Sunday, 23 October 2016 00:00

ዓለማቀፉ “ጎልደን ቱሊፕ” ሆቴል - በአዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለቤቶቹ ሌላ ባለ 5 ኮ ከብ ሆቴል ግ ንባታ ጀምረዋል
                   
        በእኛ አገር ክረምት አብቅቶ መስከረም ሲጠባ፣ ሜዳውና ጋራ ሸንተረሩ በአደይ አበባ ተውቦ ልብን በሐሴት ይሞላል፡፡ በአውሮፓም ተመሳሳይ ክስተት ይፈጠራል፡፡ ክረምቱ እንደወጣ አገር ምድሩ ጎልደን ቱሊፕ (Golden Tulip) በተሰኘች በጣም በምታምር ወርቃማ አበባ ይሸፈናል፡፡ በዚህች ወርቃማ አበባ የተሰየመው ባለ 5 ኮከቡ “ጎልደን ቱሊፕ” ሆቴል፤ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 1 ኪ.ሜ ያህል ርቀት ላይ፣ ከቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ ከአትሌት ብርሃኔ አደሬ የገበያ ማዕከል (ሞል) ገባ ብሎ ይገኛል፡፡
ባለ 5 ፎቁ “ጎልደን ቱሊፕ አዲስ አበባ” ሆቴል፣ የቦታ ጥበት ቢኖርበትም ባለቤቶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲጠብቅ ተጨንቀው ነው የሰሩት። ገና ወደ ሆቴሉ ሲገቡ ሎቢው ቀልብን ይስባል። ከበሩ በስተቀኝ የተለያዩ ጣፋጭ ኬኮች፣ ትኩስ ዳቦ፣ እንዲሁም ሻይ ቡና የሚያዙበት ወይም ገዝተው ይዘው የሚሄዱበት “ግራብ ኤንድ ጎ”  (Grab & Go) ያገኛሉ፡፡ ከፊት ለፊቱ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው “ስፓይሲ ሬስቶራንት” አለ። በስተግራ የእንግዶች ማረፊያ ሶፋዎች በወግ በወጉ ተደርድረዋል፡፡
አነስተኛ የቦርድ ስብሰባዎችና ከዚያ ከፍ ያሉ እንዲሁም ለሰርግ እስከ 200 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ አራት አዳራሾች ያሉት ከሎቢው በላይና ከ1ኛው ፎቅ በታች ባለው ወለል ላይ ነው፡፡  የስብሰባ አዳራሾቹ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተገጠመላቸው ሲሆን ቪዲዮ ኮንፈረንስ ማካሄድ የሚያስችሉ፣ የአየር ሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያ (ኤሲ) ያላቸው ናቸው፡፡ የቦታ ችግር ስላለበት የውጭ እንግዶች አያስተናግድም እንጂ አልጋ የያዙ እንግዶች የሚጠቀሙበት ደረጃውን የጠበቀ፣ ዘመናዊ ጂምናዚየም ምድር ቤት አለ፡፡ ሆቴሉ 4 የመጠጥና ምግብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ስፍራዎች አሉት፡፡ ሰፊ ስፖርት ባርም አለው፡፡ ሌመን ባርና ብቻቸውን መጨዋወት የፈለጉ ሰዎች የሚስተናገዱበት ሃቫና (ቪአይፒ) ባር የሚገኙት እዚሁ ፎቅ ላይ ነው፡፡
ሆቴሉ ሥራ የጀመረው በሐምሌ 2007 ዓ.ም ሲሆን ለግንባታውና ለውስጥ ቁሳቁሶቹ 180 ሚሊዮን ብር መፍጀቱን፣ ለ189 ቋሚና ለ15 ተለማማጅ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ የጎልደን ቱሊፕ ፕሮጀክት ኃላፊና ወኪል አቶ ታምራት በላይ ገልጸዋል፡፡ የሆቴሉ ማኔጅመንት የሚመራው በዓለም አቀፉ ብራንድ በ“ጎልደን ቱሊፕ” ነው፡፡
አቶ ታምራት ወኪል ሆነው ሆቴሉን ያሰሩት እንጂ የገንዘብና የእውቀት ምንጩ፣ በደርግ ጊዜ የስኮላርሺፕ ዕድል አግኝተው ወደ ቻይና የሄዱት ወንድማቸው የአቶ አስቻለው በላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ያላቸውን ነገሮች አገር ውስጥ ካሉ ሙያተኞች ይበልጥ ሀሳብ በማመንጨት፣ ግብዐቶችን በማቅረብ ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውን ወንድማቸው ገልፀዋል፡፡    
“ጎልደን ቱሊፕ” በ1960ዎቹ በ6 የግል ሆቴል ባለቤቶች፣ በሆላንድ ኔዘርላንድስ መመሥረቱን የጠቀሱት አቶ ታምራት፣ እ.ኤ.አ በ2009 የ“Starwood Capital” አባል ከሆነ በኋላ የ“Luver Hotels Group” ሽርክና ውስጥ ገብቶ፣ በአውሮፓ 2ኛው ታላቅ የሆቴል ግሩፕ መሆኑን፣ በዓለም ደግሞ 8ኛ ደረጃ መያዙን ተናግረዋል፡፡ በ2015 ግዙፉ የቻይናው ኩባንያ “Jin Jiang International” የሉቨር ሆቴል ግሩፕን መግዛቱን የገለጹት አቶ ታምራት፤ ኩባንያው በመላው ዓለም ከ3ሺ በላይ ሆቴሎች እንደሚያስተዳድር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ኩባንያ በአውሮፓ የሆቴሎች ኢንዱስትሪ ውስጥ በ2ኛ ደረጃ እንደሚገኝ፣ በ51 አገሮች ውስጥ 1100 ሆቴሎች እንዳሉትና ደረጃውም በዓለም ላይ ከምርጦቹ 5 ብራንዶች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።
“ጎልደን ቱሊፕ አዲስ አበባ ሆቴል” 90 የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፣ በየፎቁ 18 አልጋዎች አሉት፡፡ ሦስት ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ታምራት፤ 70 ክፍሎች ደሉክስ፣ 15 ክፍሎች ኤክስኩቲቭና 5 የዲፕሎማቲክ ሱትስ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አምስቱ የዲፕሎማቲክ ክፍሎች የአገር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአገር ተወካዮች፣ የቢዝነስ መሪዎች፣ … ያሉ ታዋቂና ጥበቃ የሚደረግላቸው ሰዎች የሚያርፉባቸው ሲሆኑ ሳሎን (መሰብሰቢያ)፣ መኝታ ቤት፣ መታጠቢያና መጸዳጃ ክፍሎች አሏቸው፡፡ የመሰብሰቢያ ክፍሉ ሰፊ ነው፡፡ ሶፋ፣ ቲቪ፣ ስልክ፣ ኤሲ፣ ለስብሰባ አስፈላጊ የሆኑ ቁሶች፣ … ያካትታል፡፡ ቲቪው እንግዳው ክፍሉን ሲይዝ፤ “ዌልካም” ይለዋል፡፡ ክፍሉን ሲለቅ ደግሞ፤ “ይህን ያህል ተጠቅመሃል፣ ይህን ያህል ሂሳብ ትከፍላለህ” ይለዋል፡፡ መኝታ ክፍሉ ሰፊ ነው፡፡ ቲቪ፣ ስልክ፣ ፍሪጅ፣ ካዝና፣ ወዘተ … አሉት፡፡ መታጠቢያ ክፍሉ ገንዳና የቁም መታጠቢያ አለው። ገንዳ ያላቸው 5ቱ ክፍሎች ብቻ ናቸው፡፡ ሽንት ቤቱ አውቶማቲክ ነው። ቁልፎቹን ሲጫኑ ከፍና ዝቅ ይላሉ፡፡ መኝታ ክፍሉ 3 ስልኮች ሲኖሩት፣ አንዱ መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ነው፡፡
ኤክስኩቲቭና ደሉክስ ክፍሎች በስፋትና በአገልግሎት በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁሉም ክፍሎች ሁለት ክፍል (መኝታና መታጠቢያ) አንድ ቲቪ፣ ሁለት ስልኮች (መኝታና መታጠቢያ ክፍል) ፍሪጅ (ሚኒ ባር)፣ ካዝና፣ አየር መቆጣጠሪያ፣ የቁም መታጠቢያ፣ ቡናና ሻይ ማፍያ ---- አሏቸው፡፡
ግንባታው ሲጀመር የተሰጣቸው ፈቃድ ባለ 4 ኮከብ ሆቴል እንዲሰሩ ነበር - አቶ ታምራት እንደሚሉት፡፡ በተሰጣቸው ፈቃድ መሰረት፣ ባላቸው ጠባብ ቦታ ባለ 4 ኮከብ ደረጃ ለማሟላት ተጨንቀውና ተጠብበው ሰሩ፡፡ ለትላልቅ ሆቴሎች ደረጃ ሲሰጥ የባለ 5 ኮከብ ደረጃ መመዘኛውን አሟልተው ስለተገኙ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ደረጃውን እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በቦታ ጥበት የተነሳ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዳላሟሉ አቶ ታምራት ያምናሉ፡፡ አቶ ታምራት፤ “ጎልደን ቱሊፕ” ሲሰራ የእውቀት፣ የአቅርቦት፣ የዲዛይን ካልሆነ በስተቀር ከገንዘብ ጀምሮ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪው ዘልቀው ገብተዋል፡፡ በሊዝ ባገኙት 5 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ላይ ከአሁኑ ሆቴል በ5 ደቂቃ የእግር ጉዞ ርቀት ላይ፣ ሌላ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ግንባታ መጀመራቸውን ገልፀዋል፤ አቶ ታምራት፡፡
“ጎልደን ቱሊፕ”ን ሲገነቡ ከቀረጥ ነፃ ዕድል ስለተሰጣቸው በአግባቡ ተጠቅመውበታል። ማዕከላዊ ሲስተም ያለው የአየር ማመጣጠኛ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ለሆቴል አገልግሎት የሚሆኑ ቁሳቁሶች፣ …ያለ ቀረጥ አስገብተዋል፡፡ “በዕድሉ ባንጠቀም ኖሮ በራሳችን አቅም ይህን ሆቴል ለመገንባት በጣም ይከብደን ነበር፡፡ ስለተደረገልን እገዛ በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል፤ አቶ ታምራት፡፡

Read 2288 times