Saturday, 10 March 2012 11:13

የሁለት ሊጐች ወግ! “ኑሮውንም እንደ ኳሱ ያስወድደን!”

Written by  የጣና ልጅ
Rate this item
(0 votes)

በቅርቡ አንድ ቱባ የመንግስት ባለስልጣን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የሚል ቱባ መጽሐፍ ጽፈዋል - የታዋቂውን እንግሊዛዊ ደራሲ ቻርለስ ዲከንስን እውቅ መጽሐፍ “A Tale of Two Cities” ወይም “የሁለት ከተሞች ወግ” ርዕስን በመዋስ፡፡ እኔም የዚህን እውቅ መጽሐፍ ርዕስ ተውሼ፣ ይችን ሀይ ባይ ተመልካች ያጣች የኑሮ ሊግ፣ በተመልካች ከተትረፈረፈው የውጭዎቹ የእግር ኳስ ሊግ ጋር ያነፃፀርኩበትን ቀጭን ወግ እንካችሁ ብያለሁ፤ ተቀበሉኝ፡፡

ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ እህቴ ቀላል የሚባል ኦፕራሲዮን አድርጋ ስለነበረ እሷን ለመጠየቅ ጐተራ ኮንደሚኒየም ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ነው፡፡ ያንለት በጉጉት የሚጠበቅ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነበር - በማንችስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል መካከል፡፡ ጨዋታው ሊካሄድ አንድ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ነበር ጐተራ ኮንደሚኒየሙ ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ ባር ጨዋታውን ለመመልከት ጐራ ያልኩት፡፡ ባሩ ባርነቱን ረስቶ ጨዋታውን ለማሳየት ከተለመደው ስራው ወጣ ብሎ ወንበሮቹን እንደ አዳራሽ ደርድሮ በሰው ተሞልቷል፡፡ እንደምንም አንድ ቦታ አግኝቼ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ከቲቪው በቅርብ ርቀት ስር የሚተዋወቁ የሚመስሉ ጐረምሶች ተቀምጠዋል፡፡ ግማሾቹ የማንችስተርን፣ ግማሾቹ ጨዋታው የማይመለከተው የአርሰናልን እንዲሁም የሊቨርፑልን መለያ የለበሱ ነበሩ፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ብሽሽቅ ይዘዋል፤ ድራፍት እየተጐነጩ፡፡ የማንችስተርን መለያ የለበሰው ወደ አንዱ ዞሮ “አቻ ልስጥህና አምስት መቶ ብር ብላ” ይለዋል፡፡ በቡድኑ መተማመኑ ከልክ በላይ ሆኖ፡፡ ሌላው “ሱዋሬዝ ያገባና ኤቭራ ፊት ሄዶ ይጨፍርበታል፤ ያን ላይ ነው የመጣሁት” “ዳኛው ሀላል ካጫወቱ ማንቼ ይጠበጠባል” ይላል አንደኛው የአርሰናልን መለያ የለበሰው በክርክሩ መሃል ዘው ብሎ፡፡ “ኧረ ላሽበል (ዞር በል ማለቱ ነው) ለአቅመ እግር ኳስ ያልደረሱ ልጆች እየደገፍክ ትቃጠላለህ” ይለዋል፤ የማንችስተርን ተጨዋቾች ባየ ቁጥር የሚያጨበጭበው፡፡ ብሽሽቃቸው ለተመልካች አዝናኝ ነው፡፡ ሁሉም ግን አንድ ነገር የረሱ ይመስላሉ - ኑሮን፡፡ ኑሮው ህዝቡን እንደ እግር ኳስ ሊግ ወራጁ ቀጠና ከቶት ላለመውረድ ቢታክርም፣ አይዞህ ባይ ደጋፊ አጥቶ ቢንገታገትም፣ ከዚህ በላይ የሚያሳስበው የሚያስጨንቀው ነገር ግን አላጣም፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያዊ እግር ኳስን የሚወደው ኑሮን ስለሚያስረሳው ይሆን እንዴ ብዬ አስባለሁ፡፡ የነዳጁ ጭማሪ፣ የታክሲው ታሪፍ፣ የምግቡን፣ ኧረ ስንቱን ጠርቼ እችላለሁ … የማይጨምረውን ብጠራ ይሻላል፤ አዎ “ደሞዝ!” እሱ ብቻ ነው ባለበት አጥሮ የቀረው፡፡ ጓደኞቹ እነ ወጪ የት ደርሰዋል! እሱ ባለበት ከቀረ ግን ዘመናት ተቆጠሩ፡፡ ከደሞዝ ውጭ ያሉትን ጭማሪዎች ሁሉ ህዝቡ የሚረሳው በሩኒ ወይም በቫን ፐርሲ ጐል ይመስለኛል፡፡ እግዜር ይስጣቸውና ሁለቱም ጐል ማግባታቸውን ተያይዘውታል፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ጥሎ አይጥለንም መቼስ ምግብ የራበው ህዝብ ጐል ለምን ይርበዋል ያለ ይመስላል፡፡  የሚዲያዎቹ ዋና ስራም ህዝቡን በእግር ኳስ መካከለኛ እውቀት አላቸው ከሚባሉት አገሮች መመደብ ይመስላል፡፡ ጠዋትና ማታ አንድ አይነት ወሬ እያወሩ ሰው ዜናውን እስከሚሸመድድው ድረስ ያስረዱታል፡፡ የሚገርመው ሁሉም አንድ አይነት ሰዓት ላይ አንድ አይነት ዜና ይዘው መቅረባቸው ነው፡፡ ሁሉም ደግሞ አንድ ምንጭ ነው ያላቸው፡፡ ቻናል ብትቀይሩ እራሱ እዛው ያላችሁ እስኪመስላችሁ ድረስ የመግቢያ ሙዚቃቸው እንኳን ሳይቀር አንድ አይነት ነው፡፡ አንደኛው ላይ ብቻ የስፖርት መወያያ ፕሮግራም መግቢያ ላይ የታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ኤምነም “Am not afraid” ዜማ ከቅንጭብ የስፖርት ዜማዎች መሀል ቀላቅሎታል፤ አልፈራሁም ማለቱ ነው - ዘፋኙ፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው ጋዜጠኛው መናገር የፈለገው ግን ያልቻለው ቅኔ መሆን አለበት፡፡ ይህንኑ ጉዳይ ላንድ ቅርብ ጓደኛዬ ሳሰማው “ገዳይ ነው” ብሎኛል፡፡ አንድ ደግሞ ከሴት ጋር ሆኖ የእግር ኳስ ትንተና ለመስጠት የሚገባ አለ፡፡

እግር ኳስ ከመተንተኑ ብዛት የመሃል ዳኛው ከአራጋቢው የተነጋገሩትን ልክ አብሮአቸው ሆኖ እንደሰማ አድርጐ ያወራል፡፡ ማውራት ከመውደዱ ብዛት አብራው ለማስተዋወቅ የገባችውን እንኳን እድል አይሰጣትም፡፡ እራሱ ሁሉንም ይለዋል፡፡ አይፎርሽም፡፡ ለመሰነባበት እንኳን አይፈቅድላትም፡፡

ሌሎቹ ደግሞ ሦስት ሆነው ይገቡና ሁሉንም በነፃነት ይተቻሉ፡፡ ሀፍረት ሳይሰማቸው፡፡  በተለይ አንዱ የፈረንሳዮች ፍቅር እንደፀናበት በግልጽ የሚያስታውቅበት ዊንገርን “ሪፈር” ካላደረገ እውነት ያወራ አይመስለውም፡፡ ሁሉንም የሚቃወመው “ኖኖኖ” አርሴን ዊንገር ያሉትን እንደ ምሳሌ እያቀረበ ነው፡፡

አውሮፓ በቅዝቃዜ ተመታች፡፡ ጨዋታዎችም ሊስተጐጐሉ ይችላሉ የሚል ዜና ሲወራ “ጨዋታው ላይ ዊንገር ያደረጉትን ጃኬት እንኳን አላየህም፤ በጣም ብርድ አለ” ነበር ያለው፡፡

ሌላኛው በሆነው ባልሆነው እየሳቀ በእንግሊዝኛ ማውራት ይቃጣዋል፡፡ የሦስተኛው ሚና ቀልድ እየፈለጉ ማምጣት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ህዝቡ ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድራቸው ራዲዮ ጣቢያዎች ነው፡፡ ለምን የዘይት ዋጋ ጣራ እንደነካ መጠየቅ አይችልም፡፡ ግን አርሴናል አዲስ ስላስፈረመው ተጨዋች አስተያየት እንዲሰጥ ይጋብዙታል፡፡ ፈረንጆቹ “The people have the right to know” ይላሉ፤ ህዝቡ የማወቅ መብት አለው እንደማለት ነው፡፡ ይህ ታዲያ የሚሰራው እግር ኳስ ላይ ብቻ ይመስላል፡፡ ህዝቡም ትንሽ ትልቅ ሕፃን አዋቂ፤ አሁን አሁን ደግሞ ሴት ሳይል በየመስሪያ ቤቱ፣ ትምህርት ቤቱ፣ ዩኒቨርስቲው፣ ካፍቴሪያው፣ ሆስፒታሉ፣ ለቅሶ ቤቱ፣ ሰርግ ቤቱ፣ በየዕምነት ቦታው ሳይቀር የጦፈ ክርክር የሚያካሂደው ስለምን ይመስላችኋል? ስለ ኳስ፡፡

ስላለፈው ቀን ጨዋታ ወይንም ስለሚመጣው ጨዋታ፤ ምክንያቱም ስለኑሮ ማውራት አይችሉማ! ማን የማንን ብሶት ይሰማል? ኳሱ ደህና አድርጐ ብሶታቸውን ያስረሳቸዋላ! ጤፍ ስንት እንደገባ ሰምታችኋል ብለው መርዶ ከሚነግሩ ቫን ፐርሲ እንዴት እንዳገባ አይታችኋል? ብለው ሰፊ መወያያ መድረክ ቢፈጥሩ ይሻላቸዋል ወይንም ሱዋሬዝ ኤቭራን መጨበጥ ነበረበት አልነበረበትም ብለው አቧራ የሚያስነሳ ክርክር መፍጠር ከዘይት ሰማይ ጨበጠ አይደል? ብለው የሰውን ምሬት ከመቀስቀስ ይሻላል፡፡

በኑሮ ውድነት የሚሰቃይ ህዝብ ኳስ መውደዱ አይፈረድበትም፡፡ ምክንያቱም የሚፈልገውን ቡድን የሚደግፈው በፍጹም ነጻነት ነው፡፡ ማንም ይህንን ቡድን ካልደገፍክ ብሎ አያሳስበውም፡፡ የትኛውንም ቡድን ቢደግፍ “ሽብርተኛ” ተብሎ  አያስጠረጥረውም፡፡ መደራጀት አያስፈልገውም፡፡ የራሱን ቡድን ተጨዋቾች በነጻነት ይተቻል፡፡ አሰልጣኙን ባደባባይ ይወቅሳል፡፡ ቡድኖቹም ቢሆኑ በሆነው ባልሆነው የድጋፍ ስብሰባ አይጠሩትም፡፡ እየተሸነፉ ጨጓራውን ቢልጡት ቡድን መለወጥ ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ፍቅርና ድጋፍ ግን ለምን ለውጭ እግር ኳስ ብቻ ሆነ ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ከሰሞኑ የሆነውን ላጫውታችሁ፡፡ አንድ ጓደኛዬ በዕረፍት ቀናቶች አንዱ ስልክ ስደውል አያነሳም፡፡ እኔም ብዙም አልጨቀጨኩትም፡፡ አመሻሽ ላይ እሱ ደወለልኝ እና “አዲስ አበባ እስታዲየም ነበርኩኝ፤ ለዚያ ነው ያላዋራሁህ” አለኝ፡፡  ገርሞኝ ከዚህ ቀደም እስታዲየም የሚገባ ስላልሆነ “ከመቼ ጀምሮ ነው እስታዲየም መግባት የጀመርከው?” ብለው “ባክህ ጓደኛዬ እስታዲየም ወስደህ ሲሰዳደቡ ሲበሻሸቁ ካላሳየኸኝ ብላኝ ነው” ብሎኝ እርፍ! “በጣም ተዝናንተን ነው የወጣነው” አለኝ፤ እየሳቀ፡፡  ግርምቴን የጨመረው ግን ማን ከማን ጋር ጨዋታ እንደነበራቸው እንኳን አለማወቁ ነው፡፡ “ቡናና የሆነ ነጭ ማሊያ የለበሱ ሲጫወቱ ነበር” አለኝ፡፡

እንግዲህ ስንቶቻቸው ናቸው ብሽሽቅ ለመስማት ብለው እስታዲየም የሚሄዱት? ተጫዋቾቹም ያንን እየሰሙ ተዘናግተው ይሆናላ ለውድድር የማይበቃ ጨዋታ የሚጫወቱት ስል አሰብኩኝ፡፡ ኢቴቪም ከጨዋታው ይልቅ ብሽሽቁን ቢያስተላልፍ በርከት ያሉ ተመልካቾችን ሳያገኝ ይቀራል? የኢቴቪ ካሜራ ማን ምን እያየ ይሆን ጎል ሚያመልጠው ለሚለው ጥያቄዬ ግን መልስ አግኝቻለሁ፡፡

ጨዋታው በማንችስተር ዩናይትድ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ነው፡፡ ዝማሬውና ጭብጨባው ደርቷል፡፡ የማንችስተርን መለያ የለበሰ ወጣት እስላሽ ጎልማሳ ተነስቶ ያስጨፍራል፡፡ እስክስታም እንደመምታት እያለ “ወያላ አፈር ብላ” ይላል፤ ሊቨርፑልን ሊደግፉ የመጡ የአርሰናል ደጋፊዎችን መሆኑ ነው፡፡ እኔም ሳላስበው በዝማሬው ተመስጬ እራሴን እያጨበጨብኩኝ አገኘሁት፡፡ ወዲያውም ምን ያህል የራስ የሆነ የሚያስጨፍር የሚያስደስት ነገር እንዳጣን ታሰበኝ፡፡ ኑሮ ኳስ ሆኖበት ኳስ የሚወድ ህዝብ፡፡

በቴሌቪዥን አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ያለው ትዝ አለኝ፡፡ መንግስት  ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የአፍሪካን ዋንጫ ጨዋታዎች እንድንመለከት አድርጓል፡፡  ከአምስት ሚሊዬን በላይ ረሀብተኛ ባለበት ሀገር፣ ስራ አጡ ከሰራተኛው የማይተናነስበት ሀገር፣ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ መሆኑ ቀርቶ ከእጅ አፍ ላይ መድረስ ባቃተበት ዘመን፣ መንግስት ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚከፍለው እግር ኳስን በቀጥታ ለማስተላለፍ ነው፡፡  ምክንያቱም ህዝቡ ያንን ሁሉ ችግሮቹን ይረሳበታላ! ሆዱ ባዶ እንኳን ቢሆን በግብ ጠግቦ ይጨፍርበታላ!

አያቴ የሰው ወርቅ አያደምቅ ትል ነበር ነብሷን ይማረውና፡፡ እኛ ግን በሰው ወርቅ እንኳን ሳይሆን በሰው ኳስ ድምቅምቃችን ወጥቷል፡፡ የኛ የሆነ ነገር የት ሄደ? ምን ነካው? ልጅ ሳለሁ የኛ ቀበሌ ጨዋታ ሲኖረው ሰዐቱ አልደርስ ይለኝ ነበር፡፡

የሰፈሬን ልጆች ሲጫወቱ ለማየት፡፡ አሁን አሁን የቀበሌ ጨዋታዎች አሉ? ባይሆን የቀበሌ አዳራሾች አሉ፤ የውጪውን ኳስ ለማሳየት በህዝብ ተጨናንቀው፡፡ እኔ የኛ ቀበሌ ዋንጫ ሲያነሳ ማየት እመርጣለሁ፤ አርሰናል ዋንጫ ሲያነሳ ከማይ፡፡

ነጮቹ የራሳቸውን ወደው እኛንም እንድንወደው አድርገውናል፡፡ እኛም የራሳችንን ጥለን የሰው ተሸክመናል፡፡ የራሳችንን ኮከቦች በየታክሲው በየቤቱ የምንለጥፍበት ጊዜ ያምጣልን፡፡ ኑሮውንም እንደ ኳሱ ያስወድደን፡፡ እንደ ኳሱም ያስደስተን ያስጨፍረን፡፡ አሜን በሉ፡፡ መልካም ቅዳሜ!!!

 

 

Read 2656 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 11:18