Sunday, 30 October 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሃሳባቸው
ጆሮ አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የመፍትሄ
ሃሳቦቹ ቀውሱ እልባት እስኪያገኝ ድረስ መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት በመጀመር፣ሰላምና መረጋጋት ያሰፍናል ብለን
ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችንም በሂደት እንደሚጎለብት እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ለዛሬ
የፖለቲከኞችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን አስተያየት አጠናቅሯል፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ፣በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ
መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ክፍት ነው፡፡


“የአገዛዙ ሆደ ሰፊነት ወሳኝነት አለው”
አቤል ዓለማየሁ - (ጋዜጠኛ)

በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ድብርት የዋጠው ነው ብዬ አስባለሁ። የማይናገሩና ዝም እንዲሉ የተደረጉ ብዙኃን ስላሉ፣ ነገሮች ሁሉ ሰላም እንደሆኑ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ኃይልና ፍርሃት የመናገር ነፃነትን ሲገፉ፣ ዴሞክራሲ ተስፋዋ ይዳፈናል።
መንግሥት በአገራችን የተፈጠሩት ፖለቲካዊ ቀውሶችና ግጭቶች ከሥር መሠረታቸው እንዲወገዱ ከልብ የመነጨ ቁርጠኝነት ካለው፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ቀርቦ በጥልቀት ማነጋገር አለበት። ለዚህ የሚረዱም ስልጡን የአገራዊ ውይይት መድረኮች ያስፈልጋሉ። ማግለል፣ አሉታዊ ስያሜዎች እየሰጡ መግፋትና የተወሰኑ የራስ ሰዎችን ብቻ ለውይይት አምጥቶ፣ተወዳድሶ መለያየት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ‹‹አገሬን›› ብለው በየአደባባዩ የሚሞግቱ ጥቂት ሰዎችን መግፋት ሳይሆን ወደ ውይይት ጠረጴዛው ማምጣት ይገባል። በየእስር ቤቱ ያሉ፣ በየድረ ገጹና በውጪ ሚዲያዎች ላይ አፍ አስከፋች ሙግት የሚያቀርቡ በውጪ የሚኖሩ በርካታ ምሁራንም ከውይይት ጠረጴዛው አንድ ጫፍ ላይ ቦታ ሰጥቶ ማነጋገር ተገቢ ነው፡፡
ለውይይት የሚረዱ ፈንጣቂ ሀሳቦችን በማንሸራሸሩ በኩል መገናኛ ብዙሐን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በአሁን ሰዓት ነፃ ፕሬስ ተዳፍኗል። ያሉት የኅትመት ውጤቶች ቁጥር ከአንድ ጣት አንጓ የሚበልጥ አይደለም። ሚዲያው ጠፍቶ ይቅርና ኖሮ እንኳን ሀሳባቸውን በነፃነት የሚያንሸራሽሩ ምሁራንና ልሒቃንን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። በአዲስ አበባ ከምናገኛቸው ብቁ ጋዜጠኞች ይልቅ ናይሮቢና ዋሽንግተን ላይ ተሰደው የከተሙ ጋዜጠኞች ቁጥር ይልቃል። መንግሥት ከራሱ በሚጀምር ተነሳሽነት ፕሬስ እንዲያብብ ጠንካራ ሥራ ማከናወን አለበት። ያለ ሀሳብ፣ ያለ ውይይት፣ ያለ ሙግት፣ ያለ ትችት ያሉብንን ቁልል አገራዊ ችግሮች ንደን ልናቃልል አንችልም። ለዚህ ደግሞ የአገዛዙ ሆደ ሰፊነት ወሳኝነት አለው። ሀሳብ በውስጥ ሲታመቅ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎች እንደተፈጠረው ዓይነት ለግጭት መንስዔ ስለሚሆን፣ ሀሳብ ማብላያ መድረኮች ሊኖሩ ይገባል።
አገራችን ያለባት የአይዲዮሎጂ ችግር ይሁን፣ የሥርዓተ መንግሥት ቅርዕ መፋለስ፤በውይይት ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ውይይት ማመቻቸት መሰልጠን ነው። ሕዝቡ የሚመጥነው የአስተዳደር ሥርዓት ግንባታ እንዲኖርም ትልቅ ሚና ይጫወታል። ብዙዎች ‹‹በአፋጣኝ የሽግግር መንግሥት ሊቋቋም ይገባል›› ሲሉ እሰማለሁ። በሀሳቡ ላይ ቅራኔ ባይኖረኝም ተቃዋሚ ጎራው ለማስገደድና ለመደራደር የሚያበቃ አቅም ሳይገነባ፣ ኢሕአዴግ. ጥያቄውን ይቀበላል ብሎ ማሰቡ ፍጹም የዋህነት ይመስለኛል።


=================================

“ሁሉን አቀፍ ውይይት ያስፈልጋል”

አቶ ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ)


በአገራችን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ህዝብ በአገዛዙ ሥርዓት ላይ በከፋ ደረጃ ቅሬታ እንዳለው የሚያመላክት ነው፡፡ ገዢዉ መንግሥት በአገራችን የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሸፋፍኖ ለማለፍ ያልተቻለው ከመሆኑም በላይ፣ ተቃውሞ መኖሩን አምኖ ተቀብሎአል፡፡ ነገር ግን የተቃውሞው ምክንያት አገዛዙ እንደሚለው፤ “የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡” ለማለት በግሌ እቸገራለሁ፡፡ እኔ ለህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቀሴው ትክክለኛው ምክንያት፣ህዝባዊ ቅቡልነት ያለው የመንግሥት አስተዳደር እጦት ያመጣው ነው! ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ዋናው ምክንያት ለህዝብ የቆመ፣ ከህዝብ የተመረጠ የመንግሥት አስተዳደር መሻት እንደሆነ በግሌ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ የኑሮ ሸክሙ የከበደው፣የእለት እንጀራ ከስንት አንዴ በእድል የሚመገብ ህዝብ በበዛበት አገር፣ የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው ጥያቄ ነው፤ ማለት ግራ ያጋባል። ዛሬ ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተነሳው ተቃውሞ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፣የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር በማድረግ፣ የዜጎች ጥያቄ እንዲመለስ በተለያየ መልኩ ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ ለሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ በአገዛዙ በኩል ይሰጥ የነበረው ምላሽ ተገቢ ባለመሆኑ ችግሩ  ሊከሰት ችሎአል፡፡ ይህም እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር፡፡
ዛሬ ማን ምን መስማትና ማየት እንዳለበት በአዋጅ የሚደነገግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።  ህዝባዊ ተቃውሞ መኖሩን አምኖ የተቃውሞ ምክንያቱ ደግሞ “የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ” ነው፡፡ በማለት ያመነ መንግስት፣ በአስቸኳይ አዋጅ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት መሞከሩ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ የአገዛዙ ስርዓት አሁንም ቢሆን እየሄደበት ያለው መንገድ ነገሮችን ይበልጥ የሚያወሳስብ እንጂ ወደ-መፍትሔ የሚያመራ አይደለም፡፡ የመንግሥት ምላሽ ከህዝቡ ጥያቄ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግሁ ነው የሚለው መንግሥት፣ እንደ መፍትሔ የተጠቀመው የዜጎች መሰረታዊ መብት በአዋጅ መገደብ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በፍፁም ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ሊሆን አይችልም ፡፡
አሁን በአገራችን የሚታየው ችግር ከስርዓት አቅም በላይ ነው፡፡ “ላልተካደ ጉዳይ” ማስረጃ ማቅረብ በህግ አስገዳጅ አይደለም እንደሚባለው፣ገዢው መንግሥት ተቃውሞውን ለመቋቋም ከመደበኛ ህግ አልፎ የተለየ አዋጅ ለማውጣት ተገድዷል።   ይህም የችግሩን አሳሳቢነት አመላካች ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔ የሚገኘው ግን በችግሩ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በቅድሚያ የጋራ ግንዛቤ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ሁሉን አቀፍ ውይይት ሊካሄድ ይገባል፡፡ መፍትሔው ህዝብ ላነሳው መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ሁሉን አሳታፊ ውይይት በአስቸኳይ መካሄድ አለበት፡፡ አሁን ሥልጣን ይዞ የሚገኘው አካል ከማንም በላይ ለዚህ ጉዳይ ተባባሪ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት እንዲረዳ፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣በትጥቅ ትግል ተሳታፊ የሆኑ (የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ)፣ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የህዝብ እንደራሴዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው በሙሉ የሚገኙበት አስቸኳይ የመፍትሔ ሃሳብ የሚመነጭበትና ስምምነት ላይ የሚደረስበት ውይይት  መካሄድ አለበት፡፡ የውይይቱ ቅድመ ሁኔታና የመወያያ ነጥቦች እንዲሁም ተዛማች ነገሮች የዚሁ አካል ሊሆን ይገባል የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡
(ይህ አስተያየት በግል የቀረበ እንጂ የፓርቲ አቋም የሚመለከት አይደለም)

=================================


“በሃሳብ የበላይነት መታመን አለበት”  ኤልያስ ገብሩ - (ጋዜጠኛ)

መንግስትና ህዝብ የሚገናኙባቸው መንገዶች መታፈናቸው ነው ችግር የፈጠረው፡፡ ቀደም ሲል ተቃዋሚዎች ፓርላማ ገብተው ይብዛም ይነስም የህዝቡን ድምፅ ያስተጋቡ ነበር፡፡ ከ1997 ዓ.ም በፊት ሚዲያዎችም በርካታ ነበሩ፡፡ ከዚያም በኋላ በምክንያታዊነት መንግስትን የሚተቹ ሚዲያዎች በጥቂቱም ቢሆን ተፈጥረው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ዛሬ የሉም፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ ሲወጣ፤ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ፣ ፖለቲከኞችም በሽብር ሲከሰሱ … ብዙ ድምጾች ተዳፍነዋል፡፡ ሚዲያዎች በጅምላ የተከሠሡበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ራሱን ለምርጫ ሲያዘጋጅ የነበረው ትልቁ “አንድነት” ፓርቲም እንዲበተን ተደርጓል፡፡ ጠንከር ያሉ ሚዲያዎችና የህዝብ ውክልናን በጥቂቱም ቢሆን ያገኙ ፓርቲዎች እንዲህ ሲሆኑ ህዝብ በራሱ ለመተንፈስ ወደ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ሰው ሃሳቡን የሚገልፀው ከተፈጥሮ የተቸረው ስጦታም ስለሆነ ጭምር ነው፡፡
ህዝብ በጨዋነት ነበር ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ የነበረው፡፡ ግን የመንግስት ምላሽ ይሄን የሚመጥን አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ ስብሰባዎችን ሲያዘጋጅ የነበረው ራሱን በሚጠቅመው መንገድ ብቻ ነው። ስብሰባዎቹ ላይ የተለየ ሃሳብ ያንፀባረቀ ብዙ ችግር ይደርስበታል፡፡ እኔ በአጠቃላይ ይሄ ችግር ህገ መንግስት ያለ ማክበር ውጤት ነው እላለሁ። ኢህአዴግ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሰፊውን ህዝብ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መንቀሳቀስ አለበት። ከ25 አመት በኋላም ዲሞክራሲ ገና ሂደት ነው ልንባል አይገባንም፡፡
አሁን ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጭ ስለወጣ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው፡፡ ይህ አዋጅ ውጤት ያመጣል አያመጣም የሚለው በሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ እንደኔ ግን በዚህ ሁኔታ አልነበረም አዋጁ መታወጅ ያለበት፡፡ ኢህአዴግ በቅጡ ህገ መንግስቱን ማክበር አለበት፡፡ ህገ መንግስቱ ከተከበረ የሃሣብ የበላይነት ያብባል፡፡ በሃሳብ የበላይነት መታመን አለበት፡፡ ሰው በሰላማዊ መንገድ ነው ወደ አደባባይ እየወጣ የነበረው፡፡ ይህ ሰላማዊነቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ሚዲዎች በሙሉ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡


=============================


“ህዝብ የሚተማመንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት”
ነብዩ ኃይሉ (የቀድሞ የ”አዲስ ፕሬስ” ዋና አዘጋጅ)


የችግሮች ሁሉ መነሻ ምክንያት የኢህአዴግ ሁሉን ነገር የመቆጣጠር ባህሪ ነው፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ አንፃራዊ በሚባል መልኩ የፕሬስ፣ የሲቪክ ተቋማት … የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ በአብዛኛው በ97 ተፈጥሮ የነበረውን መነሳሳት ለማዳከም ሲባል ብዙ ነገሮች ተዘጉ፤ ብዙ አፋኝ ህጎች ወጡ፡፡ የሽብርተኝነት አዋጁ፣ የፕሬስ ህጉ፣ የፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ የመሳሰሉት ወጥተው በፊት ነፃ የሚመስሉ ነገሮች በሙሉ ታፍነዋል፡፡ በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ያለመመለስ ችግር ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች መፍትሄ አግኝተው ሊስተካከሉ የሚችሉበት ዕድልም በገዳቢ አዋጆች የተዘጋ ሆነ፡፡ ለምሳሌ በዚህ ረገድ የሲቪክ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የሚዲያዎች ሚና ቀላል አይሆንም ነበር፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህ መንገዶች ሲዘጉ ቅሬታውን የሚያቀርብበት አማራጭ አጥቶ በራሱ መንገድ ለማቅረብ ተገደደ፡፡ ይሄው ነው በሀገሪቱ የተከሰተው፡፡  
አሁን ችግሩ ተባብሶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ተደርሷል፡፡ እርግጥ ነው ችግሩ አስቸኳይ አዋጅ ሊያሳውጅም ላያሳውጅም ይችላል። ይሄን የሚገመግሙት ቦታው ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የተቀመጡት አብዛኞቹ ገደቦች በፊትም ነበሩ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ ፓርቲዎች ለረጅም ጊዜ ስብሰባና ሰልፍ ሲጠይቁ ተፈቅዶላቸው አያውቅም፡፡ አሁን ይሄ አዲስ እገዳ አይደለም፡፡
በግሌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መፍትሄው የተፈጠሩ ችግሮችን አጥርቶ፣ የጥፋቱ መንስኤ ናቸው የተባሉ የመንግስት ባለስልጣናትንም ሆነ ሌሎችን ማጣራትና ለህግ ማቅረብ ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ እርምጃዎችም መወሰድ አለባቸው፡፡ ህዝብን በሚገባ ሊያደራጁ የሚችሉ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንደገና ሊመሰረቱ ይገባል፡፡ አሁን ያሉት ህዝብን ይወክላሉ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም እውቀቱና ፍላጎቱ ያላቸው ግለሰቦች ከመድረኩ በተለያየ መንገድ ተገፍተው ወጥተዋል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የጠቀሱት የምርጫ ስርአት ቢሻሻልም ብዙ ነገሮችን ማስተካከል የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ እንደ አንድ ባለድርሻ ሆኖ ምሁራንን፣ የሲቪክ ተቋማትን ያካተቱ ውይይቶች ቢደረጉ ጥሩ ነው። ለጠፋው የሰው ህይወትና በማይመለከታቸው ሁኔታ ንብረታቸው ለወደመ ሁሉ ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ የማይተካ የሰው ህይወትም ያለፈበት ስለሆነ እርቅ ወርዶ፣ ህዝብ የሚተማመንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

Read 1887 times