Sunday, 30 October 2016 00:00

‹‹መድረክ ምርጫ ቢያሸንፍ ብቻውን መንግስት የማቋቋም አላማ የለውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

· ይህቺ ሃገር በመበታተን ስጋት ላይ ወድቃለች የሚለውን አልቀበለውም
· ኢህአዴግ መደራደር ያለበት ከዋነኛው ተቃዋሚ ከ”መድረክ” ጋር ነው
· መንግስት በተለወጠ ቁጥር ህገ-መንግስቱን መቀየር መቀጠል የለበትም
· የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡ እዚህ ያለነውን ኃይሎች ዋጋ አሳጥቶናል

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ በአንጋፋነት ከሚጠቀሱት ተርታ የሚሰለፉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ከፖለቲካ የሚለያቸው የወዲያኛው ዓለም ብቻ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ የገለጹ ሲሆን
ላለፉት 25 ዓመታት ያሳለፉት የፖለቲካ ህይወትም ስኬታማ ነው ብለው እንደሚያምኑ  ናግረዋል፡፡ ፕ/ር በየነ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በፖለቲካ ቀውሱና መፍትሄው ንዲሁም በመድረክና ኢህአዴግ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


በሃገሪቱ በተፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እንግዲህ በህዝቡ ውስጥ ያለው ብሶት ለረጅም ጊዜ በተለያየ መንገድ ሲንፀባረቅ የኖረ ነው፡፡ በየጊዜው መንግስት እየወሰደው ያለው እርምጃም ጠንከር እያለ መምጣቱም አዲስ  አይሆንም፡፡ የ2007 ምርጫም እንዲህ ያሉ ግጭቶች ብቅ ብቅ ማለት በጀመሩበት ወቅት ነው የተካሄደው፡፡ እኛ በምንሰጣቸው መግለጫዎች ሁሉ፤ ‹‹መንግስት በህጋዊነት ከተደራጁ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር አለበት፤ ብዙ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ፤ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ሂደቱ ላይ መነጋገር ይኖርብናል፤ ከህዝብ ጋር በምርጫ ስርዓቱ ላይ መተማመን ላይ መድረስ ያስፈልጋል›› ስንል ነው የከረምነው። ህዝቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ደግሞ መመለስ ያለባቸው በዴሞክራሲያዊ አግባብ መሆን እንዳለበት ስንናገር ቆይተናል፡፡ በሌላ በኩል እኛ ህጋዊ ፓርቲዎች ደግሞ ይሄን የህዝቡን ምሬት ለመምራት ወይም ለማስተጋባት እንዳንችል ተደርገናል፡፡ ይሄ ነገር ከኛም ከመንግስትም ውጭ እስኪወጣ ድረስ መገፋት የለበትም በሚል ሠላማዊ ሠልፎችን ጭምር እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሳይቀር ደጋግመን ጠይቀናል፡፡ ሁሌም የሚሰጠን መልስ፣ “ለሠልፍ ጥያቄያችሁ እውቅና አልሰጠነውም” የሚል ነበር፡፡ ያንን ደግሞ ተጋፍተን እንሂድ ብንል፣ ህግ መጣስና ወዳልተገባ ግጭት መሄድ ስለሚሆን፣ እኛ በወቅቱ ያንን አልመረጥንም፡፡ ደጋግመን ‹‹መንግስት ሠላማዊ ሰልፍ ከለከለን፣ ምህዳሩን አጠበበብን፤ አማራጮችን ለህዝብ እንዳናቀርብ ተደረግን” እያልን መግለጫ ብቻ በመስጠት ነው የኖርነው፡፡
 ይሄ በሆነበት ሁኔታ ሌሎች ሃይሎች ከህዝብ ጋር የሚገናኙበት መስመሮች ነበሩ፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ፣ እነዚህ ሃይሎች መንግስትም ሊቆጣጠር ያልቻለውን፣ እኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም መምራት ያልቻልንበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡ ያየነው ሂደትና ውጤት ይሄ ነው፡፡ ህዝቡ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከኛ ከ‹‹መድረክ›› ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም፡፡ የእኛም ድርሻ ወርዶ ወርዶ እንደ ማንም እንዳልተደራጀ ዜጋ፣ ቆመን ማየትና ሪፖርት መስማት ብቻ ነው የሆነው፡፡
አሁን እንግዲህ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ምን ውጤት ይገኛል ብለው ይጠብቃሉ?
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምልክቱን ነው የሚያክመው እንጂ በሽታውን እያከመ ያለ አይመስለኝም፡፡ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የ2007 ምርጫ ነው፡፡ ህዝብ በዚህ ምርጫ ተናዷል። እነሱም ደስተኞች አልነበርንም እያሉ ነው፡፡ ህዝቡ የሚደግፋቸው ፓርቲዎች ስልጣን እንኳን ባይዙ በሚፈለገው መጠን በፓርላማው ይወከላሉ የሚል ተስፋ ሰንቆ ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ እኛም እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ወርደን ተንቀሳቅሰን ነበር። በምርጫው ተሳተፉ፣ በቁርጠኝነት ታገሉ ብለን ህዝብን ቀስቅሰናል፡፡ በመጨረሻ ግን ከዳር ዳር ተንቀሳቅሰን ያደራጀነው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ፣ ከምርጫው የጠበቀውን ውጤት አላገኘም። ይሄኔ ለተቃዋሚዎችም ድጋፍ ሰጥተን የማንደመጥ ከሆነ ብሎ፣ እኛ ላይ ተስፋ ማድረጉን ትቶ፣ በራሱ ወደ አደባባይ እንደወጣ አድርገን ነው የምናየው፡፡ መፍትሄውም እንግዲህ እነዚህን ችግሮች በአግባቡ ማከም ነው፡፡ በቀጣዩ ምርጫም የህዝቡ ድምፅ በአግባቡ ተቆጥሮ፣ ተስፋ ሰጪ ውጤት የሚገኝበትና ህዝቡ ተስፋ የሚሰንቅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የተስፋ ምልክቶች መታየት አለባቸው፡፡ ቀጣዩን ጊዜ በዚህ መንገድ ነው የማስበው፡፡  
በሃገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች በአግባቡ ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ውጭ ሃገር ያሉ ተቃዋሚ ሃይሎችና የፖለቲካ ታጋዮች ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል… የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ እርስዎ በዚህ አስተያየት ይስማማሉ?
እንግዲህ እዚህ ሃገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች የገቡትን የሠላማዊነት ቃል አክብረው፣ ሃገሪቱ ውስጥ ባለው የህግ ማዕቀፍና ተጨባጭ ሁኔታ ስር ነው መንቀሣቀስ የሚችሉት፡፡ ከዚህ አልፈን እንሂድ ማለት ትርፉ ያልተፈለገ ግጭት ነው፡፡ እኛ የማንፈልገውን ግጭት ደግሞ አሁን አይተናል፡፡ ውጤቱ ምንድን ነው የሆነው? እንደኔ የዜሮ ድምር ውጤት ነው የሆነው፡፡
ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፈለ፡፡ እቺን መልዕክት ለማስተላለፍ ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት መክፈል አይገባም፡፡ በህይወትም በንብረትም ይሄን ያህል ዋጋ መከፈል አልነበረበትም፡፡ እኔ በግሌ እንደማምነው፣ ከጥቅሙ ኪሣራው ነው የበዛው፡፡ በሃገሪቱም ደረጃ ሆነ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ በሚሰጡት ደረጃ ይሄን ያህል ጥቅም የተገኘበትን ሁኔታ እያየሁ አይደለም። ውጭ ያሉት ተቃዋሚዎች ድብልቅ ናቸው፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚጮኸውን ብቻ ነው ሚዲያው የሚሠማው፡፡ በዚህ ስርአት ላይ ጫና ለመፍጠር ግፋ ቢል እስከ እምቢታ ድረስ ሊኬድ ይችላል እንጂ ዱላ ወርውሮ፣ ጥይት ተኩሶ፣ ብዙ ሕይወት እስከ መቀጠፍ ደረጃ ሳይደርስ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ በዚህ አስተሣሠብ የሚያምኑ ዳያስፖራዎች በርካታ ቢሆኑም እነሡ እንደሌሎቹ ጯሂ አይደሉም፡፡ በጣም የተናደደውና ተስፋ የቆረጠው ነው ድምፁ እየተሠማ ያለው፡፡ እነዚህ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት መቼም ከጨረቃ የወረዱ አይደሉም፤ ‹‹የእናት ሆድ ዥንጉርጉር››  እንደሚባለው ሆነ እንጂ እኛንም የፈጠረችና ያስተማረች ሃገራችን ነች እነሡንም የፈጠረቻቸው፡፡ ወንድሞቻችንና ወገኖቻችን ናቸው፡፡ እነሡ ያመኑበትን ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ የሚሠሩትን ስህተት ነቅሶ ማውጣትና መታገል ተገቢ ነው፡፡ በጣም የተናደደ ያመረረ፣ አንዳንዱም ተዋረድኩ የሚል ስሜት ያለው ዳያስፖራ እናያለን፡፡ ከነዚህ ወገኖች የሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች፣ ባለው ህገ መንግስት አግባብም መልስ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡
“መድረክ” ሲቋቋም ደግሞ ከእንግዲህ ወዲህ ይህ ህገ መንግስት መሻሻል ካለበት ይሻሻል እንጂ እሱን አስወግዶ ከዜሮ የመጀመር አላማ የለውም። ይሄን ያለፈ ስርአት የአዙሪት አካሄድ መድገም አንፈልግም። የሚሻሻለውን አሻሽሎ፣ ባለው ላይ ጨምሮ መሄድ ነው የሚያዋጣው፡፡ ህገ መንግስቱን በየመንግስታቱ እየቀየሩ መሄድ ከዚህ በኋላ መቀጠል የለበትም፡፡ በኛ እምነት ህገ-መንግስቱ ውስጥ የሚሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም፣ አሁን ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ በቂ ቦታ አለው፡፡ በህገ መንግስቱ አግባብ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄዎች መፈለግ አለባቸው የምንለው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ በአከራካሪ ጉዳዮች ላይ ህዝበ ውሳኔ ይደረግ ስንል፣ በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ ስላለ ነው፡፡ ውጭ ያሉት አካላት ብዙ ሊመኙ፣ በብዙ መልኩ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። ይሄን ደግሞ ማቀብና ማጠር ለመንግስትም ሆነ ለኛ ቀላል የሚሆን አይደለም፡፡ ከመናደድ በመነሳት ሃገር ማስተዳደር ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ በዚህ ረገድ የኛ አካሄድ ያልተስተካከሉ ነገሮችን በሠከነ መንገድ ማስተካከል ይቻላል፤ መፍትሄ ማምጣትም ይቻላል በሚል እምነት ነው፡፡ ስርአቱም ሃገር ውስጥ ላሉ ተቃዋሚዎች ይሄን እንቅስቃሴ ሊፈቅድ ይገባል፡፡
‹‹ተቃዋሚዎች የሃገሪቱን ተጨባጭ እውነታ በአግባቡ አልተረዱም›› የሚል ክርክር ከኢህአዴግ አካባቢ ይደመጣል…  እርስዎ ምን ይላሉ?
ለምሣሌ የ‹‹መድረክ››ን አካሄድ ብናይ፣ከ2 ዓመት በላይ ፈጅተን፣ ከብዙ ክርክርና ልፋት በኋላ ነው እውን ያደረግነው፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች በተናጥል ብቻቸውን በመሄድ የሃገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ጥያቄዎች ይፈታሉ የሚል እምነት የለኝም። መተማመን ያለበት፣ ማንንም ውጪ በማያስቀር መልኩ፣ ሁሉንም ጥያቄዎች ማዕከል አድርገን ነው ፕሮግራማችንን ያዘጋጀነው፡፡ እኛ የሃገሪቱን ችግሮች በሚገባ አጥንተን ነው ይሄን አደረጃጀት የፈጠርነው። ለዚህ ነው አንዲት ኢትዮጵያ ከሚለው አንስቶ፣ ለራሳቸው ብሄር የሚታገሉ ፓርቲዎችን በዚህ ጥላ ስር ያሰባሰብነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ውጭ ያለው ተቃውሞ የጠነከረው ሃገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች በመዳከማቸውና በርካቶች ከምርጫ 97 በኋላ ወደ ውጪ ተገፍተው በመውጣታቸው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…
እኛ ከፖለቲካ አመራሩ ማን ወደ ውጪ እንደሄደ እናውቃለን፣ ማን ውጪ ተቀምጦ እንደሚናገር ይታወቃል፡፡ ይህቺ አገር ደግሞ መኃን አይደለችም። በቂ ታጋዮች በየጊዜው ታፈራለች፡፡ ዋናው በሽታ የፖለቲካ ምህዳሩ ያለመስተካከል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አዲስ ነገር አይደለም፤ ስንለው የኖርነው ነው። የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡ፣ እዚህ በአግባቡ ተደራጅተን ያለነውን ሃይሎች ዋጋ አሣጥቶናል፡፡ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ወደ ጠርዝ ገፍቶናል፡፡ በአንዳንድ ሚዛንም ዋጋችንን ዝቅ የሚያደርግ ሆኗል፡፡ ህዝቡ፤ “ባለፈው ምርጫም ተሸነፉ፣አሁንም ተሸነፉ›› እያለ ዋጋችንን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት ተደርገናል። በዚያው ልክ ደግሞ አባሎቻችንን ይንገላታሉ፡፡ ታች ያለው ካድሬ በአባሎቻችን ላይ ብዙ እንግልት ሲፈፅም፣ ለበላዮቹ ‹‹እባካችሁ ይሄን ነገር አርሙ›› እያልን መታገል ሆኗል ስራችን፡፡ ወደ ውጪ ተገፍቶ ወጥቷል ለሚለው፣አዎ ብዙ ጋዜጠኞች ተገፍተው ተሠደዋል ግን ፖለቲከኞች በተለይ አመራሮች ያን ያህል ተገፍተው ስለመውጣታቸው ብዙ የማውቀው የለም፡፡ የፖለቲካ መሪዎቹ ወደ ውጪ ወጥተዋል የሚለው ዝም ብሎ ነው፡፡ ይኸው በ1997 ምርጫ ወቅት ትግሉን የመራነው አለን፡፡ አሃዙን ማስቀመጥ ቢያስቸግረኝም፣ ህብረትን ስንመራ የነበረው እዚሁ ነው ያለነው፡፡ ከቅንጅት መሪዎች አብዛኞቹ አሁን ሃገር ውስጥ አሉ፡፡ ለነገሩ መሪ ቢወጣ ሌላ ይተካል። እንደኔ ለነዚህ አካላት ተሰሚነት ያላበሰው ሃገር ውስጥ ላሉት ተቃዋሚዎች ምህዳሩ አላንቀሳቅስ ማለቱ ነው፡፡ ብዙ እንዳንሰራ መደረጋችን ነው፡፡ እኛ እላፊ ሄደን መጋፈጥ ማለት ግጭት መፍጠር መሆኑን ስለምናውቅ፣ ድምፃችንን በወረቀትና እስክሪብቶ ብቻ ለማሠማት ነው የመረጥነው፡፡
ለዚህ ነው “መድረክ” ትዕግስት ባጡና ቶሎ ለውጥ በሚፈልጉ ሃይሎች የሚተቸው። እኛ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ነው መቋቋም ያለበት እንላለን። ይህ ማለት “መድረክ” ቀንቶት ምርጫ ቢያሸንፍ ያገኘውን ውጤት ይዞ ብቻውን መንግስት የማቋቋም አላማ የለውም፡፡ ሌሎችን ወደ መድረክ ይጋብዛል። በምርጫ የመሣተፍ እድል የሌላቸው ሁሉ ወደ መንግስቱ ይጋበዛሉ፤ ያ ጊዜ የብሄራዊ አንድነት ጊዜ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ በሚገባ እንዲደለደል ይደረጋል፡፡ ከዚያ በኋላ እያንዳንዱ በራሱ አጀንዳ ለቀጣይ ምርጫ ይወዳደራል፡፡ ይሄ ነው የ”መድረክ” ዋና እቅድ፡፡ ይሄን መነሻ በማድረግ እኛን በጣም የተለሳለሰ አድርገው የሚያብጠለጥሉን አሉ፡፡ በእኛ በኩል ደግሞ እነሱ የያዙት አቋም ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄ አይሆንም እንላለን፡፡ የኢትዮጵያ ነገር መረጋጋትን ይጠይቃል፡፡ ለውጥን ቀስ በቀስ እያመጡ መሄድ እንጂ ግብታዊ ለውጥ አያስተማምንም የሚል አቋም ነው ያለን፡፡
ከዚህ በኋላ ባለፉት 25 ዓመታት በብሄር ላይ ተዋቅሮ የተሠራውን የኢትዮጵያ አደረጃጀት በሌላ ለማካተት የሚያስችል እድል ይኖራል?
በሽግግር ወቅት 14 ክልሎች እስከሚከለሉ ድረስ እኔም ነበርኩ፡፡ በወቅቱ 14 ክልሎች ነበር የተነጋገርነው፡፡ ዛሬ ደቡብ የተባለው ያኔ በ5 ክልሎች ነበር የተዋቀረው፡፡ በኋላ ነው ወደ አንድ ያመጡት፡፡ ያኔ እኛም  በቋንቋም ሆነ ተመሳሳይ ስነ ልቦና ያላቸው ማህበረሰቦች በአንድ ላይ እንዲሆኑ ብለን ነበር፡፡ ይሄ አሁን ያለው አደረጃጀት ለኢህአዴግ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ሌሎችም በሽግግሩ ወቅት የነበሩ ፓርቲዎች ይሄን ሃሳብ ይጋሩ ነበር፡፡ ሃገር አቀፍ የሆኑት እነ ኢዲዩ፣ ኢዲአግ የመሣሠሉት ሳይቀሩ በዚህ የፌዴራሊዝም አደረጃጀት ላይ እጃቸው አለበት፤ ኢህአዴግ ብቻ ያመጣው አይደለም፡፡ እኛም በሂደቱ ብዙ ጊዜ ወስደን ተሣትፈናል፡፡ እንደውም ከኢህአዴግ አልፎ በደርግ ጊዜም የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ትኩረት እየተሠጠው ነበር፡፡ አሁን የምርጫ ቦርድ ዋና ፅ/ቤት ያለበት ግቢ ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች ኢንስቲትዩት›› ተብሎ በደርግ ጊዜ ተቋቁሞ ነበር፡፡ በወቅቱ የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ እጀንዳም ይሆን ነበር፡፡
አሁን ኢህአዴግ የሚመራትን ኢትዮጵያን በማደራጀቱ ረገድ የኦነግም እጅ አለበት፡፡ ከኢህአዴግ ቀጥሎ ብዙ ሠራዊት የነበረው ኦነግ ነው፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ ኢህአዴግ የሠራት፣ እንዲህ ያደረጋት ሃገር… የሚለው እውነታውን ለመሸሽ ተፈልጎ ይመስላል፡፡ ይሄ ስርዓት ከዚህ አንፃር ዝም ብሎ በቀላሉ የሚናድ አይመስለኝም፡፡ ከስሜታዊነት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ መንግስት በአንድ ሠሞን እንቅስቃሴ ይወድቃል ማለት ከስሜታዊነት የሚመነጭ ነው፡፡  እንዲህ የሚያስቡ ወገኖች የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ አያውቁም ማለት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያን 50 ከመቶ እንኳ አያውቁም የሚሉት የኢህአዴግ ሰዎች፣ የማያውቁት እነሡ ናቸው፡፡ እኛማ እዚሁ ህዝቡ መሃል አድገን እየኖርን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያን ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው ህዝቡ ለሉአላዊነቱ ደጋግሞ ሲሠዋ የኖረው፡፡
በተደጋጋሚ “መድረክ” ከኢህአዴግ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ ሲል ይደመጣል፤ ኢህአዴግ ደግሞ የጋራ ምክር ቤት የስነ ምግባር ደንብ ፈርሙና እንነጋገር ይላል፡፡ እናንተም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ታስቀምጣላችሁ፡፡ ይህ አለመግባባት መቋጫው ምንድን ነው? የሁለታችሁ አቋም እንዴት ነው  ሊታረቅ የሚችለው?
አዳዲስ ካድሬዎች በየጊዜው እየመጡ ነገሩን ያበላሹታል እንጂ ከነባሮቹ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በመጠኑም የስነ ምግባር ደንቡ ላይ ተግባብተናል። የስነ ምግባር ደንቡን እንደ ትልቅ ነገር አናነሣም በሚለው ላይ ከነባር አመራሮች ጋር ተግባብተናል። አዳዲሶቹ ግን ‹‹መድረክ ደንቡን አልፈረመም›› ምናምን እያሉ ሲያስተጋቡ አያለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ የግንዛቤ ችግር ነው፡፡
ደንቡን ለመፈረም ምንድን ነው አስቸጋሪ የሆነባችሁ?
ሳንፈርም የቀረነው ከአንድም ሁለቴ ድርድር ሲደረግ ጉዳዮችን ከጠበቅነው ውጪ ሆነው ስላገኛናቸው ነው፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚኒስቴር በ97 ምርጫ፤ “ውጤቱን ተቀብላችሁ ፓርላማ ግቡ፤ ከሠማይ በታች የማንነጋገርበት ጉዳይ አይኖርም›› ብለው ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን ኋላ ላይ አካሄዱን ራሳቸው አደጋ ላይ ጣሉት፡፡ ምንም የተቃውሞ ቁመና የሌላቸው አካላት በተለይ ተሠሚነትና ተገቢውን ቦታ እንዳናገኝ ያደረጉን ሰዎች ጭምር ወደ መድረክ እንዲመጡ ተደረገ፡፡ ለምሳሌ እነ ልደቱ አያሌው በፈጠሩት ችግር ተቃዋሚው ከኢህአዴግ ጋር በምርጫ ስርአቱ ላይ እንዳይደራደር አድርገውታል፡፡ ኋላም በተፈጠረው መድረክ ላይ እኚህን የመሳሰሉ አካላት ከኛ ጋር ቁጭ ብለው ‹‹በዚህ ጉዳይ ችግር የለብንም፤ አይ በዚህ ላይ የኛ እንጂ የኢህአዴግ ችግር አይደለም›› እያሉ እንዴት ነው መነጋገር የምንችለው፡፡ እርስ በእርስ መጠራረስ ሆነ፤ መድረኩ፡፡ ስለዚህ ለድርድር አመቺ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ነው እኛ መድረኩን የተውነው። ከኢህአዴግ ጋር ችግር ለሌለባቸው ራሱን የቻለ መድረክ፣ ከኢህአዴግ ጋር ችግር ላለብን ለኛ ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ መድረክ ይዘጋጀልን ነው ያልነው። ሲጀመር የድርድር ጥያቄውንም ቢሆን የጠየቀው ‹‹ህብረት›› ነበር፡፡ ኋላ ላይ እነዚህ ከኢህአዴግ ጋር ችግር የሌለባቸው ስብሰቦች በመድረኩ ተጋበዙ፤ ስለዚህ “ከነዚህ ጋር ተቀምጠን መነጋገር አንችልም” የሚለውን ሃሳብ ማንፀባረቅ ስላልፈለግን መድረኩን ትተንላቸው መውጣቱን መረጥን፤ ይሄ ነው ሂደቱ። በ97 ምርጫ የታዩ ግድፈቶችን ከኢህአዴግ ጋር ለመነጋገርና እንዲታረሙ ለማድረግ የነበረው ጥረት በዚሁ ተቀጨ፡፡ ያንን ቪዲዮ መላልሠው እያሣዩ፣ ‹‹መድረክ ረግጠው ወጡ›› እያሉ ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀሙበታል፡፡ ያሣዝናል፡፡
አሁን በተፈጠሩት ወቅታዊ የሃገሪቱ ችግሮች ላይ በምን አግባብ ልትወያዩ ትችላላችሁ ታዲያ?
በሃገሪቱ አሁን ላለው ችግር መፍትሄ ለማምጣት በፖለቲካ ብልጠት ሳይሆን በቅንነት ልናካሂደው የሚገባ ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደደም ጠላም በዚህ ሀገር በህጋዊነት ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር አለበት (ራሱ በተቀበለው እኛ ግን ባልተቀበልነው የምርጫ ውጤት መሰረት፤ከኢህአዴግ ቀጥሎ መድረክ ነው ሁለተኛው፡፡) ይሄ ማለት በዲሞክራሲ ስርአት ልምምድ ውስጥ ዋናው ተቃዋሚ ነው የሚባለው፡፡ ድርድርም ካለ እንግዲህ መደራደር የሚያስፈልገው ሠፊ ህዝባዊ መሠረት ካለው ከዋናው ተቃዋሚ ሃይል ጋር ነው፡፡ አሜሪካን ሃገር አሁን ዲሞክራትና ሪፐብሊካን ዋናዎቹ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ግን ከ50 በላይ የተመዘገቡ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ምንም ያህል ድምፅ ስለማያገኙ አይቆጠሩም፡፡ ስለዚህ የዴሞክራሲ ስርዓት የሚባለውን ጨዋታ እንጫወት ከተባለ፣ኢህአዴግ መደራደር ያለበት ከዋነኛው ተቃዋሚ ከ‹‹መድረክ›› ጋር ነው፡፡ ለምን ከተባለ፣ ‹‹መድረክ›› በልፋቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከጎኑ አሰልፏል፡፡ የሌሎቹን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ስለዚህ ከነዚህ አካላት ጋር እንደራደራለን የሚባለው ለመፍትሄ አይሆንም፤ ዝም ብሎ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው የሚሆነው፡፡ ያ እንዳይሆን አሁንም እኛ  በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረብን ነው፡፡ እኛ እንደ ዋና ተቃዋሚ ከኢህአዴግ ጋር መነጋገር ነው የምንፈልገው፡፡
መንግስት  የምርጫ ስርአቱን አሻሽላለሁ ብሏል። በዚህ ላይ ሃሳብዎ ምንድን ነው?
በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመግባት ለሚጥር ሃገር፣ ይሄ ‹‹ከ50 በመቶ በላይ ያሸነፈ ሁሉን ይወስዳል›› የሚለው አይሰራም። ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ተመጣጣኝ ውክልና የሚባለው ግን እድሎች ይከፍታል፡፡ እሡም ቢሆን ግን ለማምታታት ቦታ የለውም ማለት አይደለም፤ ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ በጎ ፍቃደኝነት ነው፡፡ የዚህ ሃገር ፖለቲካ በኛ እጅ ብቻ ካልሆነ የሚለውን አመለካከት ትቶ፣ መፍትሄ የመፈለግ ጉዳይ መኖር አለበት። ተመጣጣኝ የሚለው ጥሩ ሊሆን ይችላል ግን አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩ መስተካከል ይኖርበታል።  ኢህአዴጎች በምን አግባብ ሊያስተካክሉ እንደፈለጉ ባላውቅም፣ ተመጣጣኝ ስርአትን ለማምጣት ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ከ50 በመቶ በላይ ያሸነፈ ሁሉንም ይወስዳል ነው የሚለው፡፡ ከመኮረጅ ይልቅ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚሆነውን አዲስ መፍትሄም መፈለግ ያሻል፡፡ ዋናው ነገር ግን መፍትሄ ለማምጣት ቆራጥነቱ አለ ወይ? የሚለው ነው፡፡
በሃገሪቱ ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች እርስዎ እንደ መፍትሄ ምንድን ነው የሚያስቀምጡት?
እኔ በግሌ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህቺ ሃገር በመበታተን ስጋት ላይ ወድቃለች የሚለውን አልቀበለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን ስላወቀ ነው አብሮ ያለው እንጂ ብዙ ከፍታና ዝቅታዎችን እያየ የኖረ ነው፡፡ ደቡብ ጠረፍ ብንሄድ እንኳ “ኢህአዴግ ጠረፋችንን አላስከበረም” እየተባለ ሲወቀስ ነው የኖረው እንጂ እቺ ሃገር አታስፈልገንም አይልም፡፡
ለዚህች ሀገር አዳኟ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሌላ ምንም መፍትሄ የለም፡፡ ህዝብ መወያየት አለበት፡፡ መገናኛ ብዙሃንና የሲቪክ ተቋማት… የዲሞክራሲ ግንዛቤ ሰጥተው፣ ህዝቡን የሚያረጋጉበትና “አብረን ብንሆን ነው የምጠቀመው” የሚለውን የሚያስተምሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ‹‹መድረክ›› እንዴት ነው የተመለከተው?
እኛ እንግዲህ ዝርዝሩ ላይ አሁንም ግልፅነት የለም ብለን ስለምናምን፣ ለኮማንድ ፖስቱ የማብራሪያ ጥያቄ በነገው እለት (ቃለ ምልልሱ ረቡዕ ነው የተደረገው) በደብዳቤ እንጠይቃለን። አዋጁ በፖለቲካ ስራችን ላይ ያለው ተፅዕኖ ምን ድረስ ነው? ቃለ ምልልስ መስጠት አንችልም? የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ማካሄድ አንችልም? ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት አንችልም? የአዳራሽ ስብሠባዎችን ማካሄድ አንችልም? ከአዲስ አበባ ውጪ አዳዲስ ፅ/ቤቶችን ከፍተን መንቀሳቀስ አንችልም? የሚሉ ጥያቄዎችን እናቀርባለን፡፡ ግልፅነት ያለው ማብራሪያ እንጠይቃለን፡፡ በዝርዝርም እንዲያሳውቁን እንፈልጋለን፡፡ አዋጁን መተርጎም የሚችሉት እነሱ ናቸው፡፡ በአዋጁ ላይ ብዥታ ስላለን እስካሁን መግለጫ አላወጣንም፡፡
ላለፉት 25 አመታት እርስዎ ሰፊ የፖለቲካ ተሣትፎ አድርገዋል፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴ እስከ መቼ ይቀጥላሉ?
ፖለቲካ ከህይወታችን ጋር አብሮ የተጣመረ ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ፍጡር ሁሉ ፖለቲከኛ ነው። ስለዚህ እድሜና ጤና እስካለኝ ድረስ በዚህ ህይወት ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ለህዝቡ አስተዋፅኦ ማበርከት እስካለብኝ ድረስ አበረክታለሁ፤ጥረቴን እቀጥላለሁ፡፡ ከፖለቲካው የሚለየኝ የወዲያኛው አለም ነው የሚሆነው፡፡
በእስካሁን የፖለቲካ እንቅስቃሴዬ ስኬታማ ነኝ ይላሉ?
አዎ! እኔ በፖለቲካ ህይወቴ ስኬታማ ነኝ፡፡ እኔ ተሣክቶልኛል ነው የምለው፡፡ ከ25 አመት በፊት ደፍሮ ወጥቶ ማንነቴ ተረሣ ብሎ መጠየቅ መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የማንነት እንቅስቃሴ ትልቅ ውጤት አምጥቷል። በፊት የማይታወቁ የህብረተሰብ አካላት አሁን እየታወቁ ነው፡፡ ይሄ የኛም የትግል ውጤት ነው። ከብሶትና ከብስጭት ከፍ ብሎ በመውጣትና ሌላውንም ማህበረሰብ ከዚህ በማውጣት ትንሽም ቢሆን አስተዋፅኦ ነበረኝ፡፡ ለሃገራችን የሚበጀው ዲሞክራሲያዊነት ነው የሚለውን መንፈስ አስፋፍተናል፡፡ በምርጫ ስርአት ማመንን አሳይተናል። ብዙ የትግል ፍንጮችን አምጥተናል። “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቅ” ብለን አልተቀመጥንም። እኛ አገር ትልቁ ችግር ያለው ምሁራኑ ዘንድ ነው። ዝም ብሎ ከመተቸት በቂ ተሳትፎ አድርጎ፣ መስዋዕትነትም እየከፈሉ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ በትናንት አንኖርም፤ ስለዚህ ያለፈን ነገር እያለፍን፣ ራዕያችን ምንድን ነው ብለን እየመዘንን፣ ወደፊት መንቀሳቀስ አለብን፡፡

Read 5556 times