፣ በተቋሙና ተገልጋዩ ህብረተሰብ መሀል መተማመን ያሳጣል፡፡ በዚህም የተነሳ በማህበረሰቦችና የተቋማት ሰራተኞች ውስጥ የስራ ተነሳሽነትና ምርታማነት እንዳያንሰራራ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኗል፡፡
“ምን እውቀትና የሥራ ልምድ አለህ?” ብሎ የሚጠይቅ ሳይሆን “ጎሳህ ምንድነው? የየትኛው ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት አባል ነህ?” የሚል ነው መስፈርቱ፡፡ በደርግ ዘመንም ቢሆን ግትር፣ የሰራተኛንና የንግዱን ማህበረሰብ እድገት አንቆ የሚይዝ አመራር ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ መዝባሪና ጎሳን መሰረት አድርጎ የተቧደነ አመራር በመሆኑ፣ብሄራዊ ኢኮኖሚና ዜግነት ምኑም አይደሉም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ፤ በየክልሉ ባሉ የዞንና ወረዳ አመራርና አስተዳደር አባላት ስለ ዜግነትና የብሔራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን አመለካከት መፈተሸ ነው፡፡ ከደርግ ዘመን የሚሻለው የግል ንግድ እንዲስፋፋ በመፍቀዱ ነው፡፡
በእያንዳንዱ የሙያ ዘርፍ የስነ ምግባር ድንጋጌዎች ቢኖሩም ተግባራዊ ማድረግና አሰራሩም ህግና ደንብን የተከተለ እንዲሆን ክትትል እስካልተደረገበት ድረስ፣ በተቋማት መካከል ያለመቀናጀትና ያለመናበብ ችግር፤ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ማሻሻያም ከሌለ፤ የአመራሩና አስተዳደር ድክመት በስንት ጥረትና የገንዘብ ድጋፍ የተቀረፀን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ለሰፊው ህዝብ ጥቅምና የኑሮ መሻሻል እንዳይውል ያደርጋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን እየተስፋፋ ነገር ግን ዘመናዊ አመራርና አስተዳደርን መተግበር ለምን አቃተን? ጥሩ አባላት ቢኖሩም መልካም አመራሮች በተቋማት ውስጥ ያነሱበት (የሳሱበት) ምክንያት ምን ይሆን? ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በአመራርና አስተዳደር ዘርፍ እየተመረቁ የወጡት የአገሪቱን አስተዳደር ስርአት ለምን አላዘመኑትም? በአቶ መለስ ስም የሚቋቋመው የአመራር (Leadership) ማሰልጠኛ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? ምን አልባት የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩ በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተጽዕኖ በመፍጠሩ ይሆን? ፖለቲካዊ መዋቅሩ፡- ዕውቀት፣ አስተዳደራዊ ዝንባሌና ትጋትን መሰረት አድርጎ እንደገና ቢሰራ፣በየዘርፉ ያለውን አስተዳደራዊ ችግር እንዲስተካከል ያግዛል? “There is no substitute for character. You can buy brains, but you cannot buy character.” Robert A. Cook

Read 1250 times