Sunday, 30 October 2016 00:00

የቀድሞ የአንድነት አመራሮች አዲስ ፓርቲ እያወዛገበ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“የለፋንበትን ፓርቲ ተነጥቀናል” ቅሬታ አቅራቢዎች

    በቀድሞ የ“አንድነት” አመራር አባላት እንደተመሰረተ የሚነገረው ‹‹ነፃነት ለአንድነትና ለፍትህ›› ፓርቲ፤ ገና ከምርጫ ቦርድ እውቅና ሳያገኝ በአመራር አባላቱ መካከል ውዝግብ የተፈጠረ ሲሆን ቅሬታ አቅራቢዎች ‹‹ፓርቲውን በማንፈልጋቸው አካላት ተነጥቀናል›› ብለዋል፡፡፡ በፓርቲው የምስረታ አስተባባሪነት ከፍተኛ አስተዎፅኦ እንደነበራቸው የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢው፤ የአዲሱ ፓርቲ 9 የብሄራዊ ም/ቤት አባላት በቀድሞ አንድነት ውስጥ ለተፈጠረው የመከፋፈል ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች እንደሆኑ ጠቅሰው፣ የአዲሱን ፓርቲም አመራር በአቋራጭ በመያዝ፣ ‹‹ብዙ ያለፍንበትን ፓርቲ ነጥቀውናል›› ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ለአዲሱ ፓርቲ ስጋት ናቸው የሚሏቸው ግለሰቦች የመስራች አባልነት ፊርማ ሳይፈርሙ በተሳሰተ መንገድ ሆን ተብሎ የምርጫ አዋጁን በሚፃረር መልኩ የብሔራዊ ም/ቤት እጩ ሆነው እንዲመረጡ ተደርገዋል ብለዋል፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡
‹‹በዚህም በመስራች ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ም/ቤት ምርጫ የድምፅ ውጤት የተዛባና የተጭበረበረ ሆኗል፤ ይህም የፓርቲውን ህገ-ደንብ የጣሠና የምርጫ ህጉን የተፃረረ ነው›› ሲሉ ይከሳሉ፡፡
በአጠቃላይ ህግና ደንብ ሣይከበር ነው የካቢኔና የብሄራዊ ምርጫ የተካሄደው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እነዚህ ጉዳዮች እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ በፕሬዚዳንትነት ለተመረጡት ዶ/ር ንጋት አስፋው ብናቀርብም የተፈጠረውን ስህተት ለመፍታት ፍላጎት አላሣዩም ብለዋል፡፡
ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት የተደረገው ጥረትም በፕሬዚዳንቱና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በተመረጡት አባላት እምቢተኝነት ከሽፏል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ሌሎች አማራጮችን እንወስዳለን ብለዋል፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳት ዶ/ር ንጋት አስፋው በበኩላቸው፤ የቀረቡት ቅሬታዎች በራሱ በፓርቲው ሊፈታ የሚችል መሆኑን ጠቁመው፣ ጥያቄያቸውን ለመመለስና ግለሰቦቹን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ 9 ሰዎች የብሄራዊ ም/ቤቱን ህልውና ሊፈታተኑ አይችሉም ያሉት ዶ/ር ንጋት፤ መፍትሄው በህጋዊ መንገድ መነጋገር ነው፤ ቅሬታቸውን በህጋዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል፡፡

Read 1548 times