Sunday, 30 October 2016 00:00

ዳሽን ባንክ ከ727 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ዳሽን ባንክ ባለፈው ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከ727 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ባደረገው የባለ አክሲዮኖች 22ኛ መደበኛና 20ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተካ አስፋው ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ በበጀት ዓመቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 950.6 ሚ. ብር፣ ለመንግስት ታክስ ከከፈሉና 182 ሚ. ብር ህጋዊ መጠባበቂያ ከያዙ በኋላ 727 ሚሊዮን 49 ሺህ 909 ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸውንና አንድ ዕጣ (አክሲዮን) 487 ብር እንደሚያስገኝ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ችግሮች በኣመቱ የቀጠሉ ቢሆንም ባለአክሲዮኖች በ19ኛው ልዩ መደበኛ ጉባኤ የባንኩ የተከፈለ ሂሳብ ከፍ እንዲል በወሰኑት መሰረት፣ ሰኔ 30, 2016 የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 1.5 ቢ. ብር እንደነበርና ይህም የባንኩ ካፒታል ወደ 2.8 ቢሊዮን ብር እንዳሳደገው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ፣ አዳዲስ የባንክ አሰራሮችን ለደንበኞቹ እያስተዋወቀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተካ በወዲያኛው ዓመት አሜሪካን ኤክስፕረስ ካርድ መጀመሩን፣ በበጀት ዓመቱ ደግሞ ወርቃማና አረንጓዴ የዳሽን ኤኤም ኢ ኤክስ ካርድ ማቅረቡን፣ ኢንተርኔት፣ ወኪልና ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የባንኩን ተደራሽነት ከማስፋት አኳያ ባለፈው ዓመት 64 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመላ አገሪቱ በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 220 ማድረሱን፣ አበይት ደንበኞች ብቻ (ከ5 ሚ. ብር በላይ) የሚስተናገዱበት በዓይነቱ የተለየ የደንበኞች ማዕከል በወሎ ሰፈር ቦሌ ታወር ህንፃ ላይ በቅርቡ እንደሚከፈት ተናግረዋል፡፡
የዋና መ/ቤት ህንፃ ግንባታ ከውጭ ከሚገቡ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት ቢዘገይም ኮንትራክተሩ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በጥር ወር ግንባታውን አጠናቆ እንደሚያስረክባቸውና በዚህ ዓመት ወደ ህንፃው እንደሚገቡ የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ የአራት ኪሎና የደሴ ህንፃ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ብለዋል፡፡
በዓመቱ፣ በዓለም አቀፍና በአገር ደረጃ የተከሰቱ ፈታኝ ችግሮች ባንኩ እንዳሰበው እንዳይንቀሳቀስ እንደገደቡት የጠቀሱት የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ በወዲያኛው ዓመት (2014/15) 963.8 ሚ. ብር የነበረው የባንኩ ጠቅላላ ትርፍ አምና ወደ 950.6 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
ባንኩ በዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ጥሩ መንቀሳቀሱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ጠቅላላ ሀብት (እሴት) በ15.4 በመቶ አድጎ 28.6 ቢ. ብር መድረሱን፣ ጠቅላላ ተቀማጭ ከወዲያኛው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 14.9 በመቶ ዕድገት አሳይቶ፣ 22.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ጠቅላላ የተሰጠ ብድርና አድቫንስ ከወዲያኛው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ባለፈው ዓመት 10 በመቶ አድጎ፣ 12.5 ቢ. መድረሱን፣ ችግር ቢከሰት የመቋቋም አቅሙ ከፍ እያለ መሆኑን ጠቅሰው አጠቃላይ ካፒታል 18.3 በመቶና የተከፈለ ካፒታልም 20.5 በመቶ ከፍ ማለቱን ለአብነት ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 20ኛ ዓመቱን ያከበረው ዳሽን ባንክ፤ የደንበኞቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን፡፡ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ከወዲያኛው ዓመት የ12.6 በመቶ ዕድገት በማሳየት በተጠናቀቀው ዓመት 1.4 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ የባንኩ ሰራተኞች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ ቋሚ፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ ኮንትራት ሰራተኞችን ጨምሮ ባለፈው ዓመት ከ3,033 ወደ 5,630 መድረሱ ታውቋል፡፡  

Read 1307 times