Sunday, 30 October 2016 00:00

ያልተመለሰልኝ ጥያቄ?

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(7 votes)

 የሰባት ከንቱዎችን ምክር ስሰማ ነው ያደግሁት። ሁሉም ሰው መሆኔን ሊያሳምኑኝ ብዙ ዳክረዋል፡፡ አስቀድማ እርግጠኛ የሆነችውን የልምድ አዋላጅ ጨምሮ፣ እናትና አባት፣ አስተማሪ፣ የቀበሌው መታወቂያ አዳይና ሌሎችም ---- ነበሩ፡፡ አንዳቸውም ግን ሰው ለመሆኔ ማረጋገጫ የላቸውም፡፡ ‹‹ሰው አይደለሁም ካለ መብላቱን አይተውም… ሆዳም… ውሻ በቁልቁለት የማይጎትተውን እንጀራ ሲቀረድድ እየዋለ… ሰው አይደለሁም ይላል!?›› እያሉ ማማት ብቻ፡፡
እኔ ግን ቂመኛ ነኝ እንዴ? ልሆን እችላለሁ። ተደብድቤ አውቃለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተቀውሬአለሁ። (የአንድ ጥርሴን መውለቅ የማልናገረው የሽንፈት ስሜት አድሮብኝ አይደለም፤ ጥርሴን ያወለቀኝን ሰው ሃጢአት ላለማብዛት ብዬ ነው) የአንድን ጎልማሳ መሃል አናት በደቦል ድንጋይ ካዋለቅሁ በኋላ መደባደብ እርም ብያለሁ፡፡ (ሰው ያን ሁሉ ደም ተሸክሞ መዞሩ ይገርማል!) መጣላት አልወድም፤ ከሰው ጋር መነጋገርም ደስ አይለኝም፡፡ ሰው ማማት ቁስል ነው፤ ሲነካኩት የሚያመረቅዝ፤ መተውን የመረጥኩት ለዚያ ነው፡፡
የምተዳደረው ሰው በማስቸገር ነው፤ ወይም አይደለም፡፡ (የራሳቸው ጉዳይ!)
ከንቱነት የሚጀምረው ከሆድ እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በሰው ሆድ ውስጥ ከንቱነት ሌሊትና ቀን ይንከላወሳል፡፡ ቋንቋ የተማርኩት ይሄን ከንቱነት ለማድመጥ አልነበረም፤ ሳልወድ በግድ ግን እሰማለሁ፡፡ ቀፋፊ ሆድ! (ቦጭረቅ… ጨረቅ..ጩርርር… ዥውውው.. ግግግግግውውው)
የመጀመሪያ ሰሞን ደመናን የምፈራውን ያህል ለሆድ ጩኸትም ፍራቻ ነበረኝ፡፡ ደመና ሲዳምን፤ ሰማይ ሲጠቋቁር፤ ደግሞ ምን ሊመጣ ይሆን እያልኩ እፈራለሁ፤ በተለይ መብረቁን እንዳያባርቅ። በቅርቡ ግን ሆድ ምንም ያህል ቢዳምን የሰማይን ያህል እንዳልሆነ ተገነዘብኩ፡፡ ሆድ ያችን አመለኛ ጩኸቱን ሲያሰማ ጥቂት ጉርሻ ከሰጡት ጸጥ ይላል፡፡ (አይገርምም? እዚህ ጋ ስደርስ አንድ ከንቱ አስታወስኩ፡፡ ከሰባቱ ከንቱዎች አንዷ መሆኗ ነው። የፍቅር ይሁን የትዳር ጥያቄ ያቀረበችልኝ ልጅ ነበረች) ኤጭ! እርሷንም መርሳት ያስፈልጋል፡፡  
ቦርጭ መጥላት ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፤ ቦርጫምም እንዲሁ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ አድጓል፤ ቦርጫሞች ማሰብ የተሳናቸው ይመስሉኛል፡፡
አስራ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ወይም በታች ቢሆነኝ ነው፡፡ የራሴን ምስል ድንጋይ ላይ ቀርጬ፣ ከኔ ጋር የማነጻጸር ፍቅር ነበረኝ፤ ሲመሽና ሲነጋ እጆቼንና ፊቴን በድንጋይ ፍላጭ ፍንጣሪ እየኮረኮምኩ፣ አመድ አለብሳለሁ፡፡ አንድ የተንቀዠቀዠ የድንጋይ ፍንጣሪ የግራ አይኔን ቀውሮት አስነባኝ፡፡ ግን አልተበሳጨሁም፤ አመመኝ እንጅ፡፡
እንባዬን በሸሚዜ እጅጌ ጠራረግሁና በትክክል ማየት አለማየቴን ለመፈተሽ ወደ ጎረቤታችን ቤት አይኔን ወረወርኩ፡፡ የእኔ አባት ምስጉን ገበሬ ነው፤ የእኛ ጎረቤት አመስጋኝ ድሆች ናቸው፡፡ ሴትየዋ ጠጅ መጠጣትን ሙያው ያደረገ  ባል ነበራት፡፡ ጀርባዋ ላይ ያዘለችው ጨቅላ እሪታው ይሰቀጥጣል። የቆረፈደ ቀሚሷን የያዘ ሌላኛው ልጇ፣ እንባውና ንፍጡ እኩል እየወረዱ እናቱን ይከተላል፡፡ እኔ ደግሞ በአይኔ እሷን እከተላለሁ፡፡
ጎረቤታችን ወደ እኛ ኩሽና አመራች፤ እናቴ እህል ከምትፈጭበት የድንጋይ ወፍጮ አጠገብ በርከክ ብላ የወዳደቁ የበቆሎ ፍሬዎችን መልቀም ጀመረች። (የሁለቱ ልጆቿ ለቅሶ እንዳጀባት ነው) እየለቀመች በቀሚሷ ጫፍ ላይ ታስቀምጣለች፡፡ አንድ እፍኝ ሞልተው ይሆን? ወደ ቤቷ ታዛ ተመልሳ እሳት ማቀጣጠል ጀመረች፤ ፍሬዎቹን በብረት ምጣድ ላይ በተነቻቸው፡፡
ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ እኛ ቤት ገባሁ። እናቴ በማዳበሪያ ከተቀመጠው ማር እየዛቀች ወደ ጠጁ ማድጋ ትከታለች፡፡ አይኔን ወረወርኩ። አባቴ የሚያደልበው ፍየል ወንፊቱ ላይ የቀሩትን የባቄላ ፍሬዎች ይቆረጥማል፡፡ እልፍ ብሎ በወራንታ የተቀመጠ ባቄላ አለ፡፡ ሁለቱ ኪሶቼ እስቲሞሉ ዛቅሁኝና ወደ ጎረቤታችን ቤት አመራሁ፡፡ብረት ምጣዱ ከተጣደ በኋላ ብደርስም የኪሴን ባቄላ እየቆነጠርኩ ምጣዱ ላይ ከመበተን አልተመለስኩም። ኪሶቼ ሲራገፉ ሴትየዋ ቀና ብላ አየችኝ፡-
‹‹ተባረክ … ያሳድግህ!›› መረቀችኝ፡፡ እኔ ዝም ብዬ እመለከታታለሁ፡፡
የቀሚሷን ጫፍ ይዞ ሲያለቅስ የነበረው ህጻን፤ እኔን እኔን እያየ ማልቀሱን ረሳው፡፡ የጀርባዋ ጨቅላ ግን እሪታው እንደ በርበሬ መለብለቡን ቀጥሏል፡፡ ምጣዱ ላይ የሚታመሰው ባቄላና በቆሎ ድብልቅ ይንኳኳል.. እኔ አይኔን ወደ ማዶ አሻገርኩ። ቦርጫሙ የግብርና ባለሙያ ወደኛ ቤት ሲመጣ አየሁት፡፡ ጠጅ ወይም ጠላ መጠጣት ሲያምረው ወደኛ ቤት ይመጣል፡፡ ቦርጩ በጣም ትልቅ ነው፤ ሲናገር ያለከልካል፡፡ አባቴን ‹‹ጎበዝ ገበሬ›› እያለ ያሞካሸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ከእኛ ቤት አይጠፋም፤ መንግስት በሰጠው ቢሮ ውስጥ ብዙ አይቀመጥም፡፡ እስኪበቃው ድረስ ከጠጣ በኋላ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ካርታ ይጫወታል፤ ወይም ያንቀላፋል፡፡
‹‹እንዴ እንዴ የምን ለቅሶ ነው!›› አለ ወደ እኛ እየቀረበ፡፡ የሴትየዋን ጨቅላ ሊቆጣ የፈለገ ይመስላል፡፡ እናትየው ከምጣዱ ወደ ሰፌዱ እያወረደች የነበረውን ቆሎ ሲያይ መቆጣቱን ተወ፡፡
‹‹ቆሎ! አቤት ቆሎ! እንደምወድ ማን ነገረሽ!?››
ሴትየዋ አይኗ ተንከራተተ፤ሰፌዱን ወደ እሱ ዘረጋች፡፡
ሲያለቅስ የነበረው ህጻን፣ አይኑ እኩል ከሰፌዱ ጋር ተንከራተተ፡፡
‹‹ያዝ እንጅ … ደሞ ለቆሎ›› አለች እናቲቱ፡፡ ምርጫ አልነበራትም፡፡
ህጻኑ በድንጋጤ ፈዝዞ ቀረ፡፡ ቦርጫሙ ደህና አድርጎ አፈሰ፤ ያፈሰውን ኪሱ ውስጥ ከተተ፤ ድጋሚ ሊያፍስ እጁን ሲሰድ እኔ አላስቻለኝም፡፡ አይኔ የሚፈልገው ድንጋይ ነበር፡፡ ጫፉ የሾለ ሻፎ ድንጋይ እጄ ገባ፡፡ ሰውየው ቆሎውን እየጎረደመ ወደ እኛ ቤት ሲሄድ፤ ሴትዮዋ በሽብር ይሁን በሀፍረት ስሜት ፊቷ ሲዳምን፣ ህጻኑ እንደገና ለቅሶውን አቀለጠው። የሰውየው እግር የእኛን ቤት ከመርገጡ በፊት የወረወርኩት ድንጋይ ሊመለጥ የዳዳው አናቱ ላይ አረፈ፡፡ ተጋድሞ መንፈራፈር ሲጀምር፣ ፊቴን አዙሬ እግሬ አውጭኝ አልኩ፡፡
በዚያ ሰሞን ምን እንደተፈጠረ አላስታውስም። ጎረቤታችንና ልጆቿ ምን በልተው እንዳደሩ አላውቅም፡፡ ሰውየው በምን እንደታከመ የሰማሁት የለም፡፡ እኛ ቤት ውስጥ ምን ሲወራ እንደነበር አላውቅም፡፡ ከከብቶቻችን እረኞች ጋር እየዋልኩ፣ ሲመሽ የከብት በረት ከእነሱ ጋር ስጠቅብ ለካ ሶስት ቀን ሞልቷል፡፡
ወደ ቤት ስመለስ የተቀበለኝ የእናቴ የመጫኛ ግርፋት ነው፡፡ በመጫኛው አንደኛ ጫፍ የፍጥኝ ጠፍራ አሰረችኝና በሌላኛው ጫፉ ራቁት ገላዬን ለበለበችኝ፡፡ አላለቅስ ብያት ስለነበር እጇ እስቲዝል ነው የገረፈችኝ፡፡  እንባ አልወጣኝ ማለቱ አበሳጭቷታል መሰለኝ፣ ስትገርፍበት የነበረውን የመጫኛ ጫፍ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ፈጥርቃ አሰረችው። አሁን የማላስታውሳቸው የእርግማንና የስድብ ቃላት ለግማሽ ቀን ዘነቡብኝ፡፡
ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ የአባቴ ጥፊ ነው፤ለሁለተኛ ዙር ግርፋት ታጭቼ ኖሯል፡፡ የተከበረና ምስጉን ገበሬ እንዲሆን ያስቻለውን የግብርና ባለሙያ መፈንከቴ አስቀይሞታል፡፡ ማዳበሪያ ወይም ምርጥ ዘር ከመከልከሉ በፊት ስለ ሰውየው እኔን ሊበቀለኝ ፈልጓል፡፡ ከትራሱ ስር የሚያስቀምጣትን ሰንጢ አወጣና እሳት እስክትመስል በእሳት አጋላት፡፡ ቆይቶ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ (ብዙ ጊዜ እረሳለሁ መሰለኝ) በስንተኛው ቀን ነው፣ ግንባሬ ላይ ትልቅ ጠባሳ  ያገኘሁት?
የዚያ ሰሞን ነገሮች አንድ ቁልፍ ጥያቄ በአእምሮዬ ውስጥ ጥለው አለፉ፡፡  አባቴ ፍትህን ሳይሆን ንብረትን ለምን ወደደ? ሰውየው የድሃ እራት ቀምቶ መብላቱ ሊያስቀጣው አይገባም ነበርና ነው እኔ ጥፋተኛ የሆንኩት? እኔ የግብርና ባለሙያውን ስለፈነከትኩት አባቴን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መከልከል ይችል ነበር? ከወራንታ ሙሉ ባቄላ ጥቂት ጭብጥ መቆንጠሬ እናቴን ለምን አስከፋት? ፍየል ከሚደልብበት ይልቅ ድሆች በልተውት ቢያድሩ ምን ችግር ነበረው? አሁን ይሄ ሁሉ ሰው ነው?
ዛሬም ድረስ አብሮኝ ያለው ጥያቄ፤ ‹‹አሁን ይሄ ሁሉ ሰው ነው?›› የሚለው ነው፡፡
ሰው እያስቸገሩ መኖርን አሃዱ ብዬ ከጀመርኩ ወዲህ ብዙ ትምህርት ጀምሬ ብዙ ትምህርት አቋርጫለሁ፡፡ ፊዚክስ ወይም ባዮሎጂ፣ ኬምስትሪ ወይም ታሪክ፣ ጂኦግራፊ ወይም ፍልስፍና፤ ”አሁን ይሄ ሁሉ ሰው ነው?” የሚለውን ጥያቄ አልመለሱልኝም። የምታለቅስን እናት ሰቀቀን የሚገልጽ፣ የተራበን ህጻን ……. የተራበ? (ይሄኔ ይመስለኛል ሆድ ምቀኛ መሆኑን የተረዳሁት)ሆድ ከንቱ ነው! …. እና “ይሄ ሁሉ ሰው ሆድ ነው ወይስ ሰው?”
ያልተመለሰ ጥያቄ!!  

Read 3122 times