Sunday, 06 November 2016 00:00

በውዝግብ የተሞላው የአሜሪካ ምርጫ ማክሰኞ ይለይለታል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    አስገራሚ ክስተቶች፣ ያልተጠበቁ ሁነቶች፣ አስቂኝ ምልልሶች፣ አስደንጋጭ መረጃዎች፣ ኃይለኛ ፉክክሮች፣ ብዙ ብዙ ትኩረት የሚስቡ ያልተለመዱ ነገሮች የተስተናገዱበት የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  የፍጻሜው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ የፊታችን ማክሰኞ ይለይለታል፡፡
ማን ይጠበቃል?
በዘንድሮው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ላይ የከረሙት ሁለቱ እጩዎች፣ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው አንዳቸው ሌላኛቸውን እያብጠለጠሉና እያንኳሰሱ ጎልተው ለመውጣትና የመራጩን ቀልብ ለመግዛት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡  በቅድመ ምርጫ ትንበያ ተጠምደው የሰነበቱት ታላላቅ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማት በምርጫው ማን ያሸንፋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የየራሳቸውን ጥናት በመስራት ውጤት ይፋ ሲያደርጉ ሰንበተዋል፡፡ አንዳንዶች የዲሞክራቷን ዕጩ ሄላሪ ክሊንተንን ለአሸናፊነት ሲያጩ፣ ሌሎች አነጋጋሪውን የሪፐብሊን ዕጩ ዶናልድ ትራምፕን ለድል አጭተዋቸዋል፡፡
ዲሞክራቷ ሄላሪ፣ በአንዳንድ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ለሳምንታት በሰፊ ልዩነት ሲመሩ ቢቆዩም፣ ልዩነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መምጣቱና በተለይም ኤፍቢአይ በሄላሪ ላይ የኢሜይል ቅሌት ምርመራ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ በአንዳንድ ትንበያዎች ትራምፕ መምራት መጀመራቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አገር አቀፍ የቅድመ ምርጫ ትንበያ፣ሄላሪ ቢሊዬነሩን ትራምፕ በሶስት ነጥብ በመምራት ላይ እንደሚገኙ ያስታወቀ ሲሆን፣ ኤቢሲ ኒውስና ዋሽንግተን ፖስት በበኩላቸው፤ ልዩነቱን ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጉታል - ለሄላሪ 47፣ ለትራምፕ 45 ነጥብ በመስጠት፡፡
ኦባማም በቅስቀሳ ተጠምደዋል
ሄላሪና ትራምፕ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን በማስተዋወቅ፣የተሻለ ያደርገኛል የሚሉትን ነጥብ በማስተጋባት፣ አንዳቸው የአንደኛቸውን ጉድ በመዘክዘክና በማሳጣት የህዝቡን ቀልብ ለመግዛትና የበለጠ ድምጽ አግኝተው ለፕሬዚዳንትነት ለመብቃት በየፊናቸው በምርጫ ቅስቀሳ ቢጠመዱም፣ ኦባማ የትራምፕን ምላስ ለመቋቋም ተስኗቸው አስሬ “ሴት ትንቃለህ” የሚል ነገር የሚደጋግሙትን ሄላሪን ለመደገፍ ባለቀ ሰዓት አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የፓርቲ አጋራቸውን ሄላሪን በምርጫ ቅስቀሳ ለመደገፍ ከእነ ሚስታቸው ታጥቀው የተነሱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ አዮዋን ጨምሮ በተለያዩ ስቴቶች በመዘዋወር “ትራምፕ አይበጃችሁም፤ ሄላሪን ምረጡ” በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲቀሰቅሱ ሰንብተዋል፡፡ ኦባማ ባለፈው ረቡዕ በኖርዝ ካሮሊና ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ፣ የዘንድሮውን የአሜሪካ ምርጫ፣ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የመላው አለም ጉዳይ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ዲሞክራቶች ሆይ!... ይሄ ምርጫ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለም ጭምር ወሳኝ ነው፡፡ ዶናልድ በሚሉት ሰው ሳቢያ፣ የዓለማችን ዕጣ ፈንታሽ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ሰው ወደ ስልጣን እንዲመጣ አትፍቀዱለት፡፡ በነቂስ ውጡና ለሄላሪ ድምጻችሁን ስጡ!...” ብለዋል ኦባማ፡፡
መልስ የማያጡት አሽሙረኛው ትራምፕ፤ፍሎሪዳ ውስጥ ሆነው ይሄን ሰሙ፡፡ ሰምተውም እንዲህ አሉ፣ ይላል ቢቢሲ...
“ይሄ ኦባማ የሚሉት ሰው፣ ለሄላሪ  ማሽቃበጡን ትቶ፣ አገሪቱን በመምራቱ ላይ ማተኮር አለበት!...”
ቀድመው የመረጡ
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሰራር መራጮች ከመደበኛው የድምጽ መስጫ ዕለት በፊት ለሚደግፉት ዕጩ ድምጻቸውን መስጠት ይችላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ከ22 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን፣ ማክሰኞን መጠበቅ ሳያስፈልጋቸው ለመረጡት ዕጩ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ኮሚ ምን ነካቸው?
የምርጫ ቅስቀሳው በተጧጧፈበት፣ አንደኛው የሌላኛውን ዕጩ ድብቅ ገበና በሚያነፈነፉበት፣ የቆየ ወንጀላቸውን ነቅሰው በማውጣት አደባባይ ለማስጣትና ተፎካካሪያቸውን ትዝብት ላይ ለመጣል ደፋ ቀና በሚሉበት፣ ትራምፕ እና ሄላሪ አይጥና ድመት በሆኑበት ወሳኝ ወቅት ላይ፣ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ተሰማ፡፡
አሜሪካውያን ለሚደግፉት ዕጩ ድምጻቸውን የሚሰጡባት ወሳኝ ዕለት የምትደርስበትን ቀን ሲቆጥሩ ከርመው፣ 11 ቀናት ብቻ ሲቀራቸው፣ ዲሞክራቷን ሄላሪን ክው ያደረገ፣ ሪፐብሊካኑን ትራምፕ በደስታ ያስፈነጠዘ ሰበር ዜና ተሰማ፡፡ የሄላሪን የኢሜይል ቅሌት ክስ መርምሬ፣ አንዳች እንኳን የሚያስከስሳት ወንጀል ባለማግኘቴ ክሱን ወደ መዝገብ ቤት ልኬያለሁ ብሎ የነበረው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚ፣ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና፣ ሌላ የኢሜይል ቅሌት አግኝተንባታልና ልንመረምራት ነው አሉ፡፡
ሄላሪ ደነገጡ፤ ትራምፕ በደስታ ፈነጠዙ፡፡
“ምን!?...” አሉ ሄላሪ፣ የሰሙትን ባለማመን፡፡
“አላልኳችሁም!?... ይህቺ ወንጀለኛ፣ ገና ወህኒ ትወርዳለች!...” አሉ ትራምፕ፣ ሲሉት የከረሙትን ነገር የሚያረጋግጥ ጮማ ማስረጃ እጃቸው ላይ ሲወድቅ፡፡
“ጄምስ ኮሚ ምን ነካቸው?...” አሉ ብዙዎች በሰሙት ነገር ተገርመው፡፡
ኤፍቢአይ በምርጫ ውጤቱ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን እያወቀ፣ በወሳኝ ወቅት ይህን አደገኛ ውሳኔ ማሳለፉ ብዙዎች በጥርጣሬ ሲያዩት፣ አንዳንድ የህግ ተንታኞችም የተቋሙን ውሳኔ ህግን ያልተከተለ ብለውታል፡፡ ዳይሬክተሩ ይቅር የማይባል ጥፋት ሰርተዋልና፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ ስልጣናቸውን ይልቀቁ ያሉም አልታጡም፡፡ የኤፍቢአይ ውሳኔ የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉልና የዲሞክራቷን ዕጩ አሸናፊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አደገኛ ነገር ነው ያሉ ተንታኞች የመኖራቸውን ያህል፣ ተጽዕኖው እምብዛም ነው ብለው ያጣጣሉትም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ የጄምስ ኮሚን መርዶ ተከትሎ፣ የሄላሪና የትራምፕ የቅድመ ምርጫ የአሸናፊነት ትንበያ ልዩነት እየጠበበ ሲመጣ፣ አንዳንዴም ትራምፕ ሲመሩ ታይቷል፡፡
ጠመንጃ ተወዷል!...
የአሜሪካ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ፣በአገሪቱ የጦር መሳሪያ ገበያው መድራቱ ተነግሯል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በአገሪቱ ባለፉት ሶስት ወራት የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ሽያጩ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ30 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ያለው ዘገባው፣ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ161. 4 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ መሸጡን ገልጧል፡፡
የዚህ ሰበብ ደግሞ፣ ዲሞክራቷ ሄላሪ ናት ይላል ዘገባው፡፡
በአገረ አሜሪካ ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ግብይቱ የተጧጧፈው፣ አገሬው ዲሞክራቷ ሄላሪ ታሸንፍ ይሆናል ብሎ በመስጋቱ ነው ተብሏል። እሷ ካሸነፈች ደግሞ የጦር መሳሪያ ቁጥጥሩን የበለጠ ታጠብቀዋለች፣ ስለዚህ አበክሮ መሸመት  ያወጣል በሚል ነው ምድረ አሜሪካዊ ጠመንጃ ገበያ የወረደው ብሏል - ዘገባው፡፡
እሷም እንደ ኮንጎ?...
ከሳምንታት በፊት...
የዲሞክራሲ ባህል ያበበባት፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የሰፈነባት፣ በስርዓት የሚገዛ ፖለቲካ ስር የሰደደባት ልዕለ ሃያል አሜሪካ፣ ለሺህ ዘመናት ወደ ኋላ ተንሸራትታ እነ ኮንጎ የተዘፈቁበት አዘቅት ውስጥ ልትነከር ማቆብቆብ ጀመረች እንዴ? የሚያሰኝ አጉል ነገር ሆነ፡፡ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የሚያዝባት፣ የምርጫ  ስርዓቷ ነጻና ፍትሃዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባባትን አሜሪካን ለመምራት ታጥቀው የተነሱት፣ የእነ አብርሃም ሊንከንን ወንበር ለመቆናጠጥ የቋመጡት አነጋጋሪው ትራምፕ፣ በመጨረሻው ዙር የምርጫ ክርክራቸው ሌላ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካን ዲሞክራሲ ቁልቁል የሚጎትት ነገር ተናገሩ፡፡
“እሷ ካሸነፈች፣ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ያዳግተኛል!...” አሉ ትራምፕ፡፡
ትራምፕ እንዲህ ማለታቸውን ተከትሎ፣ አሜሪካም እንደእነ ኮንጎ በምርጫ ሳቢያ ብጥብጥ ውስጥ ትገባ ይሆናል የሚል ስጋት መፈጠሩን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
ዩኤስኤ ቱዴይ እና ሱፎልክ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በጋራ በሰሩት ጥናት፣ ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት አሜሪካውያን 51 በመቶው፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ጆ ዋልሽ የተባሉት የቀድሞ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ስጋት ግን ከዚህም ያልፋል ይላል - ዘገባው፡፡
“ማክሰኞ ድምጼን ለትራምፕ እሰጣለሁ፡፡ ረቡዕ ማለዳ ትራምፕ ተሸንፏል የሚል ነገር ከሰማሁ ግን፣ጠመንጃዬን መወልወሌ አይቀርም!... እናንተስ?...” ብለዋል ዋልሽ ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ስጋት አቀጣጣይ ወጋቸው፡፡
የአሜሪካ ዕድሜ ጠገብ የዲሞክራሲ ሥርዓትና ባህል፣እንደ ዘንድሮም ተፈትኖ አያውቅም፡፡ ከዓይን ያውጣው!!

Read 3955 times