Sunday, 23 October 2016 00:00

ተመራማሪዎች በጠፈር ላይ አዲስ “አገር” ሊመሰርቱ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የአገሪቱ ዜጎች ለመሆን አመልክተዋል
      ተቀማጭነቱ በቪየና የሆነው ኤሮስፔስ ኢንተርናሽናል ሪሰርች ሴንተር የጀመረውን አዲስ ፕሮጀክት የሚያስፈጽመው የጠፈር ተመራማሪዎች ቡድን፤ በጠፈር ላይ አስጋሪዳ የተባለች አዲስ አገር ሊመሰርት ማቀዱ ተገለጸ፡፡
የእቅዱ ባለቤቶች የሆኑት ሳይንቲስቶች፤አገሪቱ የሆነ ጊዜ ላይ በተመድ እውቅና እንደሚሰጣት ተስፋ አለን ቢሉም፣ አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በጠፈር ላይ የሚቀርብን የአንዲት አገር ብሄራዊ ሉአላዊነት ጥያቄ የሚከለክሉ አለማቀፍ ህጎችን ጠቅሰው፣የእቅዱን ተፈጻሚነት ተጠራጥረውታል፡፡
የአገሪቱ ዜጎች መሆን የሚፈልጉ ሰዎች በድረ-ገጽ አማካይነት ለፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት ማመልከቻ በማቅረብ መስፈርቱን ካሟሉ፣ ዜግነትና ፓስፖርት ይሰጣቸዋል ብለዋል፤ የፕሮጀክቱ አባልና በአውሮፓ የጠፈር ምርምር ማዕከል ለ15 አመታት ያገለገሉት ሌና ዲ ዋይን፡፡ ሳይንቲስቶቹ በጠፈር ላይ ሊመሰርቷት ላሰቧትና አዲስ የንግድና የሳይንስ ምርምር አማራጭ ትሆናለች ለሚሏት አገር አስጋሪዳ የሚል ስም ያወጡላት ሲሆን በአንድ አፈታሪክ ውስጥ በሰማይ ላይ ትገኛለች ተብሎ ከሚነገርላት አስጋሪዳ የተባለች አገር የተወሰደ ነው ተብሏል፡፡
ለአዲሲቱ አገር ብሄራዊ መዝሙርና ሰንደቅ አላማ ለማውጣት ውድድር እየተደረገ ነው ያለው ዘገባው፤ እስካሁን ድረስ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በድረ-ገጽ አማካይነት የአገሪቱ ዜጋ መሆን እንፈልጋለን በማለት ለፕሮጀክቱ ባለቤቶች ማመልከታቸውንም አስታውቋል፡፡

Read 2554 times