Sunday, 30 October 2016 00:00

አገር ለማፍረስ አስተማማኙ ዘዴ “የአካባቢ ጥበቃ” እና “አረንጓዴ ልማት”

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(6 votes)

• የከብት ብዛት በግማሽ የመቀነስ እቅድ፣የጤንነት ነው? ለዚያውም፣ ተራ እቅድአይደለም።
• በየቀኑ በቲቪ የሚወደስ በጣም ዝነኛ እቅድ ነው - “የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ!”ይሉታል።
• የከብት ብዛት የሚቀነሰው ለምንድነው?አላማችንን አየር ይበክላል ብሎናልኢቢሲ። Really?
• “ስራ አጥነትና ድህነት፣ አንገብጋቢ ችግር ነው” የሚለው የፓርላማ ንግግር በሳምንትተረሳ?
• “የአረንጓዴ ልማት” እቅድ ካልተለወጠ፣አገሪቱ ከድህነት ልትወጣ እንደማትችልይገልፃል - እንስሳት ሚኒስቴር አዲስ ጥናት።
• ከጎዳና ውሾች በሚተላለፍ በሽታ፣ 60 ሺ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ይሞታሉ። 40 ሺ ያህሉ ህፃናት ናቸው። ቢሆንም ግን…
• ህፃናትን ከሞት ለማዳን፣… የጎዳና ውሾችን መግደል ተገቢ አይደለም፤ ስነምግባርን ይጥሳል ተብለናል። ይሄስ የጤና ነው?

  “ከድህነት መላቀቅ፣ የህልውና ጉዳይ ነው”… ይህንን አባባል፣ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ ሺ ጊዜ እየደጋገሙ ሲናገሩ ሰምተናል። ኢኮኖሚው በፍጥነት ካላደገና የዜጎች ኑሮ በፍጥነት ካልተሻሻለ፤ አገሪቱ እንደምትበታተን ለማስረዳት፣ አደጋውን በመዘርዘር ለማስጠንቀቅ፣... ያልሞከሩት ዘዴ የለም። ያ ሁሉ ዝርዝርና ድግግሞሽ፣ አስፈላጊ ነው? ነገሩኮ ግልፅ ነው። ማለቴ...
በመዓት ውስብስብ ችግሮች የተተበተበች አገር፣ እንደምንም ከአደጋ አፋፍ የመዳን እድል ልታገኝ የምትችለው፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የዜጎች ኑሮ ከተሻሻለ ብቻ ነው። ይሄ ግልፅ አይደለም እንዴ? ይህንን ሃሳብ፣ ሺ ጊዜ እየደጋገሙ መናገርና ለማስረዳት መድከም አስፈላጊ መሆን አልነበረበትም። ነገር ግን... ለካ አስፈላጊ ነው። ለምን?
አሃ! ብዙ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችና ባለስልጣናት ጭምር፣ አስፈሪው አደጋ በግልፅ የሚታያቸው፣ አገሪቱ በረሃብ ስትወጠር ወይም የዜጎች ቅሬታ ጣሪያ ድረስ ተከማችቶ አገር ምድሩ በተቃውሞ ሲታመስ ብቻ ነው። ረሀቡ፣ በእርዳታ እህል ጋብ ካለ፤... ተቃውሞውና አመፁ ትንሽ ረገብ ካለ … በቃ፣ አደጋውን ይረሱታል። ፊት ለፊት አፍጥጦ እስኪመጣ ድረስ፣ ያንን የህልውና አደጋ ይዘነጉታል።
ለዚህም ነው፤ “ከድህነት መላቀቅ፣ የህልውና ጉዳይ ነው” በማለት እየደጋገሙ ለማስረዳት መሞከር የግድ ሆነው። አሳዛኙ ነገር እንደዚያ ሺ ጊዜ ተደጋግሞም፣ ውጤት ያስገኘ አይመስልም።
የ“ኢቢሲ” ስርጭትን መመልከት ትችላላችሁ። ከሁለት ሳምንት በፊት፣ አብዛኛው የኢቢሲ ወሬ፤ ምን ላይ ያተኮረ እንደነበረ ታስታውሳላችሁ። የወጣቶች ስራ አጥነት፣ የዜጎች የኑሮ ችግርና ቅሬታ፣ በፍጥነት መፍትሄ ካልተበጀለት፣ አገሪቱ ለትርምስ እንደምትዳረግ ነበር ኢቢሲ የሚገልፀው። የስራ እድል በብዛት እንዲፈጠርና የኑሮ ችግር እንዲቃለል ማድረግ፤ አንገብጋቢ የመንግስት ትኩረት ይሆናል ሲል ነበር - ኢቢሲ።
የአገሬው ትርምስ ትንሽ ረገብ ካለ በኋላስ?
የሰሞኑ የኢቢሲ ወሬ፣ ተቀይሯል። “የአካባቢ ጥበቃ”፣ “አረንጓዴ ልማት”፣ “የእንስሳት መብት” … የሚሉ የስካር ሃሳቦች የበዙበት ሆኗል።
እንግዲህ አስቡት። ትልቁ የግልገል ጊቤ ግድብ ለ10 ዓመታት የተጓተተው፤ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ባካሄዱት አለም አቀፍ የተቃውሞ ዘመቻ አማካኝነት ነው። የወንዞች “ተፈጥሯዊ” ፍሰት እንደወትሮው “ተጠብቆ” መቀጠል አለበት ባይ ናቸው። የአካባቢያችን ገፅታ ላይ፣ አንዳችም ለውጥ ከታየ፣ ትልቅ ሃጥያት ነው። ግድብ ገንብተን፣ አዲስ ሃይቅ መፍጠር የለብንም። የወንዞችን “ነባር” ፍሰት፣ ቅንጣት ሳትነኩ መጠበቅ አለባችሁ... ነው የሚሉት - የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች።
ይሄ “የአካባቢ ጥበቃ” ሃሳብ፣... እጅጉን የሰከረ ሃሳብ ከመሆኑ የተነሳ፣ እንዲሁ በሃሳብ ብቻ የሚቀር ሊመስላችሁ ይችላል። ግን በተግባር የግድብ ግንባታ ለአመታት እንዲጓተት ሲያደርግ አየን። ቀላል ኪሳራ አይደለም። ትልቁ የግልገል ጊቤ ግድብ፣ ለአራት ለአምስት ዓመት ሲጓተት፤ ኪሳራው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር (ከ20 ቢሊዮን ብር) በላይ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።
“በግድብ ምትክ የነፋስ ተርባይኖችን ተጠቀሙ” በሚለው የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ግፊት ሳቢያ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብዙ ኪሳራ ደርሷል። ለነፋስ ተርባይኖች ከወጣው ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ውስጥ፣ 10 ቢሊዮን ብሩ በከንቱ የባከነ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ወይም የአረንጓዴ ልማት ሰካራም ሀሳቦች፣ በተግባር ሲታዩ ይህን ይመስላሉ።
የ10 ቢሊዮን ብር፣... የ20 ቢሊዮን ብር ብክነት... በየትኛውም አገር፣ አሳፋሪ ብክነት ነው። ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ድሃ አገራት ግን፣ ብክነቱ የሕይወትና የሞት፣ የረሃብና የምግብ ጉዳይ እንደሆነ አትጠራጠሩ። ያ ሁሉ የባከነ ሃብት፣ ለሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ሊረዳ የሚችል ትልቅ ሀብት ነው። ሀብት ከባከነ ግን፣ የስራ እድል አይፈጠርም። ኑሮ አይሻሻልም። ቅሬታ እየበረከተ ሰላም ይጠፋል። የትርምስ አደጋ አፍጥጦ ይመጣል።
በሌላ አነጋገር፣ እንደቀላል ወንጀል አትቁጠሩት። አገርን አተራምሶ ለማፍረስና ህልውናዋን ለማጥፋት አስተማማኝ ዘዴ ነው - “የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት”።
እንዴ! አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ በዓመት... አንዴ ስጋ መብላት የሚቸገርባት ድሃ አገር ውስጥ እንደምንኖር አትርሱ። ከመቶ የአገራችን ገበሬዎች መካከል፣ 30ዎቹ የእርሻ በሬ እንደሌላቸውም አትዘንጉ። በዓመት አንዲት ብርጭቆ ወተት ለመቅመስ ያልቻሉ በርካታ ሚሊዮን ዜጎች ያሉባት አገር ናት። ታዲያ፣ በዚህች አገር ውስጥ፣ የከብቶችን ቁጥር ለመቀነስ እቅድ ሲወጣ ትርጉሙ ምንድነው? ተራ ብክነትና ተራ ኪሳራ አይደለም። ትርጉም፣ ከዚህ በላይ ይገዝፋል። በድህነት ወደ ህልውና አደጋ መንደርደር እንደማለት ነው።
ካላመናችሁ፣ በቅርቡ የወጣውን የራሱ የመንግስትን ጥናት መመልከት ትችላላችሁ። “አረንጓዴ ልማት” የተሰኘው አቅድ ካልተለወጠ፣ ከድህነት መውጣት አይቻልም Ethiopia livestock master plan የተሰኘው ሰነድ - ገፅ 116።
የአረንጓዴ ልማት እቅድ ግን፣ እስካሁን አልተለወጠም። የከብቶች ቁጥር፣ በ2002 ዓ.ም፣ 50 ሚሊዮን ገደማ ነበር። ዛሬ 57 ሚሊዮን አካባቢ ነው። እንዲያው፣ ከህዝብ ብዛት ጋር፣ የዛሬው የድህነት ኑሮ እንዳይባባስ ብቻ፣ በ15 ዓመታት ውስጥ፣ የከብቶች ቁጥር 90 ሚሊዮን መድረስ ይኖርበታል።
የአረንጓዴ ልማት እቅድ ውስጥ እንደተገለፀው ግን፣ የአገሪቱ የከብቶች ቁጥር፣ የዚህ ግማሽ መሆን አለበት። የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደረ፣ የከብቶች እበት የአለምን አየር ስለሚበክል፣ ሲያገሱ የሚወጡት ትንፋሽ ለአለም ሙቀት አስጊ ስለሆነ... የሚሉ የስካር ምክንያቶችን እየደራረበ፣ ምን ያህል ላሞች፣ ምን ያህል በሬዎች እንደሚቀነሱ ይዘረዝራል - ከገፅ 122 እስከ ገፅ 128።
45 ሚሊዮን ከብቶችን ለመቀነስ የወጣው እቅድ ተግባራዊ እንዲሆንም፣ ለመነሻ ያህል ከ2002 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ፣ በእቅዱ ተገልጿል። እስከ አምና ድረስ፣ 40 ቢሊዮን ብር እርዳታ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ለማግኘት ነበር የታቀደው። እንዴት ተቀልዷል! ጠብ ያለ እርዳታ የለም። እርዳታ ቢጎርፍ እንኳ፣ እቅዱ፣ የሰከረ እቅድ ነው።
እርዳታ አግበሰብሳለሁ በሚል ተስፋ፣ የከብቶችን ቁጥር ለመቀነስ መነሳት፣ ፈፅሞ የጤንነት ሊሆን አይችልም። ድህነትን የሚያባብስ የስካር እቅድ ነው። ይህም፣ የራሱ የመንግስት አዲስ የጥናት ሰነድ ሊክደው አልቻለም።       

Read 5926 times