Sunday, 06 November 2016 00:00

አንድ ዶላር፤ በጥቁር ገበያ ከ26 ብር በላይ እየተመነዘረ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)

   የዶላር ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ ሲሆን 1 ዶላር በጥቁር ገበያ ከ26 ብር በላይ እየተመነዘረ ነው ተብሏል፡፡ ለዶላር ምንዛሬ መናር ዋነኛው ምክንያት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና በኢትዮጵያ የዶላር የምንዛሬ መጠን አለመሻሻል መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ዓለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF)፤ የዶላር ምንዛሬ እንዲሻሻል የሰጡትን ምክር መንግስት አለመስማቱ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው፤ የዶላር ምንዛሬ መናር በአንዳንድ ወቅቶች በሚናፈሱ ወሬዎች ተከስቶ ወዲያው የመጥፋት ባህርይ እንዳለው ጠቁመው፤ ይህ የተለመደና አዲስ ነገር እንዳልሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስለመኖሩ የተጠየቁት ምክትል ገዢው አቶ ዮሃንስ አያሌው፤ እስካሁን ምንም አይነት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳላጋጠመና ባንኮችም በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ የምንዛሬ ዋጋ ማሻቀቡ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ባለመሆኑ ብዙ እንደማያሳስብ ገልፀዋል፡፡
‹‹የትኛውም አካል ኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሬ እንድትጨምር ወይም እንድታስተካክል ምክርም ሆነ አስተያየት አልሰጠም›› ያሉት ምክትል ገዢው፣ በጥቁር ገበያ 1 ዶላር፤ ከ26 ብር በላይ እየተመነዘረ መሆኑን እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ መንግስት ከዶላር ምንዛሬ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በአግባቡ ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ገዢው፤  ህጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴን ለመገደብ የተቀመጠ ህግ መኖሩን አስታውሰው፤ እስካሁንም ብዙ እንቅስቃሴ መደረጉንና እንቅስቃሴው እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል አንድ ዶላር በባንክ በ22.6 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።

Read 6375 times