Sunday, 06 November 2016 00:00

የ“ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ታሰረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   የሣምንታዊ “የኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ፤ በመንበረ ፓትሪያሪክ ቅድስት ቅዱሳን ማርያም ገዳም ላይ በሠራው ዘገባ፣ በከባድ ስም ማጥፋት ወንጀል በፍ/ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ታሠረ፡፡
‹‹በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ቅዱሳን ማርያም ገዳም ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ተጠየቀ›› በሚል ርዕስ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ላይ በታተመው ዘገባ፣ የገዳሙን ስም አጥፍቷል በሚል “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ እና ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ መከሰሳቸው ይታወቃል፡፡
ጉዳዩንም ሲመለከት የቆየው ፍ/ቤት፤ በሁለቱም ወገኖች የቀረቡ ማስረጃዎችን መመርመሩን ጠቅሶ ከትናንት በስቲያ በከሳሽ የቀረበውን ማስረጃ፣ ተከሳሾች በተገቢው ሁኔታ ማስተባበል እንዳልቻሉ በመግለፅ በተከሣሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሣልፏል፡፡
ፍ/ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የከሳሽና የተከሳሾችን የቅጣት አስተያየት የተቀበለ ሲሆን ከሳሾች ባቀረቡት የቅጣት አስተያየት፤ ጋዜጣው በሠፊው የተሰራጨ መሆኑን እንዲሁም ሙያን በመጠቀም የተሠራ ጥፋት መሆኑን በማስረዳት፣ በከባድ ቅጣት ሊያዝልን ይገባል ያሉ ሲሆን ተከሳሽ በበኩሉ፤ የጋዜጣው ስርጭት አዲስ አበባ የተወሠነ መሆኑን በክፉ ልቦና ተነሳስቶ የተሰራ ዘገባ አለመሆኑን፣ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለባቸውና ከግል ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን ሙያን በመጠቀም ህዝብን ለማገልገል የተደረገ መሆኑን ገልፀው ዜናውን ሚዛናዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት ማድረጉንና ዜናው ከወጣ በኋላም “ማስረጃችሁን አቅርቡና ቅሬታችሁን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን” ማለቱን መግለፁን በመጥቀስ፤ በቀላሉ ሊያዝልን ይገባል ሲል አመልክቷል፡፡
የግራ ቀኙን የቅጣት ማቅለያ ያዳመጠው የፌዴራል መጀመሪያ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል ችሎት፤ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 6 መዝገቡን ቀጥሮ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ እስከዚያው በማረሚያ ቤት እንዲቆይ መወሰኑን የጋዜጣው ጠበቃ አቶ በሃይሉ ተስፋሁን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 3647 times