Sunday, 23 October 2016 00:00

የፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ዳናዎች! (ካለፈው የቀጠለ)

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 እምቡጡ አበባ እየፈካ … ውበት እየፈሰሰ … የተስፋ ጡንቻ እየፈረጠመ መጣ፡፡ … አይኖች እየተከፈቱ … ሕይወት በመዐዛዋ ንቦችን የምትጋብዝበት ቀን ደረሰ። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናውን የወሰደው ወጣቱ ሽብሩ ተድላ፤ ጥሩ ውጤት አምጥቶ አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋካሊቲ ተመደበ፡፡ አሁን ከተለያዩ ሥፍራዎች በተለያዩ መምህራን የተማሩ ተማሪዎች፣ መጋቢ ወንዞች በአንድ ሀይቅ ይጠራቀሙ ይመስል ዥንጉርጉር ማንነታቸውን ይዘው ተከተቱ፡፡ …
አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ፡- ረዳ ተክለሃይማኖት፣ መኮንን በለው፣ ኃይሌ ፊዳ፣ ተወልደ ገብረ እግዚአብሔርን ከመሳሰሉ ወጣቶች ጋር ቀላቀላቸው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በኋላ ሚኒስትር፣ ፕሮፌሰር፣ ዕውቅ ፖለቲከኛ ---- ለመሆን የበቁ ናቸው፡፡ ከሽብሩ ተድላ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ዩኒቨርሲቲ የገባም ሰው አለ፡፡ በዓሉ ግርማ፡፡
ፕሮፌሰር ሽብሩ በዓሉ ግርማን እንዲህ ይገልጹታል፡- “…ክፍሉን በፅዳት በመያዝ በጣም የታወቀ፣ ወለሉን በባና ቁራጭ በየቀኑ በሰም የሚፈትግ፣ እኛ የሱን ምሳሌነት ለመከተል የምንሞክር፤ እኔን በአንድ ዓመት የሚቀድመኝ፣ በዓሉ ግርማ ነበር፣ በዓሉ ግርማ መኝታ ቤቱም እሱም የፀዱ ነበሩ፡፡ …”
ሌላም ታዋቂ ሰው በታሪኩ ብቅ ይላል፣ ጌታቸው ቦሎዲያ፡፡ የወጣቱ ሽብሩ ተድላ መምህር ነበር። በዘመኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ባብዛኛው የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ በተለይ በሳይንስ ፋካሊቲ። “በመጀመሪያ ዓመት ፕሮፌሰር አለማየሁ ኃይሌና አቶ ዮሐንስ መንክር ብቻ ነበሩ፤ ከዚያ ዶክተር አሰፋ ተክሌና ጌታቸው ቦሎዲያ (በኋላ ዶክተር) ሁለተኛ ዓመት ስንገባ መጡ፡፡፡ አቶ ዓለሙ መላኩ የሚባል የሂሳብ አስተማሪ ነበር፤ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅና እኛ ዘንድ የሚያስተምር፣ ያን ጊዜ አልጀብራ የሚያስተምረንም አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ ነበር፣ ስሙ አቶ መሐመድ ሸሪፍ ይመስለኛል፣ … የማስታውሰው ሰዎች እነዚህ ነበሩ ….”
ፕሮፌሰር አለማየሁ ኃይሌ በአንድ ወቅት ስምንተኛ ክፍል ፈተና አርሞ፣ ወደ ፐርሰንታየል ለመለወጥ የተሻሉ ተማሪዎች ሲመረጡ፣ ተማሪ ሽብሩን መርጦ በገንዘብ አንበሽብሾት ነበር፤ እሱም ከወረደለት የበረከት ዝናብ ለጓደኞቹ አካፍቶ እንደነበር ፅፏል፡፡ ተማሪ ሽብሩ ተድላ የገንዘብ ዕድል ያለው ይመስላል፣ ሳንቲም በተማሪነቱም ያካፋለት ነበር፡፡ እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ፣ ረዳ ተክለሃይማኖትና እሱ በሳምንት አንድ ቀን ቆቃ ግድብ እየሄዱ፣ ለክፍል ኃላፊዎች ረዳት ሆነው እንዲሰሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ማደሪያቸው ራስ ሆቴል ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት እንደጠቀስኩት፤ የግለሰቦች ታሪክ መርገጫ ማህበረሰብንና ህብረተሰብን ሳይነካ እንደማይንቀሳቀስ ሁሉ የፕሮፌሰር ሽብሩም ታሪክ በሀገሪቱ ውስጥ ያለፉትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ነፋሳት ሁሉ ቀምሷል፡፡፡ የያኔው ተማሪ ሽብሩ ተድላ፣ የ1954 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ወጀብ ከተማዋንና ስርዓቱን ሲያናውጥ እዚያው አፍንጫው ስር ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደተለመደውም ተማሪዎች የተቃዋሚውን ክፍል ደግፈው ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡
የለውጡ አንቀሳቃሽ የትግል አናት ላይ ስሙ ፊጥ ያለው ግርማሜ ነዋይ፣ እንደ ሽብሩ ተድላ  የኮተቤ ተማሪ ነበር፡፡ ከዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ከዚያም ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ታዲያ እነ ሽብሩ ለመፈንቅለ መንግስቱ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ሲነሱ፣ አንዲት ተማሪ ያለችውን ደራሲው ያስታውሳሉ፡-
“በዚህ የሰልፍ መሰናዶ ሂደት ላይ ምግብ ቤት (ካፍቴሪያ)፣ ምግብ ከምናነሳበት የምግብ መደርደሪያ በላይ የተሰቀለ የጃንሆይ ፎቶግራፍ ነበረ፤ ያንን አውርደን ሰበርን፡፡ ያኔ የተከሰተ ትዝ የሚለኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ያን ድርጊት ያስተዋለች ጓደኛዬ፣ ዝማምነሽ አዳሙ፣ “ጃንሆይ የተመለሱ እንደሆን የት ልትገባ ነው” ብላ አስፈራራችኝ፡፡”
በርግጥ ያለችውም አልቀረ፤ ጃንሆይ ነገሩ ተቀልብሶ ወደ ዙፋናቸው ተመለሱ፡፡ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነበር ነገሩ!
በመፈንቅለ መንግስቱ ሰሞን ተማሪዎች ከገጠሟቸው ነገሮች አንዱ፣ የሀገራችን ሰዎች ውስጣዊ መልክ ዛሬም እንዳልተቀየረ የሚያሳይ ይመስለኛል። ነገሩ እንዲህ ነው፡- ተማሪዎች (ሽብሩን ጨምሮ) ከአራት ኪሎ ግቢ ለሰልፍ ሲወጡ፣ በሩ ላይ ጫማ ይጠርግ የነበረ ሊስትሮ እያጨበጨበ በቲፎዞነት ሸኝቷቸው ነበር፡፡ በኋላ ጃንሆይ ተመልሰው ነገሩ ሲገለበጥ፣ ያው ሊስትሮ፤ “የማላውቃችሁ መሰላችሁ፤ አንድ በአንድ ነው የማወጣችሁ” እያለ ተማሪዎችን ማስፈራራት ጀመረ። ታዲያ ይሄኔ ሽብሩ ምኑ ሞኝ ነው! እያጨበጨበ እንደሸኛቸው የሚያሳይ ፎቶግራፍ እንዳለው ነገረውና አፉን አስያዘው፡፡ የትግላችንም ሆነ የኛ ውስጣዊ መልክ ዥንጉርጉር አይደለም ትላላችሁ!
ፊተኞች ከኋላ፣ ኋለኞች ፊት ሲገለባበጡ፣
“ቀን ይመጣል” ማለት ከሰልፍ እየወጡ …
ማላገጥ ነው በሏት
ጆሮሽ ስለራሱ ሰርክ ቢሆን ባዳ፣
እስከ መቼ ልጅሽ … አንችን እየሸሸ … ይኑር ምድረ በዳ?
ብሎሻል በሉልኝ .. ይላል ገጣሚው አሌክስ አብርሃም ለሀገሩ!
በክቡር ዘበኛ አባላት ላይ የደረሰው ጭፍጨፋም (ገጽ 191) ይህንኑ ዥንጉርጉር መልካችንን የሚያሳይ ነው፡፡ የተሟሟቱለትን የሚገድል ጨካኝ ልብ ባለቤት መሆናችን ያሳዝነኛል፡፡  
የተማሪ ሽብሩ ተድላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዓለም፣ የአበባነት ጊዜ ሲያበቃ፣ አሁንም ወደ መሶቡ እንጀራ፣ ወደ መስኩ ፍሬ አልሄደም፡፡ ይልቅስ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ሊቨርፑል አቀና፡፡
በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ መጽሀፍ ውስጥ ያየሁዋቸው በርካታ በጎ ነገሮች አሉ፡፡ ለራስ ያለማዳላት፣ ነገሮችን ሁሉ ያለመደበቅና በራስ መተማመን! ይህ አይነቱ ብቃት እንኳ በእኛ ሽፍንፍን ባህል ለታጀለ ሀበሻ ቀርቶ በነፃ መንፈስ፣ በነፃነት አድገናል ለሚሉትም ምዕራባውያን ይፈታተናል። እውነት ለመናገር እኒህ ሰው ከተፈጥሮ ሳይንስ ምሁርነት ይልቅ ወፈፍ የሚያደርገው ነፃ የስነ ጽሑፍ ሰው አይነት ዝንባሌ አላቸው፡፡ ሌላው እጅግ የወደድኩላቸው ሀቀኝነታቸውን ነው፡፡ ፈተና የወደቁ ጊዜ፣ ትምህርት የሰለቻቸው ወቅት የነበራቸውን ስሜት ሁሉ አፍረጥርጠው ነግረውናል፡፡ … ድንቅ ሰው ናቸው!
ውጭ ሀገር እንደሄዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢራ ፍለጋ ብቻቸውን ይወጣሉ፡፡ አንድ ቤት ገብተው ቢራ አዘዙ፡፡ አስተናጋጁ፤ ምን ዓይነት ቢራ? ሲል ጠየቀ፡፡ እሳቸውም፤ “የእንግሊዝ ቢራ” አሉት። “እዚህ ቤት ያለው ሁሉ የእንግሊዝ ቢራ ነው፡፡ የትኛው የእንግሊዝ ቢራ?” ብሎ አፋጠጣቸው፡፡ ከዚያም በምልክት አንዱን ቢራ ጠቆሙና ተገላገሉ። ቢራቸውን አምጥቶ ከቀዳላቸው በኋላ ወንበር ቀይረው ይጠጡ ጀመር፡፡ አስተናጋጁ ተመልሶ መጣና፤ “እኛ ሀገር ቢራ የምንጠጣው እየከፈልን ነው” አላቸው፤ በሽሙጥ፡፡ ለካስ ሂሳብ ቅድሚያ ነበር፡፡
እኒህ ሁሉ ገጠመኞች ደስ ይላሉ፡፡ ያስተምራሉ። ያዝናናሉ፡፡
አንዴ ባቡር ውስጥ ከነጮች ጋር እሰጥ-አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ሽብሩና ጓደኞቻቸው በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት የተበደሉ መስሏቸው ከተነታረኩ በኋላ ነጮቹና ሀበሾች ተደራድረው በየተራ ለመቀመጥ ተወስኖ ነበር፡፡ ታዲያ አቶ ሽብሩ በባቡሩ ሲጋራ ወደ ሚጨስበት ኮሪደር ወጣ ብለው ሲያጤሱ፣ ኮሪደር ላይ ቆሞ እንደሳቸው የሚያጨስ እንግሊዛዊ ወጣት ጠጋ ብሎ፤ “እናንተ ሀበሾች መሆን አለባችሁ” ሲል ተናገረ፡፡ አቶ ሽብሩም፤ “በምን አወቅህ?” ብለው ጠየቁት፤ በመገረም፡፡ እርሱም፤ “ሌላ እንዲህ የሚደፍረን የለም” አላቸው። ያ እንግሊዛዊ ወጣት፣ አባቱ የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡
እንግዲህ አቶ ሽብሩ ተድላ ከዚህ በኋላ በሳይንስ ፋካሊቲ ከዶክተር አክሊሉ ለማ ጋር በቢልሃርዚያ ጥናት አብረው ሰርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም እያሉ ጓደኝነታቸው በጣም ያሥቀናል፡፡ እንደ ወንድም ይተያያሉ፣ ያንዱ ጉድፍ ሌላውን ያስጨንቀዋል። ለምሳሌ ኃይሌ ፊዳ ከፈረንሳይ ሀገር እጮኛውን ይዞ ሲመጣ አቶ ሽብሩ መኖሪያ ቤታቸውንና መኪናቸውን ጭምር ነበር የለቀቁለት!
ሦስቱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማለትም ሽብሩ ተድላ፣ እሸቱ ጮሌ፣ አበራ ዋቅጅራ አንድ ግቢ ውስጥ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር፡፡ የወር ባጀታቸውንም ያዋጣሉ፡፡ ይሁንና የመጀመሪያ ወር ኃላፊ የነበሩት አቶ ሽብሩ ተድላ፣ ወር ሊሞላ ሦስት ቀናት ሲቀሩ ሁሉም ነገር ተሟጠጠባቸው፡፡ ይሄኔ ኢኮኖሚስቱ እሸቱ ጮሌ፤ “የትል ሊቅ” ብሎ አሽሟጠጠ፡፡ ቀጣዮቹ ተረኞች ግን የባሱ ሆነው ተገኙ፡፡ “ከበሮ በሰው እጅ ያምር …” እንዲሉ! የእሸቱ ጮሌ በጀት በ19 ቀናት ተጠናቀቀ፡፡ ሌላው የምግብ አብሳያቸው ትዝታ ነው፡፡ ሰራተኛዋ ምጣድ ተሰብሮባት ከጎረቤት እየተዋሰች ትጋግር ኖሯል። በኋላ ግን የተዋሰችው ምጣድም ተሰበረባት፡፡ አቶ ሽብሩ ይህን አያውቁም፡፡ ከግቢ መኪናቸውን አስነስተው ሲወጡ፣ የቆሸሸ  ፎጣ ያገለደሙ አንዲት ባልቴት በስድብ አጣደፏቸው፡-“የእኛ ባለ መኪና፤ ምጣድ አትገዛም ኖሯል፤ ይህን ቆርቆሮ ከምትገዛ?” አሏቸው፡፡ ዱብ ዕዳ ነው! ለካስ ሰራተኛዋ የተዋሰችና የሰበረችው የባልቴቷን ምጣድ ነበር፡፡
የፕሮፌሰር ሽብሩ ግለ-ታሪክ በርካታ መልኮች ያሉት ነው፡፡ የእርሳቸውም ህይወትና ገጠመኝ ዥንጉርጉር ነው፡፡ በባዕድ ሀገር ሳይቀር ታስረዋል። በሀገር ውስጥ ብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተቀምጠው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። የዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩ ጊዜም በርካታ ተማሪዎችን በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ያኔ ለገሰ ዜናዊ) የሳይንስ ፋካሊቲ የኮንግረስ አባል በነበሩበት ጊዜ አማካሪያቸው ነበሩ፡፡  
ፕሮፌሰር ሽብሩ በዚያ ዘመን ላስተማሯቸው ተማሪዎች ትልቅ ክብር እንደነበራቸው ይገልፃሉ፡- “ለዚያ ዘመን ተማሪዎች ብዙ ትዝታ፣ ብዙ ከበሬታ አለኝ፣ በምንም መልኩ ይሁን በብዛት ለወገን የቆሙ፣ እኩልነትን፣ ያገር ብልፅግናን፣ መተሳሰብን፣ ፍትሀዊነትን፣ ነፃነትን ያለሙ ነበሩ፡፡ ለዚያ አቋማቸው ብዙዎቹ ብዙ፣ በጣም ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ …”
ፕሮፌሰሩ የሰዎችን መልካም ሥራ ማድነቅ ይወድዳሉ፡፡ የማንንም አይንቁም፣ ሁሉን ወደራሴ ልሰብስብ አይሉም፡፡ በዚህ ከብዙዎቻችን የተለዩና የተሻሉ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ገፅ 237 ላይ ስለ አንዱ መምህር ሲናገሩ፡- “ታደሰ ገብረእግዚአብሔር በትምህርት አሰጣጡ ከማናችንም በበለጠ ደረጃ በተማሪዎች ይወደድ እንደነበር እኔም ሌሎችም የትምህርት ክፍሉ መምህራን ተገንዝበን ነበር …” ይላሉ፡፡ ባልንጀራህ ካንተ እንደሚሻል ቁጠር የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ተግባራዊ ያደረጉ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ዓይነት አድናቆት ለዶ/ር ፍስሀ ገብረአብም ሸልመዋል፡፡ … ግሩም ነው!
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ዲን በነበሩ ጊዜ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በተለያዩ ሀገር አቀፍ ዘመቻዎችም ተሳትፈዋል፡፡ ዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ፣ የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ (አሥመራ) በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ላይ በተሰማሩበት ወቅት በዘመቻው ያልተሳተፉት መለስ ዜናዊ ከሁለት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን መጥተው ጠይቀዋቸዋል፡፡ ገፅ 334 ላይ እንዲህ ይገልጹታል፡- “አንድ ቀን በዕድገት በሕብረት ዘመቻ ጊዜ፣ ረፋድ ላይ ሶስት ሆነው ከአድዋ ሽሬ እንደ ሥላሴ ከተማ እኔ ዘንድ መጥተው ነበር፤ የማስታውሰው መለስ ዜናዊን ብቻ ነው፡፡ ሽሬ የመጡ ዕለት እንደሥላሴ ከከተማ ዳር አንድ ጠላ ቤት ተቀምጠን ስለ እነ መለስ ተክሌ መገደል ብዙ አወጋን፡፡ የተወያየነው በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር፡፡ እሱም በጣም አዝኖ፣ ተክዞ፣ እያነባ ነበር ስለ እነ መለሰ ተክሌ መገደል ያወጋን … በመጨረሻም ስንሰነባበት የማስታውሰው የነበረኝን የተጀመረ የዊንስተን ሲጃራ ፓኮ ሰጠሁት፤ቀደም ብሎም ተማሪ በነበረበት ወቅት አንዳንዴ ሲጃራ ከእኔ እየወሰደ ያጨስ ነበር፡፡ …”  ከኮሎኔል ፍስሀ ደስታ ጋር የነበራቸውንም ገጠመኝ ይተርካሉ፡፡ ሌላው ለኔ አስገራሚው ነገር የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጉዳይ ነው። ዛሬ የምናውቃቸው ፕሮፌሰር በዚህ መጽሐፍም ያው ራሳቸው ናቸው፡፡ ያኔም አያጎበድዱም፤ አያስመስሉም፡፡ ለዚያውም ከደርግ አባላት ጋር ሳይቀር ያደረጉት መፋጠጥ፤ ያውም ከኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባል ጋር! ሰውየው ትናንትም ዛሬም ጥያቄያቸው ነፃነትና ፍትህ ነው! … ሰው አንድ መልክ ኖሮት፣ እንዲህ ሲመሰከርለት ደግሞ ክብሩን ይጨምረዋል!
ወደ ትዳር ህይወታቸውም ስንመጣ፣ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ዛሬም ሚስታቸውን የሚያደንቁ ሥልጡንና የፍቅር ሰው ናቸው፡፡ ሚስታቸውን ብቻ ሳይሆን ህዝብንም ያደንቃሉ፤ ለምሳሌ ዕድገት በህብረት ዘምተውበት ስለነበረው የትግራይ እናቶች ፍቅርና ርህራሄ በእጅጉ አድንቀዋል፡፡ ፀሐፊ ያየውን ውጦ ዝም ከማለት ይልቅ እንዲህ ቢያደንቅ፣ ሃሳቡ እንዲያድግና እንዲጠነክር ስለሚረዳ፣ በሌሎች ውስጥ የሚበቅል መልካም ዘር ነው፡፡
በጥቅሉ ሳየው፤ “ከጉሬዛ ማርያም እስከ አዲስ አበባ” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ፤ እጅግ ውብና ተዐማኒነቱን የሚያጠነክሩ፣ ቀጥተኛ ማስረጃዎችንም ያካተተ መጽሐፍ ነው፡፡ እንደ ቅሬታ የማነሳው ነገር ቢኖር ርዕሱ ነው፣ ምክንያቱም ርዕሱ የመጽሐፉንና የሰውየውን አድማስ ከልሎታል፡፡ ስፋታቸውና ጉዟቸውም ከርዕሱ የራቀና የመጠቀ ነው! ሌላው የመጽሐፉ የመጨረሻ መዝጊያ ላይ ያሉት ሁለት አንቀፆች፣ የተቋጨውን ታሪክ እንደገና እንደመተርተር የሚቆጠር ነው፡፡ ባይኖር ይመረጥ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ (አንድ አምስት ቦታ ያህል) የስም ብዜት መፋለስ አይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ “ጠበብት” ሊባል የሚገባው “ጠበብቶች” ተብሏል፡፡
ከዚያ ውጭ ፀሐፊው ስለ ጎጃምና ኢትዮጵያ ፖለቲካ ያጠኑትን ጥናት፣ ነጥለው ሌላ መጽሐፍ ሊሰሩበት እንደሚችሉ ብጠቁም ደስ ይለኛል፡፡ … ስለ በላይ ዘለቀና ስለ ሌሎች መኳንንት የተተረከው ከሥነ-ቃሉ ጋር ሆኖ፣ ብቻውን ሌላ መጽሐፍ ይወጣዋል ብዬም አምናለሁ! በተረፈ ግን በእጅጉ የሚጥም፣ በርካታ እውነቶችን ያጨቀ፣ ለዛ ያለውና ሀቀኝነት የሚንፀባረቅበት ውብ መጽሐፍ ነውና ማንም ሰው ቢያነብበው፣ ራሱንና ሀገሩን ያይበታል። ረጅም ዕድሜ ለፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ!
(መጽሐፉን እንዳነብ የጋበዘኝን ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሀን በእጅጉ አመሰግነዋለሁ፡፡)    

Read 1405 times