Saturday, 29 October 2016 12:14

በየአመቱ ...ሁለት ሚሊዮን... ሴቶች ላይ ግርዛት የሴት ልጅ ግርዛት አይነቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

 የሴት ልጅ ግርዛት በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው።
የሴት ልጅ ግርዛት ከተወለዱ እስከ አስራ አምስት አመት እድሜ ድረስ በሚገኙት ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።
የሴት ልጅ ግርዛት ማለት ሆን ተብሎ የህክምና ተግባር ባልሆነ መንገድ የሴትን ልጅ ብልት መጉዳት ማለት ነው። ድርጊቱ ለሴቶች ወይንም ሰሌት ልጆች ምንም የጤና ጥቅም አይሰጥም።
የሴት ልጅ ብልት በሚገረዝበት ወቅት ከፍተኛ መድማት እና ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ሽንትን ለመሽናት መቸገር በሁዋላም መመረዝን እና የተለያዩ የጤና ችግሮችን ያስከትላል።
በ30 አገሮች ማለትም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በኤሽያ ወደ 200/ሚሊዮን የሚጠጉ ልጃገረዶችና ሴቶች ግርዘት የተከናወነባቸው ናቸው።
 - WHO -
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአንድ ለጋሽ ድርጅት ጋር በመተባበር በአገራችን በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸመውን ግርዛት በሚመለከት በቅርቡ አንድ አገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ለማድረግ አስቦአል። የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ቁምቢ ለዚህ እትም ስለሁኔታው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ አገላለጽ፣ “ከሴት ልጅ ግርዘት የሚገኝ ምንም የጤና ጥቅም የለም። የሚገኘው ስቃይ እና ጉዳት ብቻ ነው። የሴት ልጅ ግርዛት ጠቃሚ እና ጤናማ የሆነውን ተፈጥሮአዊ ስሜት ሰጪ አካል እና በአካባቢው ያሉ ተፈጥሮአዊ ገላ ቆርጦ ከማስወገድ እና ጥቅም እንዳይሰጥ ከማድረግ እንዲሁም የሴቶችና ልጃገረዶችን ተፈጥሮአዊ የሰውነት እና ስሜታዊ እንቅስቃሴ ደብዛው እንዲጠፋ በማድረግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ገፈፋ ማድረግ ነው። እውነቱን ለመናገር ግርዘት ማለት በሴት ልጅ ስብእና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል እና ድርጊቱ በጣም መጥፎ ተብሎ የሚገለጽ ነው። ”
የሴት ልጅ ግርዛት አይነቶች
1/ የሴትን ብልት ስሜት ሰጪ አካል በከፊል ወይንም በሙሉ ማስወገድ፣
2/ የሴትን ልጅ ብልት ስሜት ሰጪ አካል በከፊል ወይንም በሙሉ እና በውስጥ በኩል ካለው ከንፈር ጋር ማስወገድ የውጭውን ቆዳ ሳይነካ ወይንም አብሮ ማለት ነው።
3/ የስሜት ሰጪ ክፍልን በማስወገድ ወይንም እንዳለ በመተው አብይ ከንፈሩን በመቁረጥ ብልትን በመስፋት መዝጋት ወይንም ማሸግ፣
4/ የሴት ልጅ ብልት በእሾህ ወይንም በመርፌ በመውጋት፣ መብጣት ወይንም ማለብ፣ የብልት ውስጠኛውን አካል መቁረጥ ባጠቃላይም ሁሉም ጎጂ ነገሮች የሚከናወኑበት ነው። በመርፌ መሰል ነገር እየወጉ መስፋት፣ መቁረጥ፣ ደም እንዳይፈስ ሲሉ ማቃጠል የመሳሰሉት ጎጂ ነገሮች ሁሉ የሚከናወንበት እጅግ አስከፊው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው።
ዶ/ር ሰሎሞን እንደሚገልጹት ለአደጋው ተጋላጭ የሚሆኑትና ግርዛት የሚፈጸምባቸው በአብዛኛው በወጣት ልጃገረዶችና አንዳንድ ጊዜም ገና በተወለዱ ሕጻናት እና በታዳጊዎች ላይ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ከፍ ባሉ ሴቶች ላይ ይፈጸማል።
እንደ የአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ዘገባ ከ200/ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች እና ልጃገረዶች 30/ በሚሆኑ ሀገራት ማለትም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና ኤሽያ ግርዛቱ ተፈጽሞ ባቸዋል። ግርዘት ይበልጥ የሚከናወንባቸው የአፍሪካ ሀገራት በምእራብ፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ እና በኤሽያ እንዲሁም ከእነዚህ ሀገራት ፈልሰው ወደሌሎች ሀገራት በገቡት የህብረተሰብ ክፍሎች አማካኝነት ነው።
የሴት ልጅ ግርዘት አለም አቀፍ ችግር ነው
የሴት ልጅ ግርዛትን ለማከናወን ምክንያት ከሚሆኑ ባህላዊና ማህበራዊ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
የሴት ልጅ ግርዛት የሚከናወንበት ምክንያት ከአገር አገር እንዲሁም እንደየህብረተሰቡ ልማድና አስተሳሰብ እንደጊዜው ሁኔታ ይለያያል። የማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች በቤተሰብ ውስጥና በህብረተሰቡ አኑዋኑዋር ተጽእኖ ያደርጋል።
የልጃገረዶች ግርዛት አንዳንድ ጊዜ የሚፈጸመው በማህበራዊ ስምምነት ማለትም ሌሎች ሲያደርጉት ስለኖሩና ስለሚያደርጉት በሚፈጠር ግፊት እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ላለመገፋትና ተቀባይነትን ለማግኘት ነው።
የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸመው ሴት ልጅን በአግባቡ ለማሳደግ የሚረዳ እና ልጅትዋን ለጋብቻና ኃላፊነትን ለመሸከም የማብቃት ስራ ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው።
የሴት ልጅ ግርዛት በወሲብ ባህርይ ሴትን ልጅ ተቀባይ ያደርጋታል እንዲሁም ከጋብቻ በፊት ከወንድ ጋር የሚኖርን ግንኙነት እንዳይኖር ወይንም ሕግን የመጠበቅ ተግባር እንዲሁም በትዳር ዘመን ታማኝነትን ያመጣል የሚል እምነት አለ።
በሴት ልጅ ግርዛት ከብልታቸው ላይ የሚቆረጠው አካላቸው የማይፈለግና ቆሻሻ ነገር ከሰውነታቸው እንደተወገደ ተቆጥሮ ሴቶቹ ንጹሕ እና ቆንጆ እንዲሆኑ ይረዳል የሚል ባህላዊ አስተሳሰብ አለ።
በየትኛውም እምነት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ድርጊቱን የሚፈጽሙት አካባቢዎች በተወሰኑ እምነቶች እንደሚደገፍ ያምናሉ።
በእርግጥ በተለያዩ የእምነት ተቋማት ዘንድ የተለያየ ድርጊት ይታያል። አንዳንዶች ድርጊቱ መፈጸሙን የሚደግፉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ። እንዲያውም ተግባሩን ለመቅረፍ የሚደረገውን ተግባር ይደግፋሉ።
አንዳንድ የህብረተሰብ መሪዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ግርዘቱን የሚያከናውኑት እንዲሁም አልፎ አልፎ በሕክምና ስራ ላይ ያሉም ድርጊቱ ሲፈጸም እንዲቆይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ይታያሉ ይላል አለምአቀፉ መረጃ።
በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና ለጋሽ ድርጅት ትብብር ሊሰራ የታቀደወ ፕሮጀክት ወደፊት ምን ሊያደርግ እንዳቀደ ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ እንደሚከተለው አብራር ተዋል።
“...በየአመቱ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች ላይ ግርዛት እንደሚፈጸም መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይም ይህ ተግባር የሚፈጸመው በብዛት በአፍሪካ ውስጥ ሲሆን ከሴራሊዮን እስከኢትዮጵያ እንዲሁም ከግብጽ እስከ ደቡብ አፍሪካ ይደርሳል። የመን፣ ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን ውስጥ ግርዛት የሚፈጸም ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ደግሞ በስደት የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይፈጽሙታል። ነገር ግን እንደስዊድን፣ ኖርዌይ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ የመሳሰሉት አገሮች ሴቶች እንዳይገረዙ ቢከለክሉም ስደተኞቹ ግን ወደሀገራቸው እየወሰዱ አስቆርጠው መመለስ የጀመሩበት ሁኔታ ተስተውሎአል። በኢትዮጵያ ከ10/አስር አመት በፊት የተደረገው የስነህዝብና የጤና ዳሰሳ እንዳመለከተው ወደ 74% የሚሆኑት ሴቶች ግርዛት እንደተፈጸመባቸው አመልክቶአል። በእርግጥ ይህ መረጃ ከቦታ ቦታ ያለውን ልዩነትም ያሳያል። ለምሳሌም ቤንሻናጉልና ትግራይ ላይ የሚያንስ ሲሆን ከ20-29% በሱማሌ ክልል ግን እስከ 97% ይደርሳል። አፋር ወደ 92% ግርዛት ይፈጸማል። በአፋርና ሱማሌ ምናልባትም የተወሰኑ ቁጥሮችን መቀነሱ ከሌሎች መስተዳድሮች የሄዱ ነዋሪዎች ስለሚኖሩ ነው የሚል ግምት አለ። እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ይህ ፕሮጀክት ሊሰራ ያሰበው በመጀመሪያ ከጤና ጥበቃ ጋር በመተባበር አንድ የምክክር ስብሰባ ለማድረግና ከዚያም ባለፈ በተለያዩ መንገዶች የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት ለማድረግ ነው። በመገናኛ ብዙሀን ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ የሴት ልጅ ግርዛት ድርጊቱ በከፋ ሁኔታ በሚፈጸምባቸውም ሆነ በቀላሉ በሚፈጸምባቸው ወይንም በማይፈጸምባቸው አካባቢዎች ያሉ ከተለያዩ ጤና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ማሰል ጠን ነው። የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን ያስፈለገበት ሁኔታም በአብዛኛው ባለሙያው በተማረበት ቦታ ይህ የጤና ጉዳይ በስፋት የማይዳሰስ በመሆኑ በስራ ላይ ከማየት ባለፈ በትምህርት የተደገፈ በቂ መረጃ የለም። ከዚህም ባለፈ የጤና ባለሙያው ይህን ድርጊት በመከላከሉ ረገድ ብዙም ስለማይታይ ስልጠናው የመከላከል ዘዴዎችንም ባካተተ መልክ ይዘጋጃል። ሰልጣኝ ባለሙያዎችም ወደ ስራ ገበታቸው ሲመለሱ በስልጠናው የታገዘ ምን ያህል ስራ እንደሰሩ ሪፖርት ሲያደርጉ የብቃት ማረጋገጫው ሰርተፊኬት ይሰጣቸዋል። ባጠቃላይም ለህብረተሰቡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግንዛቤ መፍጠር የሚቻልባቸው ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት ተደርጎአል።

Read 5431 times