Saturday, 29 October 2016 12:50

“የመናፍስቱ መንደር” ውይይት ይካሄድበታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    በየወሩ መጨረሻ ባሉት ቅዳሜና እሁድ በቋሚነት በሚካሄደው “ትራኮን የመፅሀፍ ሂስ፣ ጉባኤና አውደ ርዕይ” የጋዜጠኛ ታደሰ ፀጋ ወ/ሥላሴ “የመናፍስቱ መንደር” የተሰኘ መፅሀፍ ላይ በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ከ8፡00 ጀምሮ በትራኮን ታወር ውይይት እንደሚካሄድ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገለፁ፡፡
እነሆ መፅሀፍት መደብር፣ ‹‹ክብሩ›› መፅሀፍት መደብርና ‹‹ሊትማን ቡክስ›› “መፅሀፍትን እንደመሰረታዊ ፍላጎት” በሚል መርህ በጋራ በሚያዘጋጁት በዚህ የሂስ፣ ጉባኤና አውደርዕይ ላይ ውይይት፣ በተመረጠው መፅሀፍ ላይ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በፎክሎርና በማህበረሰብ ጥናት እጩ ዶ/ር የሆኑት መምህር ሰለሞን ተሾመ ባዬ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ “የመናፍስቱ መንደር” ባልተለመደ አቀራረብና ይዘቱ አነጋጋሪ ሲሆን ጋዜጠኛ ታደሰ ፀጋ ሙያውን ተጠቅሞ በተለይ በሰሜን ልዕለ ተፈጥሮ እንቅስቃሴና ጥንታዊ ህብረተሰብ ቅሪትና ቅብብሎሽ ላይ ረጅም ጊዜ የወሰደ ጥናት አድርጎ የፃፈው፣ ለዘመናት ያልተደፈረ ሀሳብም ያነሳበት ነው ተብሏል፡፡ ለስምንተኛ ጊዜ በሚዘጋጀው በዚህ የመፅሀፍ ሂስ፣ ጉባኤና አውደ ርዕይ ላይ የሚታደሙ ጎብኚዎች ከ20-50 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ መፅሀፍትን መግዛት እንደሚችሉ አቶ በፍቅሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ መፅሀፍት አቅራቢዎች፣ አከፋፋዮች፣ ደራሲያንና አንባቢያን የሚገኙ ሲሆን የጥበብ ቤተሰቦች የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ትራኮን ታወር ላይ በመገኘት የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አዘጋጆቹ ጋብዘዋል፡፡ 

Read 2888 times