Sunday, 30 October 2016 00:00

የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ለኢትዮጵያ ክለቦች ፕሮፌሽናሊዝምና እድገት ወሳኙ አቅጣጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 3 እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን፤ ዘንድሮ በርካታ የደንብ ማሻሻያዎች በማካተቱና 16 ክለቦችን በማሳተፉ የተለየ ይሆናል፡፡ የ2009 ዓ.ም ፕሪሚዬር ሊግ ከመጀመሩ በፊት ግን የወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሲሆን ለኢትዮጵያ ክለቦች  ፕሮፌሽናሊዝምና እድገት ወሳኙ አቅጣጫ መሆኑ እየተገለፀ ነው፡፡ የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬትን የሚሰጠው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር የተቋቋመው  የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ሲሆን መንቀሳቀስ ከጀመረ 4 ወራት አልፈዋል፡፡  የክለቦች ላይሰንሲንጉ በአገር ውስጥ የሊግ ውድድርና በአህጉራዊ የክለብ ሻምፒዮናዎች የሚሳተፉ ክለቦችና ስፖርተኞችን ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ ለማድረስና በስፖርቱ የዕድገትና የለውጥ እንቅስቃሴ መፍጠር የወቅቱ አስፈላጊ አቅጣጫ ነው፡፡  በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ደንቦች የተቀረፀም ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በፊፋና የካፍ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ደንብና የውድድር መስፈርቶችን አሟልተው እንዲንቀሳቀሱ የተቀመጠው የግዜ ገደብ እስከ 2018 እኤአ መሆኑን በማሳወቅ እየሰራ ነው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በደንቡ አፈፃፀም ተግባራዊነት ላይ ግፊት ማሳደር የጀመረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በመተዳደርያ ደንቡ አንቀፅ 52 ይህን ደንብ ማካተቱን ፤ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት መመስረቱንና እና ማናጀር መመደቡን፤ በዲፓርትመንቱ የግምገማ ውሳኔዎች ላይ ተጨማሪ ግምገማ የሚያደርጉት ሁለት ነፃ አካላት ማለትም የመጀመርያ ውሳኔ ሰጪ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች መመስረታቸውን እንዲሁም ክለቦች በተቀመጠው አቅጣጫ በመስራት ላይ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት በተለይ የፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎችን የመገምገሚያ ቅፅ በማዘጋጀት በማኔጀሩ አቶ ተድላ ዳኛቸው አማካኝነት ስራን ጀምሯል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  ፊፋ የዓለም እግር ኳስ በፕሮፌሽናል የክለብ አደራጃጀቶች፤ የውድድር መስፈርቶችና መዋቅሮች እንዲመራ ለአባል ፌዴሬሽኖቹ መመሪያውን ካሰራጨ  ዓመታት አልፈዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ደግሞ በተለይ በ2016 እኤአ በተለያዩ የአህጉሪቱ ከተሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሴሚናሮችን በማካሄድ ይህንኑ መመሪያ ፌዴሬሽኖቹ እንዲያስፈፀሙ እያሳሰበ ቆይቷል፡፡ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ መስፈርቶችን በሚያሟላ ሊግና ክለቦች የተወዳደሩ ብቻ በአህጉራዊ ውድድሮች የመካፈል ፈቃድ ይኖራቸዋል በሚልም ጥብቅ ትዕዛዙንም አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል የሚባለው የክለብ ላይሰንሲንግን በተመለከተ ያሉትን ሁኔታዎች  ስፖርት አድማስ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ማኔጀር የሆኑትን አቶ ተድላ ዳኛቸው በማነጋገር ይህን ትንታኔ አቅርቦታል፡፡

       የክለብ ላይሰንሲንግ ማናጀሩ ማናቸው?
አቶ ተድላ ዳኛቸው ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ማናጀር ሆነው ስራቸውን የጀመሩት ከሐምሌ 1 2008 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በሃላፊነቱ የተመደቡት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፤ በስፖርቱ ያላቸውን በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ የዳበረ እውቀት፤ መጠነ ሰፊ ልምድ እና ቅርበት ትኩረት በመስጠት ቅጥሩን ባከናወነው የእግር ኳስ ፌደሬሽን አማካኝነት ነው፡፡ አቶ ተድላ የሙያው ሰው መሆናቸውን ለማመልከት ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአሁን ወቅት በእግር ኳስ ስልጠና የማስትሬት ዲግሪ ያላቸው ቢሆንም የረጅም ጊዜ ግልጋሎት ያላቸው በስፖርቱ አስተዳደር ነው፡፡  ከ25 አመት በላይ ባሳለፉበት የስራ እና የትምህርት ልምዳቸው ከዲፕሎማ ተነስተው፤ በመጀመርያ ዲግሪ እና በማስትሬት ዲግሪ የስፖርቱን መስክ አጥንተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በስፖርት አስተዳደር  የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እያጠናቀቁ ሲሆን የመመረቂያ ፅሁፋቸውን እያዘጋጁ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አቶ ተድላ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በውድድር ዋና የስራ ሂደት ዲያሬክተር በመሆንም ከ4 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
ስለ ክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት
የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር ለመጀመርያ ጊዜ የተመሰረተ ነው፡፡ የክለቦች የህጋዊነት ሰርተፍኬት መስጫ ክፍል ነው፡፡ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሃላፊ ሲሆን በተግባራቱም ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ጋር በቀጥታ በመገናኘት የክለብ ላይሰንሲንግ ስርዓተ ደንቦችና መመርያዎችን ያስፈፅማል፡፡ ዲፓርትመንቱ ላይሰንሱን የሚሰጠው በካፍ የተወከለ እና በፌደሬሽኑ ስር የሚንቀሳቀስ አካል  ሲሆን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ደንብ መሰረት ክለቦች በተለይ  አስገዳጅ እና በዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላት በአህጉራዊ ውድድሮች የመሳተፍ መፈቃድን የሚያጋግጥ ሰርተፊኬት በግምገማው የሚያረጋጥ ይሆናል፡፡
የክለብ ላይሰንሲንግ ስርዓትን በተመለከተ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ   ክለቦች በህጋዊነት እንዲደራጁ ካፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በርካታ ሴሚናሮች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በመሳተፍ ላይ እንደነበር  አቶ ተድላ ዳኛቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከወራት በፊት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የካፍ ብሔራዊ የክለብ አደረጃጀት ሥልጠና እንዲሁም የካፍ ናሽናል ክለብ ላይሰንሲንግ በማተኮር ያካሄደው ሴሚናር በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ ከ9 የክልል መስተዳድሮችና ከ2ቱ ከተማ አስተዳደሮች የስፖርት ኮሚሽኖችና ፌዴሬሽኖች እንዲሁም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ሴሚናሩ የክለቦችን ጥራት ደረጃ እና ሌሎች ለእግር ኳስ ስፖርት ጠቃሚ የሆኑ የአሰራር ሥርዓቶችን ለማስተዋወቅና በአፍሪካ ደረጃ የተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት አስተዋፅኦ ነበረው፡፡
አቶ ተድላ ዳኛቸው የክለብ ላይሰንሲንግ ዋና ዓላማዎች በዝርዝር ሲያስረዱ የአፍሪካን እግር ኳስ በተለያዩ ደረጃዎች የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ለማስቻል እና ለማስተዋወቅ፤ ክለቦች በተሟሉ መሰረተልማቶች፤ አደረጃጀቶች እና አስተዳደሮች መመራታቸውን ለማረጋገጥ፤ የክለቦችን የስፖርት መሰረተልማቶች ለማሻሻል እና ለማሳደግ፤ ክለቦች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተከታታይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማደላደል ፤ በየአገራቱ ያሉ ክለቦች በተመሳሳይ ደረጃ እንዲወዳደሩ፣ በህጋዊ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሰሩ፤ ፍትሃዊ እና መደበኛ መስፈርቶችን በእኩል ደረጃ አሟልተው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡
በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስር የሚገኘው የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ዋንኛ መሰረቱ ከላይ በተዘረዘሩት ዓለማዎች ላይ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተድላ፤ የአገራችን እግር ኳስ የብቃት ደረጃን ለማሻሻልና፤ ክለቦች የራሳቸው የእግር ኳስ መሰረተ ልማት ያለው አደረጃጀት እና አተገባበር እንዲኖራቸው ማስቻል መሆኑን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረዳታቸው አሁን በዲፓርትመንቱ በኩል የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለመስጠት ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች የመገምገሚያ ቅፅ በማዘጋጀት ወደ ግምገማው መገባቱን አመልክተዋል፡፡
የብሔራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እና የግምገማ መስፈርቶች
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ማናጀር የሆኑት አቶ ተድላ ዳኛቸው ለስፖርት አድማስ በሰጡት ማብራርያ በካፍ የቀረበው የክለቦች የህጋዊነት ሰርተፍኬት የሚረጋገጥባቸው አምስት መመዘኛዎችና መስፈርቶች ያሉት ሲሆን ሦስት የተለያዩ መለያዎችንም እንደሚያካትት ነው፡፡
የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለማግኘት ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች በሚቀርብ የመገምገሚያ ቅፅ የሚከተሉት  የግምገማ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው ከወጣቶች ልማት አንፃር የተቀመጠው ነው፡፡ በዚህ የግምገማ መስፈርት ንዑስክፍል 1 ላይ የክለቦች የፀደቀ የወጣቶች የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራም፤ የወጣቶች እግር ኳስ ልማት ዓላማና የወጣቶች የእግር ኳስ ልማት ፍልስፍና፤ የልማት ፕሮግራሙ አደረጃጀት፤ የሰው ኃይል መዋቅር፤ ከክለቡ ጋር ያለው ግልፅ ግንኙነት፤ ተገቢ የትምህርት ዝግጅት ያለው የሰው ሃይል፤ የእግር ኳስ ወይም የስፖርት ባለሙያ፤ የህክምና ባለሙያ፤ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፤ የውድድርና የመለማመጃ ስፍራ፤ ግልፅ የፋይናንስ አቅም፤ የእግር ኳስ ትምህርት፤ ስልጠናና ህጎች ፕሮግራም፤ የህክምና  ፕሮግራምና የመደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ዝግጅነት መኖራቸው ይገመገማል፡፡ በሌላ በኩል ከወጣቶች ልማት አንፃር በቀረበው የግምገማ መስፈርት ንዑስ ክፍል 2 የወጣት ቡድን አደረጃጀትን በተመለከተ በቅፁ በሚቀርቡ መስፈርቶች ክለቦች ከ15 እስከ 21 ዓመት እንዲሁም ከ10 እስከ14 ዓመት እድሜ ያላቸውን ቡድኖች በየደረጃ ስለመያዛቸው ይገመገማሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዳያድግ እንቅፋት ከሆኑት ምክንያቶች ዋንኛው ከወጣቶች ልማት አንፃር በክለቦች የሚከናወኑ ተግባራት በተሟላ ሁኔታ የተደራጁ ባለመሆናቸው ነው የሚሉት አቶ ተድላ፤ ክለቦች ተተኪዎችን በሚያፈሩበት አደራጀጀት እንዲሰሩ የሚያደርገውን መስፈርት የፌደሬሽኑ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት በየክለቡ የሚቀርቡ ሰነዶችን በመከለስ እና በመስክ ጉብኝት የመገምገም ተግባራን እንደሚያከናውን ገልፀዋል፡፡ ከወጣቶች ልማት አንፃር  ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በታህሳስ ወር የሚያስመርቀው  የወጣቶች ማሰልጠኛ አካዳሚ እንዲሁም የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በዚህ ረገድ ተምሳሌት ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከወጣቶች ልማት አንፃር የተሟላ እንደሆነና በተለይ ለአፍሪካ ሞዴል ሊሆን ይችላል የተባለው በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተገነባው የይድነቃቸው ተሰማ ትሬኒንግ ሴንተር ሲሆን ማዕከሉ በታህሳስ ወር ላይ ሲመረቅ የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ መረጃዎች እየገለፁ ናቸው፡፡
ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች በቀረበው የክለብ ላይሰንሲንግ የመገምገሚያ ቅፅ በሁለተኛነት የተቀመጠው የግምገማ መስፈርት ከስፖርት መሰረተልማት አንፃር ነው፡፡ በዚሁ መስፈርት ንዑስ ክፍል 1 ላይ የክለብ ስታድዬም ራሱን ችሎ የተከለለ፤ ቦንክሪት የተሰራ የተመልካቾች መቀመጫ ያለው፤ ሜዳው በአርቴፊሻል ወይም በሳ የተሸፈነ፤ ለተቀያሪ ተጨዋችለታዛቢዎች ለህክምና ቡድን አባላት እና ሌሎች ለየብቻቸው የተዘጋጁ ቦታዎች፤ አጠቃላይ የስታዬሙን እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚያችል ክፍል፤ ለክብር እንግዶችና ለሚዲያ ሰዎች ማረፊያዎች፤ ከ20ሺ በላይ ሰው መያዙ፤ የማታ ጨዋታዎች ለማካሄድ የሚያችል መብራት፤ የተቃራኒ ቡድኖችን ለመለየት የሚያችል ከለላ፤ ለአካል ጉዳተኞች የመግቢያ በር እንዲሁም የመጀመርያ ህክምና እርዳታ መስጫና የአበረታች መድሃኒቶች መቆጣጠርያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ በግምገማው የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ የክለብ ላይሰንሲንግ የመገምገሚያ ቅፅ ከስፖርት መሰረተልማት አንፃር የግምገማ መስፈርት ንዑስ ክፍል 2 ከስታድዬም ባለቤትነት የሚያያዝ ሲሆን ተገምጋሚው ክለብ በባለቤትነት ወይም በኪራይ የሚተዳደር የመጫወቻ ሜዳ እንዳለው እንዲሁም በስታድዬሙ ውስጥ በግልዕ የሚታዩ ገዢ ህጎች መቀመጣቸውን የሚመለከት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከስፖርት መሰረተልማት አንፃር በቅፁ የሰፈረው የግምገማ መስፈርት  በንዑስ ክፍል 3 የመለማመጃ ስፍራዎችን  እንዲሁም በንዑስ ክፍል 4 መፀዳጃን የተመለከተ ይሆናል፡፡
አቶ ተድላ ዳኛቸው እንደሚገልፁት የካፍ ክለብ ላይሰንሲንግ ክለቦች በተለይ ከስፖርት መሰረተልማት አንፃር የየራሳቸው ስታድዬም ማስተዳደር እንደሚኖርባቸው የሚያሳስብ ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ይህ ፈታኝ መስፈርት ሊሆን ቢችልም በኢትዮጵያ የሚገኙት የእግር ኳስ ክለቦች በመንግስት ሙሉ ድጋፍ የሚተዳደሩበትን ሁኔታ በመቀየር በራሳቸው የተሟላ በጀት የሚንቀሳቀሱበትን አቅም ለመፍጠር የሚያግዝ አቅጣጫ መሆኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የሚያስገነዝብው ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ንግድ ባንክ፤ ደደቢት… የየራሳቸውን ስታድዬም ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የሚጠቅሱት የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ማኔጀሩ፤ ከስፖርት መሰረተ ልማት አንፃር የቀረበውን መስፈርት ለማሟላት ክለቦች ባላቸው አማራጭ አንድም የየራሳቸውን ስታድዬም በመገንባት ከላይ የተጠቀሱትን ዝርዝር መስፈርቶች በየደረጃው በማሟላት መስራት እንደሚኖርባቸው ወይም ደግሞ  በሚጠቀሙበት ስታድዬም የኪራይ ኮንትራት ፌደሬሽኑን ባካተተ ውል ፈፅመው እንዲሰሩ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች በቀረበው የክለብ ላይሰንሲንግ የመገምገሚያ ቅፅ በሶስተኛነት የተቀመጠው የግምገማ መስፈርት ከሰው ኃይል አስተዳደር አንፃር ነው፡፡ በዚህ መስፈርት በተዘረዘሩት 8 ንዑስ ክፍሎች ክለቦች ክለቦች ተገቢውን ያህል የቢሮ መገልገለያ መሳርያዎችና ሰራተኞች ያሉት ቋሚ ፅህፈት ቤት እንዳለው፤ በተገቢው አካል የተመደበ የክለብ ማናጀር፤ የፋይናንስ እና የፀጥታ ሃላፊ እንደለው፤ የህክምናና የፊዚዮቴራፒስት ባለሙያ ማሟላቱን፤ ከሲ እና ከዚያም በላይ የማሰልጠን ፈቃድ ያለውንና በፕሪሚዬር ሊጉ አምስትና ከዚያ በላይ የማሰልጠን ልምድ ያለው ዋና አሰልጣኝ መቅጠሩን፤ በአሰልጣኝነት ተምሮ ዲፕሎማ፣ የ2 ዓመት የወጣቶች አሰልጣኝነት ልምድ እንዲሁም በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሰራ የወጣቶች ልማት ፕሮግራም ሃላፊ  እንዳለው እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አውቅና ያለው የአሰልጣኝነት ፈቃ ያመዘገበ የወጣቶች አሰልጣኝ መያዙን የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓትመንቱ በሚያደርገው ግምገማየሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
በመጨረሻም ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች በቀረበው የክለብ ላይሰንሲንግ የመገምገሚያ ቅፅ በአራተኛ እና በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጡት የግምገማ መስፈርቶች ከፋይናንስ፤ ከአስተዳደር እና ከህጋዊ ጉዳዮች አንፃር ናቸው፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መመዝገባቸውን፤ ተጨዋቾቻቸው በፌደሬሽኑ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች መመዝገባቸውን፤ ለተጨዋቾች የሚከፈሉት ክፍያዎች እና የተገቡ ውለታዎች በግልፅ መቅረባቸውን፤ ከተጨዋቾች ገቢ ላይ ተገቢው የመንግስት ግብር መከፈሉን እንዲሁም የክለቦች አጠቃላይ እንቅስቃሴን ለሚመለከከው አካል የተሟላ ሪፖርት መቅረቡን የሚዳስስ  ይሆናል።
የግምገማው መስፈርቶች የውጤት መግለጫዎችና አፈፃፀም
ለፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊዎች በቀረበው የክለብ ላይሰንሲንግ የመገምገሚያ ቅፅ  ከላይ የቀረቡትን ዝርዝር የግምገማ መስፈርቶች በአቶ ተድላ ዳኛቸው የሚመራው የፌደሬሽን ዲፓርትመንት በተለያዩ የውጤት መግለጫዎች ነጥብ ሰጥቶ በመመዘን በድምር ውጤት ለክለቦች የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬቱን ይሰጣል ወይም ይከለክላል። በውጤት መግለጫው ዝርዝር መሰረት 5 ነጥብ ክለቡ መስፈርቱን ሙሉ ለሙሉ አሟልቷል ፈቃዱን ማግኘት ይችላል ነው፡፡ 4 ክለቡ መስፈርቱን አሟልቷል ነገር ግን መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ ፈቃዱን ማኘት ይችላል ነው፡፡ 3 መስፈርቱን ለማሟላት በዝግጅት ላይ ነው፤ ፈቃዱን ማግኘት አይችልም፡፡ 2 ደግሞ በፕሪሚዬር ሊግ ውስጥ ለመጫወት የሚያችል ዝግጁነት የለውም፤ ፈቃዱን ማግኘት አይችልም ይሆናል፡፡
የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ ከላይ የተዘረዘሩትን የውጤት መግለጫዎች ለማስፈፀም የሚከተለው ሂደቶችን አቶ ተድላ ዳኛቸው እነደሚከተለው ያረዳሉ፡፡ በመጀመርያ ክለቦች የብሄራዊ የፈቃድ ማረጋገጫው ሰርተፊኬት እንዲሰጣቸው ለፌደሬሽኑ ዲፓርትመንት ያመለክታሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የዲፓርትመንቱ ማናጀር የግምገማ ቅፁን ይዞ በክለቦቹ ፅህፈት ቤት በአካል ተገኝቶ በሃላፊነት ክለቡን የሚያገመግሙ  ሃላፊዎች በማስፈረም በዝርዝር የግምገማው መስፈርቶች የመገምገሚያ ቅፁን ይሞላል፡፡ ከዚያም በውጤት መግለጫው ላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ድምር በመግለፅ በመመርያው የቀረቡትን መስፈርቶች ላሟሉት ክለቦች በካፍ በኩል ሰርተፍኬቱ እንዲሰጣቸው የሚገልፅ ሰነድ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ አቶ ተድላ ዳኛቸው ጨምረው እንደገለፁት ይህን የዲፓርትመንቱ ውሳኔ ሁለቱ ነፃ አካላት የሚገመግሙት ሲሆን የመጀመርያ የውሳኔ ሰጪ አካል የተባለው እና በሶስት የስፖርት ባለሙያዎች የተዋቀረው ኮሚቴ የሚመለከተው እንደሚሆንና ከባለሃብት፤ ከስፖርት ባለሙያዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚዋቀረው ሌላው ነፃ የይግባኝ ሰሚ አካል ኮሚቴ ደግሞ በዲፓርትመንቱ ውሳኔ ቅሬታ ያላቸውን ክለቦች እንደሚያተናግድ ነው፡፡
የብሄራዊ የፈቃድ ማረጋገጫው ሰርተፊኬት ለክለቦች የሚሰጠው በቋሚነት አለመሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ እንዳስፈላጊነቱ በየሁለት አመቱ በተሰጠው ሰርተፊኬት ላይ ዳግም ግምገማ በማድረግ ፈቃዱን ሊያስ ወይንም የክለቦቹ አደረጃጀት እየወረደ ከሄደ የሚያግድበትን ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል ብለዋል፡፡
የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫና የኢትዮጵያ ክለቦች  እንደማጠቃለያ
የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ማናጀር የሆኑት አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ እግር ኳስ ምርት መሆኑን ሲገልፁ፤ ምርቱን በተሟላ ብቃትና አደረጃጀት መቅረብ እንዳለበት፤ ይህን ማሳካት ከቻለ የስፖርት አፍቃሪውን ፍላጎት ማርካት እንደሆነ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ክለቦች በሁሉም ደረጃ መጠነ ሰፊ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ በካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ኮሚቴ አባልነት እየሰሩ መሆናቸው ለብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫው አፈፃፀም አስተዋፅኦ እንዳለው በመጥቀስ፤ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ የቆየ ታሪክ ያለውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ወጥቶ በምእራብ እና በሰሜን አፍሪካ እንዳሉ ክለቦች በተሟላና ብቁ አስተዳደር እንዲመራ፤ ግልፅ፤ ህጋዊ፤ ተወዳዳሪ፤ ሃላፊነት የሞላበት፤ ተጠያቂነት ያለውና በግልፅ የፋይናንስ ሁኔታ የሚሰራ እንዲሆን ጥልቅ ጥናቶች የመስራት ፍላጎት እንዳለውም አቶ ተድላ ይናገራሉ፡፡ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ ከአገሪቱ ክለቦች ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በክለብ ላይሰንሲንግ ዙርያ ያቀመጠው የሁለት ዓመታት ገደብን በመንተርስ የኢትዮጵያ ክለቦች በተለይ በሰው ሃይል፤ በፋይናንስ፤ በአስተዳደር እና በህጋዊ ሁኔታዎች ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች በሚያሟሉበት አደረጃጀት ትኩረት አድረገው መስራት እንዳለባቸው አቶ ተድላ ዳኛቸው በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ በተለይ በ2017 በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሚሆነው መከላከያ፤ በክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ መገምገማቸውንና በአብዛኛው የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላት እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ተድላ፤ በፕሪሚዬር ሊጉ ሁሉም 16 ክለቦች ይህን ተምሳሌት በማረግ በተመሳሳይ አቅጣጫ መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከወጣቶች ልማት አንፃር፤ የመከላከያ ክለብ ከሰው ኃይል ልማት አንፃር በተምሳሌትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሲሆን በተጨዋቾች ምዝገባ፤ በክለብ ስራ አስኪያጆች፤ በቴክኒካል ዲያሬክተር፤ በህክምና እና ፊዜዮቴራፒስት ሰራተኞች ቅጥር አብዛኛዎቹ ክለቦች በሚያበረታቻ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኙ እና የተወሰኑትም በትኩረት በመስራት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። በተለይ ግን ከክለብ ላይሰንሲንጉ ጋር በተያያዘ ክለቦች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩበት የሚገባው መስፈርት በግልፅ የፋይናንስ አደረጃጀት መመራት መሆኑን መጠቆም ግን ግድ ይላል፡፡ የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንቱ ማናጀር አቶ ተድላ ዳኛቸው እንዳስገነዘቡት ክለቦች በየውድድር ዘመኑ የሚኖራቸውን የፋይናስ እንቅስቃሴ በግልፅ ሪፖርት ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑና ለደጋፊዎቻቸው በሚያሳውቁበት አሰራር መንቀሳቀስ አለባቸው። ግልፅ የፋይናንስ ሪፖርት ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠቃሚ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ተድላ ዳኛቸው፤ ክለቦች በፋይናንስ ሪፖርታቸው የሚያወጧቸው መረጃዎች በአትራፊ ሁኔታ መንቀሳቀሳቸውን ወይንም በኪሳራ እየተዳካሙ መምጣታቸውን በማወቅ ደጋፊዎቻቸው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ስለሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

Read 1604 times