Sunday, 30 October 2016 00:00

የአንጎላው ፕሬዚዳንት ልጃቸውን በመሾማቸው ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 - የፕሬዚዳንቱ ልጅ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር ናት

       የአንጎላው ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ህግን ጥሰው ሴት ልጃቸውን ኤሳቤል ዶስ ሳንቶስን የአገሪቱ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርገው መሾማቸው አግባብነት የሌለው አድሏዊ ተግባር ነው በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነቺው ኤሳቤል፣ በአንጎላ መንግስት ስር የሚተዳደረውን ሶናንጎል የተባለ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንድትመራ ባለፈው ሰኔ በአባቷ መሾሟን ያስታወሰው ዘገባው፣ 14 የአገሪቱ ጠበቆች ሹመቱ የአገሪቱን ህግ የጣሰ ነው በማለት በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ መመስረታቸውን ገልጧል፡፡
ክሱን በመከታተል ላይ የሚገኘው የአንጎላ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፣ ኤሳቤል በምን መንገድ የኩባንያው ሃላፊ ተደርጋ ልትሾም እንደቻለች ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ ባለፈው ረቡዕ ለፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስና ለልጃቸው ጥሪ በማስተላለፍ የስምንት ቀን ጊዜ መስጠቱን ዘገባው አብራርቷል፡፡
በአገሪቱ ህግ መሰረት አንድ የመንግስት ባለስልጣን የቤተሰብ አባሉን በሃላፊነት ቦታ ላይ እንዲቀመጥ በዕጩነት ማቅረብ ወይም እንዲቀርብ መፍቀድ አይችልም ያለው ዘገባው፤ አንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞችም ፕሬዚዳንቱ ልጃቸውን የግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ መሪ አድርገው መሾማቸው በአገሪቱ ቤተሰባዊ አስተዳደርን በዘላቂነት ለመመስረት የያዙት የስልጣን አፍቃሪነት ማሳያ ነው ሲሉ መናገራቸውንም ገልጧል፡፡
ኤሳቤል ዶስ ሳንቶስ የአገሪቱን የነዳጅ ምርትና ኤክስፖርት በበላይነት የሚመራውን ሶናንጎልን እንድትመራ በአባቷ መሾሟን ተከትሎ ለጋዜጠኞች ባደረገቺው ንግግር፣ ኩባንያውን ከገባበት ችግር ለማውጣትና በአለማቀፍ ደረጃ ስኬታማ ለማድረግ የአደረጃጀትና ሌሎች ለውጦችን ለማድረግ ማቀዷን አስታውቃ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች በሆነቺው ናይጀሪያ ከሽብርተኝነትና ከኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ችግር የአገሪቱን የነዳጅ ምርት መጠን ማሳነሱን ተከትሎ፣ የአለማቀፉ የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ድርጅት አባል የሆነቺው አንጎላ በአህጉሩ ቀዳሚዋ የነዳጅ አምራች አገር ለመሆን መብቃቷንን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1270 times