Sunday, 30 October 2016 00:00

ለ1 እንግዳ ተቀባይ የሥራ ማስታወቂያ፣ 10ሺ ቻይናውያን አመልክተዋል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 - አምና ለ300 ክፍት የስራ ቦታዎች፣ 2 ሚ. ህንዳውያን ቀርበው ነበር

       በቻይና በቅርቡ አመልካቾችን አወዳድሮ አንድ የእንግዳ ተቀባይ ለመቅጠር ይፋ በተደረገ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ 10 ሺህ ያህል ቻይናውያን ስራ ፈላጊዎች ማመልከታቸውን ቢቢሲ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
እምብዛም እውቅና የሌለውና የቻይና ዲሞክራቲክ ሊግ የተሰኘው የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ያወጣው ይህ የእንግዳ ተቀባይነት ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ፣ በአገሪቱ የስራ ቅጥር ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አመልካች የቀረበበት ነው ያለው ዘገባው፤ በዚህ አመት ብቻ 1.4 ሚሊዮን ቻይናውያን የስራ አመልካቾች ለተለያዩ የስራ መደቦች የሲቪል ሰርቪስ ፈተና መውሰዳቸውን ጠቁሟል፡፡ በቻይና በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ለወጡ የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች መቅረባቸውንና፣ ለአንዱ የስራ ቦታ በአማካይ 49 አመልካቾች በተወዳዳሪነት ቀርበው ማመልከታቸውንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
የወቅቱ የአገሪቱ የስራ አጥነት ምጣኔ 4 በመቶ ነው ያለው ዘገባው፤ ተመሳሳይ የስራ አጥነት መጠን ባለባት ህንድ ባለፈው አመት ለወጡ 300 ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያዎች 2 ሚሊዮን አመልካቾች ቀርበው እንደነበርም አስታውሷል፡፡

Read 8483 times