Sunday, 30 October 2016 00:00

ዓለማቀፍ የቱሪዝም ክለብ፣ ከ40 ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ተቋቋመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

· በዓለም ላይ ከ15ሺ በላይ አባላት፣ከ400 በላይ ክለቦች አሉት
· በርካታ ቱሪስቶች የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን መሰረዛቸው ቱሪዝምን ጎድቶታል
· ኢቦላ ባልተከሰተበት ሁኔታ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ተከልክለው ነበር
· ኤርታአሌ አሁንም አደገኛ ቀጣና በሚል ለጉብኝት ከተከለከሉ ሥፍራዎች አንዱ ነው
· በእስራኤል የሮኬትና የሚሳኤል ተኩስ እያለ፣ብዙ ቱሪስቶች አገሪቱን ይጎበኛሉ

ስካል ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ክለብ ከ40 ዓመት በፊት በጃንሆይ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም መንግስት ሲለወጥ ክለቡም እንቅስቃሴውን አቁሟል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ፣ የአሜሪካው ስካል ቱሪዝም ክለብ አባል ሚስተር ስቴፈን ቢ ሪቻርድ እንዲሁም የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ኃላፊዎችና እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡ ክለቡ ከ40 ዓመት በፊት ተከፍቶ ለምን ስራ አልቀጠለም? ድርጅቱን በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን መክፈት አስፈለገ፣ በቀጣይስ ምን ለማከናወን አቅዷል በሚሉትና ተያያዥ ዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የስካል አዲስ አበባ አስተባባሪ፣የ “ግራንድ ሆሊዴይ ኢትዮጵያ” አስጎብኚ ድርጅት ባለቤትና የኢትዮጵያ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር የቦርድ አባል ከሆኑት ከአቶ ደሳለ ምትኩ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች::

እስቲ ስካል ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ክለብ ምን እንደሆነ ይንገሩኝ ?
ስካል በቱሪዝም ዙሪያ ማለትም፡- በሆቴል በመስተንግዶ፣ በአስጎብኚነት፣ በመኪና ኪራይና በአጠቃላይ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ የቱሪዝም መሪዎችና ባለቤቶች ማህበር ነው፡፡ የተመሰረተው በ1934 እ.ኤ.አ ሲሆን በዓለም ላይ ከ85 አገራት በላይ ይንቀሳቀሳል፡፡ ዋና መቀመጫውም ስፔይን ውስጥ ነው፡፡
ዛሬ ስካል ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ክለብ በኢትዮጵያ ተመስርቷል፡፡ እስከ አሁን እንዴት ዘገየ?
ከ40 ዓመት በፊት በንጉሱ ጊዜ ተቋቁሞ ነበር፤ ነገር ግን ወዲያው የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ቀረ። አሁን ከ40 ዓመት በኋላ በጣም በከፍተኛ ጥረት፣ በተለይ ላለፉት አራት አመታት ከስካል ዩኤስኤ እና ከስካል ናይሮቢ ጋር በመተባበር ሊመሰረት ችሏል፡፡
የስካል አዲስ አበባ ዋና ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው?
በዋናነት የጉዞ ወኪሎች፣ የሆቴል ባለቤቶችና ማናጀሮች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ በቱሪዝም ላይ የሚሰሩ እንደ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በመስተንግዶ ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶችና ስራ አስኪያጆች ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡
ክለቡን በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ማቋቋም ለምን አስፈለገ?
ክለቡን በአሁኑ ሰዓት አገራችን ላይ ለማቋቋም የመረጥንበት ዋነኛ ምክንያት አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ በተለያዩ ዓለማትና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች እየወጣ ያለው መመሪያ የተጋነነና ከእውነታው ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለጉብኝት አስጊና ምቾቷን ያጣች አገር አድርገው በመሳል፣ ዜጎቻቸው ወደዚች አገር ድርሽ እንዳይሉ እያደረጉ ነው፡፡ እየወጡ ያሉት የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችና ክልከላዎች፣ በአብዛኛው እጅግ የተጋነኑ ናቸው። ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም አሁንም ሁሉም ነገር ተረጋግቶ ነው ያለው፤ ሁሉም ስራውን እየሰራ ይገባል፤ ቱሪስቶችም እየጎበኙ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ብዙ ኤምባሲዎች፣ የውጭ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚያወሩት ለቱሪዝም እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ይህንን የተዛባ አመለካከት መቶ በመቶ እንኳን ባይሆን በተወሰነ መልኩ ለማሻሻልና ገፅታችንን ለመመለስ፣ “ስካል አለም አቀፍ አዲስ አበባ”ን በአሁን ወቅት ማቋቋማችን ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርግልናል ብለን በማመን ነው ወቅቱን የመረጥነው፡፡ ይህ የተጋነነ አሉታዊ መረጃ እየተናፈሰ ባለበት ወቅት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን የቱሪዝም ክለብ በአገራችን ማቋቋማችን ብዥታውን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያጠራዋል ብለን አምነንበታል፡፡ ስካል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ15 ሺህ በላይ አባላት አሉት፡፡ ይህ ዜና ቢያንስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላሉ 15 ሺህ ሰዎች ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ በዓለም ላይ ኢትዮጵያ በጥሩ ጎኑ ትነሳለች፤ የቱሪዝሙም ችግር ቀስ በቀስ እያገገመ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ስካል በዓለም ላይ ከ400 በላይ ክለቦች አሉት፡፡
 ከአራት ዓመት በፊት ቱሪስቶች አፋር ኤርታአሌ ላይ ጥቃት ደርሶባቸው ከሞቱ በኋላ ቦታው በቱሪስቶች ከማይጎበኙ አደገኛ ቦታዎች አንዱ ሆኖ በካርታ ላይ ቀይ ተቀብቷል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ በርካታ ቱሪስቶች እየጎበኙት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን የቱሪስት መስህብ ከ”አደገኛ ቀጣና” ለማውጣት እንደ አስጎብኚዎች ማህበር ምን ጥረት አደረጋችሁ?
የውጭ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በአብዛኛው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን ሲያወጡ፣ በተለይ አፍሪካ ውስጥ ከሆነ፣ ሁሌም የአደጋ ቀጠና አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢቦላ ወረርሽኝ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በተለይም በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተ ጊዜ ምንም ኢቦላ ባልተከሰተበት ሁኔታ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያም ጭምር እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያዎችና ክልከላዎች ሲደረጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ኢቦላ በወቅቱ ከአፍሪካ ይልቅ በአውሮፓ ውስጥ ነበር የተከሰተው፡፡ ይህ ለአፍሪካ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት የሚያሳይ ነው፡፡ በአፍሪካ ላይ አንድ ትንሽ ነገር ሲከሰት ተሯሩጠው ሪፖርት የሚያደርጉትን ያህል፣ ሁኔታው ሲሻሻልና ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሲመለስ ለማስተካከል ግድ የላቸውም ወይም አይፈልጉም፡፡ እንዳልሺው ኤርታአሌ ላይ የተከሰተው ነገር ሶስት ወይም አራት  አመት ሆኖታል፤ ነገሩ በተከሰተ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የፀጥታው ሁኔታ ተስተካክሎ፣ ለጎብኚዎች ክፍት ከሆነ ከሁለት አመት በላይ ሆኖታል፡፡ እኛ እንኳን በድርጅታችን በኩል በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎችን ወደ ቦታው  ልከናል፡፡ አሁን እኔና አንቺ እያወራን ባለንበት ሰዓት እንኳን በእኛ ድርጅት በኩል ሄደው፣ኤርታአሌን የሚጎበኙ ብዙ ቱሪስቶች አሉ፡፡ ቦታው በጥሩ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ከመሆኑም በላይ እንደዚያ ቦታ የሚያስደንቅ መስህብም የለም፡፡ እንዳልኩሽ አንድ ጊዜ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ከወጣ በኋላ ይረሳል፤መልሰው ወቅታዊ ሁኔታውን ለዜጎቻቸው አይገልፁላቸውም፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ይህንን ጉዳይ በየጊዜው የማስታወሱ ስራ የማን ነው?
እኛ ሁሌም ጥረት እናደርጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትም ሆነ የአስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር እንዲሁም አስጎብኚ ድርጅቶች በየግላቸው ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን የውጭ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ትኩረት አይሰጡትም። ይህን ትኩረት የሚነፍጉት ደግሞ አፍሪካ ላይ በመሆኑ ነው፡፡
በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋትና በተለይ በኢሬቻ በዓል ላይ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ በርካታ ቱሪስቶች የጉብኝት ፕሮግራማቸውን እየሰረዙ መሆኑ ይነገራል፡፡  ስካል ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ክለብ በአዲስ አበባ መመስረቱ፣ ‹‹ሀይ ሲዝን›› ተብለው በሚታወቁት የታህሳስና ጥር ወራት ቱሪስቶች ሀሳባቸውን ቀይረው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ይኖራል ብለው ያምናሉ?
ችግሩ የተከሰተው በጣም መጥፎ ወቅት ላይ ነው፡፡ ወገኖቻችንም ህይወታቸውን ማጣታቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ ቶሎ ለመርሳት ያስችግራል። እኛ እንደ ኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማህበር፣ ለ“ሀይ ሲዝኑ” ቱሪስቶች መጥተው እንዲጎበኙ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ችግሩ ተከስቷል ወይ አዎ፤ ይህን መካድ አንችልም፤ ነገር ግን አሁን ሁሉም ተረጋግቶ ወደነበረበት ተመልሷል፡፡ ይህንን ደግሞ ለተለያዩ ኤምባሲዎች ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በመላክ፣ ያለውን ትክክለኛ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ ለዓለም ለማሳየት እየሞከርን ነው፡፡ ስካል አለም አቀፍ አዲስ አበባ በእዚህ አገር መመስረቱም፣ የጥረታችን አንዱ አካል ነው፡፡ በሌላ በኩል ችግሩ ሲከሰትም ሆነ ከተከሰተም በኋላ እዚህ መጥተው ጎብኝተው የተመለሱ ቱሪስቶች የነበራቸውን ቆይታ ለአገራቸው እንዲገልፁ፣ ሁሉም ነገር ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱን እንዲመሰክሩ እያደረግን እንገኛለን፡፡
ጥረታችን እንዳለ ሆኖ “ሀይ ሲዝን” ከመቅረቡ አንፃር ብዙ ነገሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሊከብደን ይችላል፡፡ ብዙ የጉብኝት ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል፡፡ የተወሰኑ ጎብኚዎች ሊመጡ ይችላሉ። ይህ ለየአገሩ እንዳለው አመለካከት የሚወሰን ነው። ለምሳሌ እስራኤልን ብንወስድ፣ በየቀኑ የሮኬትና የተለያየ ሚሳኤል ተኩስ እያለ፣ በርካታ ቱሪስት አገሪቱን ይጎበኛል፡፡ በሌላው አገር ቱሪስት እየሞተ እንኳን አሁንም ቱሪስት ወደዚያው ያመራል፡፡ እኛ አገር ከስንት ጊዜ አንዴ ነው ይሄ ነገር የተከሰተው። ባይከሰት መልካም ነበር፡፡ ከተከሰተ በኋላ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ሲመለሱም ግን የሚሰማን የለም፡፡ ይሄንን ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ ጥምረት ይፈልጋል፡፡ በጋራ በመስራት አገራችንን ወደ ቀድሞ ገፅታዋ ለመመለስ እንጥራለን፡፡
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዥታን ፈጥሯል” የሚል አስተያየት ከአስጎብኚ ድርጅቶች ይደመጣል። እርስዎ ይሄን አስተያየት ይጋሩታል?
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ የሚመለከተው አካል ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ድርጅቶች ግልፅ በሆነ መልኩ ጎብኚዎቹን እንደማይነካ፣ ይበልጥ የጎብኚዎችንም ሆነ የአገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣ መሆኑን ገልፆ በጥብቅ ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፈረንሳይ ውስጥ አለ፤ ቱርክ ውስጥ አለ፤ነገር ግን በርካታ ቱሪስቶች ይሄዳሉ፡፡ እስካሁንም በነዚህና በሌሎች አገሮች በርካታ ቱሪስቶች እየሞቱ እንደሆነ ይነገራል። በአገራችን ለጉብኝት መጥቶ ጥቃት የደረሰበት አንድም ቱሪስት የለም፡፡ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዥታ ላለባቸው ወገኖች፣ያለ ማቋረጥ መግለፅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ቱሪዝም ወደ ቀድሞው ቦታው ይመለሳል፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ቱሪዝም የሰውን ህይወት የሚለውጥ ዘርፍ የለም፡፡ የሆቴል አስተናጋጅ፣ ጀልባና በቅሎ አከራይ፣ ቱር ጋይድ፣ ቤተ-ክርስቲያንና ገዳማት፣ መስጊድና መሰል ተቋማትና ግለሰቦችን ህይወት ቱሪዝም ይይዛል፡፡ አገራችን ላይ አንድም ቱሪስት ሳይሞት፣ በጨለምተኝነት አፍሪካ ውስጥ ስለተገኘን ብቻ እንዲህ አይነት የከረረ ማስጠንቀቂያና የጉዞ ክልከላ የሚያደርጉ አካላት ኃላፊነት እንደጎደላቸው ይሰማኛል፡፡
ብዙ ቱሪስቶች የሚመጡባት ጀርመን ቻንስለር የሆኑት አንጌላ መርከል አገራችንን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ በርካታ የጀርመን ቱሪስቶች የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን መሰረዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ነገር ለማረጋገጥ እዚህ አገር ከተገኙት የጀርመን መሪ በላይ ማንም ምስክር ሊሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡ መጥተው በሰላም ጉዳያቸውን ፈፅመው ተመልሰዋል፡፡ እርሳቸውም ለብዙ ጎብኝዎች ምስክርና ማረጋገጫ መሆን ነበረባቸው። ግን የሆነው በተቃራኒው ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ግን የለብንም፤ መንግስትም ሆነ እኛ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያለነው በውጭ አገር በሚገኙ ኤምባሲዎቻችንና እዚህ አገር ባሉ የየአገራቱ ኤምባሲዎች አማካኝነት ተገቢውን ጥረት በማድረግ ወደቀደመ ገፅታችን መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን እያደረገ ነው። አገራት መቶ በመቶ እንኳን ማስጠንቀቂያውን ባይቀንሱት ቢያንስ ደረጃውን ቢቀንሱት መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ስካል አዲስ አበባ ወደፊት ምን ለመስራት አቅዷል?
 አሁን ተመስርቷል፡፡ ለሁሉም የስካል አባል አገራት መመስረቱን አሳውቀናል፤ ብዙ ሽፋን ያገኛል። በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ጭምር ማለት ነው፡፡ ሚያዚያ ላይ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ክለቡ የሚያዘጋጀው ጉባኤ አለ፤ ከ80 በላይ የስካል ክለብ አባላት ይሳተፋሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም አገሪቷንና ያለችበትን ሁኔታ አይተው ይሄዳሉ፤ በቀጣይ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን ስካል ይሰራል ብለን እናምናለን፡፡
እስቲ ስለ አስጎብኚ ድርጅትዎ ደግሞ አጠር አድርገው ይንገሩኝ?
ድርጅታችን “ግራንድ ሆሊዴይስ ኢትዮጵያ” ይባላል፤ የተመሰረተው ከ13 ዓመት በፊት ነው፡፡ ከተለያዩ አገራት የተለያዩ ጎብኚዎችን በማምጣት፣በከፍተኛ መስተንግዶ አስጎብኝተን፣ የአገራችንን መልካም ገፅታ አሳይተን እንመልሳለን። ሁሉም እንግዶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው ብለን ስለምናምን፣ ለእንግዶቻችን ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በዓመት ከ500 በላይ እንግዶች ተቀብለን የምናስተናግድ ሲሆን ከ15 በላይ ቋሚ ሰራተኞች አሉን፡፡ እንደየወቅቱ ሁኔታ ብዙ ጊዜያዊ ሰራተኞችንም እንቀጥራለን፡፡ ለምሳሌ ብዙ ቱርጋይዶችን፣ ሹፌሮችን፣ ምግብ አብሳዮችን እንቀጥራለን፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ያሉ የቱሪስት ቦታዎችን እናስጎበኛለን፡፡  
የጉብኝት ፕሮግራማቸውን የሰረዙ ቱሪስቶች አልገጠሟችሁም?
ብዙ የተሰረዙ ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በቁጥር ለማስቀመጥ ብቸገርም ከተለያዩ አገራት በርካታ ስረዛዎች አጋጥመውኛል፡- ከቤልጂየም፣ ከአሜሪካ ከፊንላንድና ከሌሎችም አገራት የጉብኝት ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል፡፡       

Read 1611 times