Sunday, 23 October 2016 00:00

ትናንት እና ዛሬ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 ወርቅ የሚያከማቸው ዲታ፤ በተንጣለለው መኖሪያ ቅጽሩ አፀድ ውስጥ ያዘግማል፤ ከእርሱም ጋር መከራዎቹ  አጅበውት ይራመዳሉ፡፡ ከአናቱም በላይ ጭንቀቶቹ፤ በሬሳ ላይ እንደሚያንዣብቡ ጥምብ አንሳዎች ያንዣብቡበት ነበር፤ በእፁብ ድንቅ የእምነበረድ ሀውልቶች ከተከበበው ውብ ሀይቅ እስኪደርስ፡፡
በዚያም አረፍ ብሎ፤ ከየሀውልቶቹ አፍ የሚፈልቀውን ውኃ፤ ከአፍቃሪ ሰው ምናብ በነፃነት ከሚፈልቅ ሀሳብ ጋር አነፃፀረው፤ በጉብታ ላይ ያረፈውን የመኖሪያ እልፍኙን ደግሞ በልጃገረድ ጉንጭ ላይ እንዳረፈ የቁንጅና ምልክት አሰላሰለው። ህሊናውም፤ የህይወቱን ተውኔት ገጾች እየገለጠ ሰተረለት፤ እርሱም የሰው ልጅ ለተፈጥሮ ያለውን ደካማ ፋይዳ ከማየት በከለከሉት የተጋረዱ አይኖቹ  እንባውን እያዘራ አነበበው፡፡
አጥንት በሚሰብር ፀፀት ያሳለፈውን ዘመን መልክ ያመነዥክ ጀመር፤ በአማልክቱ የትዝታ ጥለት ተሸምኖ፤ ውጥረቱን መቆጣጠር እስኪሳነው ደረሰ፡፡ ጮክ ብሎም እንዲህ አለ፤ ‹‹ትናንት በጎቼን በለምለም ሸለቆ መሀል ለግጦሽ እያሰማራሁ፤ በህይወት በመኖሬ እየተደሰትኩ፤ ዋሽንቴን እየተጫወትኩ፤ ራሴን በሀሴት ከፍታ ላይ አገኘው ነበር፡፡ ዛሬ ግን የስስታምነት እስረኛ ነኝ፡፡ ወርቅ ወደ ወርቅ ይመራል፤ ከዚያም ወደ እረፍት አልባነት እናም በመጨረሻ ቅስምን ወደሚሰብር ስቃይ፡፡››
‹‹ትናንት እንደ ዘማሪ ወፍ ነበርኩ፤ በመስኮች ላይ ወዲያ ወዲህ እያልኩ በነፃነት እምፈነጥዝ፡፡ ዛሬ ግን ባሪያ ነኝ፤ ሀብትን በማካበት፡ በማህበረሰቡ ወግ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር፣በከተሜ አኗኗር የልማድ እስረኛነት፤ እንደ እስስት እምቅበዘበዝ፤ ወዳጆችን በገንዘብ የምሸምት፤ ህዝቡን ለመጤና አስገዳጅ የሰው ልጅ ህግጋት እንዲያጎበድድ በማሞዳሞድ የተጠመድሁ፡፡ ነፃ ሆኜ እንድኖር ነበር የተፈጠርኩት፤ የህይወትን የጸጋ ትሩፋቶችንም እንድደሰትባቸው፤ ነገር ግን ራሴን ጽኑ መከራ ያጎበጠው አጋሰስ ሆኜ አገኘሁት፤ ከባድ የወርቅ ሸክም እንደተጠገረረና ሸክሙም ጀርባውን እንደሰበረው፡፡››
‹‹የት አለ ሰፊው የመኖሪያ ቀዬ፣ የፏፏቴው ዜማ፣ ንፁህ አየሩ፡ የተፈጥሮ ቅዝቃዜው? የኔ አምላክስ ወዴት ነው? ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ! በከንቱ ያተረፍኩት ብቸኝነቴን - በሀዘን የሚደቁሰኝን፤ ወርቅ - የሚያጃጅለኝን፤ አሽከሮች - ከጀርባዬ የሚረግሙኝን፤ እንዲሁም ይህን ሰፊ የመኖሪያ እልፍኜን - ሀሴት አደርግበት ዘንድ ያሳነጽኩትን መቃብሬን፤ ከግዝፈቱ የተነሳ ቀልቤን ያጣሁበትን።››
‹‹ትናንት ከበረኸኛው የዘላኑ ሴት ልጅ ጋር ሆነን፣ በመስክና ኮረብታዎቹ ዙሪያ ስንንቀዋለል፤ ደግነት ስንቃችን ነበር፤ ፍቅር ደስታችን፤ጨረቃ ጠባቂያችን። ዛሬ ግን የሚያብለጨልጭ ውበታቸውን ለወርቅና ለአልማዝ በሸቀጥነት በሚያቀርቡት ወይዛዝርቶች መሀል ነው እምኖረው፡፡››
‹‹ትናንት ፎልፏላ ነበርኩ፤ የህይወትን ፌሽታ ሁሉ ከእረኞች ጋር የምካፈል፤ መብላት፤ መጫወት፤ መስራት፤ መዝፈን፤ መጨፈሩ፤ በልብ እውነት በተቃኘ ዜማ የታጀበ፡፡ ዛሬ ራሴን በሰዎች መካከል ያገኘሁት በቀበሮዎች መካከል በፍርሀት እንደሚንዘፈዘፍ የበግ ግልገል ሆኜ ነው፡፡ በመንገድ ሳልፍ በጥላቻ የሚንቦገቦጉ አይኖች አፍጥጠውብኝ በንቀትና በቅናት ጣታቸውን ወደኔ ይቀስራሉ፡፡ ወደ መዝናኛ ስፍራዎች ብቅ ስልም፣ ግንባራቸውን የቋጠሩብኝ ፊቶችን ነው እማየው፡፡
‹‹ትናንት የደስታ ሀብታም ነበርኩ፤ ዛሬ መናጢ ድሀ ባለ ወርቅ፡፡››
‹‹ትናንት ደስተኛ እረኛ ነበርኩ፤ ራሱን ቀና አድርጎ እንደሚራመድ፣ ያለኝ ርስት ይበቃኛል ብሎ በእርካታ እንደሚኖር ደግ ንጉሥ፡፡ ዛሬ ለሀብቴ የማጎበድድ ባሪያ ነኝ፤ በአንድ ወቅት አውቀው የነበረውን የህይወትን ውበት ለነጠቀኝ ሀብቴ፡፡››
ይቅር በለኝ የኔ ዳኛ! ሀብታምነት ህይወቴን ብጥቅጥቅ አድርጎ አነኳኩቶ እንዲህ ወደለየለት ኦናነትና አስከፊ የጽልመት አዘቅት እንደሚያደርሰኝ አላወቅኩም ነበር፡፡ የማስበው ክብር ማለት ከንቱ መሆኑን ነበር፤ ግን ዘላለማዊ ቅጣት ነው፡፡››
ራሱን አረጋግቶ ተነስቶ እየተጎተተ፣ወደ መኖሪያ እልፍኙ ሲያዘግም ቁና ቁና እየተነፈሰ በድጋሚ እንዲህ አለ፡- ‹‹በእውኑ ይህንን ነው ሰዎች ሀብት ብለው የሚጠሩት? እኔስ የማገለግለውና የማመልከው ወርቅን ነውን? በምድር ላይ ስኖር ያለኝ መሻቴ ሁሉስ ይኸው ነው? ስለ ምን ነው ከዚህ ይልቅ ቅንጣት ታህል እርካታን ለማግኘት ያልነገድኩት? ማነው አንዲት ውብ የሀሳብ ዘለላ በወቄት ወርቅ የሚሸጥልኝ? በአንድ እፍኝ የከበረ ድንጋይ አንዲት ቅጽበት ፍቅርን የሚሰጠኝ? የወርቅ ማከማቻ ሳጥኔን የሌሎች ሰዎችን ልብ ማስተዋል እምችልበትን አይን የሚለውጠኝ?››
ከቅጽሩ መግቢያ ሲደርስ ፊቱን ወደ ከተማዋ ዞር አድርጎ አተኩሮ አየ፤ ነቢዩ ኤርሚያስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳስተዋለው፡፡ እጆቹን በሀዘን ከፍ አድርጎም ልብ በሚነካ አንደበት ጮክ ብሎ፤ ‹‹እናንት የዚህች ምስኪን ከተማ ሰዎች ሆይ፤ በጨለማ ውስጥ የምትዳክሩ፤ወደ ሰቆቃ የምትጣደፉ፤ ሀሰትን የምትሰብኩ፤ ‹በብልግና አነጋገር የምትሳደቡ›...እስከ መቼ በእንዲህ ያለ ጭፍንነት ውስጥ ትኖራላችሁ? ባንድነት ለመቆም ሲቻላችሁስ የህይወት ውበትዋን በማጉደፍ እስከ መቼ ልምላሜዋን ወደ በረሀነት በመለወጥ ትዘልቃላችሁ? ስለ ምንስ አንቆ የሚይዛችሁን ጠባብ መናኛ መጎናጸፊያ ትመርጣላችሁ፤ ሰፊው ሀር የተፈጥሮ ውበት አልባሳት ሳለላችሁ? የጥበብ ቀንዲሉ ብርሀን ደብዝዞ ጭል ጭል እያለ ነው፤ በአዲስ ላምባ ተሞልቶ የሚቀጣጠልበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የእውነተኛው ሀብት መገኛው ታዛ ተደርምሶ ወድቋል፤ ዳግም የሚቆምበትና በጽናት የሚጠበቅበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የድንቁርና ቀማኞቹ የሰላም ሀብታችሁን ነጥቀዋችኋል፤ መልሶ መረከቢያ ጊዜው አሁን ነው!››
በዚህ ቅጽበትም አንድ ምስኪን ድሀ ፊት ለፊቱ ቆሞ ምጽዋት ጥየቃ እጁን ዘረጋ-፡ ለማኙን እንዳየው ክናፍሮቹ ተላቀቁ፤ አይኖቹ በልስላሴ ፀዳል ፈኩ፤ ፊቱ በደግነት አንፀባረቀ፡፡ በሀይቁ ዳርቻ በሀዘን ያንጎራጎረለት ትናንቱ ሊዘይረው የመጣ ይመስል ነበር፡፡ የኔ ቢጤውን በፍቅር እቅፍ አድርጎ መዳፉን በወርቅ ሞላለት፤ በሩህሩህ ቅላፄ በሚርገበገብ ድምፁም እንዲህ አለው፡- ‹‹ነገም ተመልሰህ እንድትመጣ፤ ካንተም ጋር በስቃይ ውስጥ የሚዳክሩትን መሰሎችህን ይዘሃቸው ና፡፡ የተወሰደባችሁ ጥሪት ሁሉ ይመለስላችኋል፡፡››
ወደ መኖሪያ እልፍኙም ውስጥ እንዲህ እያለ ዘለቀ፡- ‹‹በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር መልካም ነው፤ ወርቅም ቢሆን፤ ግንዛቤን ማግኛ ይሆናልና። ገንዘብ እንደ በገና እና ክራር ነው፤ በምን መልኩ መጠቀም እንዳለበት የማያውቅ ሰው፤ ቅኝቱ የፈረሰን ዜማ ብቻ ይሆናል የሚሰማው፡፡ ገንዘብ እንደ ፍቅር ነው፤ ንፉጉን ሰው ቀስስስ እያለ አሰቃይቶ ይገድለዋል፤ ከሌሎች ጋር ተካፍሎ የሚበላውን  ደግ ሰው ብሩህ ህይወት ያጎናጽፈዋል፡፡
ምንጭ - YESTERDAY AND TODAY
from - A TEAR AND A SMILE
by - KHALIL  GIBRAN

Read 941 times