Sunday, 23 October 2016 00:00

በአፍጋኒስታን ጦርነት፤ በ9 ወራት 2ሺህ 600 ሰዎች ሞተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ከ370 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል

      በአፍጋኒስታን በተደረገው ጦርነት ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ2 ሺህ 600 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ5 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑትም የመቁስል አደጋ እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍጋኒስታን ድጋፍ ልኡክ ረቡዕ ዕለት ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በጦርነቶች ሳቢያ 639 የአገሪቱ ህጻናት ለሞት ተዳርገዋል፤ 1 ሺህ 822 ያህሉም የከፋ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ድርጅቱ ከ61 በመቶ በላይ ለሚሆነው ሰብዓዊ ጥፋት ተጠያቂ ያደረገው የመንግስቱን ተፋላሚ ቡድን ታሊባንን ሲሆን፣ ሁለቱ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች በዜጎች ላይ ጥፋት ከሚያስከትሉ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ባለፉት ሰባት አመታት በአገሪቱ በተደረጉ ጦርነቶች ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ45 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜናም ባለፉት 9 ወራት ብቻ በጎረቤት ፓኪስታን የስደት ኑሮን ሲገፉ የነበሩ ከ370 ሺህ በላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በመጠቆም፣ በፓኪስታን ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች እንደሚገኙም ተመድ ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ 52 ሺህ የሚሆኑ አፍጋኒስታናውያን ድንበር አቋርጠው ወደ አገራቸው መግባታቸውን ዘገባው ጠቅሶ፣ በሳምንት ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኛ ወደ አገሩ ሲገባ ባለፉት 7 አመታት ይሄ የመጀመሪያው ነው ብሏል፡፡

Read 976 times