Sunday, 23 October 2016 00:00

ሥጋ በላቹ (ስላቃዊ ወግ)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 መዳፌ ካራን ያሰከነዳል? እሳት የላስኩ ሥጋ በላች ነኝ፡፡ የዕድሜዬን ገመድ ለማርዘም በሁለት መንታ ግብር ስማስን ነው የኖርኩት፡፡ ጭራን እየነሰነሱ አሳዳሪ ጌታ ፊት ነጥብ ማስቆጠር፣ ሲለጥቅ የሚጣል ዳረጎትን መቃረም፡፡ የአከራረሜ ምስጢሩ ከእዚህ ወዲያ የሚጎነጎን ሴራ የለውም፡፡ ገራገር ባልንጀሮቼ፣ ይህ ግብር ጠፍቷቸው፣ አፈር ተጭኗቸው ቀርተዋል።
ከእኔ ሥጋ መበለቺያ መደብር ገጥ ለገጥ፣ የመጽሐፍ አስቤዛ መሸመቺያ ደቃቃ ሱቅ ተሰይማለች፡፡ ጀንበር አዘቅዝቃ፣ ቀና ባለች ቁጥር ከሰው ዘር የተራቆተው ደጃፏ አፍ አውጥቶ ሲያዛጋ አላፊ አግዳሚውን ያባንናል፡፡ ማልዶ የእኔን እልፍኝ ከሚረግጠው ወፈ-ሰማይ ሸማች ሲሶውን እመኝላታለሁ፡፡ የአሳዳሪዋ ፀዳል ከጥላ-ቢስዋ ሱቅ ጋር አይገጥምም፡፡ የሰውነት አወቃቀሩ ለተመልካች ግራ ነው፡፡ ጭራሮ ገላው ላይ የተሰካው ገናና የራስ ቅል፣ የመሬት ቀለብ እንዳይሆን ያሳሳል፡፡ እንዲህ አንጀት እርቆት የተላበሰው ግርማ ሞገስ፣ ሙክት ገላን ማስከንዳቱን ስመለከት ደግሞ ሌላ መደነቅ ይወረኛል፡፡
የእኔ ሥጋ መበለቺያ እልፍኝ ትከሻውን የሚታከኩትን መደብሮች እንደ አሳ ነባሪ እየሰለቀጠ ዕለት በዕለት መወደልን ተክኖበታል፡፡ የጥላ ቢሷ ሱቅ ዕድገት ግን እያደር ቁልቁል ነው፡፡ እግር የጣለው ባተሌ ከሩቅ ሲያነጣጥርባት፣ ልክ በሻንጣ ለመሸከፍ የተሰናዳች ጓዝ መስላ ነው የምታጥበረብረው፡፡
 ከየት ነህ ለሚለኝ አጥብቆ ጠያቂ፣ አንደበቴ ልጉም ነው፡፡ ሥጋ መበለት እንጂ ዘር መብላት አልተካንኩም፡፡ ለሥጋ መጠቅለያ ከተሰናዳ ጋዜጣ ላይ የቃረምኩት ግሩም አባባል በልቤ እንደተጣፈ ቀርቷል፡፡ “እንኳን የበቀልኩበት ዘውግ፣ ጦቢያም ትጠበኛለች፡፡” ይላል፤ የጋዜጣው ፍሬ ነገር ካልተዘነጋኝ፡፡ ይህን በአእምሮዬ ለማመላለስ የቀለም እርከኔ ብዙም አልፈተነኝም፡፡ የቀለም ደረጃዬ ከስምንት ክፍል አልዘለለም፡፡ ሥጋ መበለቱን፣ ሥጋ ማደለቡን ማን ይወጣልኝ ብላችሁ ነው ጎበዝ፡፡
ቧልተኛው የመንደሯ ነዋሪ፣ የልኳንዳውን ብርንዶ መቁረጥ ቢሳነው ነገር እየከታተፈ በሆድ ይፍጀው ብሒል ቀን መቁጠር ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ በእርከን በተከፋፈሉት የልኳንዳው የሥጋ ፍሬዎች ላይ ጉንጩን ያለፋል፡፡ የልኳንዳው የሥጋ ፍረጃ ማዶ ለማዶ ነው፡፡ እነ ሻኛ፣ ነብሮ በኪራይ ሰብሳቢነት ሹመት  ሲቀቡ፣ የእነ ይመኙሻል የሠርክ ቀለብ ቅንጥብጣቢ ሥጋ ከአደገኛ ቦዘኔ ጎራ ተመድቧል። ይመኙሻል የመንደሯ ታዋቂ ዘማዊት ነች፡፡ ጭራሮ እግሮቿን ወዲህ ወዲያ እያመናጨረች ትመጣና ከፊት ለፊቴ እንደ ጅብራ ትገተራለች፡፡ የተበሳጩ የብር ኖቶችን በትና፣ አደገኛ ቦዘኔውን ሰብስባ እብስ ትላለች፡፡ አንድ ቀን እንደ ልማዴ ከሩቁ ውልብ እንዳለችብኝ፣ ካራዬን እያፋጨሁ የሰርክ ቀለቧን ሳሰናዳ፣
“አይ ዛሬ ምድባችንን ቀይረናል” አለችና ጢሜን አበረረችኝ
“ምን ተገኘ”
“በለስ ቀንቶኝ ኪራይ ሰብሳቢን አጠመድኩ..ቂቂቂቂቂቂቂቂቂ”
እኔም በደረቅ ሳቋ ተኮርኩሬ እየተርገፈገፍኩ ለታማኝ ደንበኛ “ሪዘርቭድ” ተብሎ ከተፈረጀው ሽንኩርት የሥጋ ዘር ጀባ አልኳት፡፡
አደገኛ ቦዘኔውን ከኪራይ ሰብሳቢውጋር በአንዲት ጣሪያ ሥር ቀይጬ የመንደሯን ነዋሪ ለሁለት አስርተ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ሳገለግል ከረምኩ። ጭራ እየነሰነሱ የአሳዳሪን ውዳሴና ግሳጼ ቀለብ ማድረግ ታከተኝ። እህል ውሃዬ አለቀ መሰለኝ፤ የሆነ ብረር ብረር የሚል አጓጉል ሹክሹክታ በጆሮ ግንዴ እያስተጋባ ወተወተኝ፡፡ ሹክሹክታውን በጄ ብዬ ድንገት በዕለተ ሰንበት፣ የልኳንዳውን ጌታ ገፍቼ እንደወጣሁ ቀረሁኝ፡፡
ከአምስት አመታት በኋላ
አሁን የመዳፌን ሚና ጫንቃዬ ተክቶታል፡፡ በሽክም ሥራ ግራ ቀኝ ስማስን እውልና ለዓይን ያዝ ሲያደርግ፣ ከራሴ ጋር ሸንጎ ልቀመጥ ካቲካላ ውስጥ እመሸጋለሁ፡፡ በእዚህ ሰዓት ጭራዬን የምወዘወዝለት አሳዳሪ የለኝም፡፡ ባይሆን የአሳዳሪዬን መንበር ተክቶ የሚወዘወዝኝ ሞልቶ የማይሞላው ጎተራዬ ነው። ሸክም እንደ ሥጋ መበለት ቀላል አይመሰላችሁ፡፡ ከጠሐይ፣ ከሐሩሩ ጋር ግብግብ መፍጠሩ ይበዛል። ይሁን ግድ የለም፤ አይከፋኝም፡፡ ለነጣነት የተከፈለ ዋጋ ነው፡፡
እንደ ወትሮው የናላዬን ጥም በካቲካላ ልቆርጥ ከመሸታ ቤት መሽጊያለሁ፡፡ መሸታ ቤቷ በሰው ብርካቴ ጭንቅ ጥብብ ብላለች፡፡ ተናዳፊ ስንኞችን እየደረደረ፣ ዜማውን የሚያንቆረቁረው አዝማሪ መንፈስን ይኮረኩራል፡፡
እህህ..እህህ..እህህ..እህህሀህሀ.እህህ.እህሀ
ደጉንም ክፉንም አይተን ገምተነው
ከዛሬ ደርሰናል ሁሉንም አልፈነው
ከዜማው ጋር በስሜት እየተናጥኩ ባለበት ቅጽበት ድንገት አንድ ክንድ የሚያህል ጭራሮ ሰው መሽታ ቤቷን ተወዳጀ፡፡ ዓይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡ አዎ መጽሐፍ ቸርቻሪው ነው፡፡ በእጁ ጭብጦ የምታህል ቦርሳ አንጠልጥሏል፡፡ በምልክት ጠራሁት፡፡
“ተዘናጋኹ እንዴ” አልኩ ጥላ ቢሷ ሱቅ በሻንጣው ውስጥ መሸከፍ አለመሸከፏን እየሰለልኩ፡፡  
 “እረ በጭራሽ”
 “ምን እግር ጣለህ?”
“ኽረ ተወኝ ወደጄ፤ በላተኛ በዛ፣ መጽሐፍ ገላጭ ጠፋ” አለና፤ ፊቱን ወደ ወለሉ አዘመመ፡፡
ለአፍታ ጽሞና ውስጥ ገባን፡፡ ተናግሮ አናጋሪው አቀንቃኝ፣ ኮርኳሪ ስንኞችን ከመደርደር አልቦዘነም።
እህህህ..እህህ..እህህ..እህህህህህ..እህህ..እህህ
እሳት ቢያዳፍኑት ሲጠጉት ይሞቃል
ሁሉን ችሎ ማለፍ መላ ይጠይቃል
ዜማው ከወሰደኝ ሰመመን እነቃ ዘንድ፣ የመጽሐፍ ቸርቻሪውን ጉሸማ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡
“እግርህን የተካው ሥጋ በላች እኮ ሞገደኛ ሆነ፡፡” አለ፤ ገጽታዬን እየሰለለ፡፡
“ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገን” ሐሜታው እንዲቀጥል ፈጣን መልስ ሰጠሁት፡፡
“ካራውን ሲያፋጭ ሸማቹን ለመበለት የሚያቆበቁብ ነው የሚመስለው”
“ለመሆኑ፣ የነውጠኛነቱ መንስኤ ምን ይሆን?” የሥጋ በላቹን ሥረ መሠረት ለማወቅ ዳዳሁ፡፡
“ለሥጋ ዘር የተለጠፈው ታፔላ ጤና አልሰጠውም”
“ኸረ ኤዲያ፤ወግ ጠራቂ በለው፤ይልቅ ሸማቹ ላይ ዓይንን ከማጉረጥረጥ፣ ጫንቃው ላይ የተከመረውን የልኳንዳ ጌታ ወግድ ብሎ አይገፋም”
ወጋችን እንደቆረፈደ የተረዳሁት መጽሐፍ ቸርቻሪው ድንገት ከተቀመጠበት እምር ብሎ ሲነሳ ነው፡፡
“ጦስህ እንዳይተርፈኝ ወዳጄ፡፡ ይህቺ መሸታ ቤት እኮ የጆሮ ጠቢዎች መናኸሪያ ናት፡፡ የልኳንዳው ጌታ መምጪያው ብዙ ነው” ይህን ተንፍሶ መሸታ ቤቷን ወደ ኋላ ገፍቶ ሲበር፣ የወሰደበት ቅጽበት ከዓይን ጥቅሻ ይቀድማል፡፡
ግራ ቀኙን አማተርኩ፡፡ መሸታ ቤቷ በጆሮ ሠራዊት ምርኮ ስር የወደቀች መሰለኝ፡፡ የምጠጣበት የካቲካላ ብልቃጥ፣ የተቀመጥኩበት በርጩማ፣ ኮማሪቷ፣ ቤቱ፣ ጣሪያው፣ግድግዳው --- ድንገተኛ ፍርሃት ውስጤን ሊደባበስኝ ሲከጅል፣
“ኸረ ወግድ፣ ደሞ ይሄም ኑሮ ተሁኖ ተሙቶ፣ ማንሽ ኮማሪት እስቲ አንድ መለኪያ እዚህ ጋ”  ብዬ እያንዣበበብኝ ያለውን ቆፈን ለማብረር ተውተረተርኩ፡፡ ተናግሮ አናጋሪው አዝማሪ፣ የማሳረጊያ ስንኞችን እየደረደረ ነው፡-
እህህህ..እህህ..እህህ..እህህህህህ..እህህ..እህህ
ግንዱ ቀን ካልጣለው ከስለት ያመልጣል፣
ድፍርስም ይጠራል ክረምትም ይወጣል፣
መላው የጠፋበት በሐሳብ ይበላል
እህህህ..እህህ..እህህ..እህህህህህ..እህህ..እህህ

Read 1112 times