Sunday, 30 October 2016 00:00

“ኖት 7” ያቃወሰው ሳምሰንግ፣ “ኤስ8”ን አዘግይቶታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባትሪው እየጋለ እሳት በሚፈጥረው አዲሱ ምርቱ ጋላክሲ ኖት 7 ሳቢያ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት ደፋ ቀና የሚለው ሳምሰንግ ኩባንያ፤ በመጪው አመት ለገበያ ያቀርበዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን አዲሱን ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ፎኑን መስራት የሚጀምርበትን ጊዜ በሁለት ሳምንታት ማራዘሙ ተዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ ኤስ8ን ማምረት የሚጀምርበትን ጊዜ ያራዘመው፣ የኩባንያው የቴሌኮም ኢንጂነሮች በጋላክሲ ኖት 7 ላይ የተፈጠረውን ችግር ትክክለኛ መንስኤ በማጣራት ስራ በመጠመዳቸው ነው መባሉን የዘገበው ኤክስፕረስ ጋዜጣ፤ ሳምሰንግ አዲሱን ምርቱን ተጣድፎ ወደገበያ በማስገባት የጋላክሲ ኖት 7 የቀመሰውን መከራ ዳግም እንዳያስተናግድ ሰግቷል ብሏል፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ በዚሁ ጦሰኛ ምርቱ በጋላክሲ ኖት 7 ሳቢያ የገባበት ቀውስ ህልውናውን አደጋ ላይ እንደጣለው የዘገበው አፍሪዶትኮም በበኩሉ፣ ከሰሞኑ ደግሞ ኖት 7 ገዝተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሩ ደንበኞች “አጉላልቶናል ካሳ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ ክስ እንደመሰረቱበት ገልጧል፡፡
527 ደቡብ ኮርያውያን የሳምሰንግ ደምበኞች ለእያንዳንዳችን 440 ዶላር ካሳ ሊሰጠን ይገባል በሚል በኩባንያው ላይ ሰኞ ዕለት ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ፣እኛም እንከሳለን የሚሉ አመልካቾች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱንና የከሳሾቹ ቁጥር በሺህዎች ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 1073 times