Sunday, 30 October 2016 00:00

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 349.7 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ። ትርፉ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ27 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል፡፡
ባንኩ፣ 12ኛውን የባለ አክሲዮኖች መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ያካሂዳል፡፡ ባንኩ በዓመቱ 923.3 ሚ. ብር አጠቃላይ ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከብድር ወለድና ከዋስትና ኮሚሽን የተገኘው 63.2 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ተገልጿል፡፡
ባንኩ ካስመዘገበው አጠቃላይ ትርፍ ውስጥ 88.1 ሚ. ብር ለመንግስት ግብር በመክፈልና 65.3 ሚ. ብር ህጋዊ መጠባበቂያ በመያዝ፣ በበጀት ዓመቱ 196.1 ሚ. ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን፣ ይህም ትርፍ ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍያ፣ ለተቀማጭና ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ እንደሚውል ታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የባንኩ ፋይናንሻል አፈጻጸም ሲታይ ጠቅላላ ሀብቱ 8.1 ቢ. ብር የደረሰ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ30 በመቶ ወይም የ2.9 ቢ. ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የብሄራዊ ባንክ ህግ፣ የባንኮች የተከፈለ ካፒታል 2 ቢ. ብር እንዲሆን በደነገገው መሰረት፤ ባንኩ የ230 ሚ. ብር አክሲዮን በመሸጥ የተከፈለ ካፒታሉን 872 ሚ. ብር ማድረሱና አጠቃላይ ካፒታሉ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ ባንኩ፣ ከ2-3 ቢሊዮን ብር በላይ ለደንበኞች አዲስ ብድር የሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል። ከተሰጠው ብድር ውስጥ ወደ ውጪ ለመላክና ከውጪ ዕቃዎች ለማስገባት፣ ለሀገር ውስጥ ንግድ፣ ለኮንስትራክሽንና ህንፃ ግንባታ፣ ለማምረቻ ዘርፍ የተሰጠው ብድር መጠን ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ፣ ለትራስፖርትና ኮሙኒኬሽን፣ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለግብር እና ለሌሎች ዘርፎች የተሰጡ ብድሮች ጉልህ ስፍራ እንደነበራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባንኩ በዓመቱ 31 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ በመላ ሀገሪቱ ያሉትን የቅርንጫፎች ብዛት 120 ማድረሱ ታውቋል፡፡ በሞባይልና ወኪል ባንኪንግ አገልግሎት 1,200 ወኪሎችን በመመልመል ከ35 ሺህ በላይ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት፣ ከ35 ሚ. ብር በላይ አንቀሳቅሷል፡፡ “ላየን ካርድ” በሚል ስያሜ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት የተቀላቀለ ሲሆን ብሄራዊ ባንክ ባስተባበረው “ኢትዮ ስዊች” ጋር በመጣመር፣ ደንበኞቹ ባንኩ በተለያዩ ቦታዎች በተከላቸው ኤቲኤሞች ወይም በሌሎች ባንኮች ኤቲኤሞች “ላየን ካርድን” በመያዝ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከ16 ዓመት በኋላ በ2035 ዓ.ም በሀገሪቱ መሪ ባንክ የመሆን ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ የሚገኝ ታዳጊ ባንክ መሆኑን ጠቅሶ፣ ጠንካራ ጎኖቹን የበለጠ በማጠናከር፣ ክፍተቶቹንና ድክመቶቹን ወደ ስኬት በመለወጥ እስካሁን ካስመዘገበው የበለጠ ውጤት ለማግኘት እንደሚጥር አስታውቋል፡፡ ባንኩ ለ2,401 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ 

Read 2861 times