Print this page
Sunday, 23 October 2016 00:00

“ህፃኑ ዶክተር”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(6 votes)

ጓደኞቼን ሳገኝ ደስ ይለኛል፡፡ የጥንት ጓደኞቹን ሳገኝ ደግሞ እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ያገኘኋቸው ጓደኞቼ ያገቡ መሆናቸውን ሲነግሩኝ ደስ ይለኛል። አግብተው ወልደው ከብደው፣ ከልጆቻቸው ጋር ሳገኛቸው ደግሞ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ግን ይህ የገለፅኩት የደስታ ስሜት የሚሰማኝ እውነተኛ ጓደኞቼን ሳገኝ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ ጓደኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ መጥተዋል፡፡ እንዲያውም ከእነአካቴው ሳይጠፉስ ይቀራሉ ብላችሁ ነው?
እውነተኛ ያልሆነውን ጓደኛዬን ባቡር ውስጥ አገኘሁት፡፡ ደስም አላለኝም … አልከፋኝምም፡፡ በቀስታ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ካንገት በላይ ማውራት ጀመርን፡፡ ልጅ ወልዷል፡፡ ልጁ በሁለታችንም መሀል ተቀመጠ፡፡ ከአባትየው ጋር ያስመዘገብነውን ድል እርስ በራሳችን ተጠያየቅን፤ ከተፎካከርን በኋላ ተሰለቻቸን፡፡ ምክኒያቱም የእውነተኛ ጓደኝነት በመሀላችን የለም፡፡ ዝም ተባባልን፡፡
ልጅየውን ማዋራት ጀመርኩኝ፡፡ በጣም ኮስታራ ልጅ ነው የወለደው፡፡ ስሙን ጠየኩት፡፡ “ዶክተር” አለኝ፡፡ ቀልድ መስሎኝ ሳቅሁኝ፡፡ ግን ማንም አብሮኝ ስላልሳቀ … ስሙ የቀልድ እንዳልሆነ ተረዳሁኝ፡፡
“ዶክተር ምትኩ” አለኝ ህፃኑ፡፡ ህፃን አይመስልም፡፡ ኮትና ሱሪ ነው የለበሰው፡፡ አዋቂ ሰው አጥሮ መሰለኝ፡፡ ኮስታራ ህፃን ከአዋቂ በላይ ያስፈራል፡፡ …
የውሸቱ ጓደኛዬ ስም ማን እንደነበር ለማስታወስ መጣር ጀመርኩኝ፡፡ … የሰፈራችን ጉረኛ ነበር ድሮ። አሁንም ልጅ ከወለደም በኋላ ከጉራ በሽታው ፈውስ ያገኘ አይመስልም፡፡ እንደ ሰጎን አንገቱን መዝዞ ተቀምጧል፡፡ ድሮ አባቱ የመንደራችን መርፌ ወጊ ነበሩ፡፡ ግማሽ እንደ ፈላስፋ ግማሽ እንደ ጠንቋይ የሚያረጋቸው ሰውዬ ናቸው፡፡ አሁን ይሙቱ ይኑሩ አላውቅም፡፡ … የጓደኛዬም የአባቱም ስም አሁን ተዘንግቶኛል፡፡
“አዋሽ ሰፈር ነበር የምትኖረው፤ የማን ልጅ ነህ?” አለኝ፤ ህፃኑ፡፡ ከጥያቄው በላይ የገረመኝ የፀጉሩ አጠቋቆር ነበር፡፡ … ሽበቱን በጥቁር ቀለም እንደደበቀ ሽማግሌ፤ የማጅራቱ ጥጋ ጥግ ተላጭቷል፡፡ የመሀል አናቱ ደግሞ እንደ ጎፈሬ ቆሞ ወደ ግንባሩ እንዲሾል ተደርጎ ተበጥሯል፡፡ በመበጠሩ እንደ እስቴዲየም ጥላ ፎቅ የመሰለ ጣራ ነገር ከግንባሩ በላይ ሰርቶ ተገትሯል፡፡ የኋላ ፀጉራቸውን አስረዝመው የግንባራቸውን ራሰ በራ ለመከለል እንደሚጣጣሩ ሰዎች አይነት፡፡
ትንሽ ልጅ፤ “የማን ልጅ ነህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ የመጀመሪያ ጊዜዬ በመሆኑ ደንግጬ መልስ ሰጠሁት፡፡ “የወይዘሮ አስቴር”
“አስቴር … የወፍጮ ቤቷ?” ሲለኝ በገንኩኝ፡፡ ቤታችን ወፍጮ ቤቱ አጠገብ በመሆኑ ምክኒያቱ፣ የቤተሰባችን አባል በሙሉ “የወፍጮ ቤቱ” የሚል ተቀፅላ ሲጨመርበት ድሮም አልወድም ነበር። አሁን ተቀፅላው ከዚህ ፈልፈላ ሲወጣ ግን በገንኩኝ። በኩርኩም ብደነቁለው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ … እንደ ድሮው ዘመን፡፡ የአሁኑ ልጆች ተለውጠዋል። እንክብካቤ በዝቶባቸዋል፡፡ ሽቅብ መናገር ጀምረዋል።
“አዎ የወፍጮ ቤቷ” አልኩት፤ “ቀስ ብለህ እደግ” በሚል ቅላፄ፡፡ ደግሞ የእጅ ሰዓት አድርጓል፤ ህፃኑ። የድሮ ውሃ ቆጣሪ የሚመስለው የብረት ሰዓት ነው። የልጁ አባት አንገቱን አስግጎ ፀጥ ብሏል፡፡ ልጁ ፊት መናገር የፈራ መሰለኝ፡፡ ልጆች ናቸው ዘንድሮ አባቶችን የሚያስፈራሩት፡፡ ልጁ ከአባቱ የበለጠ ጉራ አለበት፡፡
ሰው እንደ ደህና ነገር የጉራን ዘረ-መል ለልጅ ያወርሳል? አባቱስ ያለውን አወረሰ፤ ልጁ ተቀብሎ የመውረሱ ነገር ነው እጅግ የሚደንቀው፡፡ እኔ ለልጄ ምንም የማወርሰው ነገር የለኝም …፡፡ ይሄኛው ህፃን ከአባቱ ጉራን እንደወረሰው … ምናልባት እኔ ደግሞ ልጅ ቢኖረኝ … “መገረምን”  ይሆናል የማወርሰው። ምክኒያቱም እኔ አብዝቼ የምገረም ሰው ነኝ፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን የመገረም አቅሜ እጥፍ ድርብ ጨምሯል፡፡ ሁሉም ነገር ይገርመኛል። ለመገረም የማውለውን አቅሜን በሌላ ነገር ላይ ባውለው … አስገራሚ ተግባርን ማከናወን በቻልኩኝ ነበር፡፡ እና በዚህም ልጅ ተገረምኩ፡፡ በኩራቱ ተገረምኩኝ፡፡ እንደገና አባትየውን አንገቱን አስግጎ ከሰቀለበት የኩራት ከፍታ ስሙን ጠርቼ ላወርደው ስሞክር፣ ስሙን እንደማላውቀው ታወሰኝ፡፡ ምን ያህል ብጠላው ነው … በንፁህ አእምሮ … ሁሉንም ከሚይዝ የልጅነት  ትውስታ ማህደሬ ስሙን የሰረዝኩት? ስል ተገረምኩኝ፡፡ ተገርሜ ሳልጨርስ ልጅየው ስሜን ጠየቀኝ፡፡
“ተከስተ ድንኳኑ” አልኩት፡፡
“እናትህ ደህና ናት” አለኝ፡፡ ምናገባህ ‹ቆሻሻ› ብዬ ጆሮውን ብመዘልገው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን መገረሜ ቀደመኝ፡፡
“ደህና ናት!”
“አንተም እንደናትህ ነበርክ ልጅ ሆነህ … ብዙ ያምህ ነበር … ታስታውሳለህ?” አለኝ ህፃኑ። አሁን ከመገረምም አልፌ ግራ ተጋባሁኝ፡፡ አባቱ የሚነግረውን ወሬ በደንብ ያጠና ወሬኛ ልጅ ነው። ይኼኔ ፊደል አንብብ ቢባል ያለቅሳል፡፡ ጉራና ወሬኝነት …! … ተስፋ ያለው ትውልድ ተፈጥሯል አቦ! ….
“እንዴት አወቀ?... ነግረኸው ነው?” አልኩት የአንገት በላይ ጓደኛዬን … ስሙን የዘነጋሁትን … ጓደኛዬን”
“እኔ ምንም ነገር አልነገርኩትም …” ብሎ ጭጭ አለ፡፡
አሁን የእኔ ተራ መሆን አለበት … አልኩኝ ለራሴ። ልጅ ቀደም ቀደም እያለ ሲጨማለቅ፣ ልጅነቱን እንደ አዋቂ በመሆን አደብ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡
“እና ማሙሽ … ስንተኛ ክፍል ነህ?” አልኩት። በእጄ ጭንቅላቱን ይዤ እየደባበስኩት፡፡ መቼም ከአንደኛ ክፍል አያልፍም፡፡ ጭንቅላቱን በእጄ ስዳብሰው … እንደ ኮረሪማ የጠወለገ የራስ ቅል የነካሁ ስለመሰለኝ፣ ቶሎ እጄን ካስቀመጥኩበት አነሳሁኝ፡፡
ደግሞም እንኳን ያነሳሁኝ … ህፃኑ ዞሮ እንዴት በግልምጫ ቴስታ እንደመታኝ ሳይ ተሸማቅቄ የምገባበት ጠፋኝ፡፡
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው? … አንተ ነህ የእኔን የትምህርት ደረጃ የምትጠይቀኝ? … ምን ቆርጦህ አንተ እኔን ትጠይቀኛለህ! … እናንተስ ተምራችሁ የት ደረሳችሁ? … የአገር ሸክሞች አይደላችሁ እንዴ?! ደግሞስ የተማርኩትን አንተ ያስተማርከኝ ይመስል ትጠይቀኛለህ?! ወባ ትውልድ!...”
እንዲህ ነን የልጅ አስተዳደግ! እውነት ነው ለካ፤ ልጅን ቆንጥጠው ካላሳደጉት አደጋ ነው የሚባለው። አሳዳጊ የበደለው ልጅ ነው፡፡ አሳዳጊው ደግሞ … የድሮው የሰፈር የእድሜ እኩያዬ … ከጎኑ ተቀምጧል። ጭጭ ብሏል፡፡ እንዲያውም ተሸማቋል፡፡ … ድሮ የመንደር መርፌ ወጊው አባቱ (ለወስላታው ህፃን አያቱ) በጣም ሀይለኛ ሰው ነበሩ፡፡ ልጆቻቸውን የሚቀጡበት አሰቃቂ ዘዴ በሰፈሩ ስለሚወራ፣ መርፌ ወጊውን በጣም እንፈራቸው ነበር፡፡ እና ይኼ ጓደኛዬ ድሮ በአባቱ እጅ ነበር የሚሰቃየው … ዘንድሮ ደግሞ ራሱ በወለደውና ባቀበጠው ልጅ እየተሰቃየ ይገኛል .. ብዬ ደመደምኩኝ፡፡
ህፃኑ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቆሞ፣ አይኑን እያጉረጠረጠ ቁልቁል ተመለከተኝ፡፡ በአይበሉባው ጥፊ ሊያቀምሰኝ ቃጣብኝ፡፡ ህፃንን መጉዳት በህግም ያስጠይቀኛል ብዬ ስለፈራሁ እንጂ … አንገቱን እንደ ዶሮ ጠምዝዤ፣ አባቱ እግር ስር እጥለው ነበር። … ህፃንውና አባቱ የጉራና የወሬኝነት ዘረ - መል እንደተወራረሱ ሁሉ እኔ ደግሞ ምናልባት ከአባቴ … የመገረምና የትዕግስተኝነት ዘረ-መል ሳልወርስ አልቀረሁኝም፡፡
በትዕግስት ግልፍታዬን ውጬ ዝም አልኩ፡፡ ህፃኑ ግን አይኑን እያጉረጠረጠ መወራጨቱን አላቆም አለ፡፡ አባቱ አባብሎ በስንት መከራ አስቀመጠው፡፡
ሲያባብለው “አባ … አባ … አባዬ” ይለዋል። “አባዬ .. በቃ ስላላወቀ ነው .. አባ … ህመምህ ያገረሽብሃል … አባ ተወው በቃ …” ወዘተ፡፡
ልጆቻቸውን … “እማዬ … አባዬ … ሆዴ …” እያሉ ነው ትንሽ መሆናቸውን እንዲረሱት ያደረጓቸው፡፡ ሁሉም ነገር የአስተዳደግ ውጤት ነው - በመሰረቱ። ከአስተዳደግ ይበላሻል … ከአስተዳደግ ስርዓት ይዞ ያድጋል፡፡ … ከመጠን በላይ አለንጋ እየቀመሰ ያደገ ልጅ፣ ለካ ልፍስፍስ ነው የሚሆነው፡፡ … ሲልፈሰፈስ የወለደው ልጅ፣ ከታች ሆኖ ወደ ላይ በድጋሚ ይገርፈዋል፡፡
በስንት መከራ ህፃኑ - ተባብሎ ተቀመጠ። እንዴት እንደሚያስጠላ የገባው አይመስልም። እስካሁን ስለ ህፃኑና ስለ አባትየው በውስጤ ሳስብ የነበረውን በስድብ አጅቤ በተለይ አባትየው ላይ ላዝረከርክበት ስል … የውሸት ጓደኛዬ ተነሳና ፈንጠር ብሎ እንድከተለው ጠራኝ፡፡ ተከተልኩት። ዝግ ባለ ድምፅ ለሁለት ደቂቃ አወራኝ፡፡ ካወራኝ በኋላ … ድንገት ጉልበቴ ተብረከረከ፡፡ ዞሬ ህፃኑን ተመለከትኩት፡፡ እውነትም ትክክል ነው፡፡ እንደ ኮረሪማ የተጨማተረውን ጭንቅላት፣ ቅድም ስደባብስ ማወቅ ነበረብኝ፡፡
… እንዴት ማየት ተሳነኝ? … የጓደኛዬና የልጁ ግንኙነት ተገላቢጦሽ ነው፤ እውነትም፡፡ ልጅዬው ለካ አባትየው ነው … በሆነ ተአምር ተሸማቅቆ ልጅ አስመስሎት እንጂ … ራሱ የመንደራችን መርፌ ወጊ ነው ለካ - ህፃኑ፡፡ ስሙን ስጠይቀው ‹ዶክተር› ያለኝ፣ ለካ ሀኪምነቱን ለመግለፅ ነበር፡፡ እኔ ስሙ መስሉኝ ነበር፤ እንደ ቀልድ የወሰድኩት፡፡ … የትምህርት ደረጃውን ሳነሳበት ያልተደሰተው፣ የሀኪምነት ብቃቱ ድሮ ሲጠረጠርበት ይሰማው የነበረውን ፍርሀት ማንጸባረቁ ነበር ለካ!
ተመልሼ በህፃኑ እግር ላይ ወድቄ ይቅርታ ጠየኩኝ፡፡ ይቅርታውን ተቀበሉኝ - ጋሽ ዶክተር። እንደ ጥንቱ ዘመን፣ በመጥረጊያ እንጨት ሊያንጎራድዱኝ ይችሉ ነበር … እሳቸውንማ አድጌም እፈራቸዋለሁ፡፡ በዚያ ላይ መርፌ ቢወጉኝስ? … ወይንም በርበሬ ቢያጥኑኝስ? …

Read 3941 times